Saturday, 30 April 2022 12:58

ሩሲያና ዩክሬይን - ግን አሜሪካ የት ነች?

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ- ቤተሳይዳ ሜሪላንድ አሜሪካ
Rate this item
(2 votes)


                ያለቀው ወይስ
ያልተጠናቀቀው ቀዝቃዛው ጦርነት?
 በ1992 ዓ.ም እ.ኤ.አ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤች ቡሽ ለመላ ሀገሪቱ ደስታ እየተናነቃቸው ባደረጉት ንግግር (State of the Union)፤ “በህይወቴና በምንኖርበት በዚህ ጊዜ ታላቅ ነገር ሆነ፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ቸርነት አሜሪካ የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነትን አሸነፈች፣” ብለው ነበር የጀመሩት፤ “በሁለት ወታደራዊ ቀጣናና ካምፖች ተከፍላ የነበረችው ይህች ዓለማችን አሁን ግን አንድ ብቸኛ ሀይል ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ መሆኗን አወቀች፣” ብለው አሰመሩበት። እና በእርሳቸው ፕሬዚዳንታዊ ዘመንም “አዲሱ የዓለም ስርዓት” (New world order) ተጀመረ ተብሎም ተበሰረ። ከሦስት አስርታቱ ዓመታት በሁዋላ ግን ያ የፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ አገላለጥ ፈተና ገጠመው፡፡ በዚህ ውጥረቱ በበዛበት ሰሞን - ጦርነቱ በጋመበት ጊዜ የታሪክ ተመራማሪዎችና ልሂቃንም በየሸንጎውና በየመድረኩ “የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት በእውኑ አብቅቶ ነበርን?”  ሲሉ ወትዋችና ሞጋች ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ፡፡
ወደ ሁዋላ መለስ ብሎ ታሪኩን ለፈተሸው የሁለቱ ፊናዎች ፍትጊያና በወኪል ሲያደርጉት የነበረው መገፋፋትና መጠፋፋት ከበርሊን ግንብ መፍረስ - እስከ አስራ አምስቱ የሶቪየት ህብረት ሪፑብሊክስ መለያየት ወይም መበታተን ድረስ ተጉዞ በርካታ ክስተቶችን አስከተለ፡፡ ወዲያውም በብቸኝነት ርዕሰ ሃያል የሆነችው ዋሽንግተን፣ ተከታዩን ዘመን በመዳፏ ጨብጣ ለመጓዝ ያለመችበትም ጊዜ ሆነ። የያኔው ፕሬዚዳንቷ “አሸናፊ ሆንን” ሲሉ የምዕራቡን ዓለም በፊታውራሪነት ስትመራ የነበረችው  አሜሪካም በብቸኝነት ዓለምን እንደምትፈልገው ልትዘውራት እንደወሰነችም አመልካችም ነበር። እና ወታደራዊ ልሂቃን፣ የውጭ ፖሊሲ ቀራጽያንና ምሁራኑን ያካተተ መጠነ ሰፊ ጥናትና ትንተና በመጻኢው የዓለም እጣ ፈንታ ዙሪያ - በተለይ ደግሞ  አሜሪካ ሊኖራት የሚገባውን ሚና በተመለከተ ሲያቀርቡ ቆዩ፡፡ ይህም ሂደት እስካሁንም የቀጠለ ነው፡፡
