Print this page
Saturday, 07 May 2022 13:23

እውነት መንግስት አለ?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል
Rate this item
(1 Vote)


               ባለፈው ሳምንት በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ እባክዎ ልዝብ አምባገነን ይሁኑ!” በሚል ርእስ አጠር ያለች መጣጥፍ ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ ጽሑፌን ያነበቡ አንዳንድ አንባቢያን፣ “ምን ተዓምር ተፈጠረና ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‘ልዝብ አምባገነን ሁኑ’ የሚል ምክር ያቀረብከው? ደግሞስ ልዝብ አልከው፣ ደግ አሊያም ገራም፣ ‘አምባገነን’ ያው አምባገነን ነው፡፡ አምባገነን ሁን ተብሎ አይመከርም…” የሚሉ አስተያየቶችን ልከውልኛል፡፡ እናም በዚች ማስታወሻዬ ጠቅላይ ሚኒስትሩን “ልዝብ አምባገነን ይሁኑ” ያልኩበትን ምክንያት ግልጽ ለማድረግ “እውን ኢትዮጵያ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ጠንካራ መንግስት አላት?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ልዝብ አምባገነን መሆን የሚያስፈልግበትን ምክንያት ለማመላከት ጥረት አደርጋለሁ፡፡
“እውን ኢትዮጵያ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ጠንካራ መንግስት አላት?” የሚለውን ጥያቄ ስትሰሙ “ምን ዓይነት የጅል ጥያቄ ነው!?” የምትሉ አንባቢያን ልትኖሩ እንደምትችሉ እገምታለሁ፡፡ እንደኔ እንደኔ ሞኝነትስ ይህንን ጥያቄ በዚህ ወቅት አለመጠየቅ ነው! በእኔ በኩል ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ መስጠት አልፈለግሁም፡፡ ይልቁንም ወደ ጥያቄው መልስ በቀጥታ ከመሄዳችን በፊት ስለ መንግስት ቀዳሚ ተግባራትና አንድን መንግስት “አለ” ወይም “የለም” ለማለት ስለሚያስችሉ መስፈርቶች ለመንደርደሪያ የሚሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን አስቀድመን እንይ…
*   *   *
በአንድ ሀገር መንግስት “አለ” ወይም “የለም” ለማለት በቅድሚያ የመንግስት ቀዳሚ ተግባራት ምን ምን ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ማየት ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ በጉዳዩ ላይ በርካታ በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን፣ የፖለቲካ ሳይንስና የህግ ሊቃውንት የተለያዩ ሃሳቦችን ያቀርባሉ፡፡
ክሌር አንደርሰን የተባለ ጸሐፊ፤ “ማንኛውም መንግስት የህዝቡን ደህንነት መጠበቅ፣ መሰረተ ልማት መዘርጋት እና የህዝቡን ገጽታ በመገንባት ዙሪያ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይጠበቅበታል” ይላል። በዚህ ጸሐፊ እይታ አንድ መንግስት ህልውና ያለው ስለመሆኑ ዋነኛውና ቀላሉ ማረጋገጫ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከጥቃት መጠበቅ መሆኑን አጽንዖት ይሰጣል።
ቶማስ ሆብስ የተባለው ሊቅ ሌዋታን (Leviathan) በሚል ርእስ ባሰናዳው የፖለቲካ ፍልስፍና ጽሑፉ፤ “ያለ መንግስት - የማያቋርጥ ሰላም፣ ያለ መንግስት - ህግ እና ስርዓትን ማስጠበቅ፣ ያለ መንግስት - ዜጎችን ከእርስ በርስ እና ከውጭ ጠላቶች መጠበቅ” እንደማይቻል አብራርቷል። በዓለም ላይ በርካታ ደካማ መንግስታት እና መንግስት የማያስተዳድራቸው ክፍለ ግዛቶች የሚታዩት መንግስት እነዚህን ተግባራት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለማቅረብ ያልቻለ እንደሆነ ነው ይላል ሆብስ። አክሎም፤ “ጦርነትና ስርዓተ አልበኝነት በነገሰበት ወቅት ዜጐች ከተዋጊ የሽብር ቡድኖች ይልቅ ከመንፈስ ጭንቀት የሚያወጣቸውን ጨካኝ እና ጽንፈኛ መንግስትን ይመርጣሉ” ይላል። በቶማስ ሆብስ እይታ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ነው። እናም ከመንግስት አልባነት ጨቋኝና አምባገነን መንግስት ቢኖር ይሻላል ባይ ነው ሆብስ፡፡
