Saturday, 30 April 2022 12:23

በዓል ሽሮ የከበረ፣ ጾም ገድፎ የወፈረ የለም!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ከዕለታት አንድ  የቅዳሜ ሹር ለት፣ ቤተ ክርስቲያን የ“ፈስኩ” ደውል ከተደወለ በኋላ፣ የአንድ ቤተ-ሰብ መላው አባላት እቤት ተሰብስበዋል፡፡ የመጀመሪያው ወንድ ልጅና የመጨረሻ ትንሿ ሴት ልጅ፣ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ሄደው እናትና አባታቸውን ይዘው ነው የመጡት። መካከለኛውና ሞገደኛው ወንድ ልጅ ግን ቤት ተኝቶ ነበርና በመከራ ተቀስቅሶ ነው ወደ ገበታው የቀረበው!
እንደተለመደው አባት እንጀራውን እየቆረሱ፣ “የተባረከ ይሁን!” እያሉ ለሁሉም  ሰጡ፡፡ ቀጥሎም ያው  እንደተለመደው ለአባ-ወራው ፈረሰኛ ወጣላቸው፡፡
ሞገደኛው ልጅ - “እኛስ?” አለ
እናት - “እንግዲህ ነገር አታምጣ - በተራህ ይሰጥሀል” አሉት፡፡
በድንገት አንድ ጥቁር እንግዳ፣ የአባትየው ጓደኛ ከተፍ አሉ፡፡
ሞገደኛው ልጅ - “ይሄውላችሁዋ እንደፈራሁት!; አለ
እናት - “እንግዲህ እረፍ ብዬሀለሁ፡፡ ዶሮው እንደሆነ ለአስር ሰውም ይበቃል!”
ሞገደኛው ልጅ - “ለእኔ በጊዜ ድርሻዬን ስጡኝ። ገና የእማማ ነብስ አባት ከች ይሉላችኋል!”
ከደጅ ድምጽ ይሰማል፡፡
“እንደምን አመሻችሁ?” አሉ፡፡
“ደሞ መምሬ ሞገስ መጡላችሁ! እሳቸው ደግሞ ያገሬ ዲያቆን አስከትለው ነው እሚመጡት”
ዕውነትም መምሬ ሞገስ አራት ዲያቆናት ይዘው ነው የመጡት።
አባት - “ይባርኩልና መምሬ!?”
መምሬ ሞገስ ተነስተው መድገም ጀመሩ፡፡
ሞገደኛው ልጅ ፀጉሩን ነጨ፡፡  ምን ማድረግ ይችላል? ምንም አስቸጋሪ ልጅ ቢሆንም፣ የአገር ባህል ይገባዋል፡፡ ባህልን ትኖረዋለህ እንጂ አትማረውም!
“እስቲ ደህና አርፌ የተኛሁትን ቀስቅሳችሁ ትጫወቱብኛላችሁ” አለ ወደ አባቱ እያየ።
አባቱም፤
“ለአንድ ሌሊት ብትነቃ ምን ትሆናለህ? በዓል ሽሮ የከበረ፣ፆም ገድፎ የወፈረ የለምኮ!” አሉት፡፡
አርፎ ዶሮዋን መጠበቁን ቀጠለ፡፡
ዶሮይቱ ሙሉ በሙሉ እንደቀረበች፣አባትዬው፤
“በሉ እንደተለመደው የምትፈልጉትን ብልት  ተናገሩ?” አሉ፡፡
የመጀመሪያው ወንድ ልጅ፤
“አባዬ ለእኔ እንደተዳረሰላችሁ ይሰጠኝ”
የመጨረሻዋ ሴት ልጅ፣
“ለእኔ ቆዳዋም ቢደርሰኝ ደስ ይለኛል!”
ሞገደኛው ልጅ፤
 “ከየአንዳንዳችሁ ትንሽ ትንሽ!”