የምስራቁና የምዕራቡ ግድግዳ በፈረሰበት ጊዜ ሩሲያ በራስዋ የውስጥ ጉዳይ ተጠላልፋ የነበረችበት፣ ኢኮኖሚዋም በእጅጉ የቁልቁል የተጓዘበት ጊዜ ነበር፡፡ እና ሀገራትም በየራሳቸው አካባቢ ወይም ሪጅን ጡንቻቸውን ለማሳደግና በዓለም ሚዛን ውስጥ ‘አሉ’ ለመባል ውድድር የጀመሩበትም ሁኔታም መከሰቱ አልቀረም፡፡ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ተጠናቀቀ ቢባልም፣ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልሆነም፡፡ ከቶም መደናገሩና አዳዲሱ የቅራኔ ምንጭ ያልተጠበቁ ክስተቶችን ይዞ ከች አለ፡፡ እና ዛሬ ሦስት አስርታቱ ዓመታት አልፈው ጥያቄዎችን አነሳን። አሜሪካ ከቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት በኋላ፣ ሩሲያን የመክበብና የማዳከም ዘመቻ እንደ ፖሊሲ ትከተል ነበርን? አሜሪካና የሰሜን ቃል ኪዳን ሀገሮች የሩሲያን የቆየ ‘የመስፋፋት ህልም’ እንዳያንሰራራ ለመምታት እንደ ፖሊሲ በህቡዕና በእጅ አዙር ሲተገብሩ ቆይተው ይሆን? ከቶውንስ ሩሲያ ከሶቪየት ህብረት መፍረስ የተጎዳችውና አሻግራ የምታልመው ተመልሶ የመግነንና በርዕሰ ሀያልነት ተርታ የመሰለፍ ህልም ለማሳካት ወቅቱ አሁን ነው በሚል የቀሰቀሰችው ጦርነት ነውን? የሚሉትንና ሌሎች ጥያቄዎችን እያነሱ መፈተሽም ተጀመረ፡፡ በተለይ ሩሲያ ይፋ ጦርነትን በዩክሬይን ላይ ካወጀች በሁዋላ ፍተሻው በብርቱ ተይዟል፡፡
ሩሲያ ወደ ጦርነቱ እየተክረተረተች በነበረበት ጊዜ የፕሬዚዳንት ፑቲን መንግሥት የአውሮፓንና የሩስያ ደህንነትን በተመለከተ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት በሰጡት ባለ አሥራ አንድ ገጽ ምላሽ ላይ ሁለት አንኳር ነጥቦችን አንስተዋል። አንደኛው ዩክሬይን መቼም ቢሆን፣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወይም ኔቶ  አባል እንዳትሆንና ይኸው ወታደራዊ ትብብር ማለትም ኔቶ ያሰፈረው ወታደራዊ ሀይልና ሰራዊት ከ1997 ዓ.ም. በፊት ወደ ነበረበት ድንበር መመለሱን አበክሮ ይጠይቃል፡፡ ይህን ብሎ ብቻ አያቆምም - ኔቶ አሜሪካና የቃል ኪዳን ወዳጆቿ፣ ይህን ላለመቀበል አሌ ካሉ “ሩሲያ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የምትገደድ” መሆኗን ያሰምራል፡፡ ይህን ጠንከር ያለ ምላሽ ሲመለከቱት፣ በ1990ዎቹ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት አክትሟል የሚለው አዋጅ ስህተት ነበርን? አሰኝቷል፡፡ ሞስኮን እንደ ዋነኛ ግዙፍ ሃይል የመቁጠር ይልቁንም በእኩልነት ከምዕራቡ በተለይ ከአሜሪካ ጋር የመታየት ፍላጎትና ምኞት እንደሌላት አድርጎ መገመት ስህተት መሆኑንም የዛሬው ክስተት አመልካች ነው፡፡ እርግጥ ነው ፍራንሲስ ፉኩያማ እንደሚሉት፤ “በርዕዮተ ዓለም ዙሪያ የተጠነጠነውና የተመሰረተው ውጊያ አሁን ይብልጡኑ በተለመደው የጂኦፖለቲካዊ ውድድር ተተክቷል፡፡”
የሩሲያና የዩክሬይን ግጭት ወደ ሌሎቹ እንዳይዛመት ተገቢ ስጋት አለ፡፡ ሩሲያ ከዓመት በፊት የቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት ሪፑብሊክ የነበረችው ቤላሩስ፣ የኒውክሌር መሳሪያ እንድትተክል ፈቅዳ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አድርገው ነበር። ቤላሩስ የምታዋስናቸውንና የኔቶ አባል የሆኑ ሦስቱን አገራት፡- ፖላንድ፣ ሊቱአኒያና ላትቪያን  ማስታወስ ይገባል፡፡
ሩሲያ በዩክሬይን ላይ ጦር ሰበቀች - አሜሪካስ የት ናት?
