Monday, 09 May 2022 00:00

ሕግ የሌለበት “የነጻነት ዘመን” የለም፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

  • የሕግ ሥርዓትና የስጋ ምግብ፣ በተመሳሳይ ጊዜ እንደተጀመረ ይገልጻል - የኖኅ ትረካ።
  • የስጋ ምግብ እስከዛሬ አልተቋረጠም። ቸል ሳይባል፣ እንደፀና ቀጥሏል። በአቅም ችግር፣ የስጋ ምግብ ሲርቀን ይቆጨናል። ዓመት በዓላችን ነው።
  • ሕግና ሥርዓትን ቸል ለማለት ግን፣ አጋጣሚና ሰበብ እናበዛለን። አዎ፣ ሕግ ይከበር ይባላል። ግን፣ ዛሬ ቢዘምሩለት፣ በማግስቱ ይዘነጉታል።
  • የሕግና ስርዓት ጥቅም፣ እንደ ስጋ ምግብ፣ በቀላሉ ማጣጣም ስለማይቻል ይሆን እንዴ ችግሩ? ከትክክለኛ ሕግና ሥርዓት ውጭ መዳን አይቻል!
            

 “የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ፤ ደሙ በሰው እጅ ይፈሳል”
“በጌታ አምሳል፤ ጌታ ሰውን ሠርቶታልና”
…”ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ይብዛ፤ ይንሰራፋ።”
ይሄ፣ ለኖኅ እና ለቤተሰቦቹ የተነገረ፣ “የፈጣሪ መልዕክት” እንደሆነ ይተርካል (ዘፍጥረት ምዕ 9)።
“ብዙ፤ ተባዙ”… የሚለው የቡራኬ፣ የምርቃት፣ ወይም የምክር መልዕክት አዲስ አይደለም። ለአዳምና ለሄዋንም፣ ተመሳሳይ ቡራኬ ደርሷቸው እንደነበር፣ በምዕራፍ አንድ ተጠቅሷል። እንዲህ ይላል። (ዓረፍተነገሮቹን፣ “ማለትም” ከሚል ማያያዣ ቃል ጋር ብናነብባቸው የተሻለ ነው)።
“ጌታም፣ ሰውን፣ በራሱ መልክ ፈጠረው።”
“በጌታ አምሳል ፈጠረው።”
“ወንድና ሴት አድረጎ ፈጠራቸው።”
…”ብዙ ተባዙ። ምድርን ሙሏት፤ ግዛቷም። የባሕር ዓሦችን፣ የሰማይ ወፎችን፣ እንዲሁም ምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ሕያው ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው ብሎ ባረካቸው።”
ከዚህ ቡራኬ በኋላ፣ የአመጋገብ ምክር ተሰጥቷቸዋል - ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች፣ ለአዳምና ለሄዋን።
“በምድር ላይ ያሉ፣ የእህል ተክሎችንና ፍሬ የሚሰጡ ዛፎችን፣ ለምግብ እንዲሆኑላችሁ ሰጥቻችኋለሁ” የሚል ሃሳብ ያዘለ ነው፤ ምክሩ።
“ስጋ እንዲበሉ፤ ወተት እንዲጠጡ”፣ አልመከረም ወይም ፈቃድ አልሰጠም።
ግን ደግሞ፣ የስጋና የወተት ምግቦችን የሚከለክል ሕግ አላወጀባቸውም። በአጭሩ፣ የስጋ ምግብን፣ “ባይፈቅድም፣ አልከለከለም” ማለት ይቻላል። ባይመክርም፣ እንዳትሞክሩት አላለም።
በዚሁ አጋጣሚ፣ የእንስሳትን አመጋገብ የሚገልፅ፣ ተጨማሪ መልእክት አብሮ ተጽፏል። ለሌሎች የምድር እንስሳትና ለአእዋፍ፤ እፅዋት ሁሉ ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ፤… ይላል - ጽሑፉ።
አንበሳና በሬ፣ ቀበሮና ጥንቸል፣ አንድ ላይ ሳርና ቅጠል ሲበሉ ይውላሉ ማለት ነው? ወይስ…
እነ አጋዘን፣ እነ ጥንቸል ቅጠላ ቅጠል ይበላሉ። እነ አንበሳና ነብር፤ በተራቸው አጋዘንን ይጥላሉ። ቀበሮና ተኩላ፣ ጥንቸልን ያሳድዳሉ። “የምግብ ሰንሰለታቸው”፣ ዞሮ ዞሮ፣ ከሳር ከቅጠል የሚጀምር ነው፤ food chain እንዲሉ። አንዱ የሌላኛው ሲሳይ ይሆናል።
አንዱ እንሰሳ፣ ቅጠል ሲቀነጥስ፣ ሳር ሲግጥ ይውላል። ሌላኛው ደግሞ፣ የደም ስር ሲበጥስ፣ አጥንት ሲግጥ ያድራል። በዚህም ተባለ በዚያ፣ የሰንሰለቱ ሁሉ መነሻ፣ የምግብ ሁሉ ምንጭ፣ እፅዋት ናቸው። ይህን ለመግለፅ ካልሆነ፣ እንሰሳት ሁሉ፣ የሳር የቅጠል ተመጋቢዎች ነበሩ እንደ ማለት ይሆናል - የጽሑፉ መልዕክት። ትርጉሙ፣ ከምር እንደዚያ ሊሆን ይችላል?
