Tuesday, 03 May 2022 00:00

ለእውነት የመታመን “እምነት”? ወይስ፣ ለእውነት የማይበገር “እምነት”?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

     ጥንታዊ የሃይማኖት መጻሕፍት፣ በብዙ ገጽታቸው፣ ከባድ ናቸው። ከባድ ማለት፤ የመልዕክታቸውን ክብደት ለመግለጽ ይሆናል። ለግንዛቤ አስቸጋሪ መሆናቸውንም ያመለክታል። የይዘታቸው ስፋት፣ የታሪካቸው የምዕተዓመታት ርቀት፣ የቋንቋቸው ጥንታዊነት፣ ቀላል አይደለም። “የእምነት” እና “የእውነት” ጉዳዮችም፣ የሃይማኖትን ነገር፣ በእጅጉ ያከብዱታል።
የሃይማኖት መፃሕፍት፣ ከመልዕክታቸው ክብደትና ከመልካም የሥነምግባር ትምህርታቸው ጎን ለጎን፣ የጥፋት ማሳበቢያና የክፋት ማመካኛ ሲሆኑ የምናየውስ ለምን ሆነና!
የሃይማኖት መጻሕፍት ከባድ በመሆናቸው፣ ብዙ ሰዎች፣ “እዚህ ጋ ተጣረሰ፣ እዚያ ጋ ተቃራነ” ለሚል ችኩል ድምዳሜ ይጋለጣሉ - በአላዋቂነት። ሌሎች አላዋቂዎች ደግሞ፤ “እገሌ የሃይማኖታችንን አንቀጽ ሰደበብን። የመጽሐፋችንን ጥቅስ ደፈረችብን” ብለው ለማውገዝ ይቸኩላሉ።
የመጽሑፉን ሙሉ መልዕክት አገናዝበው ለመረዳት ሲከብዳቸው፣ በስንፍና አንድ ሁለት ጥቅሶችን ብቻ ያንጠለጥላሉ።
የራሳቸውን እውቀት ለማዳበር ሳይሆን፤ ሌሎች ሰዎችን ለማውገዝ፣ ወይም ለማላገጥ ይሽቀዳደማሉ። ለራሳቸው ሕይወት፣ መልካም የኑሮ መመሪያ ለመቅረጽ ሳይሆን፣ የመዋጊያ ጥቅስ ለማግኘት ይጓጓሉ።
የማውገዣ ወይም የማላገጫ መሳሪያ እንዲሆንላቸው ነው የሚፈልጉት።
ስንፍና ይሆናል መነሻቸው። በጊዜ ካልባነኑ ግን፣ ቀስ እያሉ፤ ወደ ጭፍንነትና ወደ ለየለት ክፋት ይሸጋገራሉ።
ከዚያ ይልቅ፤ “ለራሴ፣ ለአእምሮዬ፣ ለህይወቴ” ብለው ቢያነብቡ ነበር የሚሻለው። እንዲህ ሲባል ግን፣ “የሃይማኖት መጻሕፍት ላይ፣ ሁላችንም ሊቅ እንሁን” ለማለት አይደለም። የቻሉ ይሁኑ። ያልቻሉም፣ በእውቀታቸው መጠን፣ አንድም ይሁን ሁለት ጥቅስ፤ ይያዙ። ከዚያ በላይ ካቻሉ፤ የአቅማቸውን ያህል መያዛቸው ችግር የለውም። ነገር ግን፤ የሰሙት አንድ ጥቅስ፣ ያነበቡት አንድ አንቀፅ፣ ለተጨማሪ ግንዛቤ እንዲረዳቸው፣ ወደ ላቀ ሃሳብም እንዲያራምዳቸው በንጹህ ልቦና ያስተውሉት፤ ያሰላስሉት።
“ሶስተኛው አንቀጽ ከሰባተኛው ጋር ይቃረናል” ብሎ ለመደምደም ከመጣደፍ ይልቅ፤ ግንዛቤ ለመጨበጥ ጊዜ ይስጡ። የሚጣረሱና የሚፋለሱ ጥቅሶችን ለመልቀም ከመዝመት ይልቅ፤ እውቀት የማስፋት ፍቅርን ያስቀድሙ።