“አሜሪካ ሩሲያን የምትዋጋው እስከ ዩክሬን የመጨረሻ ደም ጠብታ ነው” - አሉ ቻስ ፍሪማን፤ የቀድሞ የዩኤስ ከፍተኛ ባለስልጣንና ዲፕሎማት በስላቅ፡፡
ይህን መጣጥፍ እየጻፍኩ እያለሁ በሩሲያና በዩክሬይን መካከል ያለው ጦርነት እጅግ በከፋ መልኩ ቀጥሏል፡፡ ጦርነቱ ማብቂያ ጭላንጭልም የማይታይበት እንደሆነም ቀጥሏል፡፡  የሰላምና የድርድር ሀሳብ የሚያነሱ አለመኖራቸውም ይበልጡኑ መፃኢውን ጊዜ ፅልመት አልብሶታል።  አሜሪካና የቃል ኪዳን ሀገራቱ (የኔቶ አባል ሀገራት ማለቴ ነው) ሰላም ሊያሰፍኑ የሚያስችሉ መንገዶችን ከመጥረግ ይልቅ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በመስጠትና በስነልቡና ጦርነቱ አይዞን ማለቱን ተያይዘውታል።  በርዕሰ ሀያሏ ሀገርም ይሁን በሪጅናል ሀያሎቹ ዘንድ ይህን መሰል የጦር አውዶች፣ የጦር መሳሪያ መፈተሺያና አንዱ የሌላውን አቅም የመገምገሚያ አጋጣሚ አድርጎ የመገመት ሁኔታ ብዙ ጊዜ ይስተዋላል። አሜሪካ ወደ ቬትናም ጦርነት ገብታ መውጫ ባጣችበት ጊዜ፣ ሶቪየት ህብረትና መሰሎቿ  በር ዘግተው የሳቁበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሶቪየት ህብረት ደግሞ አፍጋኒስታን ገብታ በምትጨነቅበት ጊዜ፣ አሜሪካ እንዲሁ “ሶቪየት ቬትናሟን አገኘች’” ያለችበትም ሁኔታ ነበር፡፡ በቅርብ እርቀትም - አሜሪካ ኢራቅ ገብታ ማጣፊያው ሲቸግራት - ሩሲያ፣ አሁን ደግሞ ሩሲያ ከዩክሬይን ጋር ከጦርነት መጓተት ውስጥ ስትገባ - አሜሪካ ጨዋታቸውን የቀጠሉበት ይመስላል፡፡
በዚህ ጦርነት ዙሪያ የምዕራቡ ዜና ሽፋን፣ ሩሲያ ካላሰበችው አረንቋ ውስጥ ገብታለች የሚል ትርክት ያዘለ ነው፡፡ በስነ ልቡና ጦርነትና የዓለምን የፖለቲካ ትርክት በሞኖፖል የያዙት ምዕራባውያኑ፣ በገዛ ምድራቸው የተሳካላቸው ቢመስልም፣ ወጣ ባሉት እንደ አፍሪቃና እስያ ባሉት ክፍለዓለማት ስለዩክሬይን ግጭት ያቀረቡት ትርክት ውሃ የቋጠረ አይመስልም። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት እንደውም፤ የሩሲያ ትርክት ቦታ እየያዘ የመምጣት ዝንባሌ ታይቷል። በምዕራባውያኑ - ራሳቸውን የነፃ ፕሬስና የዲሞክራሲ ምሳሌዎች ተደርገው በሚቆጠሩበት ሀገራት ዩኤስ አሜሪካን ጨምሮ፣ ከዘጠና በመቶ የሚሆነው ዘገባና ሽፋን በሩሲያ ላይ አሉታዊ የሆነና የጦርነቱንም ገጽታና ውጤት ለ’ዩክሬን’ ድል እያጎናጸፈ መሆኑን የሚዘረዝር ነው፡፡ ሩሲያ በዩክሬይን ላይ የከፈተችው ጦርነት ‘ድልን’ አላስገኘላትም የሚል ጥቅል አገላለፅ ያለውም ነው፡፡ ይሁንና የሩሲያን ወታደራዊ እርምጃ አልተሳካም ብሎ ለማለት እቅዱና እደርስበታለሁ ወይም ይሁነኝ ያለው ግብ ይህ ነበረ ብሎ ማቅረብን ይሻል፡፡
