Saturday, 30 April 2022 12:50

አገራዊ ምክክሩ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱትን ሃይሎች እንዲያካትት ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፣ ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች  በአገራዊ የምክክር መድረኩ ላይ እንዲሳተፉ የጠየቀ ሲሆን አጠቃላይ ምክክሩም ሁሉን አሳታፊና አካታች ሆኖ እንዲከናወን አስገንዝቧል፡፡
53 የፖለቲካ ፓርቲዎችን  በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፣ በቀጣይ ሃገራዊ ምክክር ዙሪያ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ እና የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እንዲሁም ከምክክር ኮሚሽኑ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በዚህ ውይይት ወቅት የጋራ ም/ቤቱ በዋናነት ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች የምክክር ሂደቱ ተሳታፊ የሚሆኑበት  እድል እንዲመቻች የጠየቀ ሲሆን የምክክሩ ሂደቱን ገለልተኛና አሳታፊ ማድረግ ከተቻለ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች  በሂደቱ እምነት አሳድረው ወደ ሰላማዊ መንገድ ሊመለሱ ይችላሉ የሚል እሳቤ እንዳለው ም/ቤቱ አስታውቋል፡፡
በአገራዊ ምክክሩ ላይ በአሸባሪነት የተፈረጁት ኦነግ ሸኔ እና ሕወኃት እንዲሳተፉ ፍላጎት እንዳለው ነው የጋራ ም/ቤቱ ያመለከተው፡፡
እነዚህ ሃይሎች  ወደ ምክክር መድረኩ እንዲመጡም የሂደቱን ገለልተኛነትና አሳታፊነት በተግባር ከወዲሁ ማረጋገጥ እንደሚገባ የጋራ ም/ቤቱ አስገንዝቧል፡፡
ውይይቱን የመሩት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ “በዚህ ሃገራዊ ምክክር ላይ ማንም ተገፍቶ አይቀርም ሂደቱ ሁሉንም አካታች ነው የሚሆነው፤ ሀገራዊ ምክክሩ አካታች ነው ማለት ማንም ዳር ላይ ሆኖ እንዲመለከት አይፈረድበትም ማለት ነው” ብለዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ በበኩሉ፤ በቀጣይ  በምክክሩ እነማ በምን አግባብ ይሳተፋሉ የሚለውን ጨምሮ ምክክሩ የሚመራበትን መመሪያ እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል፡፡

Read 11551 times