Saturday, 30 April 2022 20:13

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፤ እባክዎ “ልዝብ አምባገነን” ይሁኑ!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ “ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ወያኔ ይሁኑ” በሚል ርእስ በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አጭር ማስታወሻ ማቅረቤን አስታውሳለሁ፡፡ በዚያ ጽሑፌ “ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ወያኔ ይሁኑ” ያልኩት ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ነበር፡፡ ይህንንም ያልኩበት ምክንያት በወቅቱ በያቅጣጫው ከመሬት እየተነሳ የሚጮኸው በመብዛቱ፤ “የሚታሰረውን አስረው፣ ቀጥተውና ገስጸው… እንደ ወያኔ ፀጥ ለጥ አድርገው ያስተዳድሩ” ለማለት ነበር፡፡
ይህንን ምክር እኔ ብቻ ሳልሆን በወቅቱ በርካቶች በተደጋጋሚ ያነሱት ነበር። ጠቅላይ ሚንስትሩና በዙሪያቸው ያሉ የብልጽግና የፖለቲካ ሹማምንት ምክራችንን ሰሙም አልሰሙ በርግጥ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት በርካታ ሰዎች ታስረዋል፣ ተፈተዋል። የሚገርመው ነገር “መታሰር የሚገባቸው” ዝንባቸው እሽ ሳይባል (ሳይታሰሩ)፤ መታሰር የማይገባቸው ያለ አግባብ መታሰራቸውንም አስተውለናል፡፡
በዚህ ረገድ “አሸባሪ” ተብሎ የተፈረጀ ኃይል ከራሱ መንግስት ቀለብ እየተሰፈረለት፣ ጥይት ነዳጅና ስንቅ እየተላከለት፤ እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር መድኃኒትና ቀለብ እየተጫነለት በንፁሃን ዜጎች ላይ በርካታ በደል ሲያደርስ ልባችን እየደማ አይተናል፣ ሰምተናል። መንግስት ለምን ይህንን እንደሚያደርግም በተደጋጋሚ ጠይቀናል፡፡ ግና የረባ ምላሽ ሳናገኝ ህዝብ ብዙ ዋጋ መክፈሉንና አሸባሪው ኃይል እስከ መሀል አገር ዘልቆ በመግባት ከፍተኛ ውድመት አድርሶ ተመልሷል፡፡ አሁንም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ህዝብ የሚከፍለው ዋጋ ሊቆም ባለመቻሉ ነው በተለይ ጠቅላይ ሚንስትሩ “ልዝብ-ደግ-ገራም አምባገነን” ቢሆኑ የሚል ምክር ለመለገስ ተስፋ የማይቆርጠውን ብዕራችንን ያነሳነው፡፡
ከሁሉ አስቀድሜ “ልዝብ አምባገነን” ማለት ምን ማለት ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሆኑ ሃሳቦችን አቀርባለሁ፡፡ ከዚያም ስለ “ልዝብ አምባገነን” ባህሪያትና በዓለማችን በ“ልዝብ አምባገነንነት” የሚታወቁት የሀገር መሪዎች እነማን እንደሆኑ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ በመጨረሻም የማጠቃለያ ነጥቦችንና ምክረ ሃሳብ በማቅረብ ማስታወሻዬን እቋጫለሁ፡፡
***
በእንግሊዝኛ “Benevolent Dictator” የሚለውን ሐረግ ቃል በቃል ወደ አማርኛ ስንመልሰው በአጭሩ “ልዝብ አምባገነን ወይም ደግ አምባገነን ወይም ገራም አምባገነን” የሚል ትርጉም ይሰጠናል፡፡ በስፓኒሽ ቋንቋ “dictablanda” የሚለው ቃል “አምባገነንነት” ማለት እንደሆነና “አምባገነንነት” ነፃነትን መጠበቂያ የዲሞክራሲ ስልት እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ በፖርቱጋል ቋንቋ ደግሞ “ditabranda” ማለት “አምባገነንነት” ማለት ነው የሚል ተመሳሳይ ትርጉም አለው።
“ልዝብ አምባገነን ወይም ደግ አምባገነን ወይም ገራም አምባገነን” የሚለውን ቃል በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ሰፋ አድርገን ብናየው የተለያዩ ምሁራንና ጸሐፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችንና ብያኔዎችን ሰጥተውበት እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ፡- ማንኩር ኦልሰን የተባለ ጸሐፊ “ልዝብ አምባገነንነት በግ እንደሚያድን ተኩላ ሳይሆን፤ ከብቶቹ በደንብ መጠበቃቸውን እንዳረጋገጠ አርብቶ አደር የሚታይ ነው” በማለት ይገልጸዋል።