ሩሲያ ወደዚህ የ’ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ’ የዘለቀችው ጎረቤት ሀገር ዩክሬይን ለሀገራዊ ደህንነቴ አስጊ የሆኑ ግንኙነቶችን ከምዕራባውያን በተለይም ከሰሜን አትላንቲክ ወታደራዊ ቃል ኪዳን ሀገራት ጋር አባል ለመሆን እየተክተረተረች በመሆኗና በዩክሬይን የሚገኙ ሩሲያውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚል ነው፡፡ ይህ ሩሲያ በይፋ የምትላቸው ምክንያቶች ተደምረው የዩክሬይንን ግዛት መቆጣጠር የሚል አንድምታ ግን የለውም። የሆነው ሆኖ ጦርነትን የሚያስጀምር ኹነት ወይም ክስተት አንድ ሊመስል ይችላል፡፡ በዚያ ላይ ብቻ ተጠንጥኖ ጦርነቱ ይካሄዳል ማለት ግን አይደለም፡፡ በግጭት ውስጥ አንዱ ሌላውን እየሳበና እየተሳሳበ የሚገባበት ወጥመድና ዋሻ እጅግ አደገኛና ብዙውን ጊዜ የማይታሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ በሳምንታት ዕድሜ የተባለው ዓመታትን አከናንቦ የጦርነት መጨረሻው ደብዛው ጠፍቶ - ኑሮ የሆነበት ሁኔታ ሲፈጠር ተመልክተናል፡፡
የበርዠንስኪ ምልከታና - ትንቢት መሰል
ምክር ከ25 ዓመታት በፊት፤
ዝቢግኒው በርዠንስኪ የቀድሞ የፕሬዚዳንት ካርተር የብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ የነበረ ከቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት በሁዋላ አሜሪካ ብቸኛ የዓለም ርዕሰ ሀያል ሆና እንድትቀጥል የሚያስችላትንና ልትጠነቀቅባቸው የሚገቡዋትን የሚያመለክት መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል። ከሀያ አምስት ዓመታት በፊት የታተመው ይህ መጽሐፍ “ታላቁ የቼዝ ሰሌዳ - የአሜሪካ ቀደምትነትና የጂኦስትራቴጂያዊ ትዕዛዛት” (Grand Chessboard: American Primacy and its Geostartegic Imperatives) ይላል ርዕሱ፡፡
በርዠንስኪ በመጽሐፉ የአሜሪካ የበላይነትን ከቀደምቶቹ ሮማውያን፣ ቻይናውያን፣ ሞንጎላውያንና ብሪታኒያውያን ጋር በማመሳከር የአሁኑ የአሜሪካ የበላይነት በኤኮኖሚ፣ በወታደራዊ፣ በቴክኖሎጂና ይልቁንም በባህላዊ ጫና የተገኘ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡ እንደ በርዠንስኪ አገላለጽ፤ ለአሜሪካ ባላንጣ የሚነሳባት ከአውሮፓና ከእስያ በደራሲው አገላለጥ ከዩሬዥያ (Eurasia) ነው፡፡ ስለዚህም ዋሽንግተን ለዚህ ስጋት ናቸው የሚባሉትን ለይታ በማወቅ ፖሊሲን በመቅረጽ ከወዲሁ ‘ሥራዎችን’ መሥራት እንደሚገባት ነው የሚያብራራው፡፡ ለአሜሪካ የበላይነት ፈተናዎች የሚመጡባቸውና አቢይ የጂኦፖለቲካ ዋነኛ ማጠንጠኚያ (geopolitical pivot) የሚላቸውንም ሲዘረዝር በቀዳሚነት ያሰፈረው ዩክሬይንን ነበር፡፡ የሩሲያ የመስፋፋትና የበላይነት ህልም እውን እንዳይሆን በዩሬዥያ፣ በቀዳሚነት ዩክሬይን ከዚያም የባልቲክ ሀገራት የሚባሉት ትኩረት እንደሚሹ ነው የሚገልጠው። በነገራችን ላይ የባልቲክ ሀገራት የሚባሉት ኤስቶኒያ፣ ላትቪያና ሊቱአኒያ ናቸው፡፡