የመንግስት ህልውና የሚረጋገጠው ዜጎችን ከጥቃት እና ከአስከፊ የህይወት ውጣ ውረዶች በመጠበቅ፣ የዜጎችን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር እና ማህበራዊ ደህንነትን በማስጠበቅ ተግባራት ላይ ነው። በዚህ ረገድ አንዳንድ የስነ መንግስት ተመራማሪዎች የመንግስትን መሰረታዊ ተግባራት በአምስት ይከፍሏቸዋል፡፡ እነዚህም ተግባራት፡- “አስተዳደራዊ አመራር መስጠት፣ ህግና ስርዓትን ማስከበር፣ ለህዝብ አገልግሎት መስጠት፣ ብሔራዊ ደህንነትን ማስጠበቅ፣ የኢኮኖሚ ደህንነትን ማረጋገጥና ማህበረሰባዊ ድጋፍ ማድረግ” ናቸው። አንዳንድ ጸሀፍት ደግሞ ቀዳሚ የሆኑ የመንግስትን ዋና ዋና ተግባራት ወደ 8 ከፍ ያደርጓቸዋል፡፡ ሌሎች ተመራማሪዎች እስከ 12 ያደርሷቸዋል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ዋና ዋና ተግባራት ስድስት ናቸው፡፡ እነዚህም ተግባራት በአሜሪካ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ ተገልጸዋል፡፡ እነሱም፡- “እውተኛ የሆነ ሀገራዊ አንድነት መፍጠር፣ የፍትህ ስርዓት ማቋቋም፣ ውስጣዊ ሀገራዊ መረጋጋትን ማረጋገጥ፣ የጋራ መከላከያ ማደራጀት፣ የዜጎችን የተሟላ ደህንነት ማረጋገጥ፣ የነፃነት በረከቶችን ማስጠበቅ” የሚሉ ናቸው።
የማንኛውም ሀገር መንግስት ህግ ማውጣት፣ ህግና ስርዓት ማስፈን፣ ህዝቡን ከውጭ ጠላት መከላከልና ደህንነቱን መጠበቅ ዋነኛ ኃላፊነቱ እንደሆነ በተለያዩ ሰነዶች ላይ ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። በአንዳንድ ሰነዶች ላይ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር “የህዝብን ጥቅም ማስጠበቅ፣ አገልግሎት መስጠት፣ ሕገ መንግሥና ሌሎች ሕጎችን ማስከበር እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን ማጎልበት” መሆኑ ይነበባል።
“…መንግስታት ሀገርንና ዜጎችን ከውጭ ጣልቃ ገብነት ይከላከላሉ፡፡ ለዜጎች ደህንነትና ደስታ ትኩረት ያደርጋሉ” የሚል ብያኔ የሚያቀርቡ ጸሐፍትም አሉ፡፡ ዋሊ ቤን የተባለ ጸሐፊ የማንኛውም መንግስት ቀዳሚ ኃላፊነቶች “የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማረጋገጥ ነው” ይላል፡፡
አንዳንድ የስነ መንግስት ተመራማሪዎች፤ ባደጉ ሀገሮች እና በታዳጊ ሀገሮች ሊኖር የሚገባው የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ልዩነት እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ “ባደጉትም ባላደጉትም ሀገራት የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ልዩነት የለውም፡፡ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የሁሉም መንግስታት ዋነኛ ኃላፊነት የህዝብን ሰላምና ደህንነት መጠበቅና ማስጠበቅ ነው” በማለት ይከራከራሉ፡፡
አልብረሽ ዱረር የተባለ ጀርመናዊ የስነ መንግስት ተመራማሪ “መንግስታት ለምን ተፈጠሩ?” የሚል ጥያቄ ያነሳና “መንግስታት የተፈጠሩበት ዋነኛው ምክንያት ህጎችን ለማውጣት ነው” በማለት ምላሽ ይሰጣል። በዱረር ትንተና መሰረት፤ መንግስታት የተፈጠሩት ህዝብን ከግጭት የመጠበቅን እና ህግና ስርዓት የማስፈንን አስፈላጊነት ተከትሎ ነው። በሰዎች መካከል ግጭቶች የሚከሰቱት ደግሞ በሀብት ምክንያት ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ግጭቶች መንስዔም ሀብት ነው ይላል ዱረር፡፡
