Saturday, 14 May 2022 00:00

ፋኖን እንደ ጃንጃዊድ ሚሊሻ?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

 በዚህ ሳምንት ትኩረት ላደርግበት የመረጥኩት ርእሰ ጉዳይ “ፋኖ” ነው። በቅድሚያ “ፋኖ” የሚለውን ቃል እና ጽንሰ ሃሳብ ምንነት ለማየት እንሞክራለን። “ፋኖ ማን ነው?” የሚለውንም በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡ በ“ፋኖ” ላይ የሚነሱትን አወዛጋቢ አስተያየቶች እናወሳለን፡፡ አንዳንዶች ፋኖን እንደ ጃንጃዊድ ሚሊሻ አሸባሪ እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ፋኖ እና ጃንጃዊድ ምን ያህል እንደሚለያዩ ለማሳየት ስለ ጃንጃዊድ ሚሊሻ በአጭሩ እንቃኛለን፡፡
“ፋኖ” ማለት ምን ማለት ነው?
በ1993 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ፋኖ” የሚለው ቃል መነሻ ወይም ስርዎ ቃሉ “ፋነነ” የሚለው ቃል መሆኑን ያስቀምጥና በሁለት መልኩ ይተረጉመዋል፡፡ ይኸውም፤ “ፋኖ” የሚለውን ቃል እንደ “ግስ” እና እንደ “ስም” በመውሰድ ይተረጉመዋል፡፡ “ፋኖ” የሚለው ቃል እንደ “ግስ” ሲወሰድ ሦስት ትርጉሞች ይኖሩታል፡፡ “(1) ፈረጠጠ፣ ቦረቀ፣ ፈነጨ (2) በውዴታ ወይም በገዛ ፈቃዱ ዘመተ (3) አውደለደለ፣ ቦዘነ…” ማለት ነው፡፡ ይኸው መዝገበ ቃላት “ፋኖ” የሚለውን ቃል እንደ “ስም” በመውሰድ ሲተረጉመው ደግሞ “ሳይታዘዝ በፈቃዱ የሚዘምት፣ ወዶ ዘማች” ማለት ነው ይለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ስለ ፋኖ ትርጉም በእንግሊዝኛ የተጻፉ ሰነዶችን ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ የበይነ መረብ መዝገበ ሃሳብ የሆነው ዊኪፔዲያ “ፋኖ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የአማራ ወጣቶች ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወይም የታጠቀ ሚሊሻ ሊሆን ይችላል” በማለት ብያኔ ይሰጣል፡፡ አመሰራረቱን በተመለከተ ደግሞ “ፋኖ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ ካቆጠቆጡት በርካታ የወጣት ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ለተገኙት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ለውጦች አስተዋጽዖ አድርጓል” ይላል ዊኪፔዲያ። ዊኪፔዲያ “ቄሮ የኦሮሞ ወጣቶችን ያቀፈ ሲሆን፤ ፋኖ ደግሞ የአማራ ወጣቶችን የያዘ ቡድን ነው” ካለ በኋላ፤ አደረጃጀቱን በተመለከተ “ፋኖም ሆነ ቄሮ ልቅ የወጣቶች ስብስብ ነው” በማለት ያብራራል፡፡
