Saturday, 07 May 2022 14:57

"መንደሪን መንደሪን"፤ ሞጋች ቅኔዎች

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(0 votes)

      እንዴት ሳትገልጥልኝ?፥ እኔን ያህል መና     
ጠኔ ታስሄዳለህ፥ ሰው ባለው ጎዳና
ለምን አሰሰትከኝ፥ ለምለም ሰውነቴን?
ረሃብ እስኪያወልቅ ፥ ከገላዬ ልብሴን
 ምግብ አይደለሁ ወይ፥ ለትል ለምናምን…
እንዴት አንተን መሳይ ለሆዱ ሲለምን?
(ምግባር፣ 2014፡ ገጽ 80)
መንደሪን መንደሪን፣ በያዝነው ዓመት ለንባብ የበቃ፣ በገጣሚ ምግባር ሲራጅ የተደረሱ ግጥሞችን አሰባስቦ የያዘ መድበል መጠሪያ ነው፡፡ በዚህ መድበል ውስጥ የቀረቡት የምግባር ሥራዎች የተሰነዱበት ቋንቋ የተዋበ ነው፣ የሚፈክሩት ፍልስፍና የጠጠረ፡፡ ግሩም ቅኔ እነዚህን መሠረታዊ ተፈጥሮዎች (essence) የያዘ ነው፡፡
በመንደሪን መንደሪን ውስጥ የቀረቡት አብዛኞቹ ቅኔዎች ግለ-ነፍስን የተቆራኙ ቅኔዎች (impressionistic poetries) ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ ቅኔዎች፣ በህልውናችን ዙሪያ ጠጣር ጥያቄዎችን የሚያነሱ ሞጋች ቅኔዎች ናቸው፤ ገንብተን የምንኖርበትን ግለሰባዊም ሆነ የጋርዮሽ ንጽረተ ዓለም መሠረት የሚነቀንቁ፡፡   
የምግባር ሥራዎች የተለያዩ ጭብጦችን የሚፈክሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ ፀፀት (guiltness) በገጣሚው ሥራዎች ውስጥ ከተዳሰሱ ዐቢይ ጭብጦች (central themes) መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ጭብጥ ደብዳቤዎቻችን፣ አካልሽ ከእኔ ቢርቅም፤ ከልቤ ስምሽ አይለቅም እና ልትወስደኝ መጥታለች በተሰኙት ሥራዎች ውስጥ ተዳስሷል፡፡
የማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ፀፀት መነሻ ሥነ ኑባሬአዊ አርነትን (ontological feedom) መረዳት ነው፡፡ ይኸን ፈፅሞ ሊሸሽ የማይቻል ገሀድ ያልተገነዘበ ግለሰብ፣ ነፍሱን የፀፀት አለንጋ ሊገርፈው አይችልም፡፡
ደብዳቤዋቻችን፣ የአንዲት ልባዊ አፍቃሪን ሴት እና ቃለ አባይ የሆነ ፍቅረኛዋን ሕይወት የሚተርክ አንዱ የምግባር ግሩም ቅኔ ነው፡፡ በዚህ ቅኔ ውስጥ የምናገኛት ሴት የተለየ የሞራል ልዕልና ያላት ሴት ናት፤ የማትዋሽ፣ የማትታበይ፣ አመፃን የማትቆጥር፡፡ ይኸን አስመልክቶ ገጣሚው እንዲህ ጽፏል፦   
ተበጠሰ?
ወይስ ረገበ?
የአንቺስ አንጀት ልብ ነው፡፡
የልብሽስ ነገር ከየት ነው?
(ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 37)
ከእነዚህ ስንኞች እንደምንረዳው፣ ይቺ አፍቃሪ ሴት በአመፀኛ አፍቃሪዋ እኩይ ተግባር የልቧ ፍቅር አልነጠፈም፣ ክህደቱ ሰብሯት የአብሮነታቸውን ድር አልበጠሰችም፣ ሲሸሻት መከተሉን አልሰለቸችም፡፡ ገጣሚው እንዲህ ጽፏል፦   
እኔን ባይጥልብሽ
እኔን…
አልታከክ የሆድ ቁስል
ስጥልሽ ስሜን የምትጠሪው
ምን ይዞሽ ነው ይሄን ያህል
(ዝኒ ከማሁ)
ከእዚች አፍቃሪ ሴት በተቃራኒ፣ አፍቃሪዋ ገጸባሕርይ በእሷ ልክ የተሰፋ ሰብዕና የሌለው ከሀዲ (betrayal) እና ሸንጋይ (deceiver) ግለሰብ ነው፣ ፍቅር ለሰጠው ዕምባ ያበደረ፡፡ ገጣሚው እንዲህ ጽፏል፦    
አንቺስ…
ምን አሮጠሸ ከሰው እኩል
ምን አዘለለሽ ለስንኩል
አልማርማ፡፡
እኔ እንደው …
 ማያርመኝ ወይ ማይምረኝ
ቃል የምበላ ፍጡር ነኝ
አይበቃሽም?
ይብቃሽ፡፡ አትታገይ፡፡
እኔ … ምሴ ነው ቃል መብላት
መቻል ካለሽ፤ በደሌን መርሳትሽን ቻይ፡፡
(ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 38)
በዚህ ግጥም፣ ምግባር፣ ውሎ ቢያድርም ቀድመን የሠራነው እኩይ ሥራ አእምሮአችንን በፀፀት እንደሚያናውጠው ይነግረናል፤ ከእዚህ የነፍስ ሰቀቀን ልንሰወርበት የሚያስችለን ቅያስም እንደሌለ ሐቁን ይግተናል፡፡ በእዚህ ግጥም ውስጥ የተሳለው ዋና ገጸባሕርይ፣ በንፁህ አፍቃሪው ላይ የፈፀመው ክህደት የወንጀለኝነት ስሜት ፈጥሮበት፣ ኩሸት የጋረደውን ጭንብሉን ገፎ እኩይ ተግባርን የሚናዘዝ ግለሰብ ነው፡፡ ይህ እኩይ ተግባሩ ንፁህ አፍቃሪው ፊት ሊያቆመው ስላልቻለ፣ ፍቅረኛው ኃጢያቱን ታዝባ እንድትሸሸው፣ ከነአካቴው እንድትረሳው ሲማፀናት እናገኘዋለን፤ በሰብዕና እርከኑ ከእሷ እንደሚያንስ በመግለፅ፡፡ ገጣሚው እንዲህ ጽፏል፦       
አይበቃሽም?
ይብቃሽ በቃ፡፡ አትታገይ፡፡
እኔ … ምሴ ነው ስም መጥራት
መቻል ካለሽ አቤት ማለትሽን ተይ፡፡
ባክሽ በፅድቅሽ ይዤሻለሁ
አትተይ እኔን መተውሽን
ሙቺለት እኔን መጥላትሽን
(ንጽህናሽ አቆሸሸኝ፡፡ አቃጠልሺኝ የኔ ውሃ)
(ዝኒ ከማሁ፡ ገጽ 39)


Read 1416 times