Saturday, 30 April 2022 12:55

የኑሮ ውድነቱ መንስኤዎች - በኢኮኖሚ ባለሙያው ዕይታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   • ምርታማነት ከሞተ፣ ምርት እንደ መና ከሰማይ አይወርድም
    • ህዝብ ሸመታ ሳይሆን ሽሚያ ውስጥ ነው ያለው
      • ሁሌም አምራቹን ማዘዝ የሚችለው ሸማቹ ነው

          የብዙዎችን ህይወት እያመሰቃቀለ ያለው የኑሮ ውድነቱ መንስኤዎች ምንድን ናቸው? ኑሮአችንን እንዴት ከገቢያችን ጋር እናመጣጥነው? ለኑሮ ውድነቱ መቋቋሚያ ዘዴው ምንድን ነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ፣  በምጣኔ ሃብት ላይ የሚያጠነጥኑ አራት መጻሕፍትን ካሳተሙትና በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በርካታ ኢኮኖሚያዊ መጣጥፎችን ካስነበቡት የማክሮ ኢኮኖሚው ባለሙያ አቶ ጌታቸው አስፋው ጋር የአዲስ አድማስ  ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል።

               በአገራችን ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት መንስኤው ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ የሸቀጦች ዋጋ ንረት ስንል ማወቅ ያለብን ነገር አለ። ዋጋን በገንዘብ ነው የምንተምነው። ለምሳሌ አንድን ሱፍ 8ሺህ ወይም 6ሺህ ብር እያልን እንተምናለን፡፡ ይሄ የገንዘብ ትመና ሽፋን ነው እንጂ ዋጋን የሚተምነው የሸቀጦቹ ጠቀሜታ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ  ሰው እንቁላል ድሮ 2 ብር ሊሆን ይችላል የሚገዛው፤ ዛሬ 8 ብር ሊገዛ የተገደደበት ምክንያት ከእንቁላሉ የሚገኘው ጠቀሜታ 8 ብር ያወጣል ተብሎ ስለተወሰነ ነው። ስለዚህ ሰዎች ሸቀጦችን የሚለዋወጡት የራሳቸው ሸቀጥ ሰጥተው የሌላውን ለመውሰድ ስለሆነ፣ ገንዘብ እንደ ሽፋን መሃል ቤት ይግባ  እንጂ የዋጋዎች  መተመኛው የእቃዎቹ ጠቀሜታ  ነው። ሸሚዝ ብዙ አያስፈልገኝም ከተባለ፣ ያለውን ሸሚዝ ሸጦ ሱሪ ሊገዛበት ይችላል። ስለዚህ ህብረተሰቡ ማወቅ ያለበት በዋናነት ተጠንቅቆ የቱን ምርት እንደሚፈልግ ማወቅና መወሰኑ ነው። አምራቹን ማዘዝ የሚችለው ሸማቹ ነው። የሚፈለገውን ምርት አምራቹ በሚፈለገው መጠን ማምረት ካልቻለ፣ የዛን ጊዜ  የዋጋ አለመመጣጠን ይፈጠራል። በፍላጎትና አቅርቦት መካከል አለመመጣጠን ይፈጠራል ማለት ነው። ኢኮኖሚስቶች ግን በሙያዊ ትንታኔ የዋጋ ንረት መንስኤ ብለው የሚያስቀምጧቸው አሉ። ዋናው የገንዘብ በገበያ ውስጥ መግባትን ነው። ይሄ ማለት ብዙ ገንዘብ ጥቂት ምርትን ሲያሳድድ ማለት ነው። አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች ደግሞ #የለም ይህ ብቻ አይደለም፤ አንዳንድ የኢኮኖሚ ንዝረቶች አሉ; ይላሉ። ለምሳሌ የአቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥ ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በአጠቃላይ በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ  ንረት የመጣው ከገንዘብ በብዛት ወደ ገበያው መግባት ጋር ተያይዞ ሳይሆን፤ ከአቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥ ጋር ተያይዞ  ነው። ለምሳሌ ሽንኩርት በአቅርቦት መቆራረጥ ምክንያት ሊወደድ ይችላል። አሁን ላለው የኑሮ ውድነት ግን መንስኤው፣ እኔም፣ የገንዘብ በገበያ ውስጥ  መብዛት ነው ብዬ አስባለሁ።
የዋጋ ንረት መለኪያዎች ምንድን ናቸው?
