Print this page
Saturday, 07 May 2022 12:53

የቱሪዝም ዘርፉን ያሻሽላል የተባለ ረቂቅ ፖሊሲ ለፓርላማ ቀርቧል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

    ቱሪዝሙን ለማነቃቃት የግሉ ዘርፍ ያለው ሚና ላይ ውይይት ተካሄደ
                                    ናፍቆት ዮሴፍ



                በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በሀገራችን የሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ተቀዛቅዞ የከረመውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃትና  ወደ ቀድሞው ለመመለስ የግሉ ዘርፍ ያለውን ሚና ወሳኝነት የሚዳስስ ውይይት ተካሄደ፡፡ የቱሪዝም ዘርፉን ያሻሽላል የተባለ ረቂቅ ፖሊሲ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑም በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡
ውይይቱ ባለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም በሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ አዘጋጅነት በማዶ ሆቴል ለግማሽ ቀን  የተካሄደ ሲሆን በውይይቱ ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፤የቱሪዝምና ሆቴሎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታሁን ዓለሙ የኮሌጁ አመራሮችና ባድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን የዘርፉ ተግዳሮቶችና የወደፊት መልካም   አጋጣሚዎችን የሚያሳይ ጥናት በምሁራን ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማ የውይይቱን የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዳብራሩት፤በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለውን አንጻራዊ መረጋጋትና የኮቪድ 19 ወረርሽ መቀዘቀዝ እንደ መልካም ዕድል በመቁጠር፣ ቱሪዝሙን ወደ ነበረበት ብቻ ሳይሆን ከነበረበት በላይ የማሳደግ ግዴታ አለብን ያሉ ሲሆን፤ ይህን ለማድረግ ሀላፊነቱ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የግል ዘርፉም ጭምር ነው ብለዋል፡፡ ጉዳዩን ጉዳዬ ብሎ ይህን የውይይት መድረክ ያዘጋጀውን ሉናር ኢንተርናሽል ኮሌጅንም አድንቀዋል፡፡
ሚኒስቴር ዴኤታው አክለውም፤ በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ የሆኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማጎልበትና የፀጥታ ሁኔታውን ይበልጥ አስተማማኝ በማድረግ ፣የተጎዳውንና ችግር ውስጥ ያለውን የቱሪዝም  ዘርፍ በእጅጉ ለመነቃቃት  ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ስራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአገር ውስጥ  ቱሪዝሙ ራሱን የቻለ መመሪያ የሚያስፈልገው ሆኖ በመገኘቱ ስትራቴጂ መነደፉን ያስታወሱት አቶ ስለሺ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ረቂቅ ፖሊሲ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡንና ምክር ቤቱ እስኪያጸድቀው ድረስ እየተጠበቀ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በዕለቱ ጥናታዊ ፅሁፍ ካቀረቡት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መኮንን ገ/እግዚአብሔር እንደገለፁት፣ ሀገራችን የብዙ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ሀብት ባለቤት ብትሆንም ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም ካላት ሀብት ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑና ካለን የቱሪዝም ሀብቶች ጥቂቶቹ ብቻ ወደ ቱሪዝም ሀብትነት መለወጣቸውን አስታውሰው መስህብቦቹን ወደ ቱሪዝም ሀብትነት የመቀየሩ ተግባር ግንባር ቀደም ሆኖ ሲሰራ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሆቴሎች፣አስጎብኚዎች፣ መኪና አከራዮችና በዘርፉ ያሉ ተዋንያን ቱሪዝሙን ለማነቃቃት ዝግጅት መሆን እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡
 እ.ኤ.አ በ2017 ለቱሪዝም ወደ ኢትዮጵያ የተደረጉት 933 ሺህ ጉዞዎች፣ የነበሩ ሲሆን በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በጦርነቱ ምክንያት የቱሪስት  ጉዞው ቁጥር ወደ 271 ሺህ  ማሽቆልቆሉም ተጠቁሟል፡፡ በተለይ ጦርነቱ የተከሰተባቸው የአማራ፣የአፋርና ትግራይ አካባቢዎች በደረሰባቸው ጉዳት መተዳደሪያቸውን ቱሪዝም ያደረጉ በርካታ ዜጎችም ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ተገልጿል፡፡ ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ከተቋቋመበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን፣ በፋይናንስና ኢንቨስትመንት፣እንዲሁም በፕሮጀክት ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፎች ላይ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ሲሆን እንዲህ ዓይነት ውይይቶች የሚዚጋጀው ማህበራዊ ሀላፊነቶቹን ለመወጣት እንደሆነም የኮሌጁ ፕሬዝዳንት ታሪኩ አቶምሳ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ኮሌጁ በርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎችን  ጎን ለጎን የሚሰራ ሲሆን እንደነ ሜሪጆይ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ  የሚገኙ ህጻናትን በማስተማርና አረጋውያንን በቋሚነት በመመገብ፣ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ሲሆን የኮሌጁ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የፕሮጀክት ሀሳቦችን እንዲያቀርቡና እንዲወዳደሩ በማድረግም አሸናፊ የፕሮጀክት ሀሳቦች እውን እንዲሆኑ የፋይናንስና የመስሪያ ቦታ አቅርቦትን በማመቻቸት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ስራዎች በመስራትም ይታወቃል፡፡ ኮሌጁ በቱሪዝም ላይ ያዘጋጀውን ውይይት የመመሳለሱና በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚያተኩሩ የውይይት መድረኮችን  በየወሩ ለማዘጋጀት ማቀዱንና በቀጣይም በፋይናንስና ኢንቨስትመንት፣ በፕሮጀክት ማጅመንትና ችግር ባለባቸው ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመምከር መርሃ ግብር የማካሄድ  እቅድ እንዳለው የኮሌጁ አመራሮች ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡



Read 12941 times