Wednesday, 04 May 2022 00:00

የሰላም ኖቤል ተሸላሚዋ በሙስና የ5 አመት እስር ተፈረደባቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    - የሆንዱራስ የቀድሞ መሪ በአደንዛዥ ዕጽ ንግድ የ40 አመት እስር ይጠብቃቸዋል
       - ትራምፕ የፍ/ቤት ትዕዛዝ ባለማክበር በቀን የ10 ሺህ ዶላር ቅጣት ተጥሎባቸዋል

            የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋና ማይንማርን ለአምስት አመታት ያስተዳደሩት የቀድሞዋ የአገሪቱ መሪ አን ሳን ሱኪ በተመሰረተባቸው የሙስና ክስ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የ5 አመት እስር ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ባለፈው አመት በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የወረዱት ሱኪ በድምሩ 11 የሙስና ክሶች እንደተመሰረቱባቸው የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ረቡዕ የ5 አመት እስራት የተፈረደባቸው ግን በአንዱ ብቻ መሆኑንና በሁሉም ክሶች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በድምሩ እስከ 190 አመት የሚደርስ እስር እንደሚጠብቃቸው መነገሩንም አመልክቷል፡፡
ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ለእስር የተዳረጉት የ76 አመቷ ሱኪ፤ ከዚህ በተጨማሪም ኮንትሮባንድ፣ የምርጫ ማጭበርበርና ብሔራዊ ሚስጥርን ማሹለክን ጨምሮ 18 የተለያዩ የወንጀል ክሶች እንደተመሰረቱባቸው የጠቆመው ዘገባው፣ ጠበቆቿና የመብት ተሟጋቾች ግን የክስ ጋጋታው ግለሰቧን ከፖለቲካው አለም ለማስወጣት በወታደራዊው መንግስት የተሸረበባት ሴራ ነው ሲሉ እንደሚያስተባብሉ አመልክቷል፡፡
በሌላ የወንጀል ዜና ደግሞ፣ የቀድሞው የሆንዱራስ ፕሬዚዳንት ጁኣን ኦርላንዶ ሄርናንዴዝ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርና የህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ ወንጀሎች ተከስሰው ለአሜሪካ ተላልፈው መሰጠታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከሁለት ወራት በፊት በሄርናንዴዝ ላይ በሁለቱ ወንጀሎች ክስ እንደመሰረተባቸውና ተላልፈው እንዲሰጡት ጥያቄ ማቅረቡን ያስታወሰው ዘገባው፣ የሆንዱራስ ፖሊስም በእስር ላይ አቆይቷቸው ባለፈው ሳምንት በአውሮፕላን ወደ አሜሪካ ኒውዮርክ እንዳጋዛቸው ነው ያመለከተው፡፡
የቀድሞው የሆንዱራስ ፕሬዚዳንት ጁኣን ኦርላንዶ ሄርናንዴዝ አገሪቱን ለሁለት የስልጣን ዘመናት ካስተዳደሩ በኋላ ባለፈው ጥር ወር ላይ ከስልጣን መውረዳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ የአሜሪካ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በአደንዛዥ ዕጽ ንግድ ተሳትፈው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር አካብተዋል፤ በህገወጥ የጦር መሳሪያ ንግድም ተሳትፈዋል በሚል ክስ እንደመሰረተባቸውና ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 40 አመት በሚደርስ እስር ሊቀጡ እንደሚችሉም አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለፍርድ ቤት ማቅረብ የነበረባቸውን የታክስ ሰነድ በወቅቱ ማቅረብ ባለመቻላቸው ሳቢያ ሰነዱን እስኪያቀርቡ ድረስ በየቀኑ 10 ሺህ ዶላር እንዲከፍሉ ባለፈው ሰኞ ቅጣት እንደተጣለባቸው ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ትራምፕ ከንግድ ተቋማቶቻቸው ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል የተባለውን የታክስ ማጭበርበር ውንጀላ እየመረመረ የሚገኘው ፍርድ ቤት ለምርመራ የሚያገለግሉትን የታክስና የሒሳብ ሰነዶች እንዲያቀርቡ የሰጣቸው ቀነ ገደብ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ማለፉን መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ እስካሁንም አለማቅረባቸው የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደመናቅ ይቆጠራል በሚል በየዕለቱ የተጠቀሰውን ገንዘብ እንዲከፍሉ በትራምፕ ላይ ቅጣት መጣሉን አክሎ ገልጧል፡፡


Read 338 times