የግጭቱ ምክንያት ምንም ይሁን ምን የመንግስታት ቀዳሚ ተግባር የዜጎችን የህይወትም ይሁን የንብረት ደህንነት መጠበቅ ነው ብሎ መውሰድ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ የሀገራት ሉዓላዊነት መሠረትም ይኸው የዜጎች የህይወትና የንብረት ደህንነት መጠበቅ ነው። የጥንት ቻይናውያን ነገስታት ግዛታቸውን በታላላቅ ግንቦች የሚያጥሩት የዜጎችን የህይወትና የንብረት ደህንነት፤ እንዲሁም የግዛታቸውን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ መሆኑን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዘመናችን መንግስታት ቀዳሚ ኃላፊነት በኢኮኖሚ እና በህዝብ አገልግሎት ላይ የሚያተኩር መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎች የሚስማሙት “የመንግስታት ሁሉ ኃላፊነት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ፤ ህግና ስርዓትን ማስከበር ነው” በሚለው ላይ መሆኑን አንጥሮ ማውጣት ይቻላል።
***
አንድን መንግስት “አለ” ወይም “የለም” ለማለት ስለሚያስችሉ መስፈርቶችና ሁኔታዎች ከላይ በዝርዝር የቀረቡት ማሳያዎች በቂ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ደግሞ በነዚህ መስፈርቶች መሰረት “እውን ኢትዮጵያ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ቀዳሚ ኃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ መንግስት አላት?” የሚለውን ጥያቄ እንፈትሽ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ባለፈው መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም አራት ዓመታትን አስቆጠሩ፡፡ በነዚህ አራት ዓመታት በሀገራችን በርካታ በጎም መጥፎም ሁኔታዎች ታይተዋል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለቁጥር የሚያታክቱ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ፤ በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል፤ እንዲሁም በአፋርና በትግራይ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል ደም አፋሳሽ ጦርነት ተካሂዷል፡፡ ጦርነቱ ለአንድ ዓመት ያህል የዘለቀ ሲሆን አሁንም መቋጫ አላገኘም፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ዜጎች ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ተሰደዋል። በርካታ ሀብትና ንብረት ወድሟል፡፡ ወርቃማ የስራ ጊዜ ባክኗል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት መንግስት ጦርነቱን ተዋግቶ በአሸናፊነት መቋጨት ባለመቻሉና ቀዳሚ ተግባሩ የሆነውን የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ባለመቻሉ፤ ህዝብ መጠነ ሰፊ ኪሳራ ደርሶበታል። አላስፈላጊ መስዋእትነትም ከፍሏል፡፡ በአሳዛኝ መልኩ ኪሳራውም መስዋእትነቱም አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
ዛሬ ፌዴራል መንግስቱ ከዘጠኙ ክልሎች አንዷን ክልል (ትግራይን) እያስተዳደረ አይደለም፡፡ በአማራ፣ በአፋርና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉ በርካታ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በፌዴራል መንግስት እየተዳደሩ አይደለም። በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች በቡድን የተደራጁ ሽፍታዎች ህዝብን እየዘረፉና ኬላ አቁመው እያስገበሩና ቀረጥ እየሰበሰቡ መሆኑም ይነገራል፡፡ ይህም ሁኔታ በፓርላማ አባላት ጭምር በአደባባይ በይፋ የተነገረ ሀቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ወቅት በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የሚገኝ ህዝብ ከስጋት ነፃ ሆኖ የሰላም አየር እየተነፈሰ አይደለም፡፡ እና ታዲያ… በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ቀዳሚ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ሀገሪቱን የሚያስተዳድር “መንግስት አለ” ለማለት ያስደፍራል?
ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ “የራዕይ መንገደኞች” በሚል ርእስ ለመከላከያና ፀጥታ ኃላፊዎች ስልጠና በሰጡበት ወቅት አንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎችን በስም በመጥቀስ “እናንተ ናችሁ የምታስተዳድሯቸው” በማለት ገልጸዋል፡፡ ይህስ “ቀዳሚ ኃላፊነቱን በቅጡ እየተወጣ ያለ መንግስት መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው” ብሎ መውሰድ ይቻላል?
ከላይ ለማየት እንደተሞከረው የአንድ ሀገር መንግስት ሊያከናውናቸው ከሚገቡ ቀዳሚ ተግባራት ውስጥ አንዱ የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበርና ዜጎችን ከውጭ ወራሪ ስጋት መከላከል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጎረቤታችን የሆነቺው ሱዳን፣ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በመግባት በአሰርት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደምትገኝ መንግስት ራሱ ያመነው ጉዳይ ነው። ጎረቤታችን ኤርትራም በጦርነት ያጣቻቸውን እንደ ባድመ ያሉ መንደሮችን ወስዳ ባንዲራዋን ሰቅላለች፡፡ ሌላው ቀርቶ በደቡብ ሱዳን የሚገኝ “ሞርሌ” የተሰኘ አነስተኛ ቁጥር ያለው ጎሳ ወደ ጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ እየተሻገረ ከብቶችን ይዘርፋል፣ ህፃናትን አፍኖ ይወስዳል፡፡ ይህስ ሁኔታ “መንግስት መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው” ብሎ መውሰድ ይቻላል?
በርግጥ ዶ/ር ዐቢይ በተለያዩ መድረኮች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴና የሚዲያ ንግግራቸውን ስናይ እስከ አሁን “አምባገነን ናቸው” የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ ሁኔታ በበኩሌ አላየሁም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ “መጥፎ መሪ” የሚባሉ ባይሆኑም፤ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በአግባቡ እስካላስጠበቁ ድረስ “ጠንካራ መሪ” ናቸው ብሎ ለመደምደምም ያስቸግራል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት እንዳልኩትና አሁንም የምደግመው ዶ/ር ዐቢይ “ጥሩ የፕሮጄክት መሪ” ናቸው፡፡ ይህንን በተለያዩ የፕሮጄክት አፈጻጸሞች አሳይተዋል፣ አረጋግጠዋል፡፡ ቀዳሚ ኃላፊነታቸው የሆነውን የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ግን ከቢሯቸው ወጥተው 15 ቀናት ገደማ ካደረጓት የውጊያ አመራር ውጪ (እሷም ፕሮጄክት ነበረች) የተሳካ ስራ እየሰሩ ነው ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል።
ለቃላት አጠቃቀሜ ይቅርታ ይደረግልኝና፤ እንደኔ እንደኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በሀገር ደህንነትና በፀጥታ ጉዳይ “ቸልተኛነት፣ ንዝህላልነትና መዘናጋት” ይስተዋልባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ህዝብ አላስፈላጊ ዋጋ እየከፈለ ነው፡፡
ጽሁፌን የምቋጨው ጥያቄዎችን በመደርደር ነው… ከላይ ካቀረብናቸው የንድፈ ሃሳብ ነጥቦች አኳያ፤ አንድ መሪ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ካላስጠበቀ “ሀገር እየመራ ነው፣ ህልውና አለው” ለማለት ይቻላል? አንድ መንግስት “አለ” የማያስብል ሁኔታ ካለ ደግሞ ይህንን ጉድለት ለማረም “ልዝብ አምባገነን” ሆኖ፤ ለወቅቱ የሚመጥን ቆፍጠን ያለ አመራር መስጠት አይጠበቅበትም? ከዚህ አኳያ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ እባክዎ ልዝብ አምባገነን ይሁኑ” የሚል ምክር ብንሰጣቸው ተገቢ አይሆንም?
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 3491 times