Saturday, 07 May 2022 13:26

ሪያል ማድሪድ 14 ወይስ ሊቨርፑል 7?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

    ለ67ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በሚካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ሪያል ማድሪድ ከሊቨርፑል ተገናኝተዋል፡፡  ሁለቱ ክለቦች በጋራ ለ19 ጊዜያት የአውሮፓ ሻምፒዮን በመሆን  ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግበዋል፡፡ የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ለ13 ጊዜያት እንዲሁም የእንግሊዙ ክለብ ሊቨርፑል ለ6 ጊዜያት ዋንጫውን ተቀዳጅተዋል፡፡  
በ2021 /2022 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ከ54 አገራት የተወከሉ 80 ክለቦች ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ ተሳትፈዋል። ከዋንጫው ጨዋታ በፊት በተደረጉት 124 ጨዋታዎች  379 ጎሎች ከመረብ ያረፉ ሲሆን 4,327,255 ተመልካቾች ስታድዬም በመግባት ጨዋታዎችን ተከታትለዋል፡፡ ከፍፃሜው በፊት ለ1016 ደቂቃዎች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች የተሰለፈው  የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ካሪም ቤንዜማ በ15 ጎሎች ኮከብ ግብ አግቢነቱን ይመራል፡፡ የባየር ሙኒኩ ሮበርት ሌዎንዶስኪ 876 ደቂቃዎች በመጫወት 13 ጎሎች፤ የአያክሱ ሴባስቲያን ሆለር 668 ደቂቃዎች በመጫወት 11 ጎሎች እንዲሁም የሊቨርፑሉ መሐመድ ሳላህ 918 ደቂቃዎች በመጫወት 8 ጎሎች አስመዝግበው ተከታታይ ደረጃ ይዘዋል፡፡
ነጮቹና ቀዮቹ ከ67ኛው ፍፃሜ በፊት
ሪያል ማድሪድ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ለ13 ጊዜያት ዋንጫውን በመቀዳጀት ከፍተኛውን ውጤት እንደያዘ ይታወቃል፡፡ ከፍፃሜው በፊት ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች 8 ድል አስመዝግቦ በ4 የተሸነፈው ክለቡ ለሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ያለው ጉጉት  አላቆመም፡፡  በሪያል ማድሪድ የዘንድሮ  ስኬት በተለይ ለመጠቀስ የሚበቃው ፈረንሳዊው አጥቂ ካሪም ቤንዜማ ነው፡፡  ክርስትያኖ ሮናልዶ በ2018 እኤአ ላይ ሳንቲያጎ በርናባኦን ከለቀቀ በኋላ ከባዱን ሃላፊነት ሲረከብ ብዙዎች እንደሚሳካለት አልጠበቁም፡፡ ካሪም ቤንዜማ የአውሮፓ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ በሚገኝበት ደረጃ በፍፃሜውም ላይ ለሪያል ማድሪድ ድል እንዲጠበቅ ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከፍተኛውን ስኬት ያስመዘገቡት ጣሊያናዊው ካርሎ አንቸሎቲ ይጠቀሳሉ፡፡  በ2014 እኤአ ላይ ‘La Décima’  የሚል ስያሜ ያገኘውን የሪያል ማድሪድ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 10ኛውን ድል ያሳኩት አሰልጣኙ  ባለፈው የውድድር ዘመን ወደ ክለቡ ለሁለተኛ ግዜ ከተመለሱም በኋላ ውጤታማ ሆነዋል፡፡ ካርሎ አንቸሎቲ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ለሶስት ጊዜ ካሸነፉ 3 አሰልጣኞች አንዱ ሲሆኑ በፍፃሜ ጨዋታ ላይ ለአምስት ጊዜ በመሰለፍ ብቸኛ ሰው ናቸው፡፡
