Print this page
Sunday, 08 May 2022 00:00

በሞተር ስፖርት ፍቅር የወደቀው ታዳጊ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

       ጆሹዋ ቡጌምቤ የ12 ዓመት ታዳጊ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያዊቷ እናቱ ዴሊና ቡጌምቤና ከኡጋንዳዊው አባቱ ማይክ ቡጌምቤ፣ በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ነው የተወለደው። ታዳጊው በለንደን በነጭ ቱጃሮች ብቻ በሚዘወተረው የሞተር ስፖርት ፍቅር የወደቀው ገና የ8 ዓመት ህጻን ሳለ ነው፡፡ የ12 ዓመቱ ጆሹዋ በአሁኑ ወቅት በለንደን ታዋቂ መጽሄቶች፣ ጋዜጦችና ቴሌቪዥኖች ስሙ እየናኘ የመጣ  የሞተር ስፖርት ተወዳዳሪ ለመሆን በቅቷል፡፡ በበርካታ ውድድሮችም በተደጋጋሚ በማሸነፍ በርካታ ዋንጫዎችን ተሸልሟል፡፡ "Driver of the Year" የሚል ሽልማትም አግኝቷል፡፡
 ጆሹዋ ለፋሲካ በዓል ከሁለት ታናናሽ ወንድሞቹና ከእናት አባቱ ጋር አዲስ አበባ መጥቶ የነበረ ሲሆን ወደ እንጦጦ አቅንቶ ከሞተር ስፖርት አሰልጣኙ ጋር በመወዳደር አሰልጣኙን አሸንፎ ብዙዎችን አጃኢብ አሰኝቷል። ጆሹዋ እንዴት በነጭ ቱጃሮች ብቻ በሚዘወተረው የሞተር ስፖርት ፍቅር ወደቀ? በእሱ እድሜ በዚህ ስፖርት ውስጥ ከሚወዳደሩት ብቸኛ ጥቁር በመሆኑ የሚገጥመው ተግዳሮት ይኖር ይሆን? ወላጆቹ ለውድድር የሚከፈለውን ከፍተኛ ወጪ እንዴት ተቋቋሙት? ታዳጊው ወደፊት ምን ይመኛል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከጆሹዋ እናት ወ/ሮ ዴሊና ቡጌምቤ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች። -


            ዴሊና ቡጌምቤ ነው የምትባይው፤ በባልሽ ስም፡፡ የአባትሽ ስም ማነው? ለኛ አገር እንግዳ ነገር ነው አይደል…?
ልክ ነሽ። ባሌ ኡጋንዳዊ ስለሆነ በሱ ስም ነው የምጠራው። የአባቴ ስም አበቅየለህ ይባላል።
ትውልድሽና ዕድገትሽ የት ነው?
ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ ጉለሌ ነው። የሴይንት ሜሪ ተማሪም ነበርኩኝ። ከ13 ዓመት ዕድሜዬ ጀምሮ ደግሞ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ኖሬያለሁ።
እንዴት ወደ ለንደን ሄድሽ? ከኡጋንዳዊው ባለለቤትሽ ጋርስ በምን አጋጣሚ ተገናኛችሁ?
ባለቤቴ ማይክ ቡጌምቤ ይባላል። ኡጋንዳዊ ቢሆንም ህጻን ሆኖ ገና አንድ ዓመት ሳይሞላው ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያደገው። ታናናሽ እህቶቹና ወንድሞቹ እዚሁ አዲስ አበባ ዘውዲቱ ሆስፒታል ነው የተወለዱት። እንዲያውም የእህትና ወንድሞቹ የልደት ካርድ ሁሉ በአማርኛ ነው የተጻፈው። እናትና አባቱ እዚህ አገር ለረጅም ጊዜ ኖረዋል። የዲፕሎማት ልጆች ናቸው። የባለቤቴ አባት በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ውስጥ ለ33 ዓመታት ሰርተዋል። እናም ብዙ ዓመት በኢትዮጵያ ኖረዋል። እንዴት ተገናኛችሁ ላልሽኝ፣ የተገናኘነው ለንደን ነው። ለንደን የሄድኩት እህቶቼ ጋ ነው። እዛ እህቶቼ ነበሩ። እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም ነው የሄድኩት፤ የዛሬ 19 ዓመት መሆኑ ነው። በ2007 ዓ.ም ነው ባለቤቴን ያገኘሁት። 17 ዓመት ሆኖናል ከተገናኘን። ከተጋባን ደግሞ 13 ዓመታችን ነው። የተገናኘንበት አጋጣሚ ምን መሰለሽ? አሜሪካዊት ጓደኛ ነበረችኝ፤ እናም ወደ ሀገሯ መመለሻዋ ጊዜ ደርሶ ስለነበር “ወጥተን እንዝናና” ስትለኝ መውጣት አልፈለግሁም ነበር፡፡ በግድ ነው ይዛኝ የወጣችው ማለት ይቻላል። ተያይዘን መዝናኛ ቦታ ሄድን። ከዚያ በኋላ ጓደኛዬ ስታልፍ እሱ ሳያውቅ በሀይል ገፋት። በጣም ትሁት ሰው ነውና “ይቅርታ ረገጥኩሽ”  ይላታል። በጣም ደነገጠ፡፡ “መጠጥ ልጋብዛችሁ” ሲላት “እንደዛ ከሆነ ጓደኞቼን ሁሉ ነው የምትጋብዘው” አለችው፤ ልክ ብዙ ሰው እንዳለ አድርጋ። “እሺ የታላችሁ?” ብሎ ሲመጣ፣ እኔ ብቻ ነኝ። “ከየት ነው የመጣሽው?” ሲለኝ “ከኢትዮጵያ” አልኩት። “እንዴት ነሽ?” አለኝ።
በአማርኛ ነው---?