“አንቀፆችን አያነጸጽሩ፤ አያገናዝቡ” ማለት አይደለም። መጣጣም መጣረሳቸውን ለማየት፣ በርካታ አንቀጾችን ማነጻጸርና ማመሳከር፣ ተገቢ ነው። ደግሞም፤ እርስ በርስ የተገናዘበና በቅጡ የተጎዳኘ እውቀት ነው፤ ወደፊት እየሰፋ እያደገ የሚሄደው። እናም፣ አንቀጾችን ማመሳከር፣ ጥቅሶችን ማስተያየት ጥሩ ነው።
በዚህ መሃልም፣ የሚቃረኑና የሚፋለሱ ነጥቦች ሊያጋጥሙ ይችላል። የተቃረኑ አንቀጾችን አይተው እንዳላዩ ማለፍ ተገቢ አይደለም። አይቶ እንዳላየ ለማየት የሚሞክር ሰው፣ በስንፍ ተይዞ የጭፍንነት ምርኮኛ ይሆናል።
ግን ደግሞ፣ ማጋነንና ማጮህም አያስፈልግም። “አንቀጾች ተቃረኑ፤ ጥቅሶች ተጣረሱ” ብሎ ለመጮህ መቅበጥበጥ፣ ሁሉን ነገር ለማጣጣል መጣደፍ፣ ቀሽምነት ነው። “በተቃረነ፣ ተፋለሰ” ብሎ መጮህ፤ ይህንንም እንደ ድል አድራጊነት ቆጥሮ ለመፎከር መስገብገብ፣ ሰውን ለማውገዝ ወይም ለማላገጥ መቸኮል፤ ጀግንነት አይደለም። የስንፍናና የጭፍንነት አመጽ ነው።
በአጭሩ፤ የማውገዣ ወይም የማርከሻ፣ የማሳበቂያ ወይም የማላገጫ ሰበብ ለማግኘት መቅበዝበዝ፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። የጭፍንነት ልጆች ናቸው። ባህሪያቸው ይመሳሰላል። አንዱ ሰነፍ፣ የጭፍንነት ባርያ ለመሆን ሲሮጥ፣ ሌላኛው ጭፍን አመፀኛ ለመሆን ይንደረደራል። አንዱ፣ “ወዶ ገብ የጭፍንነት ምርኮኛ”፤ ሌላኛው ደግሞ፣ “ወደ ጭፍንነት የሸፈተ ስርዓት አልበኛ” ይሆናሉ፤ እንደማለት ነው።
የጭፍንነት ባርያና ሽፍታ፣… እንደበቀቀን ናቸው። የሰሙትን ቃል፤ ያነበቡትን ጥቅስ፣ ያለግንዛቤ በጭፍን እንደበቀቀን ይደጋግሙታል። አንደኛው፣ ለማሳበቅና ለማውገዝ፣ ሌላኛው ደግሞ ለማርከስና ለመሳለቅ ይፈጥናሉ።
አንዱ ሰነፍ፣ ሌላኛውን ለማውገዝ፣ ጥቅሶችን እያሾለ ይሰብቅበታል። ሌላኛ ሰነፍም መልሶ አጸፋ ይወረውራል። ተቀናቃኙን ለማዋረድ ወይም ለማርከስ፣ ጥቅሶቹን እያጋጨ ያላግጥበታል።
እንዲህ በከንቱ ይደክማሉ። የጥቅሶች አክሮባት፤ ገና በታዳጊ እድሜ የሚታረም ከሆነ፣ መጥፎ አይደለም። እንዲያውም፣ ወደ ቁም-ነገር የሚያስፈነጥር አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። የጥቅሶች አክሮባት፤ ወደ እውቀት መንገድ የሚያሻግር ጥረት ከታከለበት፤ ጥሩ የጥበብ መግቢያ ሰበብ ይሆናል። በጥረት ካልታረመ፤… የጥቅስ አክብሮት ወደ ቀና የእውቀት መንገድ በጊዜ ካልተሻገረ ግን፣ አሳዛኝ የእድሜ ብክነት ይሆናል።
ወደ ክፋትም ይወርዳል እንጂ።
“የእንትን ሃይማኖት ተቆርቋሪ” የሚል ስልጣን ለማግኘት፣ የባጥ የቆጡን ማሳበቅ ይጀምራል። ሰዎችን ማውገዝ አባዜ እየተጠናወተው፣ በጭፍን መጮህ ያዘወትራል። ልወደድ ባይ በቀቀን ሆኖ ያርፈዋል።