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው የእንግሊዙ ክለብ ሊቨርፑል ከፍፃሜው ጨዋታ በፊት  ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች 10 አሸንፎ በ1 ጨዋታ አቻ ሲወጣ 1 ሽንፈት ብቻ ገጥሞታል፡፡ በፍፃሜው ጨዋታ ላይ የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች እንደሚሆን የተጠበቀው ግብፃዊው መሃመድ ሳላህ ነው፡፡  በ2017  እኤአ ላይ የጣሊያኑን ሮማን በመልቀቅ ሊቨርፑልን ከተቀላቀለ በኋላ የአንፊልዱ ክለብ ምልክት ለመሆን የበቃው ሞ ሳላህ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ያስቆጠራቸው ጎሎች 33 ደርሰዋል።  በሊቨርፑል ዋና አሰልጣኝነት ላለፉት ሰባት ዓመታት የሰሩት ጀርመናዊው የርገን ክሎፕ በእንግሊዝ እግር ኳስ ከፍተኛ ለውጥ በመፍጠራቸው ተደንቀዋል፡፡ በ2018 / 19 የውድድር ዘመን ላይ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በማንሳት ታሪክ የሰሩት አሰልጣኙ ሊቨርፑል ከ30 ዓመታት ቆይታ በኋላ የእንግሊዝ ሊግን እንዲያሸንፍ አድርገዋል፡፡
ሪያል ማድሪድና ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በ2022 እኤአ ላይ የሚገናኙት ለ3ኛ ጊዜ ነው፡፡ በ1981 እኤአ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ በዋንጫ ጨዋታ በፈረንሳዩ ፓርክ ደፕሪንስ ስታድዬም ተገናኝተው  ሊቨርፑል 1ለ0 በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በ2018 እኤአ ላይ ደግሞ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ውስጥ በሚገኘው ኤንኤስሲ ኦሎምፒያሲኪ ስታድዬም ሲገናኙ 3ለ1 በመርታት ዋንጫውን የወሰደው ሪያል ማድሪድ ነበር፡፡ ሪያል ማድሪድ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የተሳትፎ ታሪኩ ለ20ኛ  ጊዜ ለፍፃሜ መድረሱ ሲሆን 13 ዋንጫዎችን  (በ1956, 1957, 1958, 1959, 1960,  1966,  1998, 2000, 2002, 2014 ,2016, 2017, 2018) ላይ አሸንፏል፡፡ ሊቨርፑል ደግሞ 10ኛውን የፍፃሜ ፍልሚያ ለማግኘት ሲበቃ   6 የዋንጫ ድሎችን  (በ1977, 1978, 1981, 1984,  2005, 2019) ላይ አስመዝግቧል፡፡
ካለፉት 66 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎች የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ክለቦች 18ቱን በመውሰድ የመጀመርያውን ደረጃ ይወስዳሉ። የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች 14 ጊዜ፤ የጣሊያን  ሴሪኤ ክለቦች 12 ጊዜ፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ክለቦች 8 ጊዜ፤ የሆላንድ ኤርዲቪዜ ክለቦች 6 ጊዜ፤ የፖርቱጋል ሊጋ ክለቦች 4 ጊዜ እንዲሁም የፈረንሳይ፣ የሮማኒያ፣ የስኮትላንድና የዩጎዝላቪያ ክለቦች በነፍስ ወከፍ አንድ ጊዜ ዋንጫውን ማሸነፍ ችለዋል፡፡
 የፍፃሜው መድረክ ስታድ ዴ ፍራንስ
ሪያል ማድሪድ ከሊቨርፑል የሚፋለሙበትን የዋንጫ ጨዋታ በፈረንሳይ ሴንት-ዴኒስ የሚገኘው ስታድ ዴ ፍራንስ ያስተናግዳል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ለሁለት አገራት ስታድዬሞች የሰጠውን እድል በተለያዩ ምክንያቶች ከሰረዘ በኋላ ነው ስታድ ዴ ፍራንስ የተመረጠው፡፡ በመጀመሪያ የፍፃሜ መርሃ ግብሩን እንዲያዘጋጅ ተመርጦ የነበረው በጀርመን ሙኒክ የሚገኘው አሊያንዝ አሬና ቢሆንም በኮቪድ 19 ሳቢያ  በ2020 የነበረ ፍፃሜ መሰረዙ እድሉ  ወደ ሌላ ስታድዬም እንዲሸጋሸግ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚያም አህጉራዊው የእግር ኳስ ተቋም ባሳለፈው ሁለተኛ ውሳኔ የራሽያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በክሬስቶቭስካይ ስታድዬም ፍፃሜውን እንድታስተናግድ አቅዶ ነበር። በሩሲያ የዩክሬን ወረራ ምክንያት ግን ይህም ውሳኔ ተቀልብሶ ከሴንትፒተርስበርግ እድሉን በመንጠቅ የዋንጫ ጨዋታው ወደ ፓሪሱ ስታድ  ዴ ፍራንስ እንዲዛወር ተደርጓል፡፡