አዎ! ከዚያ በቃ ሰው ሊጠብሱ ሲሉ፣ እንደዚህ ነው የሚሉት ብዬ ኮራሁበት (ሳቅ…) “እኔ ኢትዮጵያ ነው ያደግኩት፤ ቤቴ እዚህ ቦታ ነበረ" እያለ አስረዳኝ። “ደብረዘይት መንገድ በዚህ በኩል ታጥፈሽ” እያለ ሲነግረኝ፣ "አይ ይሄ ልጅ እውነትም ኢትዮጵያ ነው ያደገው" አልኩና በቃ ማውራት ጀመርን። እንግሊዝ አገር “ምኒልክ” የሚባል ሬስቶራንት ነበረ። ባልሳሳት እዛ አገር የተከፈተ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ይመስለኛል። ባለቤቴና እህት ወንድሞቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ ኢትዮጵያ አዳሪ ት/ቤት ነው የተማሩትና፣ እናትና አባታቸው ሊጠይቋቸው ሲመጡ እንጀራ ይበሉ ስለነበር፣ “ቆንጆ እንጀራ ያለው ምኒልክ ሬስቶራንት ነው” አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ “እኔን ሀበሻዋን ስለ እንጀራ ልትነግረኝ ትፈልጋለህ” ስለው “ግዴለም አንቺም ጥሩ የምትይበት ትወስጂኛለሽ፣ እኔም ጥሩ ያልኩትን አሳይሻለሁ” ተባብለን በዚህ መልኩ ተግባባን። ስታወሪው የሚቀልሽ ሰው የለም? እኔም ቀለልኩት፤ እሱም ትሁትና ቀለል ያለ ነው፤ በዚህ ሁኔታ ተግባብተን  ነው ለዚህ የደረስነው።
እስኪ ስለ ለንደን ኑሯችሁ ትንሽ አጫውቺኝ? ባለቤትሽ ምንድን ነው የሚሰራው? አንቺስ? ይህን የጠየቅሁበት ምክንያት በየሳምንቱ ለጎካርት ውድድር ብዙ ብር ስለምታወጡበት የመጀመሪያ ልጃችሁ ጆሹዋ ጉዳይ ላነሳ በመሆኑ ነው…?
ትክክል ነው። የክፍያው ጉዳይ ከባድ ነው። ባለቤቴ ማይክ ቡጌምቢ የቴክኖሎጂ ሰው ነው።  ዳታ ሳይንስ ውስጥ ነው የሚሰራው። ለብዙ ዓመታት “Just Giving” የተሰኘ ኩባንያ ውስጥ ነበር የሚሰራው። ሰውን ለመርዳት ገንዘብ የሚያሰባስብ ድርጅት ነው፡፡ “Go Fund Me” ከመምጣቱ በፊት የነበረ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ ነው- “Just Giving” እና ባለቤቴ በዚህ ኩባንያ ውስጥ ነበር የሚሰራው። ከ3 ዓመት ወዲህ ግን የራሱን ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ መጽሐፍም ጽፏል። የሚያነብ የሚመራመርና የእውቀት ሰው ነው። አሁን ላይ ባለቤቴ ብቻ ነው  የሚሰራው። እኔ ከጆሹዋ እድሜ ጀምሮ ላለፉት 12 ዓመታት ልጆቼን የማሳደግ ስራ ላይ ነው ያለሁት።
ጆሹዋ እንዴት ወደዚህ የሞተር ስፖርት ተቀላቀለ? ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው ይህ ስፖርት የነጮች ያውም የቱጃሮች ስፖርት ነው የሚባልበትና ብዙ ብር የሚያስከፍል ነውና እንዴት ቻላችሁት? አደጋውንስ አልፈራችሁም ?
