Saturday, 07 May 2022 13:31

“ሁለት ያለው፤ አንዱን፣ አንድ ለሌለው ይስጥ!”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ቄስ ምዕመናኑን ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ሲያስተምሩ፤
“ምዕመናን ሆይ!
ዓለም ሰፊ ነው። መልክ ረጋፊ ነው። ዛሬ ያለን ሀብት፣ ንብረት፣ ነገ ከእኛ ጋር የለም። እኛ ዛሬ አለን እንላለን እንጂ ነገ ከነገ ወዲያ ሁላችንም የለንም። ወደ ማይቀረው ቤታችን እንሄዳለን። ስለዚህ ያንን ቤታችንን ዛሬ እንስራው። ዛሬ እናመቻቸው፡፡ ስለሆነም ጠግበን ስንበላ፣ የተራቡትን እናስብ። ለመዝናናት ስንጠጣ የተጠሙትን እናስታውስ። ከልኩ በላይ ስንለብስና ስናጌጥ የተራቆቱትን፣ እርቃናቸውን በብርድ የሚፈደፈዱትን፣ የተራቆቱትን “እንደምን አድረው ይሆን?” እንበል። “ታምሜ ጠይቃችሁኛልን? ታርዤ አልብሳችሁኛልን? ተቸግሬ ደጉማችሁኛልን?; እያለ ይጠይቃችኋል። ስለዚህ ስጡ። ዛሬ የሰጣችሁትን ነገ በሰማይ ቤታችሁ ታገኙታላችሁ። የዚህ ዓለም ሀብት ንብረት አላፊ ጠፊ ነው። ኗሪው ደግ ስራ ነው።
“ባለፀጋ ነን”፤ “ብልፅግና አለን”፤ “ባለ ጊዜ ነን” ብላችሁ አትታበዩ። አትደገጉ። “ከእኔ በላይ ማን አለና?” እያላችሁ፣ ሰው ጤፉ አትሁኑ። ዓለም አላፊ፣ መልክ ረጋፊ  ነውና አሁን በእጃችሁ ያለ አዱኛ፣ በእጃችሁ ያለ ፀጋ፣ በእጃችሁ ያላችሁ የጦር ሀይል፣ የእኛ ነው ያላችሁት ቤት ንብረት ሁሉ፣ ነገ የእናንተ አይደለም፡፡ በእጃችሁም የሚቆይ አይደለም። ስለዚህ ምን ያህል አጋሰስ ጫንኩ? ምን ያህል ፈረስ ለጎምኩ? ምን ያህል እህል በጎተራ ሞላሁ? እያላችሁ አትጨነቁ። ይልቁንም በስነ-ምግባር የታነፁ ልጆችን አሳድጉ። በግብረ ገብነት መንፈሱን የሞላ ብልህና አስተዋይ ትውልድ ፍጠሩ! የሰማይ ቤታችሁን ማነፅ ዛሬ ጀምሩ!
በመጨረሻም የዛሬ ትምህርቴን የማሳርገው በአንዲት አጭርና ጠንካራ መልዕክት ነው። እነሆ፡-
“ስጡ፣ ታገኛላችሁ!
አንኳኩ፤ይከፈትላችኋል!
ሁለት ያለው፣አንዱን፣ አንድ ለሌለው ይስጥ!”
አሉና ቄሱ አቡነ-ዘበሰማያት ብለው አበቁ። በቤተ-ክርስቲያን አካባቢ የተገኘውን የበዓል ቡራኬም፣ ሰምበቴም፣ ከምዕመናኑ ጋር ተቋድሰው ከደጀ- ሰላሙ ወደ ቤታቸው ሄዱ።
የቅስና ልብሳቸውን ቀይረው ወደ ግብዣ መሄድ ነበረባቸውና ወደ ቁም ሰንዱቃቸው ሲሄዱ፣ የልብሶቻቸው ቁጥር በግማሽ ቀንሶ ያገኙታል፡፡ በድንጋጤ ባለቤታቸውን ጠርተው፤
“አንቺ ልብሴን ሁሉ ምን በላው?” ሲሉ ጠየቋት፡፡
ሚስታቸውም፤ “ለተቸገረ ሰጠሁት” አለቻቸው።
“እንዴት? ለምን? ለኔ ሳትነግሪኝ?” አሉ በንዴት።
ሚስቲቱም፤
“ቅድም በተስኪያን ነገሩን እኮ! “ሁለት ያለው፣ አንዱን፣ አንድ ለሌለው ይስጥ” አላሉም?”
ቄሱ በብስጭት፤ “ታድያ #ይስጥ; አልኩ እንጂ #ልስጥ” አልኩ? ወጣኝ?!” አሉ፤ይባላል።
***
መንግስታዊ መመሪያዎቻችን፣ የምንደነግጋቸውም ህጎች ሁሉ፣ በእኛም ላይ መስራት እንዳለባቸው አንርሳ! በእኛ ባይደርሱ በልጆቻችን ላይ ተፈጻሚ ናቸው። “ህግን የሚሰራት ሰው፤ የሚያፈርሳት እራሱ ነው” ይላሉ እንግሊዞች - #a law-maker is a law breaker; እንዲል መጽሐፉ። ስንፅፈውና ስንደነግገው ቀላል፤ እንተግብርህ ስንለው ግን እጅግ አዳጋች፤ አያሌ ጉዳይ አለ። በቴሌቪዥን መስኮት  ከረቫት አስረን፤ ሽክ ብለን የተናገርነውን ሁሉ መሬት ለማውረድ ብዙ ጣጣ አለበት! ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆሞ ለማውረድ ይቸግራልና! ለዛውም ለመስቀልም ሳንቸኩል፣ ለማውረድም ሳንቸኩል ከሆነ ነው! ለማንኛውም፣ “ወዳጄ ልቤ ሆይ! የእኔ መከራ ያንተ መከራ አይደለምን?” የማለት ወኔው ቢኖረን መልካም ነው!
ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን በአፄ ቴዎድሮስ አንደበት፤
“ያለፈ ጥረታችንን፣ ሳስታውሰው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ፣ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ”
ይላል። ያልሞከርነውን እናስብ። ገና ብዙ ይቀረናል። ስለ ዴሞክራሲ ለፈፍን እንጂ ስራ አልሰራንም። ስለ ፍትህ አወራን እንጂ ገና ፍርድ ቤቱን አላፀዳንም፤ አላስተካከልንም። ዳኞች መደብን እንጂ ዳኝነታቸውን አላየንም፡፡ አሁንም ከእነ ሸረሪት ድሩ አለ። ስለዚህ ገና ነን! “በጊዜያዊ ድል አንኩራራ!” ይላል መፅሐፈ ድል ዘሱማሌ ወኤርትራ። የንብረት ክፍፍል፣ የሀብት እኩልነት አለመቀራረብ፣ በተለይ ከፓርክ መስፋፋት አንፃር እንየው ስንል፣ ዛሬም አባይን በጭልፋ ነው! የኑሮ ውድነትን ስናስብም “ኑሮ ውድነት ድሮ ቀረ!” እያልን እንድንናፍቅ ገፍቶናል። አንድ ገጣሚ እንዳለው፤ “ዱሮ፣ ዱሮ ቀረ!”
በአንድ ወቅት በሃይለ ስላሴ ዘመን አንድ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር፤ “የእኛ ችግር - ችግር ምን እንደሆነ አለማወቃችን ነው” ብለው ነበር። በቀድሞው ጊዜ የነበረ አንድ የጋምቤላ ተወካይ ደግሞ፤ “ችግር አለ፤ ግን ችግሩን ለመናገርም ችግር አለ” ብሏል። ለአገራችን፤ ችግር፤ “የአስራ ሶስት ወር ፀጋ” ነው! እንደ ዝናብና ፀሀይ ያልተለየን በረከተ- ሰማይ- ወምድር!
አንድ ስለ ኤችአይቪ የተዘፈነ መዝሙራችን፣ ብዙዎች “ማለባበስ ይቅር” በሚለው የሚያውቁት፣ “የማንፈልገውን፣ በራሳችን፣ ደርሶ
 ሌላው ላይ እንዲደርስ፤ አናርገው ጨርሶ” ይላል።
እኛ በጎረቤቶቻችን ላይ፣ ጎረቤቶቻችንም በእኛ ላይ እንዳይደረግ የምንሻው፤ ተንኮል፣ ሴራ፣ ዲፕሎማሲያዊ አሻጥር በርካታ ነው። ከስዊስ ካናል መከፈት እስከ ዐባይ ድልድይ መገንባት፤ ዘመናት አልፈዋል። ተጠቃሾቹ ሁለቱ ይሁኑ እንጂ መንግስታት ተለዋውጠዋል። አስተሳሰብ ፈርሶ ተገንብቷል። ወድቆም ተነስቷል። አንዳንድ አገሮች ልክ እንደኛ አገር- እንደ አፈ ታሪኳ ፊኒክስ ናቸው። አፈር ልሰው ሞተው ይነሳሉ! ትንሳኤ አላቸው! ዳግማይ ትንሳኤን ያለነገር አልወደድነውም! ወደፊት የሚራመድ ለአገር አሳቢ ሰው፤ መሪ መፈክሩ - ትንሣኤ - ዳግማይ ትንሣኤ ይሁን ብለናል። ጥናቱን ይስጠን! ጥናቱንም፤ ፅናቱንም ቢሆን፡-
“ሁለት ያለው፤
አንዱን፤
አንድ ለሌለው ይስጥ!!” አሜን።
መንግስት “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” የሚለውን ተረት ልብ ይበል። የእግር መንገዶች ወይ ወደ አውራው ጎዳና፤ ወይ ወደ ጫካ ማምራታቸው አይቀሬ ነውና! ቀላል የሚመስሉ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ውስብስብ የአገር ጉዳይ ሊያመሩ እንደሚችሉ ታሪክ አሳይቶናል። በቤንዚን መወደድ የአውቶቡሶች ስራ ማቆም፤ የሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ፤ የሙስሊሞች ሰላማዊ ሰልፍ፤ የክፍለ ጦሮች ጥያቄ ማንሳት ለ1966ቱ አብዮት ያደረጉትን ያየ፣ ልምድ ሊወስድ ይገባዋል። “የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” ይላል አበሻ። ታዋቂው ደራሲ ሔሚንግ ዌይም፤ “coming events cast their shadows” ይለናል። “ለከርሞ የሚቆስል እግር፤ ዛሬ ማሳከክ ይጀምራል” ይላሉ የተረት ጠበብት። ቸር ወሬ ያሰማን!     


Read 13857 times