Sunday, 08 May 2022 00:00

ባለፈው አመት ብቻ 3 ሺህ 535 ስደተኞች ለሞትና ለመጥፋት ተዳርገዋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 ብቻ በሜዲትራኒያን ባህር እና በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል አቋርጠው ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት በጉዞ ላይ የነበሩ ከ3 ሺህ 535 በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ለሞትና ለመጥፋት መዳረጋቸውን ተመድ አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ እንዳለው፤ በአመቱ የተመዘገበው የሞቱና የጠፉ ስደተኞች ቁጥር በ2020 ከነበረበት በእጥፍ ያህል የጨመረ ሲሆን፣ ከመረጃ አያያዝ ጉድለት ጋር በተያያዘ ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ በእጅጉ ሊጨምር እንደሚችልም አስታውቋል፡፡ በፈረንጆች አመት 2022 ያለፉት ወራት ብቻ 478 ስደተኞች ለሞትና ለመጥፋት መዳረጋቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ለአደጋ በመጋለጥ ረገድ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የአፍሪካ አገራት ስደተኞች መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ ሪፖርቱ በየብስ ላይ ጉዞ የሞቱትንና የጠፉትን ስደተኞች እንደማያጠቃልልም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
አገራት ስደተኞችን ላለመቀበል የሚያደርጉት የበዛ የድንበር ላይ ክልከላና ጥበቃ የስደተኞችን ለአደጋ የመጋለጥ እድል በእጅጉ እንደጨመረው የጠቆመው ኮሚሽኑ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞች በአስቸጋሪ የባህር ላይ ጉዞ የሚያጋጥማቸውን ዘርፈ ብዙ አደጋ ለመቀነስ ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

Read 2365 times