እንዳልሽው የሞተር ስፖርት ይፈጥናል፤ በፍጥነቱ ምክንያት መጋጨት ለአደጋ መጋለጥ ሁሉ አለው። በዚህ ሁሉ የእናት ልብ ጭንቅ ውስጥ ይገባል፤ የታወቀ ነው። ጆሹዋ አሁን ባለበት ደረጃ የሚነዳው “ካርት” የሚባሉ ሜካኒካሊ በቀላሉ የሚሰሩ መኪኖችን ነው፡፡ በሰዓት ወደ 100 ኪ.ሜትር ይሄዳሉ። በጣም ፈጣኖች ናቸው። እነዚህን ነድተሽ ነድተሽ ውድድርሽን አሳድገሽ መጨረሻ ላይ ስትደርሺ ወደ “Formula 1” ትገቢያለሽ ማለት ነው። ፎርሙላ ዋን እንዳልሽው የ72 ዓመት ታሪክ ያለው ስፖርት ነው። በ72 ዓመት ውስጥ አንድ  ክልስ ብቻ ደፍሮ ሲገባ፣ ሌሎቹ በሙሉ ነጮች ብቻ ነበሩ፡፡ ነጮቹም 99.9 በመቶዎቹ ቱጃሮች ናቸው። በዚህ ስፖርት ጥቁር እንዳይቀላቀል በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በብዙ መንገድ በር ይዘጋሉ። በጣም ብዙ ነገር የምንታዘብበት ስፖርት ነው።
ጆሹዋ ይህን ስፖርት የተቀላቀለው ከ8 ዓመት እድሜው ጀምሮ ነው። አንድ ቀን ከጓደኛዬ ጋር ልጆቻችንን ልናጫውት ይዘናቸው ሄድን። ያው እዚህም እንጦጦ አለ፡፡ ስፖርቱ ለ30 ደቂቃና እንደዚህ ከፍለሽ ልጆቹ ካርቶቹን ይነዳሉ። እኛም እዛ ለንደን በዚህ መልኩ ልናጫውታቸው ነው የወሰድናቸው። እንደ ትራንፖሊን ያሉ መጫዎቻዎች ያሉበትም ነው፤ አብረውን እንዲዝናኑ ነው የወሰድናቸው። ከጓደኛዬ ልጆች ጋር ነበሩ። እና እዛ ስናይ ካርቶቹን ይገጣጥማሉ፣ ያስተካክላሉ ባለሙያዎቹ። ትልልቅ ሰዎች ናቸው። ብቻ ይገጣጥማሉ፤ ያስተካክላሉ፤ ስቲከር ይለጥፋሉ። ምንድን ነው? ስላቸው፤ "አዲስ አይነት አካዳሚ ጀምረን ነው - ለአምስት ሳምንት። አንድ አንድ ሰዓት እሁድ እሁድ እናካሂዳለን” አሉኝ። ጆሹዋ ያቺን 30 ደቂቃ ሲነዳ ደስ ስላለው፣ ታናሹን ኬለብንም አብሬ አስገባኋቸው። ኬለብ የማንበብ የኮምፒዩተር ኮዲንግ፣ ዲዛይን ምናምን ነው ፍላጎቱ።
የአባቱ አይነት ዝንባሌ ነው ያለው ማለት ነው?