የራሱ መለኪያዎች አሉት። ለምሳሌ የባለፈው አመት የሚያዚያ ወርን የሸቀጦች ዋጋ፣ ከአሁኑ የሚያዚያ ወር ጋር በማነጻጸር የሚለካበት መንገድ አለ። የአንድ እቃ የዋጋ መጨመር ወይም የብዙ እቃ ዋጋ መጨመር ብቻውን የዋጋ ንረት አይባልም። የዋጋ ንረትን ለመለካት በርካታ አመላካች ሁኔታዎች አብረው ይታያሉ። ይሄን ጠቅላይ ስታትስቲክስ ባለስልጣን ነው ለክቶ የሚያቀርብልን። ከዚህ በመለስ ሸማቹ ወይም ማህበረሰቡ ራሱ የሚለካበት መንገድም አለው። ጤፍ የዛሬ አመት ስንት ነበር? ሽንኩርት አምና ስንት ነበር? እያልን የምናመዛዝንበትና የምንለካበት መንገድ አለ። የስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ ምናልባት ለባለሙያዎች ቢጠቅም ነው እንጂ ለሸማቹ ብዙም አይጠቅመውም። ህዝብ የሚገባው አምና እንቁላል ስንት ነበር? ዛሬ ስንት ነው? የሚለው መንገድ ነው፡፡ ሌሎችም አሉ። በአብዛኛው የምናውቀው የሸማቾችን የዋጋ መለኪያ ነው፤ የአምራቾች የዋጋ መለኪያም አለ። ከአምራቾችና ከሸማቾች ሌላ ደግሞ እኛ ኢኮኖሚስቶች የምንጠቀመው ጂዲፒ ዲፍሌተር የሚባል ነገር አለ። ይህ ማለት ለምሳሌ በሸማቾች የዋጋ መመዘኛ መንገድ ከሄድን እንደ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ መንገድ (ትራስፖርት)፣ የብረት ዋጋ፣ የጥሬ እቃዎች ዋጋ ታሳቢ አይደረጉም። ምክንያቱም እነዚህ ራሳቸው አስቤዛ አይደሉም። አስቤዛውን የሚያስገኙ ናቸው። ማስገኘታቸውን የሚያውቀው ደግሞ አምራቹ ነው። ዋጋውን እንደዚህ ከግምት አስገብቶ ይተምናል። ሌላው የጅምላ አከፋፋዮች የዋጋ ማመላከቻ ነው። ነገር ግን በአብዛኛው ሃገራት ዘንድ ዋጋ የሚለካው በህዝቡ ወይም በሸማቾች የዋጋ መለኪያ ማመላከቻ መንገድ ነው።
ከእነዚህ የዋጋ መለኪያዎች አንጻር በኢትዮጵያ ያለው የኑሮ ውድነት እንዴት ይገለጻል?
እንግዲህ አስቀድሜ እንደተናገርኩት የነዳጅ፣ የማዳበሪያና መሰል የማምረቻ ግብአቶች መወደድን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ለተከሰተው  የዋጋ ንረት ሁሉም አመላካቾች መንስኤ ናቸው ወይም ሁሉም ተከስተዋል፡፡ ሁሉንም የሚለካው ጂዲፒ ዲፍሌተር ነው፡፡ ጂዲፒ ዲፍሌተር ማለት አምና የተመረተው ምርት በዋጋ ተሰልቶ፣ ዘንድሮ የተመረተው ምርትም ራሱን ችሎ በዋጋ ተለክቶ፣ የዘንድሮውን ለአምናው በማካፈል የሚገኘው ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ሁሉም ነገር ጨምሯል፡፡ ለዚህ እንግዲህ ዋናው ምክንያት ሁለት ሲሆኑ አንዱ የገንዘብ  በገበያ ውስጥ መብዛት ነው፤ ሌላኛው የኢኮኖሚ ንዝረቶች ማጋጠማቸው ነው፡፡ የኢኮኖሚ ንዝረቶች ስንል ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ የመሳሰሉት ናቸው የሚፈጥሩት፡፡ በገበያ ውስጥ ያለውን የገንዘብ ዝውውር ስንመለከት፣ በየአመቱ ከፍተኛ ጭማሪ  ነው እያሳየ ያለው፡፡ ለዚህ በቂ ማስረጃዎች አሉ፡፡
የሸቀጦች ዋጋ ንረት በጣም ፈጣንና ቅፅበታዊ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው?