ከፓሪስ በስተሰሜን በምትገኘው ሴንት-ዴኒስ የከተመው  ስታድ ዴ ፍራንስ የፈረንሳይ ብሔራዊ ስታዲየም ዋና ሜዳ ሆኖ እንደሚያገለግል ይታወቃል፡፡ እስከ 80,698 ተመልካቾችን በሚይዝበት አቅሙም በአውሮፓ ከሚገኙ ግዙፍ ስታድዬሞች በሰባተኛ ደረጃ ይጠቀሳል።  ስታድዬሙ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር  ስር ለሚካሄዱ ወሳኝ ግጥሚያዎችም ተመራጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡  በ1998 እኤአ ላይ የ16ኛው የዓለም ዋንጫ  ፍፃሜን እንዲሁም በ2000 እና 2006 እኤአ ላይ ደግሞ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ፍልሚያዎች የተካሄዱበት ነው፡፡  በዩሮ 2016 ላይ ደግሞ ፈረንሳይ በፖርቱጋል 1ለ0 የተሸነፈችበትን የፍጻሜውን ጨዋታ ጨምሮ ሰባት ጨዋታዎች ተደርገውበታል። የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር 75ሺ የስታድዬም መግቢያ ትኬቶችን ለገበያ ያቀረበ ሲሆን ለዋንጫው ጨዋታ 1 ወር ሲቀረው ከ52ሺ በላይ ተሸጧል። የፍፃሜው ተፋላሚ ክለቦች እያንዳንዳቸው 20ሺ ትኬቶች ለደጋፊዎቻቸው ሲሰጣቸው፤ በዓለም ዙርያ ለሚገኙ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች የቀረበው የትኬት ኮታ 12ሺ  ነበር፡፡
አጠቃላይ ገቢ ሊቨርፑል 91.44 ሚሊዮን ዶላር፤ ሪያል ማድሪድ 89.32 ሚሊዮን ዶላር
ባለትላልቅ ጆሮዎቹ ዋንጫ የሚባለው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ 73.5 ሴ.ሜ ቁመት ርዝማኔና 7.5 ኪሎ ግራም ክብደት ያለው ሲሆን የሰራው ዩርግ ስታደልማን የተባለ ግለሰብ ስለዋንጫው በሰጠው አስተያየት “የጥበብ ድንቅ ስራ ላይሆን ይችላል ነገርግን በእግር ኳስ ውስጥ ያለ ሁሉም ሰው ሊጨብጠው የሚጓጓለት ነው።” ሲል ተናግሯል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከዋንጫው ሽልማት ጋር  ለአሸናፊው ቡድን 40 የወርቅ ሜዳሊያዎች እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ለሚያገኘው 40 የብር ሜዳሊያዎችን ይሸልማል፡፡ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በዓለም የክለብ እግር ኳስ ቁንጮ ሆኖ የሚታይ ውድድር ሲሆን የአህጉሪቱ ክለቦች በየደረጃው በሚኖራቸው ተሳትፎ በገቢ በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያስገኝላቸው ነው፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ምንም እንኳን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተፅእኖ ምክንያት ካለፉት የውድድር ዘመናት ጋር ሲነፃፀር በትንሹ ቢቀንስም ለ2022 የውድድር ዘመን ያዘጋጀው የገንዘብ ሽልማትና የድርሻ አከፋፈል ከ15 በላይ ክለቦች ከፍተኛ ገቢ አካብተዋል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ካዘጋጀው የሽልማት ገንዘብ ብቻ ዋንጫውን ለሚያሸንፈው ክለብ 22.69 ሚሊዮን ዶላር ሲበረከት በሁለተኛ ደረጃ የሚጨርሰው ደግሞ 17.59 ሚሊዮን ዶላር ይከፈለዋል፡፡ በሌላ በኩል የስታድዬም፤ የስፖንሰርሺፕ እና ሌሎች የንግድ ገቢዎችን በመጨመር በ67ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከፍተኛውን አጠቃላይ ገቢ ያስመዘገበው የእንግሊዙ ክለብ ሊቨርፑል በ91.44 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡  ሪያል ማድሪድ 89.32፤  ማንችስተር ሲቲ 67.51፤ ቪያሪያል 65.39፤ ባየር ሙኒክ 59.67፤ ቼልሲ 54.38፤ ቤነፊካ 49.09፤ አትሌቲኮ ማድሪድ 48.04 አያክስ 47.65 እንዲሁም ጁቬንትስ ከ44.48 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማድረግ እስከ10ኛ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡ ሊሌ፤ ማንችስተር ዩናይትድና ፓሪስ ሴንትዠርመን እያንዳንዳቸው 40.24 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያደርጋሉ፡፡


Read 13054 times