እንደዛ ነገር ይመስለኛል። በቃ እንደዛ አይነት ነገር ነው የሚማርከው። ጆሹዋ ደግሞ እዛ ሲገባ ደስ አለው፣ መልኩ ሁሉ ተቀየረ። ዝናብ ቢዘንብም በቃ አይሰለቸውም። ከዛ በኋላ እዛ ያለ አንድ አሰልጣኝን እስኪ አዋሪው አሉኝ። ሄጄ ሳናግረው፤ “ካርቱን ለራስሽ መግዛት ከፈለግሽ ይህን ያህል ያወጣል፤ ምናምን; ሲለኝ “አይ እንደዚያ አላሰብኩም፤ ሰዎች አናግሪው ስላሉኝ ነው የመጣሁት” አልኩት። ይህ ሰው አሰልጣኝ ነው፤ ከ18 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ እዚህ ቢዝነስ ውስጥ ነው ያለው፤ 40 ምናምን ዓመት ይሆነዋል። ትልቅ ቡድን አለው። ብዙ ካርት የሚነዱ ልጆች አሉት። “እኔ አምስት ሳምንቱን እንዲነዱ እንጂ ካርት የመግዛት ሀሳብም የለኝም፤ በጀቴ ውስጥም የለም” አልኩት። ሲያየኝ ፍላጎትም የለኝም። “እሺ ካርት አለኝ፤ ለዛች ለምትነዱባት ሰዓት 25 ፓውንድ ትከፍላላችሁ” አለን። እሺ ብለን ለ1 ሰዓት 25 ፓውንድ  እየከፈልን ከእኩዮቹ ጋር ማታ ማታ መንዳት ጀመረ። ጆሹዋ በዛን ሰዓት ይነዳ የነበረው ከ8-11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች የሚነዱትን ክላስ ነበር። እንደየ ዕድሜያቸው ክላስ ክላስ አለው። ክላሱ እየጨመረ ሲሄድ አደጋውም እየጨመረ ይሄዳል። አሰልጣኙም ይጠራውና “እንዲህ አድርግ፣ ይህን አስተካክል፣ በዚህ መልኩ አድርግ; ሲለው በደንብ ያደምጣል። አሰልጣኙ የሚለውንም ይተገብራል። እንዴት ነው ስለው አሰልጣኙን "Its ok ምንም አይልም; ሲለኝ፣ እየተከራየን ሲነዳ ቆይቶ፣ መጨረሻ ላይ “ለምን ውድድር አታስገቢውም? እዚህ እዚህ ቦታ በቡድን ተሰብስበን ለውድድር እንሄዳለን። ለምን አታስገቢውም?” ሲለኝ እኔና ባለቤቴ እየተያየን፤ "አይ ይሄ ነገር ይቅር" ተባባልን። ምክንያቱም በተለይ ውድድር ሲሆን ብዙ ሆነው ሲነዱ ፍጥነታቸው ያስፈራል። በጣም ነው የሚያስጨንቀው። ብዙ ከመሆናቸውና ከመፍጠናቸው የተነሳ ይጋጫሉ። በጣም ከባድ ነው። ሰውየው በጣም ተበሳጨና፤ “ከእናንተ ጋር ስብሰባ እፈልጋለሁ” አለን። ተሰበሰብን። “እኔ እንደ እናንተ አይነት ወላጅ አይቼ አላውቅም” አለን። “ለአንዳንድ ወላጆች ልጃችሁ አይችልም፤ ገንዘባችሁን አታባክኑ ነው" የምለው። "የእናንተ ልጅ ግን የተለየ ነው” አለን። አየሽ፤ አንዳንድ ወላጅ ገንዘቡን ስላፈሰሰ ብቻ ልጁን ጎበዝ ማድረግ የሚችል ይመስለዋል። አዳዲስ ካርት በመግዛት ገንዘብ በማፍሰስ እስከ ጥግ ስለሚሄዱ ማለት ነው። “ልጁ ጎበዝ ነው፤ እኔ ጉብዝናውን በደንብ ስላልነገርኳችሁ ነው ችላ ያላችሁት። እውነቱን ማወቅ ከፈለጋችሁ ግን ልጃችሁ ልዩ የሆነ ተሰጥኦ አለው፤ የሚባለውን በደንብ ይሰማል” አለን። ሞተር ስፖርት የጭንቅላት ስፖርት ነው። ከፊዚካል ስፖርቱ ይልቅ 99 በመቶ አዕምሮን የማሰራትና ፈጥኖ የማሰብ ስፖርት ነው። ቶሎ ውሳኔን መወሰንና የአሰልጣኝን ትምህርት ማስታወስ ይፈልጋል። ምክንያቱም አንድ ኮርነር ላይ ትንሽ ስህተት ከተፈጠረ እሷን ለማስተካከል መቶ ወይም 200 ጊዜ መንዳትና የሚፈልገው ደረጃ ላይ ማድረስ አለባቸው።
ጭንቅላትን እጅግ የሚፈትን ስፖርት ነው፡፡ ስለዚህ አሰልጣኙ “እኔ የምለውን ከማዳመጥና ከመተግበር በተጨማሪ በተፈጥሮው ልዩ የሆነ ተሰጥኦ አለው።” ሲለን “እናመሰግናለን” ብለን ሄድን፡፡ ከዚያም ወስነን ወደ ውድድሩ ለመግባት ሌላ ተጨማሪ ስደስት ወር ፈጀብን። እንደፈራነው የመጀመሪያው ውድድር ጊዜ ከባድ አደጋ ደረሰበት፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እሱ አልተጎዳም፤ መኪናው ግን ተንሻፈፈች። “በቃ  ይሄ ነገር ይቅርብን፤ ወደ ቤታችን እንሂድ" ስለው ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ። ይሄ አደጋ የደረሰው ፋይናል ውድድሩ ከመድረሱ በፊት ስለነበር፣ “በፋይናል ውድድር ተመልሼ እገባለሁ፤ አልተወውም” አለ፡፡ “መኪናህ  ተጣሟል፤ እንዴት ይደረግ” ሲባል፤ "ኖኖ እገባለሁ” አለ። ሁሉም የየራሱን ድንኳን ተክሎ ውድድሩን ይከታተል ስለነበር፣ የእያንዳንዱን ድንኳን እያንኳኳሁ “ይሄ ነገር አላችሁ” እያልኩ መለመን ጀመርኩ - ያንን የተጣመመውን የካርት አካል ለመቀየር፡፡
አደጋ አጋጥሞትም ተመልሶ ለመግባት አልፈራም ማለት ነው?
