Saturday, 30 April 2022 14:23

አሸካሚው

Written by  ዳዊት
Rate this item
(3 votes)

  አሮን ፕራግማቲስት ነው፡፡ ፕራግማቲስትነቱ እምነት የለሽነቱ ነው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ሚስቱ ከጎኑ ተኝታ ሲያያት አርጅታለች። ድንገት ሳይሆን ያረጀችው፣ ድንገት እሱ ማርጀቷ ተሰማው፡፡ ቀስ ብሎ ከአልጋው ተነስቶ ሳይሰናበታት ወጥቶ ሄደ፡፡ የት እንደደረሰ አይታወቅም፡፡
‘ሚሽቱን አንድ ምሽት ሲያያት ማርጀቷ ድንገት ተሰማው’ ነው ያልኩት?... አይደለም፤ ተሳስቻለሁ፡፡ የእሷ ማርጀት ሳይሆን እሱን እያስረጀችው መሆኑ ነው ያስደነገጠው፡፡ ከጠፋ በኋላ፣ ሚስትየዋም ሆኑ ጎረቤቶቹ፣ ዘመዶቹም ሆኑ ጓደኞቹ በመንግስት የደህንነት አካላት እንደታፈነ እንጂ፣ የትዳር ህይወት አፍኖት እንደጠፋ አያውቁም፡፡ ያኔ ሲጠፋ፣ መንግስት በጎሪጥ የሚያየው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባል ነበር፡፡
አሮን ፕራግማቲስት ነው፡፡ የእምነት ግትርነት ለየዋሆቹ እንጂ ለእርሱ እንደማይመጥነው ያወቀው ገና በጨቅላ እድሜ ደረጃ ሳለ ነው፡፡
ከሐይማኖት፣ ወይንም ከታሪክ ወይንም ከሌላ የማህበረሰብ እምነት ጋር እጅ እና አፋቸው ተበይዶ ተወልደው እስኪሞቱ የማይላቀቁት፣ እነሱ ናቸው የዋሆቹ፡፡ ዘፋኙ “ይወለድና እንከፍ እንከፉ ጋን ይሸከማል ከእነ ድፍድፉ” እያለ ሲያቀነቅን፣ አሮን ምን እያለ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እነማንን እያለ እንደሆነም፡፡ እሱ እንከፉ አይደለም። ነገር ግን፤ ጋን አሸካሚውም አይደለም። አሸካሚ መሆንም ዋና ግቡ እንዳልሆነ ያውቃል፡፡ ጋን አሸካሚውን እና እንከፉን ከበላይ ሆኖ ማሾር የሚፈልገው ብልጥ ነው።
የሐይማኖት ፅንሰ ሃሳብ ከፈላስፋ ገዝቶ ለነብዩ የሚሸጠው ነው እሱ፡፡ እሱ አሮን፡፡ ነብዩ ከፈጣሪ የተሰጠውን መገለጥ የሚናገር እስኪመስለው ድረስ አሮን ነብዩን ጠፍጥፎ ከፈጠረው በኋላ ይሰወራል፡፡ ነብዩ ደግሞ ራዕዩን በምድረ በዳ ጮሆ፣ ከመንጋው መሃል አድማጭ አጥቶ በከንቱ እንዳይጠፋ መታደግ አለበት፡፡ አሮን ታዳጊ ነኝ ብሎ ስለራሱ ያስባል፡፡ ከመንጋው መሃል፣ በመጠኑ ነቃ ያለውን ለነብዩ ጩኸት ጆሮ እንዲሰጥ አድርጎ ያዘጋጀዋል። ነብይም አድማጭ ያስፈልገዋል፡፡ አድምጦ የሚያስደምጥ ሰባኪ። ፈላስፋውን፣ ነብዩንና ሰባኪውን አስተሳስሮ ከመሃል ይወጣል። ሰባኪው መንጋውን ይነዳል። መንጋው እየጨመረ የሃይማኖት ድፍድፍ መሆን ይጀምራል፡፡ … መንጋው ህዝብ ይሆናል፡፡ ምዕመን፡፡ ጋኑን ከነ ድፍድፉ ተሸክሞ፣ ከዘመን ወንዝ ጅረት ጋር ተያይዞ ይፈሳል፡፡