ፋኖ በተለያዩ ሚዲያዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ቡድንም እንደታጠቀ ሚሊሻም ይታያል። ለምሳሌ፡- አምነስቲ ኢንተርናሽናል “የአማራ ፖሊስ ልዩ ኃይል አንዳንድ አባላት ፋኖ መሆናቸውን የሚገልጽ ልብስ ለብሰው ይታያሉ” ብሏል። ኢዜጋ የተባለ የበይነ-መረብ የዜና አውታር ደግሞ “ፋኖ የአማራ መሬት እስካልተመለሰ ድረስ ትጥቅ የማይፈታ የታጠቀ ቡድን ነው” ሲል ገልጿል። የአለም ሰላም ድርጅት የተባለ ተቋም በበኩሉ፤ “ፋኖ መንግስት ያቃተውን ህግና ስርዓት ማስጠበቅ የሚችል አድርጎ እራሱን የሚቆጥር፤ አማራን ነቅቶ የሚጠብቅ ወጣት ቡድን ነው” በማለት ጽፏል።
ከላይ ለማየት እንደተሞከረው “ፋኖ” የሚለው የመዝገበ ቃላት ትርጉምና በእንግሊዝኛ የተጻፉ ሰነዶች ስለ ፋኖ ያላቸው ትርጉም፣ አተያይም ሆነ ግንዛቤ ልዩነት አለው። በእንግሊዝኛ የተጻፉ ሰነዶች ላይ የሰፈረው ሃሳብም ሆነ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የተጻፉትና የተነገሩት ሃሳቦች የፋኖ አባላት በቅርብ ዓመታት የነበራቸውን እንቅስቃሴ የሚያመለክት እንጂ “ፋኖ” የተሰኘውን ነባር ማህበረሰባዊ ስብስብ እውነተኛ ትርጉም የሚያመለክት አለመሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡
በመዝገበ ቃላት ትርጉሙ ላይ እንደተመለከተው “ፋኖ” እንደ ስም ሲወሰድ “ሳይታዘዝ በገዛ ፈቃዱ የሚዘምት፣ ወዶ ዘማች” ማለት ነው፡፡ ከዚህ ነባር የቃሉ ትርጉም ስንነሳ የዘመናችን “ፋኖ” ከስያሜው ውጪ ምን ተግባር ፈጸመ? ፋኖ ሳይታዘዝ በራሱ ፈቃድ ዘምቶ ሀገሩንና ህዝቡን ከአሸባሪ ኃይል ጥቃት ከመመከት ውጪ ምን አጠፋ? ፋኖ ደመወዝ የለውም፡፡ ፋኖ ከመንግስት ትጥቅና ስንቅ አይሰጠውም፡፡ ስሙ እንደሚያመለክተው ፋኖ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ያለው ወዶ ዘማች ነው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ፋኖን እንደ ጃንጃዊድ ሚሊሻ፣ አሸባሪ እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል። ፋኖ እና የጃንጃዊድ ሚሊሻ ምን ያህል እንደሚለያዩ ወይም እንደሚመሳሰሉ ለመገንዘብ ስለ ጃንጃዊድ ሚሊሻ ትርጉምና ምንነት በአጭሩ እንይ፡፡
ፋኖን እንደ ጃንጃዊድ ሚሊሻ…
“ጃንጃዊድ” የሚለው ቃል ታሪካዊ አመጣጥ ግልጽ አይደለም፡፡ አንዳንዶች “ጂን/ጋኔን” እና “አጃዊድ/ፈረሶች” ከሚሉ የአረብኛ ቃላት የተወሰደ እንደሆነና ትርጉሙም “በፈረስ ላይ ያሉ ሰይጣኖች” የሚል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሌሎች ምንጮች ደግሞ “ጃንጋቪ” ከሚለው የፋርስ (ፐርሺያ) ቃል የመጣ እንደሆነና ትርጉሙም “ተዋጊ” ማለት ነው ይላሉ፡፡ ቃሉ በአረብኛ ቋንቋ “መሳሪያ የታጠቀ፤ በፈረስ ላይ የተቀመጠ ሰው” ማለት ነው የሚሉም ተርጓሚዎች አሉ። “ጃንጃዊድ” የሚለው ቃል “ሽፍታ” ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ትርጉም እንዳለውም የሚናገሩ አሉ፡፡ ይህም ትርጉም የተሰጠበት ምክንያት እነዚህ በፈረስ ወይም በግመል የተቀመጡ ተዋጊዎች አረብ ወዳልሆኑ ሰዎች እርሻ በመግባት ከብቶችን ይሰርቁ ስለነበር ነው ይባላል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ትርጓሜ መሰረት፤ የጃንጃዊድ ሚሊሻ በምእራብ ሱዳን የሚገኙ የአረብ ጎሳዎችን ያቀፈ ሲሆን፤ በዋናነት የግመል እና የከብት እረኛዎችን በመመልመል የተደራጀ ነው ይባላል። በአንዳንድ ሰነዶች ላይ ደግሞ “ጃንጃዊድ በሱዳን በተለይም በዳርፉር ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀስ የአረብ ሚሊሻ ነው” ተብሎ ተጽፏል። የጃንጃዊድ ሚሊሻዎች የአረብ ጎሳ አባላት ሲሆኑ፤ በምእራባዊ ሱዳን ዳርፉር አካባቢ የሰፈሩ፣ ቆዳቸው ጠቆር ያለ “አፍሪካውያን” ገበሬዎች ጋር ለዘመናት ሲጣሉ የኖሩ ዘላኖች መሆናቸውም ይነገራል።
“ጃንጃዊድ” በምዕራብ ሱዳን እና በምስራቅ ቻድ የሚንቀሳቀስ የሚሊሻ ቡድን ነው። ቀደም ባሉት ዘመናት የዝናብ እጥረት ሲፈጠርና ውሀ ሲጠፋ ከዳርፉር ነዋሪዎች ጋር በግጦሽ መሬት ምክንያት ግጭት ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ከዳርፉር አማፂ ቡድኖች ማለትም ከሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ ሠራዊት እና ከፍትህና እኩልነት ንቅናቄ ጋር ይጋጩ ነበር። የጃንጃዊድ ሚሊሻዎች እ.ኤ.አ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በዳርፉር ጉዳይ ዋና ተዋናዮች ሆነዋል። በዚህም ምክንያት በሱዳን የዳርፉር ግዛት በተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል (ጄኖሳይድ) ተጠያቂ ነው እየተባለ ይነገራል - የጃንጃዊድ ሚሊሻ፡፡
ከዚህ የጃንጃዊድ ሚሊሻ ስያሜና ተግባር አኳያ የጃንጃዊድ ሚሊሻን እና ፋኖን ምን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ? የሚለውን ጥያቄ እናንሳ፡፡ ከስያሜ አኳያ ፋኖ ማለት ወዶ ዘማች ማለት ሲሆን፤ ጃንጃዊድ ማለት ደግሞ “መሳሪያ የታጠቀ ፈረሰኛ ወይም ሽፍታ” ማለት ነው፡፡ ፋኖ ሀገርና ህዝብን ከአሸባሪና ከወራሪ ሽፍታ የሚከላከል የሀገርና የህዝብ አለኝታ ሲሆን፤ የጃንጃዊድ ሚሊሻ ሀገርና ህዝብን የሚያምስ ቀማኛ ሽፍታ ነው፡፡
የጃንጃዊ ሚሊሻ በዘር ማጥፋት የሚከሰስ ወንጀለኛ ሲሆን፤ ፋኖ እንደ ማይኻድራ ባሉ አካባቢዎች የዘር ማጥፋት የፈጸሙ ወንጀለኞችን የመከተ ባለ ውለታ ነው… እናም የጃንጃዊድ ሚሊሻ እና ፋኖ በአፈጣጠርም፣ በዓላማም ሆነ በተግባር ሰፊ ልዩነት አላቸው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡
ለማሳያ ያህል ስለጃንጃዊድ ሚሊሻ እና ስለ ፋኖ አንድነትና ልዩነት ይህን ካልን ወደ ፋኖ ጉዳይ እንመለስ፡፡ በዚህም ፋኖ እንዴት ይደራጅ? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት አንዳንድ ሃሳቦችን እንመልከት፡፡ (ሣምንት በክፍል 2 እመለስበታለሁ፡፡)
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1638 times