ምን ይፈራል፡፡ መኪናው እንደምንም ተገጣጥሞ መልሶ ወደ ውድድሩ ገባ፡፡ ነገር ግን ያን ቀን መጨረሻ ነው የወጣው፡፡ ግን ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ አሰልጣኙም ምን አለኝ፤  “እንዲህ አይነት አደጋ ደርሶበት ተመልሶ መግባቱ እራሱ ትልቅ ነገር ነው፤ ፈርቶ አለመቅረቱ በራሱ የልጁን ከፍተኛ ፍቅር  ያሳያል”፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ አሰልጣኙን እየሰማ፤ እየተማረ እየተማረ፣ ያ የወድድር ዓመት ከማለቁ በፊት ከ1-5 መውጣት ጀመረ። የመጀመሪያ ዓመት ሲወዳደሩ መጨረሻ ይወጣሉ፡፡ ሁለተኛ ዓመት ላይ ወደ መሃል ይገባሉ፡፡ ሶስተኛ ዓመት ላይ ነው ወደፊት የሚሄዱት፡፡ ጆሹዋ ግን በስድስት ወር ውስጥ ከኋላ  ወደ ፊት ተመንጥቆ ወጣ፡፡ አሰልጣኙ “ይሄ እኮ የተለየ ነገር ነው፤ እናንተ እኮ አይገባችሁም፣ የኔ ልጅ በሆነ” ይለን ነበር፡፡ እኔ ግን ስፖርቱን  እምብዛም ስለማላውቀው ብዙ አይገባኝም ወይም ስሜት አይሰጠኝም ነበር፡፡ ጆሹዋን ደግሞ “አንተ ይህንን ነገር ካልፈለከው ንገረኝ፤ ጎበዝ ስለሆንክ የማትፈልገው ነገር ውስጥ እንድትገባ አልፈልግም” እለዋለሁ፡፡ ምክንያቱም እኔ ልጆቼን ያለፍላጎታቸው ገፍቼ ምንም ነገር ውስጥ እንዲገቡ አልፈልግም። አንድ ነገር ላይ ፍላጎት ሲያሳዩ፣ ጊዜዬን እዛ ፍላጎታቸው ላይ አጠፋለሁ፡፡ አብሬያቸው ቁጭ ብዬ እንዲገባኝ እፈልጋለሁ፤  ልጄ የመጀመሪያ ሲዝኑ በ2020  ነበር፡፡ ሲዝኑ ሳያልቅ ሶስት ወይም አራት ዋንጫ  ተሸልሟል።
ባለፈው ዓመት በ2021 ሙሉ ሲዝን ነበር የተወዳደረው፡፡ በዚህ ሲዝን 26 ዋንጫዎችን አሸንፏል፡፡ የክለብ ሻምፒዮንሽፕ ተወዳድሮ፣ አንድ የክለብ ሻምፒዮንሽፕ አሸናፊ ሆኗል። በአንደኛው ክለብ ሻምፒዮን ሁለተኛ ወጥቷል። ሌላኛው ላይ አራተኛ የወጣበትም አለ። “Drive Of The year” የሚል ሽልማት አግኝቷል፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ ክላስ ጀምሯል። ቅድም ሲነዳ ያሳየሁሽ ቪዲዮ ከቀድሞ ከፍ ያለ ክላሰ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ይነዳ የነበረው ክላስ “ሆንዳ ከዳት” ይባላል። የአሁኑ ደግሞ “ሚኒ ማክስ” ይባላል፡፡ ሚኒ ማክስ ክላስ ጃንዋሪ ከጀመረ በኋላ አራት ውድድር አድርጓል። ከአራቱ ውድድር ቀኑን ሙሉ ሲያሸንፍ ውሎ በመጨረሻውና  ፋይናል በሚባለው ውድድር ትንሽ ስህተት ሰርቶ 2ኛ ወጥቷል፡፡ ይህ የሆነው ቅዳሜ ነበር፡፡ በነጋታው እሁድ ግን አሸነፈ። በጣም እልህ ይዞት ነበር ወደ ውድድሩ የገባው። በአንድ ዊኬንድ ብቻ አራት  ዋንጫ ይዞ ተመልሷል፡፡ ይሄ ማለት ለፋሲካ በዓል ወደ ኢትዮጵያ  ጉዞ ከመጀመራችን በፊት በነበረው የሳምንቱ መጨረሻ ማለት  ነው፡፡ አሁን ይሔ የሞተር ስፖርት  ለጆሽዋ ፓሽኑ (ፍቅሩ) ሆኗል፡፡ ታውቂያለሽ፤ ልጅሽ አንድ ነገር ላይ ጎበዝ ሲሆን አንቺ ራስሽ ሳታውቂው በዛ ነገር ውስጥ ትሰምጫለሽ፡፡ በፊት ምንም የማይመስለኝ አሁን እኔም ነገሩን ጉዳዬ ብዬ ነው የምከታተለው፡፡ ልጄም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የምችለውን ሁሉ ነው የማደርገው፡፡