አሮን ይሄንን የማድረግ አቅም ያለው ፕራግማቲስት ነው፡፡ ሚስቱን ማግባት አስፈላጊ ስለነበር አገባ፡፡ መተው ሲኖርበት ተወ፡፡ የራሱ ግብ አለው፡፡ እሱን የመሰሉት ሲወለዱ አከናውነው የሚያልፉትን አድርጎ ማለፍ ነበረበት፡፡
ሚስቱን ጥሎ ጠፍቶ ድሮ ወደ ለቀቃት ሀገሩ ተመለሰ፡፡ የውጭ ሀገር ኑሮ እያስረጀው መሆኑ ገባው፡፡ አዲስ አበባ ትልቅ ቪላ ቤት ገዛ። ስሙን እና ማንነቱን ቀየረ፡፡ ወላጆቹ ከገጠር ሳይወጡ፣ በኖሩበት እዛው ሞተው ሲቀበሩ ተገኝቶ አፈር አልመለሰባቸውም። ከሰበታ ወደ ጅማ በሚያመራው መንገድ ላይ በአንዲት ሚጢጢ መንደር ውስጥ ነበር የተወለደው፡፡ ለእሱ አቅም ፈፅሞ የማትመጥን ጠባብ መንደር፡፡ ስሙን ለመቀየር የወሰነው ገና መንደሯን ከመልቀቁ በፊት ነው፡፡ ገና ተወልዶ ትንሽ እንደተራመደ ጠፍቶ አዲስ አበባ መጣ። ስለ ተወለደባት መንደርም ሆነ ስለ ተራ ወላጆቹ ፈፅሞ ማስታወስ አይፈልግም፡፡ እየሱስ በበረት ተወልዶ በመስቀል መሞቱን ከራሱ ህይወት ጋር ሲያነፃፅረው፣ “አወላለድ ላይ እንመሳሰላለን” ይላል፡፡ አሟሟቱ ግን ፈፅሞ እንደማይመሳሰል ያውቃል፡፡ “ሰውን እሰቅል ይሆናል እንጂ እኔ አልሰቀልም” ብሎ በአስተማሪ ፊት የተናገረው ገና ድሮ ነው። ድሮ የኤለመንተሪ ተማሪ ሳለ። የነገረው አስተማሪ ደግሞ ቄስ ነው፡፡ የካቶሊክ ቄስ። ተናግሮ ነበር ገና በጨቅላነቱ፡፡ የግብረገብ አስተማሪው ከዛ ቀን በኋላ ጠላው፡፡ ሰይጣንን በእሱ የትምህርት ክፍለ ጊዜ እያስተማረ የቆየ መሰለው፡፡ ጠላው፤ ልጅ ነው ብሎ ጥላቻውን አዋቂ ቢሆን ሊደብቀው እንደሚሞክረው አልደበቀውም፡፡ እጅ በጆሮ ያዝ ብሎ ንፍጥ በንፍጥ አደረገው፡፡ ወላጅ ጥራ አለው፡፡ ከእሱ በስተቀር ሌሎቹ ወላጅ ነበራቸው፡፡
አሮን ወደዛ የካቶሊኮች ሚሽን ለመግባት ብዙ ብልሃት ተጠቅሟል፡፡ የራሱን ታሪክ እንደ አዲስ በአዲስ መልክ ፈጥሮ፣ቄሶቹ  እንዲራሩለት አድርጎ አምርሮ ማልቀስ ነበረበት፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ ሌት ተቀን እያደረ፡፡ ቢያንስ አዳሪ ትምህርት ቤት ሊያስገቡት መጨረሻ ላይ ተስማሙ። በትምህርቱ  ቀልድ አያውቅም ነበር። ከተወለደባት ጠባብ መንደር (አስጎሪ የሚባለውን ስሟን ፈፅሞ ጠርቶ አያውቅም) ከወላጆቹ እጣ ፈንታ ለመላቀቅ መኮብለል ነበረበት፡፡ ቄሶቹ በሰጡት የትምህርት እድል ብቻ ነበር እንደ መርከብ ወደ ሌላ እድል መሻገር የሚችለው፡፡ የዋህ አይደለም፡፡ ፈፅሞ እንከፍ አይደለም፡፡ ከእሱ በስተቀር፣ ሌላው ግን፣ በእርግጠኝነት ትንሽም ቢሆን እንከፍነት አያጣውም፡፡