ዩክሬይንን ለምዕራቡ ቀራቢና ቆራቢ የማድረግ ሂደት አስፈላጊነትነትን ምሁሩ ያሰምርበታል፡፡ በተለይም የዩክሬንን ብሄረተኝነት ማሳደግና የ’ተለየ’ ማንነት ከሩሲያ ያልተጣባና ያልተነካካ - ኩሩና የተነጠለ የማድረግ ሥራም ጎን ለጎን የመካሄዱን አስፈላጊነትም ይጠቀሳል፡፡ የቀድሞው የሶቪየት ህብረት የወዳጅነት ልምድ የሌለበትና ሌላውን አዲሱን ትውልድ የመያዝ ብልሃትን ወደጎን የሚተውም እንዳልሆነ ነው፡፡
ዩክሬይንን በተመለከተ በዩኤስ አሜሪካ ሌላው ታዋቂ የውጭ ጉዳይ ሰብዕና ሚስተር ሄነሪ ኪሲንጀር - የምስራቅና የምዕራቡን ዓለም የምታገናኝ ድልድይ ማድረግ እንደሚቻል የተናገሩበት፣ እንደውም በቀጣናው ዩክሬይን የፊንላንድን ዘይቤ እንድትከተል የመከሩበት መጣጥፍ በ2014 ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ላይ ተነቦ ነበር፡፡ ይህም አካሄድ ዩክሬይንን ሆነ ምዕራቡን ዓለም ከሩሲያ ጋር አዙሪቱ ካልታወቀ የባላንጣነት አዙሪት ይታደጋል በሚል ነው፡፡ በበርዥንስኪ ሥራ ውስጥ ግን ይህ እሳቤ ብዙም አይስተዋልም፡፡ ይልቁንም ከቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት በሁዋላ የአሜሪካንን ሀያልነት ለመጠበቅና ለማጽናት የጂኦፖለቲካ ማጠንጠኛ ዋነኛ የፈተና ክሂሎች ብለው በአቢይነት ከጠቀሷቸው አንዷ ናት ዩክሬይን። የጂኦስትራቴጂው ዋነኛ ማጠንጠኛና ማዕከል የማድረግንም አተያይ ነው በመጽሀፋቸው የሚያሳዩት፡፡ እንደ በርዠንስኪ አገላለጥ፤ ድህረ ቀዝቃዛ ጦርነት የጂኦፖለቲካ ማጠንጠኚያ ከሚሏቸው ዋነኛ የዩሮኤዥያ ሀገራት መካከል ዩክሬይን ዋነኛ ስትሆን የአሜሪካ የዓለም አቀፍ የጂኦስትራቴጂ የሚያርፍባትም እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ በርዠንስኪ ሩሲያ ያለዩክሬይን የዩሮኤዥያ ኢምፓየር መሆኗ ያከትማል ባይ ናቸው፡፡ “ሞስኮ 52 ሚሊዮን ሕዝብ ያላትን ዩክሬይንን እስከነተፈጥሮ ሀብቶቿና ከጥቁሩ ባህር ያላትን መንገድ መቆጣጠር ከቻለች ከአውሮፓ እስከ እስያ የሚዘረጋ ሀያል የመሆን ዕድሏ፣” እንደሚሰፋም ያሰምሩበታል፡፡
ሩሲያ በባልቲክ ባህር ላይ ያጣችውን የበላይነት በጥቁሩ ባህር (Black Sea) ደግሞ በዩክሬይን ነፃነት ሰበብ በአቢይነት ማጣቷ ቀላል ተብሎ የማይገለጽ አለመረጋጋት ውስጥ ይከታታል - ከቷትም ነበር፡፡ የሩሲያ ባህር ሀይል እስከ ሜድትራኒያን ድረስ ዋነኛ መናኸሪያው አድርጎበት ሀይሉን ከሚያሳይበት ጥቁሩ ባህር በ1990ዎቹ ዓመታት በእጅጉ መቀነሱ የፈጠረው ስጋት የሁዋላ ሁዋላ በ2014 ክራይሚያን ከመቆጣጠር ጋር ቀና ማለት የጀመረና እስካሁኑ ለዘለቀው ወታደራዊ ተልዕኮ ያንደረደረ አቢይ ጉዳይ ነው፡፡