ዞር ብሎስ ምን ይላል? በሌላ ሃይማኖት ላይ አብዝቶ ለማላገጥ በጭፍን ይንጫጫል - ጀብደኛ መሳይ በቀቀን ይሆናል።
የሃይማኖት መጻህፍት፣ በታሪካቸው ከባድ በመሆናቸው፤ ለእንዲህ አይነት የጭፍንነት ችግር ያጋልጣሉ።
አላዋቂዎች፣ በቀላሉ እየተሳሳቱ የጭፍንነት እስረኛ ይሆናሉ - በየዋህነት። ክፉዎችም ደግሞ፤ አላዋቂዎችን ለማናቆር አመቺ ሰበብ ያገኛሉ። ለምን? የሃይማኖት መጻህፍት ከባድ ስለሆኑ።
ግን፣ ይህ ብቻ አይደለም።
ለሚዛንና ለልጓምን የሚያስቸግሩ ገጽታዎች፣ በሃይማኖት ውስጥ መኖራቸው፤ ፈተናውን ያከብዱታል። ለጭፍን ስህተትና ለአደገኛ ክፋት የሚያጋልጡ ሰበቦች የሚበራከቱትም፣ በዚህ ምክንያት ነው።
“እምነት” የሚለውን ፍሬ ሃሳብ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
የእምነት አይነቶችና ልኮች።
እምነት የሚለው ቃል፣ በጣም አስቸጋሪ ነው። ለእውነታ በፅናት መታመንን ሊያመለክት ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ማስረጃና ማረጋገጫ የማያሻው ሃሳብም፣ “እምነት” ተብሎ ይገለፃል።
ለእውነታ ታማኝ የመሆን ገፅታን እንይ።
በዚህ በኩል ካየነው፤ እምነት ማለት፣ እውነት እንደማለት ይሆናል። ማመን ማለት፣ ማወቅ እንደማለት ቁጠሩት። እውነታውን ማየት፣ ዙሪያውን ሁሉ አስተውሎ መገንዘብ ነው - እምነት።
በግልባጩስ?
አይተው እንዳላዩ አለመሆን፣ እውኑን ነገር አለመካድ ነው - እምነት። በአጭሩ፤ ለእውነታ ታማኝ መሆን ነው - እምነት።
ሃይማኖቶች፣ ይህን አይነት እምነት ያቅፋሉ።
ሐሰትን የማይገስጽ፣ እውነትን የማያጸድቅ ሃይማኖት የለም።
ጽድቅ ማለት፣ ቃል በቃል፤ “እውነት” ማለት ነው። ታዲያ፣ ለእውነታ የመታመን እምነት፣ ለብቻው የተንጠለጠለ ሃሳብ አይደለም። ባለብዙ መዋቅር ነው።
ለእውነታ መታመንን የሚያስተምር ሃይማኖት፣ በዚሁ ምክንያት፣ ለሰው አካልና አእምሮ፣ ከፍ ያለ ክብር መስጠት ይኖርበታል። አእምሮ ከሌለ፣ እውነትን ማወቅና አለማወቅ ብሎ ነገር አይኖርም። እውኑን ዓለም የማይክድ አእምሮ ነው፣ “ለእውነታ የታመነ አእምሮ”። እናም፣ እውነትን ያከበረ ትምህርት፣ አእምሮን ያከብራል። ሰውን ያከብራል። ከክብር ጎን ለጎንም፣ ሃላፊነትንም ያመጣል።
አዕምሮ፣ እጅግ ተከበረ የሰው ተፈጥሮ ስለሆነ፤ ይህን ጸጋ አለመጠቀም፣ እውኑን ዓለም አለማስተዋልና አለማገናዘብ፣ ከእውነት እንደ መሸሽ ነው። አእምሮንና እውቀትን ጎን ለጎን አለማበልጸግ፣ እውነትን እንደ መካድ፣ ተፈጥሮን እንደ ማምከን ነው።
