Saturday, 07 May 2022 13:21

ፖለቲከኞች ከግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   ትኩረታቸውን በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ አድርገው የሚሰሩ 20 የሲቪል ማህበራት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ፖለቲከኞቹ ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ንግግሮች እንዲቆጠቡ የጠየቁ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ የዜጎችን  የሰብአዊ፣ መብት እንዲያከብር አሳስበዋል፡፡
ማህበራቱ በጋራ መግለጫው በሰሜን ያለው ጦርነት ከፍተኛ የሠብአዊ ውድመት ማድረሱን አሁንም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቀጥሉ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በጦርነት ቀጠናው በተደረጉ የተለያየ የሰብአዊ መብት ምርመራዎች የጦር ወንጀልን ጨምሮ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ስለመፈፀማቸው መረጋገጡን አመልክተዋል፡፡
ለዚህና በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተባባሰ ለመጣው ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በፖለቲከኞች የሚነገሩ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ የተሳሳቱ መረጃዎች  የጦርነት ፕሮፖጋንዳ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡
ከእነዚህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ባሻገር በመንግስት በኩል የመረጃ ማግኛ መንገዶች ኢንተርኔትን ጨምሮ መገደባቸው ዜጎች ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኙ ከመንፈጉም በላይ የተፈፀሙ ድርጊቶችና እውነታዎች በልካቸው እንዳይታወቁ አድርጓል ሲሉ የሲቪል ማህበራቱ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ መንግስት አሁንም የሚዲያ ነፃነትንና የጋዜጠኞችን መብት እያከበረ አለመሆኑን፣ ጋዜጠኞች በዘፈቀደ እየታሰሩና እየታፈኑ መሆኑን፤ የሚታሰሩ የጋዜጠኞች ያሉበት እንደማይታወቅና በሰዎች እንዳይጠየቁ ገደብ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል፡፡
እነዚህን ወቅታዊ የሃገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት በቀጣይ ይካሄዳል የተባለውን ሃገራዊ ምክክር ተስፋ ማድረጋቸውን የጠቆሙት የሲቪል ማህበራቱ፤ መንግስትም ግጭትና ጥቃቶችን ለማስቆም ቁርጠኛ እንዲሆን፣ የሚዲያ ነፃነትንና የጋዜጠኞችን መብት እንዲያስከብር አሳስበዋል፡፡


Read 13151 times