ቄሶቹ የሰጡትን የትምህርት እድል እንደ ገፀ በረከት ሳይሆን እንደ ደሞዝ ነው የቆጠረው። አሳዛኝ ታሪክ ፈጥሮ፣ በመንገድ ዳር አድሮ፣ ጠዋት ቤተ ክርስቲያን ተቀምጦ አምርሮ በማልቀስ... ብዙ ለፍቶ ነው እድሉን ያገኘው፡፡ የሰጡትን እድል በደንብ ተጠቀመበት።
ከመጀመሪያው አንስቶ አንዳች ታላቅነት የእሱ፣ የግሉ መሆኑ ይሰማዋል፡፡ እያቁነጠነጠ አላስቀምጥ ይለዋል፡፡ የአባቱን የጤፍ ማሳ ማረስ ወይንም ማረም አይደለም እጣ ፈንታው። ከተወለደም በኋላ መወለዱ አላሳመነውም። እርግጠኛ መሆን ነበረበት፡፡ መሆኑን መሆን ነበረበት፡፡
አባት እና እናቱ እዛው እሱን በወለዱበት ቦታ እንደ ደረቀ የዛፍ ግንድ ተጣብቀው ቀሩ፡፡ እሱ ሌላ ውልደት ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ መጣ። ትምህርት ቤት ገባ፡፡ ወደ ዳግም ውልደት እያመራ መሆኑን የሚለካው በእየአመቱ በራሱ ላይ በሚያየው ለውጥ ነው፡፡ ቄሶቹ የሰጡትን እድል እንደ ትጋት የላብ ዋጋ ቆጠረው፡፡ የሰጡትን እድል ወስዶ ነገደበት፡፡ ከዛ በኋላ ሁሉም ማትረፊያው ሆኑ።
ከዛ ቀን በስተቀር ስሜቱን ግልፅ አድርጎ አያውቅም። የግብረገብ አስተማሪው መስማት የሚፈልገውን የውሸት መልስ መስጠት ሲችል፣ የራሱን እምነት አልቦ እምነት ገለፀ፡፡ አስተማሪው ጠመደው። መጥመዱንም አልሸሸገም፡፡  በኩርኩም ውርጅብኝ ግልፅ አደረገው፡፡ በረባ ባልረባው በተማሪ ፊት እያስወጣ አዋረደው። የግብረገብ አስተማሪው ግብረገብ የሌለው መሆኑ አይደለም አሮንን ያበሸቀው፡፡ በእነዛ አሰቃቂ የቅጣት ቅፅበታት፣ ወደፊት ልጅ ሆኖ አለመቅረቱን አስረስተውት ነበር። በኋላ፣ ካደገ በኋላ ያበግነው የነበረው በሰቆቃው ምክኒያት መርሳቱ ነበር፡፡ ግን ይሄንንም እንደ ትርፉ ቆጠረው፡፡ ወደፊት ጥቅም ላይ የሚውልበትን ጊዜ እየናፈቀ የሚያስቆየው።
አንዳንዴ ሁሉም የሰው ልጆች ያሳዝኑታል። ሁሉም ጅል መሆናቸው ነው የሚያሳዝነው። የሚያምኑት ነገር እንደሚያጃጅላቸው የደረሰበት ገና ድሮ ነው። ቄሶቹ መስማት የሚፈልጉትን ያውቃል፡፡ መስማት የማይፈልጉትንም እንደዚሁ፡፡ አስተማሪዎቹ ማንን መሆን እንደሚፈልጉ ያውቃል፡፡ መስማት የማይፈልጉትንም እንደዚሁ፡፡ እሱ ግን መሆን የሚፈልገውን ቢነግራቸው እንኳን አይሰሙትም፡፡ አይገባቸውም። የማይገባቸውን ሊያምኑ አይችሉም፡፡ መስማት እና መሆን የሚፈልጉትን ለማመን ሲሉ የሆኑትን ሆነዋል፡፡
