መንግስት ጋዜጣውን የዘጋው ሆን ብሎ ፓርቲውን ለማፍረስና በመጪው የአዲስ አበባ ማሟያ ምርጫ እንዳይሳተፍ ለማድረግ ነው ሲልም አክሏል፡፡ የጋዜጣውን መታገድና የፕሬስ አፈናን በመቃወም በቅርቡ ሠላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርጉ የገለፁት የፓርቲው አመራሮች፤ ህጋዊ ሠውነት ስላለን የሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄያችን ተቀባይነት ያገኛል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ ፈቃዱን ካላገኘን ግን የራሳችንን የትግል መንገድ እንከተላለን ብለዋል፡፡ አንድነት ፓርቲ የታገደውን ጋዜጣ ለመተካት ሁለት አፋጣኝ እርምጃዎችን ለመውሰድ መወሰኑን ገልፀው፤ አንዱ ጋዜጣዋን ወደ መጽሔት በመቀየርና ከግል ማተሚያ ቤቶች ጋር በመነጋገር በቀጣዩ ሳምንት ለገበያ ማቅረብ ሲሆን ሁለተኛው ፓርቲው የራሱን የማተሚያ ማሽን በመግዛት ጋዜጦችን እራሱ ለማተም ውሳኔ ላይ መድረሱንም አመልክቷል፡፡