አንዳንድ ምሁራን ይህንን ጽንሰ ሃሳብ እንዲህ በማለት ያብራሩታል፡፡ “ልዝብ አምባገነን የመንግስት ስርዓት የመሪው ስልጣን የሚመነጨው ከህዝብ ነው። እናም ደጉ አምባገነን መሪ ስልጣኑን ያላግባብ ከተጠቀመ ዳግም አልመረጥም፣ ስልጣኔን አጣለሁ ብሎ ስለሚፈራ በህዝብ ላይ በደል አይፈጽምም፡፡ እናም የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ስልጣኑን በጥበብና በጥንቃቄ ይጠቀምበታል፡፡ በዚህም ምክንያት ድርቅ ካሉ፣ ለህዝብ ጥቅም ካልቆሙ፣ ጨፍጫፊ አምባገነኖች ይለያል” ይላሉ፡፡
ሌሎች ጸሐፍትም ተመሳሳይ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ “ልዝብ አምባገነንነት ንድፈ-ሃሳባዊ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት ቅርጽ ነው። በዚህ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት ቅርጽ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ የሆነው መሪ የፖለቲካ ስልጣኑን የሚጠቀመው የመላውን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ነው” ይላሉ፡፡
የልዝብ አምባገነኖችን ባህሪያት የተነተኑ ምሁራን ደግሞ፤ “የልዝብ አምባገነን የመንግስት አስዳደር ስርዓት ማለት አምባገነናዊ ፈላጭ ቆራጭ መሪ መንግስታዊ የፖለቲካ ስልጣኑን ተግባራዊ የሚያደርግበት የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ነው፡፡ ልዝብ አምባገነን መሪው ይህንን የሚያደርገው የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው ቢባልም፤ የተግባር እንቅስቃሴው ሲታይ ይዞት ከተነሳው ዓላማና ከሚያራምደው ርዕዮተ-ዓለም እንዲሁም ከደጋፊዎቹ ፍላጎት ጭምር በተቃራኒ የቆመ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ፤ ልዝብ አምባገነንኖች የዜጎች የነፃነትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች በህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ፣ በዲሞክራሲያዊ አግባብ (በሕዝበ ውሳኔ ወይም በህዝብ በተመረጡ ተወካዮች አማካይነት) እንዲወሰኑ ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህም አሰራራቸው ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር ጠቃሚ ተግባራትን የሚያከናውኑበት አጋጣሚ አለ” ይላሉ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን።
“ልዝብ አምባገነን” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ጆን ስቱዋርት ሚል እ.ኤ.አ በ1869 ዓ.ም “classic On Liberty” በሚል ርእስ በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል። ጆን ስቱዋርት ሚል ስለ ግለሰቦች ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሚሟገት ቢሆንም፤ በዚያ መጽሐፉ በታዳጊ ሀገሮች የተለየ የውሳኔ አሰጣጥ መንገድ እንዲኖር ሃሳብ አቅርቧል። ታዳጊ ሀገሮች የተረሱና ኋላቀር የህብረተሰብ ክፍሎችን የያዙ ናቸው። እናም “የመጨረሻ ውጤቱ የኋላ-ቀሩን ህብረተሰብ ህይወት ለማሻሻል እስከሆነ ድረስ ከኋላቀር ማህበረሰብ ጋር ስለ ዲሞክራሲና ነፃነት አለማንሳት ህጋዊ ነው” ይላል ሚል። “የሰው ልጅ በእኩልነት መንፈስ በመወያየት መወሰን የሚችልበት ሁኔታ እስከሌለ ድረስ ነፃነት ትርጉም አይኖረውም” በማለትም ለልዝብ አምባገነን አስተዳደር ያለውን ድጋፍ ይገልጻል፡፡
ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ህጋዊነት (Legtimacy) ሽፋን ለመስጠት ሲባል በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ስለ ልዝብ አምባገነን መሪ አስፈላጊነት አዘውትሮ ይነገር እንደነበር አንዳንድ እድሜ ጠገብ ድርሳናት ያስረዳሉ። ኦሊቨር ሮብሰን የተባለ ጸሐፊ፤ “አምባገነን የሚለው ቃል አሉታዊ ትርጉም አለው፡፡ ይህንን ቃል ስንሰማ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ነገር ጨቋኝ የአገዛዝ ስርዓት፣ የብዙ ሰዎች ስቃይ፣ የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት ነው፡፡ ነገር ግን አምባገነንነት ምንም ማለት አይደለም፡፡ ስህተትም አይደለም፡፡ እንዲያውም ለሁሉም ሰው የሚበጅ በጣም ጥሩው የሚባለው የፖለቲካ ስርዓት አምባገነናዊ አስተዳደር ነው። አምባገነንነት ጥሩ ነው፣ ጠቃሚ ጎን አለው ሊባል የሚችለው ግን መሪው ደግ፣ ልዝብ እና ለብዙሃኑ ህዝብ ጥቅም የሚሰራ ደግ ሰው ከሆነ ነው” በማለት ዘርዘር አድርጎ ያስረዳል፤ ጸሐፊው ኦሊቨር ሮብሰን፡፡
***
ልዝብ አምባገነኖች ከጭፍንና ስልጣናቸውን ያለ አግባብ ከሚጠቀሙ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነኖች በፍጹም ይለያሉ። ልዝብ አምባገነንነትን ከሁሉ የተሻለው፣ እንከን የማይታይበት የፖለቲካ ስርዓት ነው የሚያስብለውም ከፈላጭ ቆራጭና ከገዳይ አምባገነኖች የተለየ ባህሪ ያለው መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ዓለማችን አልፎ አልፎ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጨምሮ በርካታ ልዝብ-ደግ-ገራም አምባገነኖችን አስተናግዳለች፡፡
ፔይሲስትራቶስ፡- ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ561 እስከ 527 በነበሩት ዓመታት የኖረው ፔይሲስትራቶስ (Peisistratos) የግሪኳን ጥንታዊት ከተማ ሦስት ጊዜ ያስተዳደረ ቀዳሚ ልዝብ አምባገነን ነው ተብሎ ይጠቀሳል። ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጣን ላይ በወጣበት ወቅት በአቴናውያን ምክር ቤት “ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን” ተብሎ ተወግዞ ነበር፡፡ ተቃዋሚዎቹ በሰሩት ሸፍጥ ለእስር ተዳርጎም ነበር፡፡ ከእስር ሲወጣ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አቴንስ አደባባይ ዘለቀ፡፡ የአቴንስ ህዝብ “መሪያችን እንኳ ደህና መጣህ” ብሎ ተቀበለው፡፡ ይሁን እንጂ እንደገና ከመንበረ ስልጣኑ ተፈንቅሎ ለስደት ተዳረገ። ተስፋ የማይቆርጠው ፔይሲስትራቶስ፤ ለ10 ዓመታት በስደት ቆይቶ እንደገና ለምርጫ ቀረበ፡፡ ሰፊ ድጋፍም አገኘ፡፡ ህዝቡ ለ3ኛ ጊዜ መረጠው። በሁሉም የስልጣን ዘመኑ ፔይሲስትራቶስ ታዋቂ እና ተወዳጅ ገዥ ነበር። ለህዝብ ሰርቷል፡፡ ለአቴንስ የሰላምና የብልጽግና ጊዜ ፈጥሯል።
አሾካ፡- ታላቁ አሾካ ከ304 እስከ 231 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የኖረ ሲሆን፤ በህንድ የሞሪያን ግዛት ገዢ ነበር፡፡ አሾካ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን ሲይዝ ከሱ በፊት እንደነበሩት ገዢዎች ጨካኝ ነበር፡፡ ወታደራዊ ኃይሉን ተጠቅሞ ግዛቱን ለመቆጣጠርና ለማስፋፋት ችሏል፡፡ እስረኞች የሚሰቃዩበት “የአሾካ ሲኦል” የተሰኘ እስር ቤትም ገንብቶ ነበር። ግዛቱን ባስፋፋበት ወቅት አሾካ በርካታ ጦርነቶችን ከጎረቤቶቹ ጋር ተዋግቷል። በጦርነቱ ሂደት 300,000 የሚገመቱ ተዋጊዎቹ አልቀዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ ጦርነት በኋላ አሾካ መጸጸቱን በአደባባይ ገለጸ፡፡ በእርሱ ስር ያሉ ባለሥልጣናቱ ድሆችንና አረጋውያንን መርዳት እንዳለባቸው የሚገልጽ አዋጅ አውጥቷል። ሕክምና መስጫ ተቋማትን አቋቁሟል። ዛፎችን በመትከል አካባቢ ተንከባክቧል። ወደ ስልጣን ዘመኑ መጨረሻ የሰራቸው እነዚህ ህዝብ ተኮር ስራዎቹ አሾካን “ልዝብ አምባገነን” አሰኝተውታል፡፡