አካልንና አእምሮን በተገቢው መንገድ መጠቀም፤ ተፈጥሯዊ የሰው ሃላፊነት ነው። በአይን ማየት፣ በአእምሮ ማገናዘብ ይኖርብናል - እውነትን ከወደድን፣ አይንንና አእምሮን ካከበርን። አለበለዚያ፣ ከእውነት አፈንግጦ እንደመኮብለል ይሆናል።
“የሚያዩበት ዓይን አላቸው፤ እነሱ ግን አያዩም። የሚሰሙበት ጆሮ አላቸው፤ እነሱ ግን አይሰሙም” የሚለውን አባባል አስታውሱ።
ይሄ፣ በእጸዋት ላይ የተሰነዘረ ወቀሳ አይደለም። የዓይንና የጆሮ ተፈጥሯዊ ጸጋ ከሌለ፤ የማየትና የመስማት ሃላፊነት አይኖርም። የማወቂያ ፀጋዎችን ይዞ የተፈጠረው የሰው ልጅ ግን፣ ጸጋዎቹን የመጠቀምና ለእውቀት የመትጋት ሃላፊነት አለበት።
በግልባጩ፣ የማወቅ ሃላፊነት፣ የዕውቀትንና የእውነትን ልዕልና ይመሰክራል። የማወቅ ሃላፊነትም፣ የአዋቂን ክብር ያውጃል። ማየትና ማስተዋል፤ መስማትና ማገናዘብ፤… አእምሮና አካል፤ አይንና ጆሮ፤… ከንቱ ተራ ነገሮች ከሆኑ፤ ማየትና መስማት ፋይዳ አይኖራቸውም። “ማየት አይረባም፤ አለማየት አያስወቅስም” የሚያስብል ይሆናል - ለእውኑ ዓለምና ለአእምሮ ቅድሚያ ካልሰጠን፣ አይንና ማየትን ካላከበርን።
በአጭሩ፣ ከክብር ጋር ሃላፊነት አለ። ከሃላፊነት ጋርም ክብር ይመጣል። አእምሮና አይን ያለው ፍጡር፤ የማወቅና የማየት ሃላፊነት አለበት።
ታዲያ በዘፈቀደ አይደለም። እውኑ ዓለም፤ ሰውን ጨምሮ፤ ሁሉም ተፈጥሮ፤ የራሱ ምንነትና ልክ አለው። የማየትና የማወቅ ሃላፊነትም፤ ከአይን እና ከአእምሮ ተፈጥሮ ጋር የተጣጣመ መሆን አለበት። ቀረብ ራቅ ብሎ ማየት፣ አዟዙሮ አገላብጦ መመልከት፤ ገልጦ ገጣጥሞ ማነጻጸር፣… እነዚህ ዘዴዎች ሁሉ አስፈላጊ የሚሆኑት፤ ለአይን ተፈጥሮ የሚመጥኑ ተገቢ ዘዴዎች ስለሆኑ ነው።
አይናችን፤ በምኞት ብቻ፣ የሩቁን አቅርቦ፣ ደቃቃውን አጉልቶ አያሳየንም - ማይክሮስኮፕና ቴሌስኮፕ እንጠቀማለን እንጂ። አይናችን ኤክስሬይ ማሽን አይሆንልንም። ዙሪያ ገብ፣ ሁሉን አቀፍ የካሜራዎች ኔትወርክም አይደለም - አይናችን። ለዚህም ነው፣ ዞር ዞር እያልን፣ ነገሮችን እያገላበጥን የመመልከት ሃላፊነት የሚኖርብን።
በአግባቡ በማየት እንጂ፣ በቦዘ ወይም በፈጠጠ ዓይን ብቻ፤ ቁም ነገር አይገኝም። ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን የማክበርና የመጠቀም ሃላፊነት ማለት፤ … ጸጋዎችን በተገቢው መንገድ የመጠቀም ሃላፊነት ማለት ነው። የባለጸጋዎች፣ ማለትም የሰዎች ሃላፊነት።
አለበለዚያ ያስወቅሳል። ጸጋዎችን በአግባቡ አለመጠቀም ነውር ነው። ከእውነት ጋር ያጣላል። የሰውን ክብር ያረክሳል።
“ያያሉ፤ ግን አያስተውሉም። ይሰማሉ፤ ግን አያዳምጡም” ይላል - ግሳፄው።
ምን ለማት ፈልጌ ነው?
