Saturday, 30 April 2022 14:47

ያለምዘርፍ የኋላውና የኢትዮጵያ ማራቶን አዲስ ሪከርድ 2:17:23

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    ባለፈው ሰሞን በተካሄደው የሃምቡርግ ማራቶን ላይ አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድ አስመዝግባለች፡፡ ያለምዘርፍ ለመጀመርያ ጊዜ በተወዳደረችበት ማራቶን ያስመዘገበችው አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን  ሪከርድ 2:17:23 ነው፡፡
በዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ቡድን ኤንኤን ራኒንግ አባል የሆነችው አትሌቷን በዋና አሰልጣኝነት የያዛት የቀድሞ አትሌት ተሰማ አብሽሮ ሲሆን በኤጀንትነት የሚያገለግላት ደግሞ ዳን ቫን ደንበርግ  ይባላል፡፡ በታዋቂው የአሜሪካ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ  ስፖንሰርነት የምትሮጠው ያለምዘርፍ፤ በአገር ውስጥ የኢትዮ-ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ ክለብን እንደምትወክል ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቶችና አትሌቲክስ ዙርያ በመዘገብ የሚታወቀው ኢትዮራነርስ በማህበራዊ ገፁ እንዳወሳው አትሌት ያለምዘርፍ በሃምቡርግ ማራቶን ላይ ገና በወጣትነቷ ያሳየችው ብልጠት ያለውና የተጠና የጭንቅላት ሩጫ ሊያስደንቃት ግድ ይላል፡፡ በመጀመሪያ የማራቶን ሩጫዋ ያስመዘገበችው ሰዓት ለኢትዮጵያ ክብረወሰን ሆኖ ከመመዝገቡም በላይ በዓለም የምንግዜም ፈጣን የማራቶን ሰዓቶች በስድስተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ይሆናል። በሩጫ ዘመኗ ገና ለምታሳየው ምርጥ ብቃቷ መገለጫም ሆኗል፡፡
ለአትሌት ያለምዘርፍ ስኬት የትዳር አጋሯ የሆነው ገነቱ ሞላልኝ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ያወሳው ኢትዮራነርስ  ከገጠር ከትምህርት ቤት ጀምሮ አብረው መሆናቸውንና እንደ ወንድምና እህት እንደሚተያዩ ፅፏል። እንደ ኢትዮራነርስ ሃተታ ያለምዘርፍ በገጠር ያሰለጠናት የነበረን አሰልጣኝ፤ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ያሰለጠነቷን አሰልጣኞች፤ በሩጫ ዘመኗ አሻራ የጣሉትን በሙሉ  አትረሳም። በእምነቷ ጠንካራ፤ እጅግ በጣም ስርዓት ያላት ሩህሩህ ቁጥብ፤ ስራዋን አክባሪ፤ ላመነችበት ነገር ወደ ኋላ የማትል ደፋር፤ ንግግር አዋቂም ነች፡፡ ከስኬቷ ጀርባ ዋና አሰልጣኟ ተሰማ አብሽሮ  እንደሚጠቀስም ዘገባው ይገልፃል፡፡ በ6 አመት የማሰልጠን ቆይታው የዓለም 10 ኪሎ ሜትር ሪከርድ እንድትሰብር ያስቻለው አሰልጣኝ ተሰማ፤ ከያለምዘርፍ ሌላ ከሚያሰለጥናቸው አትሌቶች ደጊቱ አዝመራው በለንደን ማራቶን በ2:17:58 መሮጧ እንዲሁም ሃቨን አለሙ በሮተርዳም ማራቶን በ2:20:19 ማሸነፏ ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት አየተሳካለት መምጣቱን የሚመሰክር ነው ብሏል፡፡