ዩክሬይንን በምዕራቡ ምህዋር ውስጥ የማስገባት ውጥንና ሥራው የአሜሪካንን ርዕሰ ሀያልነት ጠብቆ ከማቆየትም ጋር አይታይም ብሎ ማሰብ አያሻም፡፡ ዩክሬይንን ለሩሲያ የ’ታላቅነት’ ህልም የጎን ውጋት እንደትሆን የሚያስችል ሁኔታንም ለመፍጠር በቀጥታ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ - አንድ ትውልድን በ’ብሄረተኝነት’ ስሜት ማነጽና የነጻነትን ጥቅምና ፋዳን እንዲያውቅ ማድረግ አይነተኛም ዘዴ ተደርጎ ተቆጥሯል። በ1991 ዓ.ም. የሶቪየት ህብረት መፈረካከስ በርዠንስኪ እንደሚሉት፤ “ጥቁር ጉድጓድ” (ገዋ) ፈጥሯል፡፡ በአውሮፓና በእስያ መካከል የጂኦፖለቲካ አጥኚዎች ማዕከላዊ የነበረው ስፍራ በመሰነጣጠቅ አደጋ ሲመታ በእርግጥም ጥቁር ገዋና መደናገር ረግቧል፡፡ በዚህ ሁኔታ በብቸኝነት የቀረችው አሜሪካ ማማዋን የማደላደል ዓላማዋ አብሮ ነው ታሳቢ የሆነው፡፡     
የዩክሬይን የጂኦፖለቲካ አቢይ ማጠንጠኛነት  
በቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ወቅት ዩክሬይን ለሶቪየት ህብረት የማዕዘን ደንጋይ ነበረች። በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ከአስራ አምስቱ ሪፐብሊኮች ከሩሲያ ቀጥላ በህዝብ ብዛቷ የምትጠቀስ፣ ለህብረቱ በእርሻ ምርቷ፣ በመከላከያ ኢንዱስትሪዋ መዘመን፣ ጥቁር ባህር (Black Sea) ላይ የነበሩትን መርከቦችና ጥቂት የኒውክሌር መሳሪያዎችን ይዛ የነበረች ሀገር ናት። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ጋር የዩክሬይን ከህብረቱ መውጣት ያኔ ታነክስ ለነበረችው ሩሲያ እጅግ ታላቅ ፈተና ነበር፡፡ እና ዩክሬይን ነፃ በወጣችባቸው ሦስት አስርታቱ ዓመታት ውስጥ እንደሉዓላዊ ሀገር ከምዕራባውያኑ ጋር የመቀራረቧ አጋጣሚ በዘፈቀደ የተደረገ ነው ብሎ ማመን ይከብዳል፡፡ ብሄረተኝነት ማሳደግና በተለይ በምዕራባዊው ዩክሬይን የሚገኘውን የዩክሬይን ቋንቋ የሚናገረውን ማህበረሰብ ወደ አውሮፓ ቀልቡንና ስሜቱን የማስገባቱ ሂደት ወዲያው ነበር የተከተለው፡፡ የሩሲያ ተናጋሪ ዩክሬናውያን ደግሞ ወደ ሩሲያ የመጠቃለልና የመጠጋትን ስሜት ይዘው ነው የቀጠሉት፡፡
በዋነኛነት አሜሪካ የምትዘውረው የምዕራቡ ዓለም የሩሲያ ምኞት ተዳክሞና ተልፈስፍሶ የሚቀረውና የመስፋፋት ምኞቱም የሚገደበው በአቢይነት ዩክሬይን ላይ እንደሆነ የሚያምኑ የውጭ ፖሊሲ ተንታኞች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ሩሲያን ከዩክሬይን ማፋታት የሚቻልባቸው መንገዶችም ባለፉት ሦስት አስርታቱ ዓመታት አልተከናወነም ማለት አይቻልም፣ ዛሬ ከተከሰተው መዘበራረቅ ጋር ሲስተዋል። የአሜሪካው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሊቅና የፕሬዚዳንት ካርተር የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪ ዛሬ ዩክሬይን