ይሄ ትንሽ ከባድ ነው፡፡ የገንዘብ መብዛት ነው እንዳልል  ከ10 እና 20 ዓመት በፊት ጀምሮ የገንዘብ  ዝውውሩ በ29 እና  በ30 በመቶ እያደገ ነው የመጣው፡፡ የኢኮኖሚ ንዝረቶች ናቸው እንዳልል ንዝረት በፊትም ነበረ፤ እንዳሁኑ አልባሰም እንጂ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ብዛቱ 120 ሚሊዮን ነው። ዘይት፣ ስኳርና ዳቦ የመሳሰሉትን ከ120 ሚሊዮን ህዝብ ዛሬ ላይ ተጠቃሚው ምን ያህል ነው? ዳቦስ የሚበላው ምን ያህል ነው?  የገጠር ህዝብ እኮ ዛሬም ሻይን፣ስኳርን የማያውቅ አለ፡፡ በአጠቃላይ ግን አሁን ባለንበት ቀውስ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ወደ ከተማ ወጣቶች ሲሰደዱ ስኳር፣ ዘይት፣ ዳቦና ሻይ፣ ጁስ መጠቀም  ይጀምራሉ፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ሸቀጦች ዋጋ  ሳይወድ በግድ ይንራል፡፡ ዘይት፣ ዳቦ፣ ስኳር ተጠቃሚው በየጊዜው በፍጥነት ሲጨምር የዋጋ ንረቱም ፍጥነት ተጠባቂ ይሆናል፡፡ እኔ እንደውም መጪውን ጊዜ አስፈሪ ከሚያደርጉብኝ ምክንያቶች አንዱ፣ ከ120 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ ለ30 ሚሊዮን ህዝብ እንኳን ፍላጎት ሳናረካ፣ በቀጣይ 120 ሚሊዮን ህዝብ ፈላጊያቸው የሆነ ቀን ምን ይውጠናል የሚለው ነው፡፡ ሰው ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ፣ በተፈጥሮ የህዝብ ቁጥር ሲጨምር ምን ልንሆን ነው? እነዚህን የምግብ ሸቀጦች ብቻ አይደለም ማየት ያለብን፡፡ የገጠር ህዝብ እኮ ዛሬም መደብ ላይ ነው የሚቀመጠው፣መሬት ላይ ነው የሚተኛው፤ ነገ እኮ እሱም  ወንበር ላይ ሶፋ ላይ፣ አልጋ ላይ መተኛት ይፈልጋል፣ በጣሳ መጠጣት ትቶ በብርጭቆ መጠጣት ይፈልጋል፡፡ ከዚህ  አንጻር የትኛውን ፍላጎት ነው ማሟላት የተቻለው ታዲያ፡፡ አሁን እኮ ገና ለ30 ሚሊዮን ህዝብ እንኳ ፍላጎት ማሟላት አልተቻለም፡፡ ለወደፊት ምን ይሆናል የሚለውን ሳስብ ትንሽ ይከብደኛል። አሁን ባለው አያያዝ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብዬ ራሴን መሸንገል አልፈልግም፡፡ ወደ ተሻለ ነገር እየሄድንም አይመስለኝም፡፡
እንዴት?
አንደኛ በህዝብ ደረጃ ዛሬ ህዝብ ያለችውን ምርት ሽሚያ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሸመታ ሳይሆን ሽሚያ ውስጥ ነው ያለው። ውድድር ጠፍቶ ሽሚያ ነው የነገሰው፡፡ አንዱን ሌላውን ለመንጠቅ የተቻለውን ጥረት ያደርጋል፡፡ ሙስና ለዚህ ነው የተስፋፋው። አንድ ነጋዴ ዘይት የሚደብቀው የሽሚያ መንገድ ስለሆነ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ብዙዎቹ የሽሚያው አባል አይደሉም፡፡ ጡረተኞች፣ የመንግስት ሠራተኞች የዚህ የሽሚያው አካል አይደሉም፤ መሆንም አይችሉም፤ ከሽሚያው የተረፈውን ካገኙ ነው፡፡
የኢትዮጵያን የምጣኔ ሃብት አስጊ የሚያሰኙት  ሁኔታዎች  ምንድን ናቸው?