 ያለምዘርፍ ሩጫን የጀመረችው በ12 ዓመቷ ነው፡፡ 22ኛ ዓመቷ ላይ ስትደርስ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተሳካላት ሆናለች፡፡ ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን በ2019 በራባት ባደረገችው የግማሽ ማራቶን ያስመዘገበችው 1:09:13 የሆነ ግዜ በጎዳና ላይ ሩጫ ያላትን ብቃት ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውጤት ከ1 ዓመት በኋላ በኒውደሊሂ ግማሽ ማራቶን በ64:46 ስታሸንፍ በታሪክ ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ሲሆን፤ ለዓለም ሪከርድ በ15 ሰከንዶች የዘገየ ምርጥ ውጤት ነበር፡፡ በ2021 በኢስታንቡል ማራቶን የግሏን ምርጥ ሰዓት በ6 ሰከንዶች ስታሻሽል በግማሽ ማራቶን በምንግዜም ፈጣን አጨራረስ በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠውን ሰዓት ለማስመዘገብ በቅታለች፡፡ በ2022 ላይ ደግሞ ሌላ አስደናቂ ውጤት ያስመዘገበችው በ10ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የዓለም ሪከርድን በ22 ሰከንዶች በማሻሻል በ29:14 ስፔን ካስቴሎን ላይ አዲስ ታሪክ በመስራት ነው፡፡  በ2019 እና በ2021 የታላቁ ሩጫቀ በኢትዮጲያ የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ አሸንፋለች፡፡ በ2019 በሞሮኮ ማራቶን በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳልያ የወሰደች ሲሆን በ2020 በጊዲያ በተካሄደ የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ላይ በቡድን የወርቅ በግሏ የብር ሜዳልያ ተጎናፅፋለች፡፡
አትሌት ያለምዘርፍ በሩጫ ዘመኗ ያስመዘገበቻቸው ምርጥ ሰዓቶች በ5 ኪሜ 14:53.77፤ በ10ኪሜ 29:14፤ በግማሽ ማራቶን 1:03:51 እንዲሁም በማራቶን ለኢትዮጵያ አዲስ ክብረወሰን የሆነው 2:17:23 ናቸው፡፡
ከያለም ዘርፍ በፊት በማራቶን የኢትዮጵያ ክብረወሰንን ይዛ የቆየችው በ2019 በዱባይ ማራቶን ስታሸንፍ 2:17:41 የሆነ ሰዓት ያስመዘገበችው ወርቅነሽ ደገፋ ነበረች፡፡ አትሌት ወርቅነሽ በተመሳሳይ የውድድር ዘመን የቦስተን ማራቶን ያሸነፈች ሲሆን በ2020 እኤአ ላይ የዱባይ ማራቶንን ደግማ ካሸነፈች በኋላ አልተወዳደረችም፡፡ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባበ37ኛው የለንደን ማራቶን በሁለተኛ ደረጃ ስትጨርስ ያስመዘገበችው 2፡17፡56 አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድ የነበረ ሲሆን፤ በ2012 እኤአ ላይ በለንደን ኦሎምፒክ ቲኪ ገላና በ2፡18፡58 ሰዓቷ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሆና የወርቅ ሜዳልያ ስትጎናፀፍ ያስመዘገበችው የኢትዮጵያ ማራቶን ክብረወሰንም ነበር፡፡
አትሌት ያለምዘርፍ በ2:17:23 ያስመዘገበችው አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ክብረወሰን የዓለምንም ማሻሻል በምትችልበት ደረጃ ያስቀምጣታል፡፡ በሴቶች ማራቶን ታሪክ በመጀመርያ ውድድሯ ፈጣን ሰዓትን በማስመዝገብ፤ የቦታውንና በመላው ጀርመን ምርጥ ሰዓትን የያዘችበት ሆኗል፡፡  ወርቅነሽ ደጋፋ በ2019 እኤአ ላይ በዱባይ ማራቶን ያስመዘገበችውን ሰዓት በ18 ሰከንዶች ነው በማሻሻል ነው ክብረወሰኑን የያዘችው፡፡
የአትሌቷ ኤጀንት የሆነው  ቫን ደንበርግ በሚቀጥሉት ሁለት የውድድር ዘመናት ብዙ ማራቶን እንደማትወዳደር የገለፀ ሲሆን እንደሌትስራን ዘገባ ይህም በማራቶን ፈጣን ሰዓት የማስመዝገብና የውጤት የበላይነቱን በኬንያውያን ይዞታ እንዲቆይ ያደርገዋል፡፡
የዓለም ማራቶን ሪከርድ ከ20 ዓመት በፊት በእንግሊዛዊቷ አትሌት ፓውላ ራድከሊፍ በለንደን ማራቶን ላይ በ2:18:56, እንደተመዘገበ ይታወቃል፡፡


Read 11158 times