በ72 ዓመት በዚህ የሞተር ስፖርት ታሪክ ውስጥ ተቀላቅሎ ተፅዕኖ  ፈጣሪ መሆን የቻለው ክልስ ሊዊስ  ሀምልተን ብቻ እንደሆነና እሱም በብዙ ፈተና  ውስጥ እንዳለፈ ይነገራል። በዚህ በሞተር ስፖርት ጥቁር እንዳይቀላቀል ነጭ ቱጃሮች በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በብዙ መልኩ በር እንደሚዘጉ ቀደም ብለሽ ነግረሽኝ ነበር፡፡ አሁን በጆሽዋ እድሜስ ይሄ ዘረኝነት አለ? ለመሆኑ በጆሹዋ እድሜ ያሉና የሞተር ስፖርት ውስጥ የገቡ ሌሎች ጥቁር ታዳጊዎች  አሉ?
በጣም በሚገርምሽ ሁኔታ ብዙ ችግር አለ። ጥቁር ልጆች በቁጥር በጣም ጥቂት ናቸው  እንጂ አሉ፤ ነገር ግን እንደ ጆሽዋ ውጤታማና ታዋቂ አይደሉም፡፡ ተግዳሮቱን በተመለከተ የእኛን ተሞክሮ ልንገርሽ። በ2020 ዓ.ም ገና መወዳደር እንደጀመረ ብዙ ብዙ ውድሮች ላይ ነበር የምንሳተፈው፤ አንድ ቦታ ብቻ አይደለም፡፡ እና አንድ ቦታ ላይ  የጆሽዋ እኩያ የሆነ  ተወዳዳሪ ነጭ ልጅ አጋጠመን። “አንተን ባየሁህ ቁጥር እገፋሃለው” አለው፡፡ ጆሹዋ ደግሞ ሰምቶ ዝም አለው፤ እውነትም አልመሰለውም። ለእኔም አልነገረኝም። ይሄ ልጅ ባገኘው ቁጥር ይገጨዋል፤ ይገፋዋል፡፡ እንደውም አንድ ጊዜ ልጄ ሊጎዳ ነበር፤ ጩኸት ሁሉ ነበር፤ በቪዲዮ ቀርጬ ይዤዋለሁ - ለክለቡ ሀላፊዎች ለማሳየት፡፡ የዚህ ልጅ  እናትና  አባት በጣም ወፍራሞች፣ ታቱ ያላቸው፣ በጣም የሚያስፈራሩ ናቸው፡፡ የምትጋፈጫቸው አይነትም አይደሉም፡፡
ጆሹዋ ደግሞ “እኔ መወዳደር ብቻ ነው የምፈልገው፣ ከሰው ጋር መጣላት አልፈልግም፤ ከዚህ በፊት ባገኘሁህ ቁጥር እገፋሃለሁ፤ እገጭሃለሁ ብሎኝ ነበር" አለ። የክለቡ ሀላፊዎች ያንን ልጅ ጠሩት። “እንደዚህ ብለኸዋል?” ሲባል “አዎ ብዬዋለሁ” አለ “አደረግከው ሲሉት?” “አዎ አድርጌዋለሁ” አላቸው፡፡ ቅጣት ስንጠብቅ በማስጠንቀቂያ አለፉት፡፡ ስድስት ሳምንት በተከታታይ ልጄን እንደዚህ አደረገው፡፡ ልጄ ቦታውንና ደረጃውን ያጣል፤ ውድድሩንም አይጨርስም። ስድስተኛው ሳምንት ላይ የሶስት ቀን ሬስ ነበር - አርብ፣ ቅዳሜና እሁድ ማለት ነው፡፡ አርብ በጠዋት ሄድኩኝ። ማርሺያል የሚባሉ አሉ፤ መሃል መሃል ላይ ሆነው ሲጋጩ፣ ችግር ሲፈጠር ህግ የሚያስከብሩ፤ እና ለሁለቱ  ነገርኳቸው፡- “ይሄ ልጅ፤ ልጄን  እንዲህ እያደረገ ስድስተኛ ሳምንቱ  ነው፤ ወይ ከፍተኛ አደጋ ያደርስበትና ገንዘብ እያወጣን ውድድር ሳይጨርስ ይወጣል፤ አንዳንዴ መኪናው ሲጣመም ሌላ ወጪ አውጥተን  የመኪና  እቃ እንቀይራለን፣ በሞራሉም ላይ የሚፈጥረው ጫና ከባድ ነው” አልኳቸው፡፡ “እሺ እሺ ተጠንቅቀን እናየዋለን፤ እንጠብቀዋለን” አሉኝ። ነገር ግን ከአርብ ጠዋት እስከ እሁድ ጠዋት ይገጨዋል፤ ይገጨዋል፤ ኡኡ ብል የሚሰማኝ የለም፤ "እሺ እንጠብቀዋለን" ነው የሚሉሽ፤ ግን አያደርጉትም፡፡ በጣም ያበሳጫል፡፡