ማርከስ ኦሬሊየስ፡- ማርከስ ኦሬሊየስ አንቶኒነስ በ121 ዓ.ም በሮም ተወለደ። በ161 ዓ.ም ወደ ስልጣን ወጣ፡፡ ማርከስ የሮም የመጨረሻው ደግ ንጉሠ ነገሥት እንደሆነ ይነገራል፡፡ “ግላዲያተር; - (Gladiator) በሚለው ፊልም ላይ የቀረበው ሃሳብ (በልብ ወለድ መልክም ቢሆን) ከማርከስ ኦሬሊየስ ህይወት የተወሰደ ነው ይባላል፡፡ ማርከስ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለማስተዳደር ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን በአገዛዙ ዘመን ብዙ ችግሮች አጋጥመውት ነበር። በወቅቱ በሮም ከነበረ አክራሪ ሃይማኖታዊ ቡድን ጋር የማያቋርጥ ጦርነት ገጥሞታል፡፡ በሮም ግዛት ውስጥ ያለውን ሰላም ለማስጠበቅና ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ገለልተኛ የሆነ የመንግስት አስተዳደር ለማስፈን መዋጋት ነበረበት፡፡ ይህም ሆኖ፣ ከራሱ ክብርና ምቾት በፊት የሮምን ሕዝብ ፍላጎት የማስቀደም ተግባሩ ማርከስን እንደ ደግ መሪ (ልዝብ አምባገነን) አስቆጥሮታል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት የጥንት ዘመን “ልዝብ አምባገነኖች” በተጨማሪ የፋርስ ንጉስ የነበረው ኮስሮው ቀዳማዊ፣ የፕሩሲያው ታላቁ ፍሬድሪክ፣ የፔሩው ሲሞን ቦሊቨር ተጠቃሽ ናቸው። ወደ ቅርብ ዘመን ስንመጣ ደግሞ የቱርኩ ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ፣ የቦትስዋናው ሰር ሴሬሴ ካማ፣ የጆርዳኑ አብዱላህ 2ኛ፣ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ መሪ የነበረው ጆሴፍ ብሮዝ ቲቶ እንዲሁም የሲንጋፖሩ ሊ ኩዋን ዩ በልዝብ አምባገነኖች ዝርዝር ውስጥ ስማቸው የተከተበ “ደግ አምባገነኖች” ናቸው፡፡
***
ይህ ወቅት ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ የጥላቻና የበቀል ድምፅ አየሩን እየሞላው ነው፡፡ በእነ የመን እና ሶማሊያ ስናየው የኖርነው፣ አሁንም እያየነው ያለው እሳት በእያንዳንዳችን ደጅ እየጨሰ መሆኑን ማስተዋል አለብን፡፡ በአማተር ፖለቲከኞች የተሞላው ብልጽግና ፓርቲ በታሪክ አጋጣሚ የያዘውን ስልጣን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል ባለመቻሉ በሀገሪቱ በሰላም ወጥቶ መግባትም ሆነ ሰርቶ መኖር አዳጋች መሆኑ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል። የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ ባለመቻሉ የህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መልፈስፈስ እየተስተዋለ ነው። ክልሎችና ፌዴራል መንግስቱ ያላቸው ግንኙነት ከመላላቱም በላይ የተኳረፉ ጎረቤታሞች መስለዋል፡፡
እንደሚታወቀው ዶ/ር ዐቢይ ወታደር ናቸው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ምሁር ናቸው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ መንፈሳዊ ሰው ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት ማንነቶች ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአመራር ሰብእና እና ባህሪ አስተዋጽዖ አላቸው ብሎ መውሰድ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ሦስቱ ማንነቶች ለየብቻቸው በተናጠል ጎልተው ከወጡ ችግር ሊኖር ይችላል። ይህም ማለት ኮሎኔል ዐቢይ ወታደርነታቸው ብቻ ጎልቶ ቢወጣ እንደ ኮሎኔል መንግስቱ የለየለት