ለእውነታ ታማኝ ሁኑ ብሎ የሚያስተምር ሃይማኖት፣ ለሰው አእምሮና ለሰው አካል ክብር መስጠትን ያስተምራል። አእምሮንና አካልን በተፈጥሯቸው ልክ በአግባብ መጠቀምን ይመክራል። እውነትን የወደደ ሃይማኖት፤ ማወቅን ከፍ አድርጎ ያስተምራል፣ አዋቂን (ሰውን) ያከብራል።
ለእውነት የሚቆረቆር መጽሐፍ፤ ለሰው ሕይወትና ኑሮ፣ በጣም አብዝቶ መቆርቆር ይኖርበታል።
በሌላ አነጋገር፣ “እውነት ጽድቅ ነው” ብለው ሲያስተምሩ፣ ለስራና ለጥረት፣ ለተሻለ ኑሮና ለጤንነት፣ ትልቅ ዋጋ መስጠት እንደሚያስፈልግም ይገልፃሉ - የሃይማኖት መጻሕፍት። ከእውነትና ከጽድቅ ጋር የማይነጣጠል፣ ሌላ ቁም ነገርም አለ።
ይብዛም ይነስ፣ ፈጠን ዘገየም፣ ይቅለልም ይክበድም፣… ሰዎች፣ ሕይወታቸውን ለመምራት የሚረዳ አቅም አላቸው።
ሰዎች፣ የየራሳቸውን የሃሳብና የተግባር መንገድ የመምረጥ፣
የየራሳቸውን የግል ማንነትና ሰብዕናን የመቅረጽ አስደናቂ አቅም አላቸው - ለክፉም ለደጉም።
ይህን እውነታ በመገንዘብ፤ ለዚህ እውነታ ታማኝ በመሆን ነው፤ የስነ-ምግባር መርሆችን ማስተማር የሚቻለው።
ሰዎች፣ በየግላቸው የአእምሮ ባለቤት ካልሆኑ፣
በየግላቸው ሃሳባቸውን፣ ተግባራቸውንም ባህሪያቸውንም ለመምራት የሚያገለግል አቅም ከሌላቸው፤… የስነ-ምግባር መርህ ምንም አይፈይድላቸውም፤ ሃላፊነትም የለባቸውም።
በሌላ አነጋገር፤ ሃይማኖቶች፤ በየአገሩ የስነ- ምግባር መርህ እያስተማሩ ለብዙ ዘመን የዘለቁት፤ ተወደደም ተጠላም፣ ለእያንዳንዱ ሰው ሕልውናና ለግል ነፃነት ክብር በመስጠት ነው። በቀጥታ ባይሆን እንኳ በተዘዋዋሪ፣ በተገቢው መጠን ባይሆን እንኳ በትንሹ፤ ለእያንዳንዱ ሰው ሕይወትና ለግል ነጻነት እውቅና መስጠት የግድ ነው። አለበለዚያ፣ የስነ-ምግባር ትምህርት፣ ትርጉም ያጣል።
እዚህን ሃሳቦች በሙሉ፤ እውነትን ከመውደድ ጋር ተያይዘው መምጣትና መሟላት የሚኖርባቸው ሃሳቦች ናቸው። ለእውነታ ታማኝ መሆን ነው፣ የሁሉም ሃሳቦች አስተማማኝ ስረ-መሰረት።
በአጠቃላይ ሲታይም፤ “እውነትን ውደዱ”፣ “ማየት ማመን ነው” የሚል መሰረታዊ ሃሳብ ያልያዘ ሃይማኖት የለም ማለት ይቻላል።
አይተን እንዳላየን እውነታን እንድንክድ፣ ውሸትን እንድናወራ፣… በግላጭ የሚያስተምር ሃይማኖት የለም። ሰዎች አእምሯቸውን እንዲሁም አካላቸውን የመጠቀም ነጻነት እንዳገኙ፣ “እጅና እግራቸው በብረት ይታሰር” ብለውስ ይሰብካሉ?