የዘንድሮ ዘረኝነት ምን መሰለሽ ..ፊት ለፊት አይን ያወጣ አይደለም፤ ነገር ግን አንቺ ጥቁር በመሆንሽ የበታችነት ተሰምቶሽ ወይም መስሎሽ ያንፀባረቅሽው እንዲመስል ነው የሚያደርጉት፡፡ ቅሬታ ስታቀርቢ በትክክል ተደርጓል ብለው ሳይሆን፣ መስሎሽ ይሆናል አይነት ነገር ነው የሚሉት። ይሄ ደግሞ ይበልጥ ያበሳጫል፡፡
የክፍያው ጉዳይ እንዴት እያደረጋችሁ ነው? ለውድድሩ የምትከፍሉት ብዙ ነው አይደል?
እውነት ነው ከባድ ነው፡፡ እኛም ሳናውቅ የገባንበትና የልጃችን የሞተር ስፖርት ፍቅር እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ ውስጥ  ነው ያለነው፡፡ ልጅሽ ጎበዝ እየሆነና ፍቅሩ እየጨመረ መጥቶ ነፍሱ ያረፈበትን ነገር ከስሩ መንጠቅ ከባድ ነው፡፡ ብዙ መስዋዕነት አለው። እንደነገርኩሽ ልጆቻችን ሶስት ናቸው፡፡ ጆሽዋ ብቻ አይደለም፡፡ አንድ ልጅ ቢሆን የመጣው ይምጣ  አንድ ልጄን ትያለሽ፣ የእኛ ልጆች ግን ሶስት ስለሆኑ ለእሱ ብቻ ሲደረግ የሌሎቹ መጉደል የለበትም፡፡ ብቻ አስቸጋሪ ነው፡፡ ደግሞ ልጃችን ቀልቡ ያረፈው ውድ ስፖርት ላይ ነው፡፡ እንደተባለው የቱጃር ስፖርት ነው። እኔ  እግር ኳስ ቢጫወት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ የኔ ሀላፊነት አይሆንም ነበር ለማለት ነው። የሆነ ሆኖ ከብዙ መስዋዕትነትና ከብዙ ጥንቃቄ ጋር እዚህ ደርሰናል፡፡ እያደገና ክላሱ እየጨመረ ሲሄድ፣ ክፍያውም እያደገና እየጨመረ ስለሚመጣ ያሳስባል፡፡ አሁን ላይ የእኛ ገቢ እየጨመረ አይደለም፤ ነገር ግን እግዜር ያውቃል፡፡ አሁን ላይ ሁለት ወድድር ክለብ ነው በወር የሚወዳደረው፡፡ አንዱ ሎካል ክለብ ነው፡፡ አንዱ ብሔራዊ ክለብ ነው፡፡ አቅማችን ቢፈቅድ በየቅዳሜና እሁዱ አለ፡፡ በየጊዜው ቢወዳደር የበለጠ ተሰጥኦው እየዳበረ፣ ልምድ እያካበተ ታዋቂም እየሆነ ይመጣል፤ እድልም ይከፈትለት ነበር፤ ነገር ግን ከዚህ በላይ አቅማችን አይፈቅድም፡፡ እኛ ግን እነዚህን ሁለቱን መርጠን፣ አንደኛው እንደ ፕራክቲስ ትልቅም የሚወደውም ክለብ ስለሆነ፣እዛ አስቀጠልነው፡፡ ክለቡ “ዊልተን ሚል” ይባላል። ይህ ክለብ በጣም ታዋቂና ታዋቂ ሰዎች ተሰጥኦ ያለው ሰው ለማየት የሚመጡበት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ “ሱፐር ዋን” ናሽናል ሻምፒዮንሽፕ ነው፡፡ ይህ ክለብ ታዋቂነቱ የበዛ ወደፊት እንደ ሲቪም "በዚህ  ክለብ ተወዳድሬ  አልፌያለሁ" ብለሽ በኩራት የምትታወቂበትና ተቀባይነት የምታገኝበት ትልቅ ክለብ ስለሆነ ሁለቱን መርጠናል፡፡ የገንዘብ አቅም ባይገድበን በሁሉም ላይ ቢሳተፍ ደስ ይለናል፡፡
እኛም ሀገር እንጦጦ ሞተር ስፖርት ተጀምሯል፡፡ ጆሹዋን እዚያ አልወሰዳችሁትም?