አባት፤
“አንት የማትረባ! የራስህ ምርጫ የለህም?; ብለው ተቆጡ።
ሞገደኛው ልጅ፤
“ምርጫ አለኝ ግን ያንሰኛል ብዬ ነው! በዛ ላይ የእናንተ ድርሻ (ምርጫ) ምን ምን እንደሚል ባውቅ ምናለበት?” አለ ይባላል፡፡
*   *   *
በማንኛውም መንግስት ዘንድ የህዝቡን ፍላጎት  ይሁነኝ ብሎ ማወቅ ዋና ነገር ነው፡፡ ያ ደግሞ ዋና ፍሬ ጉዳይ ነው የሚያሰኘው የህዝቡን ባህልና ልማድ መሰረት ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ፖለቲካውና ኢኮኖሚው ላይ  ስናነጣጥር፣ ባህልን ቸል የማለት አዝማሚያ ይታይብናል። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ግን የሁሉም መጠቅለያና መሰብሰቢያ የህዝቡ ሥነ-ልቦና፣ አኗኗሩና ማህበራዊ እሴቱ ሆኖ እናገኘዋለን! ዕምነቱ፣ ትውፊቱ፣ አፈ-ታሪኩ፣ ተረቱ፣ ቅኔው ወዘተ ከየትም አይፈልቅም፤ ከባህላዊ ሕላዌው ነው፡፡ ለቅሶው፣ ሙሾው፣ ዘፈኑ፣ዜማው፣እስክስታው፣ዜማውና የሠርግ ሥነ-ሥርዓቱ ከየትም አይመጣም፡፡ ስረ ነገሩ ባህል ነው፡፡ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጠበብት፤ሁሉም ፖለቲካ፣ሁሉም ኢኮኖሚ በባህል ይንፀባረቃል ይበሉን እንጂ፣ አንዳንዴ ባህል ራሱን ችሎ የሚቆም ፅንሰ ሀሳብ ሆኖ የምናገኝበት ጊዜ ሊኖር  እንደሚችል በፍጹም አንዘንጋ! ኢትዮጵያ ደግሞ የዚህ ባለቤት ናት፡፡
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፤ “መንግስትና የሕዝብ አስተዳደር” በተባለው መፅሐፋቸው ላይ፤
“በየአንዳንዱም መንግስት የሚያድሩ ብዙ ልዩ ልዩ ነገዶች ይኖሩ ይሆናል፡፡ ስለ፣ ሆነ መንግስት አንዱን ነገድ አጥቅቶ ሌላውን ነገድ ለመጥቀም ሥራው አይደለም፡፡ አስተካክለን ካሰብን ዘንድ መንግስት መቆሙ ለህዝቡ ሁሉ ጥቅም ነውና፣ መንግስት ሕዝቡን ሁሉ ለመጥቀም በትክክል ካላሰበ በዙፋኑ ሊቆም አይችልም፡፡ ላንዱ ነገድ ወይም ለጥቂት ሰዎች ብቻ ማድላት ለመንግስት የሚገባ ሥራው አይደለም፡፡; ይሉናል፡፡
በተደጋጋሚ እንደተጠቀሰው የዲሞክራሲ ረሃባችን፣ከምግብ አቅርቦት ረሀባችን ጋር ሳይነጣጠል እያጠቃን ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ማእቀፋችን፤ ከኢኮኖሚያዊ አንቀልባችን ጋር ተወዳድሮ  በአንድ ሁነኛ ማሰሪያ መቋጠር ይኖርበታል፡፡
“የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብቱና ዕውቀቱ ሊያድግ ሲጀምር ዘወት ባገሩ  ሁከትና ጦርነት ይነሳል” (ነጋድራስ ገ.ሕይወት ባይከዳኝ)
ዛሬም ይሄው አጣዬና ሸዋ ሮቢት ጦርነት ነው፡፡ ሰው ወደ ደብረብርሃን መሰደዱን ተያይዞታል። ሰሜን ሸዋም እዚያው አረንቋ ውስጥ ነው፡፡ ተሻለው ሲባል ማገርሸቱ እንደ ባህል ተቆጥሯል፡፡ የመከላከያ ኃይሉን እንደ አዲስ ማስተማር ያስፈለገበት ጊዜ መሆኑ፣ ቢያንስ የቀጠናውን የጦርነት ስጋት ያመለክታል፡፡
“ሁሉ ነገር ይለወጣል፤ ከለውጥ ሕግ በስተቀር” (Everything changes except the law of change) የሚለው የጥንት ንድፈ-ሀሳብ እየተጫነን መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ ለውጥ ሲሸታት የኑሮ ውድነትን ታስቀምጣለች።  ድርቋን ትሸሽጋለች፡፡ መሪዎቿ ዲስኩር ያበዛሉ፡፡ አዳዲስ የለውጥ ሕግ ሊያስተምሩን ይሞክራሉ፡፡ ድንቅና ተዓምረኛ ለውጥ ነው እያሉ ሲያስረዱን ቆይተው፣ “ገና ዛሬ ነው ያለቀው” ይሉናል፡፡ እንደተለመደው ኮሪያና ቻይና አርአያዎቻችን ሆነው ይጠቀሳሉ። “ቁልቋል የወደቀው ቅርንጫፍ ያበዛለት ነው” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር፣ ለመከላከያም፣ ለፖለቲካ ካድሬም፣ የሠራዊትን ከፖለቲካ መለየትም ድንገት እንደብራ መብረቅ ዱብ ዕዳ አድርገን ማየት የወቅቱ አቅጣጫ ነው፤ እንባላለን፡፡ ለማንኛውም ቅድም ተከተልን የመሰለ ለአገር የሚበጅ ጥበብ የለም! ለማንኛውም በዓል ሽሮ የከበረ፣ ፆም ገድፎ የወፈረ የለም!  

Read 12004 times