ሰዎች የነፃነት ጭላንጭል አግኝተው፣ ትንሽ ማሰብና መስራት ቢችሉ እንኳ፣ ድንገትም ፍሬያማ ቢሆኑ፣ “ያመረቱትን አቃጥሉ” ብሎ የሚሰብክ ሃይማኖትስ አለ?
ሳትሰሩ የዝርፊያ ኑሮ ይመቻችሁ ተብሏል?
በመከባበር ሳይሆን፣ በመገዳደል ሕይወታችሁ የተዋረደ፣ እድሜያችሁ ያጠረ፣ ስቃያችሁም የበዛና የመረረ እንዲሆን ትጉ ተብሏል?
“የሰዎች ህልውና ማለት፣ የግል ህልውና ማለት መሆኑን ካዱ፤ ማንም ሰው የገዛ ህይወቱ ላይ የግል ባለቤት መሆኑን አትመኑ፤ እንዳሻችሁ በባርነት ርገጡ፤ እንደ እቃ ሽጡ፤ ሲያምራችሁ ሕይወቱን ቅጠፉ፤ ቁረጡ” ተብሏል?
“በጥፋተኛው ሰው ምትክ፣ ንጹህ ሰው ላይ ፍረዱ፤ መልካሞችን አዋርዳችሁ ክፉዎችን አወድሱ” የሚል ትምህርትስ አለ? “እኔ አለሁ” የሚል ሃይማኖተኛ፣ እጁን የሚያወጣ አይመስለኝም።
ይልቅስ፣…
“እውነትን ውደድ፤ በሃሰት አትመስክር (አትወንጅል)”፤
“ተግተህ ስራ፤ ንብረት አፍራ። የሰውን አትመኝ፤ አትስረቅ”፤
“አዋቂዎችን አክብር፤ ህይወትን ውደድ፤ አትግደል”… ብሎ ያስተምራል የጥንት ሃይማኖታዊ መጽሐፍ።
የሰው ሕይወት፣ የግል ንብረትና የግል ክብር ፍፁም አይነኬ እንደሆኑ ያሰተምራል - ቅዱስ ቁርዓን።
ፍሬያማ ሃሳብና ጥበብ ማለት፤ መትከል ወይም መዝራት ማለት ብቻ አይደለም። ተስማሚ መሬት የማዘጋጀት ጥርትንም ይጨምራል። መብቀሉ ብቻ ሳይሆን፣ ማደጉና መለምለሙንም ያካትታል። አድጎ ዛፍ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ማፍራቱንም ያቅፋል ሲል አስተምሯ - ኢየሱስ። ፍሬ መበርከቱ ብቻ ሳይሆን፤ ጥዑም ፍሬ መሆኑንም ይጨምራል - ነገሩ።
ለእውነት ታማኝ መሆን ማለትም እንደዚያው ባለብዙ መዋቅር ነው። ለእውኑ ዓለምና ለአእምሮ ክብር መስጠት፣ ለሰው ሕይወትና ኑሮ፣ ለግል ነፃነትና ለግል ሃላፊነት ሁሉ ዋጋ መስጠትን ያካትታል።
“እውነትን መጨበጥ፤ በተቃና መንገድ መጓዝ፤ ፍሬማ ሕይወትን ማጣጣም” ከሚለው ትምህርት ጋር ይጣጣማል።
ከዚህ አንጻር ስናያቸው፤ የሃይማኖቶች የስነ-ምግባር ትምህርት፤ ከስረ መሰረታቸው፤ ተመሳሳይ ናቸው። ለተጨባጭ እውነታ መታመን፤ በሰው የአእምሮ ላይ መተማመን፣ ግዴታቸው ነው። ይህ ባህሪያቸው፤ ከኒውተን የፊዚክስ ቀመሮች፣ ከአርስቶተል የሎጂክ መርሆች ጋር ያመሳስላቸዋል። “ማየት ማመን ነው። ማየትና መረዳት፤ ማየትና ማስረዳት ይቻላል” በሚል ጠንካራ መሰረት ላይ ቆመው፣ ብዙ ቁም ነገር ያስምራሉ፤ እንማራለን።