በእነዛ የትምህርት ቤት ዘመናት የተማረው ነገር የቀለም ትምህርቱን አይደለም፡፡ ማንም የተሞላበትን ቀለም ይቀበላል፡፡ የተቀበለውን ደግሞ መልሶ ይተፋል፡፡ እሱ በትምህርት ቤት ዘመኑ የቀሰመው የሰዎችን ማንነት ነው። ማንነታቸው የተሳሳተ ነው። ያሳሳታቸው እምነታቸው መሆኑን ነው በጥቅሉ የተማረው። የተማረው እነሱን ያደረጋቸውን ነገር ሁሉ መጠየፍን ነው። መጠየፍን፣ ግን እንደተጠየፈ መደበቅን፡፡ “እነሱን ላለመሆን የሚቻለው ከማንኛውም እምነት በመራቅ ነው” አለ፡፡ ያለውን ብቻ አመነ።
ያለውን በሂደት ሆነ፡፡ የማይለወጠው ነገር ለውጥ ብቻ ነው፡፡ ከአስጎሪ የወጣው ልጅ የማይደረስበት ነገር ላይ ሁሉ በሂደት ደረሰ፡፡ የጠባብ መንደር ሰው ሊፈፅማቸው የማይችላቸውን ተፅዕኖዎች ፈፀመ፡፡ በአማኞች አማካኝነት የማያምንባቸውን ተግባሮች አከናወነ፡፡ ለወደፊት አቅጣጫው የሚጠቅመውን ማንኛውንም ልምምድ አደረገ።
መለወጥ ያለበትን እየለወጠ፣ መልበስ ያለበትን እየለበሰ… ሁሉንም እንከፍ የራሱን የእምነት ጋን ተሸካሚ ማድረጉን ተካነበት። የሚፈልገውም ዋና እውቀት ይሄ ነበር፡፡ ጋን ተሸካሚዎች የተሸከሙትን ሳያወርዱ እንዲኖሩ እና እንዲሞቱ ማድረግ። ተሸካሚው፣ እንከፍ መሆኑን ሳያውቅ፣ እውነት ብሎ የተሸከመው አተላ መሆኑን ሳያውቅ፣ ያሸከመውም እንከፍ እያለ እንደሚጠራው ሳይነቃ ማሸከም። የተሸከመውን ሳያወርድ እየኖረ እንዲሞት ማድረግ፡፡ የተሸከመውን እንዲወድ ማድረግ። ከሸክሙ ውድነት የተነሳ፣ ሸክሙ እሱን የተሸከመው እስኪመስለው ድረስ።
ጋኑን ማሸከም ስለመቻሉ እርግጠኛ መሆን ነበረበት፡፡ በሁሉም የአለም መንገዶች ሄዶ፣ በሁሉም አይነት የማይታመን ሁኔታ ውስጥ እየገባ ፈተነው፡፡ ተፈተነበት። ፈተናው ሲጠናቀቅ ተራ ሰው መስሎ ሚስት አገባ። ሚስቱን አንድ ውድቅት ሌሊት ተነስቶ ትክ ብሎ ተመለከታት። ድንገት እንዳረጀች ያወቀ ይመስል ደነገጠ። መደንገጥ ስለነበረበት። በሚስቱ ድንገተኛ እርጅና ተንገሸገሸ፡፡ ሀገሩ ድንገት ናፈቀችው፡፡ እንባው ፈሰሰ፡፡ ትዝ አለው የጥንቱ፡፡ የሞቱት ወላጆቹ ናፈቁት፡፡ ያልቀበራቸው። የሀገሩ አየር፣ የኩበት ጭሱ፣ አቧራው ናፈቀው፡፡
ከለበሰው ልብስ እና ካንጠለጠለው መጠነኛ ሻንጣ በስተቀር ያፈራውን ሀብት ፈፅሞ ዞሮ ሳያይ ነው  ጠያራ የተሳፈረው፡፡ አዲስ አበባ ደርሶ የቦሌ አየር ማረፊያን እግሩ ሲረግጥ በግንባሩ ተደፍቶ መሬቱን ሳመ፡፡ እንዴት ይንሰቀሰቅ እንደነበር  ያስተዋሉ ልባቸው ተነካ፣ አብረውት አለቀሱ፡፡ ከሀገሩ ከወጣ ሀያ አመት ከማለፉ በስተቀር ሌላው ትያትር ሁሉ ውሸት ነበር፡፡ እንዲያምኑ የሚፈልገውን የማሳመን አቅም ብቻ ነው ሀብቱ።
ነፍሱ ግን ያኔ የግብረገብ አስተማሪው ሲያስጨንቃት አንድ ጊዜ ብቻ እውነት ተናግራለች፤ አምልጧት፡፡ “እኔ ሰውን እሰቅል ይሆናል እንጂ ማንም እኔን አይሰቅልም”