አንድ ቀን ሄደን ጆሹዋን ነድቶ ነበረ፤ እና አሰልጣኙ “ጎበዝ ልጅ ነው፤ ማን ነው?; ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ልጄ መሆኑንና ለንደን በዚህ ዘርፍ ያለበትን ደረጃ ነገርኩት፡፡ “እኔን አይበልጠኝም፤ከኔ ጋር ይወዳደር፤ በነጻ አስነዳዋለሁ; አለ፡፡ እና አስገባውና ጀመሩ። ጆሹዋ ቀደመው፡፡ እኔ ደስ አለኝ፡፡ ጆሹዋ እዚህ አገር ሌሎች ልጆችን ቢያነቃቃ ደስ ይለኛል፡፡
በእንግሊዝ መፅሔቶች፣ ጋዜጦችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለ ጆሹዋ ስኬት ብዙ እንደጻፉና እንደዘገቡ ሰምቻለሁ። በሀገሩ በኢትዮጵያስ እንዲታወቅ ምን ያደረጋችሁት ነገር አለ?
እውነቱን ለመናገር እንደ ሀበሻነቴ "ልጄ ጎበዝ ነው፤ እንዲህ ነው" ለማለት ይከብደኛል። ነገር ግን ለንደን ከሚታወቀው በላይ እዚህ ቢታወቅ ነው ኩራቴ፡፡ ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ። ይህንን መንገድ አዲስ አድማስ ጀምሮታል፡፡ ሌላው እድሜው እዚህ እስኪደርስና በስፖርቱ መቀጠሉን እርግጠኛ እስክንሆን ድረስም ብዙ አልገፋንበትም ነበር፡፡ ምክንያቱም የልጅ ነገር አንድ ቀን "አስጠላኝ ሰለቸኝ" ብሎ ሊያቆመው ይችላል የሚል ፍርሃትም ይይዝሻል፡፡ አሁን የእውነትና አንድ ደረጃ ላይ የሚደርስ ጉዞ ላይ እንዳለን እናምናለን። የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽንም እውቅና እንዲሰጠው እንፈልጋለን። አሁን በቅርብ ጊዜ የሰማሁት አንድ ውድደር አለ፡፡ ይሄ ዓመት ሊያልቅ ሲል ዲሴምበር ላይ ጆሹዋ 13 ዓመት ይሞላዋል። በ14 ዓመቱ (በቀጣዩ ዓመት) ኢትዮጵያን ወክሎ ሊወዳደር የሚችልበት ወድድር እንዳለ ሰምቻለሁ፡፡
ይህም ሊሆን የሚችለው ከኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን ውክልና ሲያገኝና እውቅና ሲሰጠው ነው፡ ስለዚህ ግንኙነት መፍጠር መጀመር አለብኝ፡፡ በተረፈ ከዚህ ቀደም ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን፣ ስለ ጆሹዋ ፌስቡክ ላይ ፅፎልን ነበር፡፡ በወቅቱ ያለመረጋጋት ስለነበር ብዙ ትኩረት ባያገኝም፣ ጌጡ ተመስገንን አመሰግናለሁ፡፡ አንቺም ዛሬ ፋሲካ ነው፤ በዓል ትተሽ ይህን ቃለመጠይቅ ለማድረግ መጥተሻል፡፡ አንቺንም አዲስ አድማስንም አመሰግናለሁ፡፡ (ቃለ ምልልሱ የተደረገው የፋሲካ ዕለት ነበር፡፡)


Read 3243 times