Saturday, 07 May 2022 13:18

መንግስት በኦሮሚያ ክልል እየወሰደ ያለውን ወታደራዊ እርምጃ ኦፌኮ አወገዘ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በክልሉ የተፈፀመው የንፁሃን ግድያ በዓለምቀፍ ገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል

                 መንግስት በኦሮሚያ ክልል “ኦነግ ሸኔ” በሚል የሚጠራውን ታጣቂ  አማፂ ቡድን ለመደምሰስ በጀመረው  ወታደራዊ ዘመቻ በርካታ ንጹሃን  መገደላቸውን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ያመለከተው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፤ የተፈጸመው የጅምላ ግድያ በዓለም አቀፍ ገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቋል፡፡
መንግስት በክልሉ “ኦነግ ሸኔ”ን  ለማጥፋት  በሚል እያካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ፤ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ ከ278 በላይ ንፁሃን ሰዎች ተገድለዋል ብሏል -ፓርቲው  በመግለጫው፡፡
በቅርቡ የፌደራል መንግስቱና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፤ታጣቂውን አማጺ ቡደን ከክልሉ ለማጥፋት የመጨረሻውን   ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚያካሂዱ በጋራ መግለፃቸውን ኦፌኮ ጠቅሷል፡፡
በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎችና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች  “ዓሳውን ለመያዝ ባህሩን ማድረቅ” በሚል መርህ የሚመራው ወታደራዊ ዘመቻ እየተካሄደ ነው ያለው ፓርቲው፤ “በዚህም ንፁሃንን መግደል፣ቤታቸውን ማቃጠል፣ንብረታቸውን መዝረፍና ማውደም፣ ዜጎችን ለእስርና ለስቃይ መዳረግ አንዳንዴም ልጆቻቸው ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ወላጆችን መግደል …የተለመደ  እየሆነ መጥቷል”  ብሏል፡፡ በተለይም በአራቱ የወለጋ ዞኖች፣በምዕራብ ሸዋ፣በሰሜን ሸዋና ምስራቅ ሸዋ፣በምዕራብ አርሲ፣በምስራቅ ጉጂ በኦሮሚያ ልዩ የቦረና ዞኖች፣ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ዞን እንዲሁም በቤኒሻንጉል- ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞንና  አካባቢዎቹ  ወታደራዊ ዘመቻው መካሄዱን ፓርቲው አመልክቷል- በመግለጫው፡፡
 በቅርቡ  ደግሞ የመንግስት ሃይሎች  ከወታደራዊ ዘመቻው ጋር በተገናኘ የድሮንና ሄሊኮፕተር ጥቃቶችን ፈፅመዋል ሲል የወነጀለው ኦፌኮ፤ የጥቃት እርምጃው ለበርካታ ንጹሃን ሞት፣  ለመኖሪያ ቤቶችና ንብረት ውድመት፣  ከሞት ለተረፉት  መፈናቀል መዳረጉን ከጥቃቱ ሰለባዎች መረዳት ይቻላል” ብሏል፡፡
“ይህም የሸኔን ቡድን ጠራርጎ ለማጥፋት” በሚል ሰበብ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን የጥቃት መጠን ፍንትው አድርጎ ያሳያል  ብሏል -ፓርቲው በመግለጫው፡፡
ኦፌኮ፤በኦሮሚያ ክልል ለተፈፀመው የንጹሃን ዜጎች  ግድያ ከመንግስት በተጨማሪ “ፅንፈኛ ያለውን “የፋኖ ቡድን” ተጠያቂ አድርጓል፡፡
“ይህ ቡድን ለኦሮምያ ክልልም ሆነ ለአጎራባች ክልሎች የሰላም ስጋት እየሆነ ነው፡፡ ሆኖም ክልላዊ መንግስቱ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ፤  የፌደራሉ መንግስት ፈጣንና  ህጋዊ መፍትሄ እንዲሰጥ እንጠይቃለን” ብሏል በመግለጫው፡፡፡
ፓርቲው በመጨረሻ ባወጣው ባለ7 ነጥቦች የአቋም መግለጫ፤ የፌደራል መንግስቱ ከታጣቂ ቡድኖች ጋር የገባውን ጦርነት በማቆም፣ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የጠየቀ ሲሆን መንግስት በአፋጣኝ የተኩስ አቁም በማድረግ ወደ ድርድር እንዲገባ  ኦፌኮ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ በማሳረጊያው፤ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀሙ የንፁሃን ዜጎች ግድያን በዓለማቀፍ ገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቋል፡፡
የፌደራል መንግስት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር በጥምረት በጀመሩት ታጣቂውን አማፂ ቡድን የማፅዳት ወታደራዊ ዘመቻ ድል መመዝገቡ በመንግስት የተገለፀ ሲሆን ለንፁሃን ላይ ጥቃት መድረሱን በተመለከተ ግን እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም፡፡


Read 13435 times