ከዛ ቀን በኋላ፣ የነፍሱን እውነት በአንደበቱ አውጥቶ ላለመናገር ጥቁር መሃላ ማለ፡፡ ነፍሱ፣ ለአዕምሮው እንጂ ለስሜቱና ለአንደበቱ መናገር ፈፅሞ አቆመች፡፡ በአዕምሮው የሚያስበው ሁሉ፣ በፊቱ ገፅታና በሰውነቱ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ብለው የሚያምኑ ስንቶች ወደ እንከፍነት ተቀይረዋል፡፡ እንከፍ ስለመሆናቸው እንኳን ድሮውኑ ያውቃል፡፡ እምነት ያለው ሁሉ፣  ዞሮ ዞሮ ጋኑን ከነድፍድፉ መሸከሙ አይቀርም። እምነት ያለው ሁሉ እንከፍ ስለመሆኑ አሮን ያምናል፡፡ እሱ እንከፍ ስላለመሆኑ ያለው ብቸኛ ማረጋገጫ አለመሸከሙ ነው። ያሸክማል እንጂ አይሸከምም።
ከዚህ እምነቱ በስተቀር ሌላ የሚተማመነው ቀኖና የለውም፡፡ አዕምሮው ያለ ስሜት እና ያለ የዋህነት በቀጥታ ከእውነታው ላይ እቅጩን ጨምቆ ያወጣል፡፡ ያወጣውን እንደ አስፈላጊው አግባብ አነጣጥሮ ይጠቀምበታል። አሮን የሚያነጣጥርበትን ኢላማ አስቀድመን ደርሰንበታል ያሉ ሁሉ፣ የራሳቸውን እምነት ተከትለው፣ የእምነታቸው አይነት ወደ  ቆፈረው ገደል ወድቀዋል፡፡ ከእምነታቸው ጥንካሬ የተነሳ ውድቀታቸውን እንኳን እንደ ፅድቅ ነው የቆጠሩት፡፡
እስካሁን በአለም ዙሪያ በተለያየ ቦታ ሲኖር፣ ያስፈለገውን አይነት ጋን ፈጥሮ ያነጣጠረበትን እንከፍ ማሸከም ነበር የተለማመደው፡፡ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ለአንድ አላማ ነው፡፡ ባዶ የነበረው ጋን ውስጥ ይዘት ለመጨመር። እንከፎች ጋኑን ብቻ ሳይሆን ድፍድፉንም ተሸክመው እንዲጓዙ ንጥረ ነገሩን ለመቀመም ነው፡፡ ባዶ ጋን የፍርሃትና የጥርጣሬ ማጠራቀሚያ ነው፡፡ እምነት የእንከፎች ወጥመድ እንደሆነው፡፡ ዘላለማዊ ይዘት ያለውን ጋን እንከፎች ተሸክመው ከትውልድ ትውልድ ሳይጠራጠሩ እንዲኖሩ… ድፍድፉ መሰራት አለበት፡፡
አሮን የሰውን ልጅ ጠንቅቆ ያውቀዋል። የድፍድፉን ጥሬ እቃ የሚያገኘው ከዚህ እውቀቱ ነው፡፡ የሰው ልጆች የእምነት ተፈጥሮ የማይለወጥ ሀቅ ነው፡፡ የሰው ልጅ መለኮታዊ ፍጥረት ነው፡፡ ሳያመልክ መኖር አይችልም። ባንዲራውን ቢሆን ወይንም ሰማይ ላይ አለ ብሎ የሚያምነውን እግዜር... ብቻ ሳያመልክ መኖር አይችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሰማይ ለሚኖር ፈጣሪው ያዘጋጀውን አምልኮውን ለአንድ ምድራዊ አነጋጋሪ ዘፋኝ ሲከፍል ይገኛል። ለማይሆን ነገር የማይሆን ዋጋ እንዲከፍል የሚያዘጋጁት የአሮን አይነቶቹ ናቸው፡፡ አሸካሚዎቹ። የአሮን አይነቶች በምድር ላይ ቁጥራቸው እጅግ ጥቂት ነው፡፡ ጋን ተሸካሚዎቹ ግን ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡
ጥቂት ጊዜ ያስፈልገዋል ዝግጅቱን ለማድረግ። የተወሰኑ ደቀ መዝሙሮች መመልመል አለበት፡፡ አዲስ አበባ የመጣው ቤተ ዘመዶቹን ለማፈላለግ፣ ወይንም የሽንብራው ጥርጥር እና የዛፎቹ ፍሬ ናፍቆት አይደለም፡፡ ደቀ መዝሙሮቹ ከዚሁ ከሀገሩ ባህል የመነጩ ከሆኑ፣ ሀገር በቀል ጋን እና ድፍድፍ ጠንስሶ  ሀገሬውን ማሸከም እንደሚችል እርግጠኛ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ እርግጠኛ የሆነው በጥንቃቄ ቀምሮ ትልሙን ከጨረሰ በኋላ ነው።
ሁሉም የሰው ልጅ እንከፍ መሆኑን ብቻ ያምናል፡፡ ከዚህ በተረፈ ሌላ ግትር እምነት የለውም፡፡ ሁሉም ጊዜያዊ ነው። እንደ አስፈላጊነቱ ይለወጣል፡፡ ማንንም ወዶ አያውቅም፡፡ መውደድ ምን ማለት እንደሆነ ግን ጠንቅቆ ያውቃል። ስለሚያውቅ በከንቱ አይደክምም፡፡
ለሰው አውጥቶ ሊናገር ይቅርና ከራሱ ነፍስ እንኳን የሚደብቀው፣ ደብቆም ጥርሱን ነክሶ መደበቁን የረሳው አንድ ለረጅም ዘመን አብሮት የቆየ ሃቅ አለ፡፡ አንድ የሚቀናበት ማንነት አለ። ቅናት እንኳን ሊባል ባይችል… ትንሽ በንቀት ሊሳለቅበት ሞክሮ ያቃተው አንድ ማንነት፡፡
በአወላለድ እንመሳሰላለን ብሎ ስለሚያስብ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ምንነት በተመለከተ ትንሽ ስሜቱ ከእውቀቱ የበለጠ ይጎላበታል። እየሱስ ስለሚባለው ሰው ሲያስብ ትንሽ ጥንካሬው ይፈተናል፡፡
እሱ አሮን ግን በበረት ቢወለድም ራሱን ለእነዚህ እንከፎች አሳልፎ ሰጥቶ መስዋእት አይሆንም፡፡ እነሱ በራሳቸው ፈቃድ ራሳቸውን አሳልፈው ለእሱ ይሰጡታል፡፡ ለእሱ ለአሮን። መስዋአትነት የከፈሉ እና ፃድቅ የሚሆኑ ስለመሰላቸው ነው፡፡ “ጋኑን እስከ ድፍድፉ እንደ መስቀል አሳልሜ አሸክማቸዋለሁኝ” ብሎ አሮን በውስጡ ይስቃል፡፡
እንዲህ እየዛተ በውስጡ ሲስቅ፣ በፊት ገፅታው ላይ እየሳቀ መሆኑን የሚያስጠረጥር  ማረጋገጫ ለምልክት እንኳን አይገኝም፡፡ በሀዘን እና ተስፋ መቁረጥ ልቡ የተሰበረ፡፡ ባህር ማዶ ለብዙ ዘመናት ኖሮ ህልሙን ተነጥቆ የመጣ የአብዮቱ ዘመን ሰው ነው የሚመስለው፡፡ በተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን ከወጣ ጀምሮ ወደ ቀልቡ ያልተመለሰ… ግማሽ ምሁር ግማሽ ባህታዊ ቅርፅ አለው፡፡ ተሸካሚ እንጂ አሸካሚ ሊሆን እንደሚችል ማንም አይጠረጥርም።  

Read 836 times