በሰው አመጋገብ ዙሪያ ግን፣ መልዕክቱ ከምር ነው። ለምን ቢባል፣ በሌላ ቦታ፣ ሌላ የማነፃፀሪያ ምክር ተጨምሮበታልና። በሁለት ቦታ የተፃፉትን ሁለት የተለያዩ ምክሮችን መመልከት እንችላለን።
የመጀመሪያው፣ ከላይ የተጠቀሰው፣ ለአዳምና ለሄዋን የተሰጠ ምክር ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ በኖኅ ዘመን የመጣ የአመጋገብ ምክር ነው። የማሻሻያ ምክር ልንለው እንችላለን።
አዳምና ሄዋን፣ እህልና ጥራጥሬ፣ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ እንዲበሉ ነው የተመከሩት።
ስጋና ወተት አልተፈቀደም፤ አልተከለከለም።
በኖኅ ዘመንስ?
“ሕያው ተንቀሳቃሽ ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ” ይላል (ዘፈጥረት ምዕ 9)። “ለምለሙን እፅዋት እንደሰጠኋችሁ፣ አሁንም ደግሞ ሁሉንም ሰጠኋችሁ” በማለትም ያብራራል።
ታዲያ፤ “ሁሉም ተፈቅዷል? ማለት፤ “ሁሉንም ማግበስበስ? ማለት አይደለም። ለምግብ የማይመቹና ጤና የማይሰጡ ነገሮች ይኖራሉ። አማርጦ መመገብ የሰው ድርሻ ነው። የአመጋገብ ሥርዓቱንም እንዲያሳምር ጥሩ ምክር ተለግሶታል። የሰው አመጋገብ፣ እንደ አውሬ መሆን የለበትም።
ገና ከነሕይወቱ አያለ፤ ከነደሙ አትብሉ የሚል ምክር ተሰጥቶታል።
ታዲያ፤ የስጋ ምግብ ማግኘት፣ እንደ እህልና እንደ ፍራፍሬ ቀላል አይደለም። እንስሳ፣ እንደ ዛፍ ቆሞ፣ እንደ ፍራፍሬ ተንጠልጥሎ አይጠብቅም። እንስሳትን አሳድዶ መያዝ፣ ወጥመድ መስራት፣ ታግሎ መጣል... ቀላል ስራ አይደለም። ትንሽ ቴክኖሎጂም ያስፈልጋል፤ ስለታማ ድንጋይ እንደ ማዘጋጀት።
በራሱ ጊዜ ቆዳው የሚገፈፍ፣ ስጋውም ተከትፎ፣ ለጉርሻ ተመቻችቶ የሚቀርብ አይደለም - የስጋ ምግብ። ስራ አለው። በዚያ ላይ፣ የስጋ ምግብ፣ ለጤና ጠንቅ የሚሆኑ ብዙ ጣጣዎች አሉት፤ ከእህል ጋር ሲነፃፀር። እና ደግሞ፣ ቶሎ ይበላሻል። ያኔ ፍሪጅ አልነበረም።
በአጠቃላይ፣ የአደን እና የእርባታ፤ እንዲሁም እሳት የማንደድና ምግብ የማብሰል ችሎታዎች፤ በአንድ ጊዜ አይፈጠሩም፤ አይለመዱም። ለዚህ ሊሆን ይችላል፤ አዳምና ሔዋን፣ “ስጋ ብሉ” ተብለው ያልተመከሩት።
እስከዘላለሙ፣ ስጋ እንዳትነኩ ማለት አይደለም። እሳት ማንደድ፣ ምግብ ማብሰል እስኪችሉ ድረስ ብቻ ነው። ደግነቱ በኖኅ ዘመን፣ የስጋ ምግብ፣ በእሳት ጠብሶ የማዘጋጀት ዘዴ ተለምዷል። ለዚህም ይሆናል የስጋ ምግብ ያኔ የተፈቀደው።
ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን፤ እስከ ኖኅ ዘመን ድረስ፣ ለ1500 ዓመታ ገደማ፣ የስጋ ምግብ እንዳልተፈቀደ፣ የአመጋገብ ባህል እንዳልተለወጠ ይጠቁማል - ትረካው።
ለአዳምና ለሔዋን የተሰጣቸው ምክር፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ እህልና ጥራጥሬ እንዲመገቡ ነው። “ባይከለከልም፤ አልተፈቀደም ነበር”፤ ወይም ደግሞ፣ “ባይፈቀድም አልተከለከለም ነበር” ብሎ ማሰብ ይቻላል። ትክክለኛ አገላለፅ ይመስላል። ነገር ግን፣ ይህን ከግድያ ወንጀላ ጋር አነጻጸሩት።
እስከ ኖኅ ድረስ፣ ሕግ አልነበረም።
የመጀመሪያው አዋጅ፣ የመጀመሪያውና ብቸኛው የሕግ አንቀፅ የመጣው፣ በኖኅ ዘመን ነው። የውሃ ንረት ዓለምን ካጥለቀለቀ በኋላ መሆኑ ነው። ከያኔው ጥፋት፣ በህይወት የተረፉት ሰዎች፣ ኖኅና ቤተሰቦቹ ብቻ ናቸው።
እንግዲህ፣ ትረካው እንደሚገልጸው፣ በዓለም ውስጥ፣ ግፍና ጥፋት በዝቶ ነው፤ የውሃ ጥፋት የመጣው። ከጎርፍ በኋላ፣ ሕይወት እንደገና፣ ከዜሮ ሊጀመር ነው። ነገር ግን፣ የድሮውስ አለፈ። አብዛኛውም ሰው አለቀ። ግን አሁንስ?
የድሮው ትርምስ ተመልሶ እንዳይመጣ፣ የሆነ ዘዴ ያስፈልጋል። ሕግ የሚሉት ዘዴ መጣ። ታዲያ፣ ባለብዙ ገጽ ሕግ አይደለም። አንድ አንቀፅ ብቻ የያዘ ነው - ሕጉ።
“የሰውን ደም ያፈሰሰ፤ በሰው ደሙ ይፈሳል” ይላል ሕጉ።
የሰውን ህይወት ማጥፋት ክልክል ነው፤ “ወንጀል” ተብሎ ተፈረጀ ማለት ነው። ጥፋተኛው ሰው፣ የሞት ቅጣት ይፈፀምበታል።
የተከለከለ የጥፋት ተግባርን (የወንጀል ዓይነትን)፣ እንዲሁም ጥፋተኛው ተለይቶ የሚወሰንበት ፍርድን (የቅጣት ዓይነትን) መግለፅ፤ ዋና የሕግ ገፅታ ነው። ከዚህ ጋር የተጎዳኘ ሌላ ገፅታም አለ።
ሕግ፣ በተፈጥሮው፣ “ሁሉን አቀፍ” ባህሪ አለው።
ለእገሌ ወይም ለእገሊት ብቻ አይደለም፣ ሕግ የሚታወጀው።
ለዛሬ ወይም ለነገ ብቻ፤ ከረፋዱ አራት ሰዓት በኋላ፣ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በፊት የተፈፀመ ነጠላ ድርጊት ላይ ብቻ አያነጣጥርም - ሕግ።
“በዚህኛው ድንጋይ የተሰነዘረ ጥቃት፣ በዚያኛው ስለት የተሰራ ጥፋት”… ላይ ብቻ አይታጠርም - ሕግ።
የሕግ “ሁሉን አቀፍ” ባህሪይ በደንብ ለማየት፣ ከግል ትዕዛዝና ከወቅታዊ ምክር ጋር ማነጻጸር ይቻላል።
“እጃችሁን ታጥባችሁ ጥርሳችሁን ፋቁ፤ ነገ ትምህርት አለ፤ ቶሎ ተኙ”፤…