ላይ የምናየው ክስተት ከወዲሁ በመመልከት አሜሪካና የሰሜን ወታደራዊ ቃል ኪዳን ሀገራቱ ትኩረት እንዲሰጡበት ያሰመሩበት ነበር፡፡ ሚስተር በርዠንስኪ “ያለዩክሬይን የሩሲያ ኢምፓየር (ግዛት) እንደሚያበቃ አጥብቆ መናገር ይገባል፡፡ ይሁንና ዩክሬይን ለሩሲያ ጥገኛ ከሆነች ሩሲያ ወዲያውኑ ኢምፓየር ትሆናለች” ይላሉ ከሀያ አምስት ዓመታት በፊት በጻፉት መጽሐፋቸው፡፡ ልክ ከሃያ ዓመታት በሁዋላ ሩሲያ ክራይሚያን በወታደራዊ ሀይል ተቆጣጠረች፡፡
የሩሲያና የዩክሬይን ግንኙነት ብዙ ተብሎበታል፡፡ ሩሲያ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከዩክሬይን ጋር ባህላዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የጠበቀ ትስስር አላት፡፡ በሩሲያ ማንነት ውስጥ ‘ዩክሬይን ማዕከል ናት’ ይላሉ በዘርፉ የተጠበቡት፡፡ የቤተሰብ ትስስሩ ለምዕተ ዓመታት የቆየና የዘለቀ ነው፡፡ የዩክሬይን መዲና በባህላዊ ስብጥሯ “የሩሲያ ከተሞች እናት” የሚል ቅጽል የነበራትም ነች፡፡ እንደታሪኩ ከሆነ በስምንተኛውና በዘጠነኛው ምዕተ ዓመት ክርስትና ለስላቪክ ህዝቦች ከቤዛንቲን ሲመጣ በኪየቭ በኩል ነበር የገባው፡፡ በቅርቡ የቁጥር መረጃ መሰረት ደግሞ በዩክሬይን ስምንት ሚሊዮን ሩሲያውያን ይገኛሉ፡፡ በተለይም በደቡብና ምስራቅ ነው የሰፈሩት፡፡ ሩሲያ የእነዚህን ደህንነት መጠበቅ እንዳለባት በአቢይነት የምታነሳውም ይህን ተንተርሳ ነው፡፡
የሶቪየት ህብረት ከፈረሰች በሁዋላ በርካታ የሩሲያ ፖለቲከኞች ከዩክሬይን ጋር መፋታቷ ትልቅ ታሪካዊ ስህተትና በሩሲያ የታላቅነት ህልም ላይ ጠባሳ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ዩክሬይንን ማጣት በብዙዎቹ ሩሲያውያን ዘንድ እንደ ውድቀትም ይታሰባል፡፡ የኢኮኖሚውን ትስስር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለሳለሰ ቢመስልም ለማዕከላዊና ምስራቅ አውሮፓ ሩሲያ ላለፉት አስርታቱ ዓመታት ጋዝ የምታጓጉዝበት ቧንቧ በዩክሬይን በኩል ሲሆን ለዚህም በየዓመቱ ቢሊዮን ዶላር ሩሲያ እንደምትከፍል መረጃዎች ያወሳሉ፡፡
በ2014 በፕሬዚዳንት ፑቲን አጠራር ‘በምዕራባውያን የታገዘ ፋሺስታዊ መፈንቅለ መንግሥት’ ተደረገ በተባለ ማግስት ከሩሲያ ጋር ወዳጅ የነበሩት የዩክሬይን ፕሬዚዳንት ቪክቶር ያኖኮቪች ከስልጣን ሲነሱና ከዚያም ተከትሎ ሩሲያ በክራይሚያና በዶንባስ ወታደራዊ ሀይል ማስገባት ስትጀምር ከዩክሬይን ጋር መፋጠጡና አለመረጋጋቱ እንደመጣ አመልካች ነበር። ዩክሬይን ወደ ኔቶ መጠጋቷ ሩሲያን እጅግ የሚኮሰኩሳት ስለመሆኗ በተደጋጋሚ ገልጣለች። የሩሲያው ፕሬዚዳንት በ2008 ከኔቶ ስብሰባ ቀደም ብሎ ለዩኤስ ባለስልጣናት ዩክሬይንን ለማግባባት የሚደረገው መክረትረት ‘ሩሲያን ለማጥቃት የጠላትነት ፈር መቅደድ’ እንደሆነ ማስጠንቀቃቸውን ሰነዶቹ ያረጋግጣሉ። ይሁንና እስከ 2022 የሩሲያ ግልጽ ወታደራዊ ዘመቻ ድረስ ዩክሬይን ከኔቶ ጋር በርካታ ወታደራዊ ልምምዶችን አድርጋለች፡፡ አባል ካልሆኑ ሀገሮች እጅግ ቅርበት ያላትና ተወዳጅ የሚል ቅጽል የተሰጣትም ሆና ነበር - በሰሜን አትላንቲክ ወታደራዊ ቃል ኪዳን ዘንድ፡፡ በዩኤስ አሜሪካ ውስጥ የዩክሬይን ቀውስ ተብሎ ቢጠቀስም በሩሲያውያኑ ዘንድ ግን ቀውሱ የአውሮፓ የደህንነት ወይም ሴኪዩሪቲ ስርዓተ ቀብር ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡
በዚህ ጦርነት የፕሬዚዳንት ፑቲን ፍላጎት ምንድን ይሆን? ለሚለው ብዙዎች መላ ምት ይሰጣሉ፡፡ “Near Abroad” በሚል ርዕስ መጽሐፍ የጻፉት ጀራርድ ቶል፤ “የዚህ ሁሉ መጨረሻው ሶቪየት ህብረትን እንደገና ለመፍጠር  ሳይሆን ሩሲያን እንደገና ታላቅ ለማድረግ ነው” ይላሉ፡፡ በ2014 ክራይሚያን በመቆጣጠር ሩሲያ በጥቁር ባህር ላይ ይዞታዋን አስፍታለች፡፡ የተደራጀና የተባ ወታደራዊ ይዞታ በዚያ ቀጣና መኖሩ በሜድትራኒያ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪቃ ጭምር ሀይሏን እንድታሳድግ ሊገፋት ይችላል ይላሉ በሰሎቹ፡፡ ዩክሬይንን በተመለከተ ሐምሌ ወር 2021 ፕሬዚዳንት ፑቲን የጻፉት መጣጥፍ ነበር፡፡ ለብዙዎች የምዕራባውያን የውጭ ፖሊሲ አዋቂዎች ዛሬ ያለውንም ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ የሚፈታ አድርገውም ይጠቅሱታል፡፡ ፕሬዚዳንት ፑቲን የሩሲያና የዩክሬይን ህዝብ እንደ አንድና የጋራ ታሪክና መንፈሳዊ ቦታን እንደሚጋሩም ጽፈዋል፡፡ ይሁንና ‘አንድ ነን’ የሚለው ወግ አሁን እንደአንዳች ከሚዘንመው የጦር እሳት ጋር አይሄድም የሚሉ ብዙ ናቸው። ሰብዓዊው ቀውስና ይልቁንም ወደየት ያመራ ይሆን የሚለው ስጋት ደግሞ ሁሉንም አንገት አስደፍቷል፡፡
በዚህ እንቋጨው፡፡ የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ማክተምን ያኔ ያበሰሩትና በመግቢያዬ የጠቀስኳቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤች ቡሽ በዚያ የማገባደጃ ንግግራቸው ላይ “ይሁንና ግን” ብለው ጀመሩ “ይሁንና ግን ዓለማችን አደገኛ ስፍራ ናት፡፡ የጦርነትን መጨረሻ ያየ የሞተ ብቻ ነው፡፡ የትላንቱ ፈተናችን ከሁዋላችንም ቢሆን ቅሉ ነገ ግን እየተወለደ ነው” አሉ፡፡ በርግጥም የዓለማችን አደገኛነት የከፋ ነው፡፡ ግጭቱም የሚገድለውን እየገደለ ነው፡፡ መጨረሻውም ግን አልታወቀም፡፡ የጦርነት አውሎ ነፋስ ጠንክሮና ከፍቶ ማንገራበዱን ቀጥሏል፡፡ የእግዚአብሔር ፍጡር ሰው እርስ በእርሱ ጦር መማዘዙን ቀጥሏል፡፡ እና ‘የጦርነትን መጨረሻ ያየ የሞተ ብቻ ነው’ የተባለውን ደግመን አልነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1044 times