አንዱ አስቀድሜ ያልኩት፣ በተለይ ከ120 ሚሊዮን ህዝብ 30 ሚሊዮኑ እንኳ በኑሮ ያልረካ መሆኑ፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ በርካቶች (ሚሊዮኖች) አዳዲስ ፍላጎትን እያዳበሩ የሚመጡ መሆኑ፡፡ ለዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂው የሚጫወተው ሚና ተጠቃሽ ነው፡፡ ሌላው ደሞዝ ሃገር ውስጥ ካለው የሸቀጥ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ መሆኑ፡፡ በእርግጥ አብዛኛው የመንግስት ሠራተኛ ምርታማ አይደለም፡፡ በገቢ ደረጃም ዝቅተኛ ነው፡፡ የአንድ ሚኒስትር ደሞዝ እኮ የ3 ኩንታል ጤፍ ዋጋ ብቻ ነው፡፡ ይሄ የደሞዝ ሁኔታ ግን ነገ የአመፅ  መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ በዋጋ አወሳሰናችን ገና አለማቀፍ ስታንዳርድ አላሟላንም። ስለዚህ የደሞዝ  ሁኔታም ገና ከገበያው ጋር አልተመጣጠነም፡፡ ይሄ በጣም አስጊ ነው፡፡  አሁን ዜጎች በስደት መከራ እየበሉ ያለበት ምክንያት ከዚሁ ከሠራተኛ ዋጋ ማጣት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ዛሬ እኮ  የአራት ሺህ ብር ደሞዝተኛ የሆነ ወጣት ብቻውን ከሚኖር ከእናት ከአባቱ ጋር ቤት ተጋርቶ፣ ኑሮ ተጋርቶ መኖርን ነው የሚመርጠው፡፡ እንደዚህ አይነት ዝቅጠት ውስጥ  እየገባን እንደሆነ፣ ምን ያህል ሰው አውቆት ተረድቶት ይሆን? እኔ እንደ ኢኮኖሚስት መጪው ጊዜ የሚያስፈራኝ፣ ከእነዚህ ሁለት ነገሮች አንጻር ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ወደ አለማቀፍ ግብይት መግባታችን ስለማይቀር የሸቀጦቻችን ዋጋ የሚወሰነው፣ በኛ ሃገር ውስጥ ባለው ብቻ ሳይሆን ውጪ ባለው ገበያ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ቡና የተወደደው ለምንድን ነው? ከውጪ ካለው ገበያ ጋር ነው፣ የሃገር ውስጥ ገበያው የሚወዳደረው፡፡ ለዚህ ነው፣ ቡና ጥራጥሬ የመሳሰለው ዋጋ የሚንረው፡፡ በወር 40 እና 50 ሺህ ብር ከሚያገኙ የውጭ ሃገር ሰዎች ጋር ነው ቡና እየተሸማን ያለነው፡፡ እኛ 1 ሺህ ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ ይዘን ነው ወደ ገበያ የምንመጣው፤ እነሱ 20 ሺህ 30 ሺህ ዶላር ይዘው ነው የሚመጡት፡፡ ታዲያ እንዴት እንመጣጠናለን?
ሰዎች አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ምን ማድረግ አለባቸው?
በመጀመሪያ ባለቻቸው ገንዘብ እጅግ የሚያስፈልገን ነገር ምንድን ነው ብለው መምረጥ አለባቸው፡፡ ይሄ ሲሆን በስንት ጥረት ኪስ ውስጥ የገባችው ገንዘብ እንዳትባክን ይረዳል፡፡ ከእንጀራና ከጫት መካከል ማንን ትመርጣለህ? ከመኪናና ቤት ከመገንባት የቱን ትመርጣለህ? ቀን ሃብታም መስለህ መኪና ይዘህ መዋልና ማታ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ መግባት ይበልጣል ወይስ ጽድት ያለ ቤት መኖር? ቁርጥ ሥጋ እየበሉ መዋል ይሻላል ወይስ ጤፍ ሸምቶ መብላት? ከእነዚህ የተሻለውን መምረጥ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱን ብር ጠቀሜታውን እየለካ ነው ማውጣት ያለበት፡፡ ሸማቹ አዛዥ ነጋዴው ታዛዥ እንደመሆኑ፣ ነጋዴውን መምራት ያለበት ሸማቹ ነው፡፡ መንግስት የመደገፍ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት፤ ግን ይሄን ሃላፊነቱን ሲወጣ አይታይም፡፡ በአጠቃላይ በሃገሪቱ ምርታማነት እየሞተ ነው፡፡ ምርታማነት ከሞተ፣ ምርት እንደ መና ከሰማይ አይወርድም፡፡

Read 12458 times