“እዚህ ሳጥን አጠገብ እንዳትደርሱ፤ ከውስጡ አንዳች ነገር እንዳትወስዱ። ይህን ወይን እንዳትቀምሱ፤ እንዳትነኩ”፤…
እንዲህ አይነት ምክሮችና ትዕዛዞች፣… ለሁሉም ልጅ፣ ለሁልጊዜ፣ ለሁሉም ቤት የሚሰሩ አይደሉም። የሆነ አሳዳጊ፣ በሆነ ጊዜ፣ ለሆኑ ልጆች የሰጣቸው ምክር፣ የነገራቸው ትዕዛዝ፣... በቦታ የተከለከለ፣ በጉዳይ የታጠረ፣ በጊዜ የተገደበ ነው። ለሌሎች መማሪያ ሊሆን ቢችልም፣ “ሁሉን አቀፍ” አይደለም።
“በዔደን ገነት መሃል ካለችው የእውቀት ዛፍ፣ ፍሬ አትብሉ”... የሚለውን ትእዛዝ አስታውሱ። ትዕዛዙ፣ ለአዳምና ለሔዋን ብቻ ነው። በአንድ ቦታ የታጠረ፣ በአንዲት ዛፍ ላይ ያነጣጠረ ነው - ትዕዛዙ። “ሁሉን አቀፍ” አይደለም። ሕግ፣ ከዚህ ይለያል። የትዕዛዝና የሕግ ሌላ ልዩነትም አለ፤ አንደኛው ወደ ተግሳፅ ያደላል፣ ሌላኛው ወደ ቅጣት።  
ልጆች፣ የወላጅ ትእዛዝ ካላከበሩ፤ “ከዚህ በኋላ፣ ራሳችሁን ቻሉ፤ በወላጆቻችሁ ገነት ውስጥ ዘላለም መኖር አትችሉም፤ የራሳችሁን ጎጆ ስሩ፤ የራሳችሁን ገነት ፍጠሩ” የሚል ውሳኔ ከነተግሳጹ ይመጣባቸዋል፣ ይመጣላቸዋል - ለእገሌና ለእገሊት። እየተባረሩም፣ እየተሞሸሩም ነውና።
ሕግ ግን ከዚህ ይለያል። አንዲት ዛፍ ላይ ያነጣጠረ፣ ሁለት ሰዎችን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም። ሕግ ሁሉን አቀፍ ባህሪይ አለውና።
“የሰውን ደም ያፈሰሰ”... የሚለውን አባባል ተመልከቱ። የሕጉ ግዛት ሰፊ ነው። ለአንድ ለሁለት ሰው ብቻ አይደለም።
የስነ ምግባርም ግዛት፣ ሰፊ ነው። ሁለገብ፣ ሁሉን አቀፍ ነው፤ እንደ ሕግ። ከሕግ ይበልጣልም እንጂ። እንዲያውም፣ ሕግ፤ የስነምግባር ተቀጥላ ነው ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት፣ የስነ ምግባር መርሆች፣ ከሕጎች ጋር ተመሳሳይ ባህሪይ ቢኖራቸው አይገርምም።
ነገር ግን ልዩነት አላቸው። ሕግ፣ ከሌሎች የስነ ምግባር መርሆች በተለየ ሁኔታ፤ ክልከላ ላይ ያተኮረ፣ ከግዴታ ጋር የሚመጣ፣ ሽልማትን ሳይሆን ቅጣትን መተማመኛ ያደረገ ነው።
“እውነትን ብትወድ፣ ጥበበኛ ብትሆን፣ ተግተህ ብትሰራ፤… ኑሮህ የተባረከ፣ ህይወትህ ያማረ ይሆናል” የሚለውን የስነ ምግባር መርህ እዩ።
ተገቢ ተግባር ላይ ያተኮረ ነው - “ግብረገብነት” እንዲሉ። ይህን ብታደርግ፣ ይህን ብታደርግ… ይላል።
በፈቃፈኝነት ላይ የተመሰረተ ነው። “ይህን ብትወድ፣ ብትሰራ፣ ብትሆን”... ይላል።
ሽልማት ነው መተማመኛው። “በረከት ታገኛለህ”… ይላል።
ሕግ ግን፣...
