Saturday, 07 May 2022 12:43

በ4 ዓመት ውስጥ 70 ሚ. ዜጎች ብሔራዊ መታወቂያ ይኖራቸዋል ተባለ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ዳሽን ባንክ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር ስምምነት ተፈራረመ
                                         
               ብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም፣ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት 70 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ መታወቂያ ባለቤት እንዲኖራቸው ለማድረግ  እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ዳሽን ባንክ ደንበኞቹ የዲጂታል አይዲ (ብሔራዊ መታወቂያ) እንዲያገኙ የሚያስችል የስራ ስምምነት ትናንት ከሰዓት በኋላ በዳሽን ባንክ ዋናው መስሪያ ቤት፣ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቱን የተፈራረሙት የዳሽን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ ናቸው፡፡ የዲጂታል አይዲ (ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግም የዳሽን ባንክ የIT ክንፍና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ምህንድስና ቡድን በጋራ እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በባንክ ዘርፍ ላይ ያለው ትልቁ ተግዳሮት የብሔራዊ መታወቂያ አለመኖር ነው” ያሉት የዳሽን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ፤ አብዛኛው የህዝብ ገንዘብ በባንካቸው እንደመኖሩና የገንዘቡ ጠባቂ እንደመሆናቸው የብሔራዊ መታዎቂያ  ፕሮግራሙ እንዲሳካና ደንበኞቻው የመታወቂያ ተጠቃሚ  እንዲሆኑ ከፋይናንስ ሴክተሩ ቀዳሚ በመሆን የስራ ስምምነቱን መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ በበኩላቸው፤ “እኛ እንደመሰረተ ልማት አቅራቢ ሆነን በደንበኛውና በባንኩ መካከል የመተማመኛ ሥርዓት (trust frame work) መፍጠር ዋነኛ ሥራችን ነው” ያሉ ሲሆን ይህ አገልግሎት ደግሞ ከባንኩ ይልቅ ደንበኛውን በእጅጉ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡
አቶ ዮዳሄአክለውም፤ ከተለያዩ ድርቶች ጋር ፕሮግራሙ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ለአብነትም ከጤና ኢንሹራንስ ከማይክሮ ፋይናንሶችና ከሌሎችም ጋር የሙከራ ፕሮጀክቶችን እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ለምሳሌ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በኦሮሚያ አካባቢዎች ለሚገኙና በሴፍትኔት ለታቀፉ ዜጎች እርዳታ ለመስጠትና  ትክክለኛውን ተረጂ ትክከል ካልሆነው ለመለየት የብሔራዊ መታወቂያ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጿል፡፡ አቶ ዮዳሂ አክለውም በቀጣዮቹ አራት ዓመታት 70 ሚ ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነውም ተብሏል፡፡
የዳሽን  ባንክ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር ያደረገው ስምምነት የባንክ ዘርፉን እድገት የገደበውን ችግር ከመቅረፍም በላይ የፕሮግራሙን ግቦች በማሳካት የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግና ሃብትን አቀናጅቶ ለመስራትም ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጨምረው ገልጸዋል፡፡


Read 13069 times