የዚህኛው ወይም የዚያኛው ሃይማኖት ቢሆን፣ ለውጥ የለውም። “እውነት ያስተምምናል፤ ውሸት ያማስናል” ብሎ ካስተማረ፣ ሃይማኖቱ ምንም ሆነ ምን፤ እዚህ ላይ ለውጥ አያመጣም፤ ምንም አይጎድልም።
“እምነት” የሚለው ፍሬ ሃሳብ፣ ይሄን ሁሉ የሚገልጽ ነው። መልካም።
ግን፣ ከዚህ የሰፋ ወይም ከዚህ የተለየ ትርጉምም አለው። “ማየት፣ ማመን ነው” የሚለውን ሃሳብ በመቀየር፣ “ማመን፣ ማየት ነው” እስከማለት ይደርሳል። “በቅድሚያ እመን፤ ከዚያ በኋላ እውነትን ታያለህ” እንደማለት ነው።
በእርግጥ፤ ይሄም ቢሆን፣ ሙሉ ለሙሉ፤ “ጭፍን እምነት” ላይሆን ይችላል።
ሕጻናት፣ በቅድሚያ በወላጆችና በአስተማሪዎች ላይ፣ የተወሰነ ያህል እምነት ከሌላቸው፤ በትኩረት የማየት፣ የመስማትና የማገናዘብ ፍላጎታቸው ይቀዘቅዛል። ጨርሶ ሊጠፋም ይችላል።
በዚህ መነጽር ስናየው፤ በእርግጥም፣ ማመን ከማየት ቀድሞ የሚመጣ ይመስላል። ነገር ግን ሁሉንም ነገር በጭፍን እየሰሙ ያምናሉ ማለት አይደለም። ይመረምራሉ። ለሚዋሹ ሰዎች የሚኖራቸው ግምት ይቀንሳል። እውነትን በትክክል ለሚናገሩ ሰዎች ደግሞ ከቀድሞ የበለጠ እምነት ያድርባቸዋል።
ይሄ፤ ዞሮ ዞሮ ከተጨባጭ እውነታ ጋር የተጣመረ እንጂ የተጣላ እምነት አይደለም።
ነገር ግን፤ ማረጋገጫና ማስረጃ የማያስፈልገው እምነትስ?
“በቃ እመን፤ እንዲሁ አመኑ” የሚል አስተሳሰብስ? ሃይማኖት ይህን አይነት እምነት ይፈቅዳል፤ ያካትታል። “እንዲያውም የሃይማኖት ዋና መሰረቱ፣ እንዲህ አይነት እምነት ነው” የሚሉ አሉ።
በዚህ በዚህ ምክንያትም ነው፤ ሃይማኖታዊ ክርክርና ሙግት፣ መቼም ቢሆን፣ በጣም አደገኛ የሚሆነው። ማስረጃና ማረጋገጫ የማያስፈልጋቸው እምነቶች፤ እንዴት ተደርገው ይመረምራሉ? እንዴትስ ይመዘናሉ? አያስኬድም። ይልቅስ፣ ሃይማኖታዊ ክርክሮችና ውዝግቦች፣ የብሽሽቅ ስሜት ለመፍጠር ብዙ ሰበብና እድል ይከፍታሉ - የማሳበቂያና የማላገጫ ሰበብ።
ለጭፍን ስሜትና ለጥላቻ፣ ምቹ ማመካኛ ይሆናሉ። የክፋት አዝማቾች፣ በሃይማኖት ሰበብ፣ እልፍ የጥፋት ሰበብ ለመፍጠር የሚመቻቸውስ ለምን ሆነና!
ለዚህም ነው ሁሌም በእጅጉ መጠንቀቅ፣ በጣም አስፈላጊ የሚሆነው።

Read 8055 times