አምባገነን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምሁርነቱ ጎልቶ ቢወጣ እንደ ዘረኛው መለስ ዜናዊ የብሔር ከረጢት ውስጥ ገብተው ጠባብ ብሔርተኛ ብቻ ሳይሆን የለየለት አምባገነን ሆነው “ጠላቴ” የሚሉትን ሁሉ ማረሚያ ቤት በማጎር፣ ውሃ በተሞላ የሃይላንድ ላስቲክ ማኮላሸት ውስጥ መግባታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ መንፈሳዊነቱ ቢጎላ ቤተ-ክርስቲያን - መስጂድና - ፀሎት ቤት ሲያዳርሱ፤ አሊያም ቆራጥ የፖለቲካ እርምጃ መውሰድ አቅቷቸው ከራሳቸው ጋር ሲወዛገቡ ሀገርና ህዝብ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በመክፈል ሲታመስና ሲተራመስ መመልከት ሳይታለም የተፈታ ይሆናል፡፡  ዶ/ር ዐቢይ ሦስቱን ማንቶች በተናጠል አንፀባርቀዋል ለማለት ባያስደፍርም መንፈሳዊነቱ እየሳባቸው መሆኑን የሚያሳዩ መገለጫዎችን ማስተዋል ይቻላል፡፡ በዚህ ወቅት የሚታየውም ይኸው ይመስለኛል!
በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ በተቋቋመው የሽግግር መንግስት ዋና ጸሐፊ (3ኛው ባለስልጣን) የነበሩት አቶ ተስፋዬ ሐቢሶ በእኔ የፌስቡክ ገጽ ላይ ስለ ዶ/ር ዐቢይ በጻፉት አስተያየት፤ “[ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ] ተራ የወንጌል ሰባኪነቱን ትቶ ገራም አምባገነን ሆኖ (benevolent dictator)፣ ሲያስፈልግ ካሮት እያቀረበ፣ ሲያስፈልግ ደግሞ ዱላ (carrot & stick) እየተጠቀመ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት፣ የህዝብን ደህንነትና ሰላማዊ አብሮነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ የሚችል መሪ ቢሆን ኖሮ ምንኛ ደስ ባለኝ! ዛሬ እኮ ሁሉም ወገን ባለው የፖለቲካ ስርዓት ተስፋ ቆርጦ ለመሆኑ መንግስት አለ ወይ እያለ ምሬቱን በአደባባይ እያስተጋባ ነው፣ አብዱራህማን። የለውጡ ባቡር ወደ ገደል እየገሰገሰ ላለመሆኑ ምን ያህል እርግጠኞች ነን? አላህ ይታደገን እንጂ የሚገዳደሩን አደጋዎች የትየለሌ ናቸው!!!” ብለዋል። በዚህ የአቶ ተስፋዬ አስተያየት እኔም እስማማለሁ። ዶ/ር ዐቢይ “ልዝብ አምባገነን” ቢሆኑ ኖሮ ለዚህ ወቅት የሚመጥን አመራር መስጠት ይችሉ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግስት ሁሉንም ነገር ዳር ቆሞ እየታዘበ ያለበት ሁኔታ ይስተዋላል። ይህ ሁኔታ መንግስት ያለውን “የጥንካሬ ደረጃ” ለመገምገም ሆን ተብሎ የተደረገ ፖለቲካዊ ንዝረት (Political shock) ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባለ አደገኛ የፖለቲካ አወቃቀር ባለው፣ በተሰነጣጠቀና የገደል አፋፍ ላይ በዘለቀ ሀገር እንዲህ ያለ “ፖለቲካዊ ንዝረት” ጥንካሬን ከመለካት አልፎ ያልታሰበ አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል ግምት ውስጥ ማስገባት ብልህነት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
እንደኔ እንደኔ ህዝብ በጦርነት ተማሯል። በዝርፊያ ተማሯል፡፡ ሞት መፈናቀልና ስደት ሰልችቶታል፡፡ የሀገርን ሰላምና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር በመሆኑ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ልዝብ አምባገነን ሆነው፣ የሀገሪቱን ሰላምና የህዝቡን ደህንነት ሊያስጠብቁ ይገባል፡፡ ገራም አምባገነን ሆነው የሀገሪቱንና የብዙሃኑን ህዝብ ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅዎ ማንም ሊከስዎትም፤ ሊወቅስዎትም አይችልም!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻወ: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 4122 times