Saturday, 07 May 2022 15:08

ወይኔ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ከፀጉርሽ ዘለላ ከዓይኖችሽ ሽፋሽፍት
ከፈገግታሽ ላሕይ ከዚያ መቃ ደረት
ከአለንጋ ጣቶችሽ ከሎጋው ቁመትሽ
በዓይኖቼ ቆንጥሬ፤
ለከርሞ አዝመራ
እዘራው ይመስል ከልቤ ሸሸግኹት
ፍቅርሽን ቋጥሬ፡፡
ደጅ አዳሪ ልቤን
ያላደበ ቀልቤን
በተስፋ ሣባብል፤
ከአጥሬ ነቅዬ ሳበጅልሽ አልጋ፣
መደብ ስደለድል፣
እኔ የሰኔ ሟች ቀልደኛ ገበሬ
ከደጄ ላይ ሞፈር ከቁናዬም ዘሬ
ከሠራ አካላትሽ “ለዘር” የቋጠርሁት
ተሰወረ ከእጄ ከጉያዬ አጣኹት፡፡
ከዓይኔ ላይ የቀረሽ፣
ልቤ ላይ የቀረሽ፣
የተኛሽ ካንጀቴ
ያልዘራሁሽ ወይኔ፣
ያልቀጠርኩሽ ወይኔ፣
አንቺ ሆይ ስስቴ
ከሰው አፀድ በቅለሽ፣
ለሰው ማጀት ደርሰሽ፣
ከሰው ቤት ተጠምቀሸ
ከሰው አቁማዳ ከሰው ዋንጫ ተሾምሽ፡፡
ባልጤሰበት ገንቦ፣ባልታጠነ ዋንጫ
የስርቆት ወይን ጠምቆ መሆን መዛበቻ
ዘርን ለወፍ ሰጥቶ ፀፀት መሠንበቻ፡፡

Read 1943 times