Print this page
Saturday, 14 May 2022 00:00

የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች ለዳግም ጦርነት ዝግጅት እያደረጉ ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

መንግስት የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመመከት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል
                                       
             የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች ለዳግም ወረራና ጦርነት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸው የተጠቆመ ሲሆን አማፂ ቡድን  “የመጨረሻው ምዕራፍ”  ላለው ጦርነት የትግራይ ህዝብ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርቧል፡፡
እያንዳንዱ የክልል ነዋሪ ለጦርነቱ በነፍሰ ወከፍ ልጆቹን ማዋጣት እንዳለበት ያሳሰበው ቡድኑ፤ ይህንን መመሪያ ተግባራዊ በማያደርጉ ወላጆች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቀዋል፡፡
የታጣቂ ሃይሉ አመራሮች ሰሞኑን በተለዩያ የክልሉ ወረዳዎችና ከተሞች ህብረተሰቡን እየሰበሰቡ ለጦርነቱ ዝግጁ እንዲሆንና በእጁ የሚገኘውን ጥሬ ገንዘብ ታጣቂ ቡድኑ ወዳቋቋመው የገንዘብ መሰብሰቢያ ባንኮች ገቢ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። የትግራይ ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብቱ የሚረጋገጠው የሃይል የበላይነት ሲይዝ ብቻ እንደሆነም አመራሮቹ መግለፃቸው ተነግሯል፡፡
ህወሃት ህብረተሰቡ ምንም የዕድሜ ገደብ ሳያደርግ ለጦርነቱ እንዲዘጋጅ ያሳሰበ ሲሆን ሁሉም የክልሉ ተወላጅ በነፍስ ወከፍ ልጆቹን ለጦርነቱ እንዲያሰልፍም ታዟል፡፡ ትዕዛዙን ተግባራዊ  በማያደርጉ ወላጆች ላይ ከፍ ያለ የቅጣት እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል፡፡
ይህን የቡድኑን ውሳኔ የተቃወሙ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች የአማራ ክተሞች እየተሰደዱ እንደሆነም ታውቋል። ቡድኑ ህብረተሰቡ ወደ አጎራባች የአማራ  ክልል ከተሞች መግባቱን ለማስቀረትም ጥብቅ ጥበቃና ቁጥጥር እያደረገ ነው ተብሏል፡፡
መንግስት በበኩሉ በህወሃት ታጣቂ ቡድን በኩል እየተደረገ ያለውን የጦርነት ዝግጅትና ትንኮሳ የዓለም ማህበረሰብ እንዲገነዘብ በማሳሳብ በአገሪቱ ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመመከት በሚያስችል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።

Read 9877 times