መደረግ የሌለበት ነገር ላይ በማተኮር፣ ክልክል ተግባርን ይገልጻል።
ውዴታ አይደለም። ግዴታ ነው።
እና ደግሞ፤ ከነቅጣቱ ነው።
ግዴታና ቅጣት የሌለው ሕግ የለም። “ሕግን ብታከብር፣ ወንጀልም ባትፈጽም፣ ሽልማት ታገኛለህ” በማለት ወንጀልን መከላከል አይቻልም። “አዎንታዊ ማበረታቻ”፣ በእውነተኛ ሕግ ውስጥ ቦታ የለውም። ቅጣት ነው መተማመኛው።
ደግነቱ፣ ቅጣቱ፣ በዘፈቀደ ሳይሆን ስርዓትን በተከተለ መንገድ፣ ልኩን የጠበቀ ትክክለኛ ቅጣት መሆን አለበት። የወንጀሉ አይነትና መጠን ታውቆ፣ ጥፋተኛውም በማስረጃ ተረጋግጦ፣… ዝርዝሩ ብዙ ነው። መብዛቱ አለምክንያት አይደለም። የህይወትና የሞት ጉዳይ ነው - የሕግና የስርዓት ጉዳይ።
ሕግና ስርዓት ሲዝረከረክ፣ ከግራም ከቀኝም ኑሮ ሲፍረከረክ፣ የመጠፋፋት አዙሪት ይጦዛል። ያልተለመዱ አስደንጋጭ የጥቃትና የክፋት ተግባራት፣ በላይ በላይ እየተደራረቡ ይመጣሉ። ባየነው አዲስ ክፋት፣ “ክው” ብለን የድንዛዜ አፍታ ሳናገኝ፣ ሌላ የጥላቻ ጥቃት፣ በአዲስ ክውታ ያስበረግገናል። ዛሬ የገጠሙን አዲስና አሰቃቂ የጥፋት አይነቶችን የምንላመዳቸው፣ በማግስቱ የባሰ ዘግናኝ ወሬ ስንሰማ ነው።
ብቻ፣ ነገሩ ሁሉ፣ እጥፍ በእጥፍ እየጦዘ፣ በጥላቻ ባህር ውስጥ መርመስመስ ይበረክታል። የመጠፋፋት ጎርፍ፣ ሌት ተቀን እየተመላለሰ የእርቂት ማዕበል ውስጥ ይጥለናል።
ከተመሳሳይ ጥፋት ለመዳን፣ በኖኅ ዘመን የመጣው አዲስ ዘዴ፣ ሕግ የሚሉት ዘዴ ነው። “በኦርጅናሉ” ቋንቋ እንዲህ ይላል። “አዳም” ማለት፣ ሰው ማለት መሆኑን አስታውሱ።
“ሦፈክ ደም ሀ-አዳም”
“በ-አዳም ደሙ ይሠፈክ”
የአዳምን ደም ያፈሰሰ፣ በአዳም ደሙ ይፈሳል። ይሄው ነው የመጀመሪያው ሕግ - እንደ ኖኅ ትረካ ከሆነ።
ችግሩ፤ በኖኅ ዘመን የተጀመረውን የስጋ ምግብ፣ እስከ ዛሬ ቸል ብለነው አናውቅም። የአቅም ጉዳይ እየሆነ እንጂ፣ ከአጠገባችን ባይርቅ እንወዳለን። እንዲያውም፣ የዓመት በዓል ማክበሪያችን ነው።
ሕግና ሥርዓትን ግን፣ በተገኘው አጋጣሚና ሰበብ፣ ቸል ለማለት ጊዜ አይፈጅብንም። ትክክለኛ ሕግንና የተስተካከለ ሥርዓትን ከማጽናት ውጭ፤ ከጥፋት ማዕበል መዳን እንደማይቻል እንዘነጋዋለን።
የሕግና ስርዓትን ጥቅም፣ እንደ ስጋ ምግብ በቀላሉ ማጣጣም ስለማይቻል ይሆናል - ችግሩ።

Read 10859 times