Monday, 16 May 2022 00:00

“ህግ የሌለበት የነፃነት ዘመን” ምን ይመስላል?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

  ከሥርዓት አልበኝነት ጋር የተለማመደ ሰው፣ ምን ብሎ ይፎክራል? ላሜህን ጠይቁት። እንዲህ ይላል።
“አንድ ሰው ቢያቆስለኝ፣ የሆነ ልጅ ቢጎዳኝ፣ ገደልኩት
ሰባት እጥፍ ነው የቃየን በቀል
የላሜህ ደግሞ ሰባ ሰባት እጥፍ!
ከጥንቱ ዘመን ይብሳል የጥፋታችን ክብደት። የጥንቱ ጥፋት፣ ከእውቀት እጦት ነው። ሕግ አይታወቅም ነበር። የዘመናችን ጥፋት ግን ከእውቀት ጋር በመጣላት ነው።
ያለ ህግ እንዴት ነበር የሚኖሩት? አሁኑ ከወዲሁ ብናውቅ ጥሩ አይመስላችሁም? ለይቶልን ከገባንበት በኋላ፣ መውጪና መመለሻ ላይኖረው ይችላል። እና እውነት፣ “ህግ የሌለበት የነፃነት ዘመን” ምን ይመስላል?
ታስታውሱ እንደሆነ፣ ያኔ ጥንት፣ የመጀመሪዎቹ አመታት፤ ግድያ፣ በአዋጅ አልተከለከለም ነበር - ባይፈቀድም። በአጋጣሚ ይሁን በሌላ ምክንያት፣ የስጋ ምግብም፣ ከኖህ በፊት በግልፅ አልተፈቀደም ነበር ተባብለናል። ወይም አልተለመደም ነበር - ባይከለከልም።
እንዲህ ሲባል ግን፣ የግድያ ክፋትና የስጋ ምግብ አልነበረም ማለት አይደለም። ሁለቱም ነበሩ። እንዲያውም፣ የግድያ ክፋትና የስጋ ምግብ፣ በአንድ ጊዜና ከአንድ ቦታ ነው መነሻቸው። እንደ ጥንታዊው የሀይማኖት ትረካ ከሆነ፣ የሁለቱ አጀማመር ይመሳሰላል።
የአዳምና የሄዋን የመጀመሪያ ልጆች ላይ ነው፤ የትረካው መነሻ። እንዲህ ነው ነገሩ። ከአዳምና ከሔዋን ሁለት ልጆች ተወለዱ። የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች መሆናቸው ነው - ቃየን እና አቤል። የዘፍጥረት ትረካ እንዲህ ይላል።
የመጀመሪያዎቹ ሁለት ልጆችና ሁለት መንገዶች።
አቤል የበግ እረኛ፣ ቃየንም ዐራሽ ነበር። በአንድ ወቅት ቃየን ከምድር ፍሬ፣ ለእግዚሄር መስዋዕት አቀረበ። አቤልም፣ ከበኩር በጎች መካከል ስባቸውን መስዋዕት አድርጎ አቀረበ። እግዚሄርም፣ ወደ አቤልና ወደ መስዋዕቱ ተመለከተ። ወደ ቃየንና ወደ መስዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም ክፉኛ ተናደደ፤ ፊቱም ጠቆረ።
እግዚሄርም፤ ቃየንን እንዲህ አለው። “ለምን ተናደድክ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ አይበራምን? መልካም ባታደርግ ግን፣ ኃጥያት ከደጅህ ታደባለች። አንተንም ትሻለች። አንተ ግን ትገዛታለህ። “
ቃየንም ወንድሙን አቤልን፣ እስቲ ና ወደ መስኩ እንውጣ አለው። በመስኩም ሳሉ፣ ቃየን አቤልን አጠቃው፤ ገደለውም።…
ከወንጀሎች ሁሉ እጅግ የከፋው የግድያ ተግባር የተጀመረው፤ ያኔ በጥዋቱ ነው። በእርግጥ በግልፅ የታወጀ የክልከላ ህግ በወቅቱ አልነበረም። “ወንጀል” የሚለው ቃል ደግሞ፤ ከህግ ጋር የተያያዘ ነው። እናም፣ የቃየን ክፉ ተግባር፤ “ወንጀል” ተብሎ አይፈረጅ ይሆናል።
ቢሆንም ግን፤ ግድያ፣ ከሌሎች ጥፋቶች ሁሉ የባሰ ክፉ ተግባር እንደሆነ ግልፅ ነው። ይህን ለማወቅ፤ የግድ የህግ አዋጅ አያስፈልግም። “ወንጀል” የሚል ቅፅል ባንጨምርበት እንኳ፣ ክፉ ጥፋት ነው። “ ግድያ ባይፈቀድም፤ አልተከለከለም” ብሎ መከራከር አይችልም።
በቃ፤ የሁሉም ነገር ሚዛን ሌላ ሳይሆን፣ ክቡር የሰው ሕይወት ነው። ክፉ እና በጎ ማለት፤ ለህይወት ክፉ ለህይወት በጎ ማለት ነው። ሳይነኩህ አትንካ፤ ሳይደርሱብህ አትድረስባቸው። ይህን ለመገንዘብ የግድ የህግ አዋጅ አያስፈልግም። “በህግ ባይፈቀድም አልተከለከለም” በሚል ሰበብ፤ የግድያን ክፋት ለማቆንጀት ከሀላፊነት ለማምለጥ መሞከር፤ ምን ትርጉም አለው? ለተጨማሪ ክፋት ምንጣፍ እንደ ማመቻቸት ነው ትርጉሙ። በሌላ በኩልስ?
“ግድያ በአዋጅ ባይከለከልም፣ አልተፈቀደም”፤ “ስለዚህ ጥፋተኛ ነህ” የሚል አነጋገርም አያስኬድም። በዚያ በዚያማ፣ አቤልም እንደ ጥፋተኛ በተቆጠረ ነበር። ግን አልተቆጠረም። “የስጋ ምግብ አዘጋጅተሀል። ስጋ መብላት ባይከለከልም፤ አልተፈቀደም” ተብሎ አልተወቀሰም። ከምር ግን፣ ለምን አልተወቀሰም? በወቅቱ የስጋ ምግብ አልተፈቀደም ነበር። ምናልባት፤ ቃየን እንደዚያ አይነት ወቀሳ በአቤል ላይ እንደሚደርስበት ጠብቆ ከነበረ፣ እንደጠበቀው አልሆነም። በአንድ በኩል፤ ቃየን የዘመኑን ባህልና ልማድ እያከበረ ነበር።
አዳምና ሄዋን፣ አራሽ ገበሬ እንዲሆኑ ነበር ምክር የተሰጣቸው። የእህልና የተክል አይነቶችን እንዲበሉ ነበር የተነገራቸው። በዚሁ ልማድና ባህልም፤ ቃየን አራሽ ገበሬ ሆኗል። ለስጦታ ያዘጋጀው መስተንግዶም፣ ከተክል ከእህል የተዘጋጀ ከእርሻ የተገኘ ነው። ለአዳምና ለሄዋን በፈቀደው መሰረት የቀረበ ነው፤ የቃየን ስጦታ። የእህል የጥራጥሬ፣ ወይም የአትክልት ፍራፍሬ።
አቤል ያዘጋጀው ስጦታ ግን፣ የበግ ስጋ ነው። በወቅቱ የስጋ ምግብ ገና ባይፈቀድም፤ ሞክሮ ማየት ክፋት የለውም። የሙከራው ውጤት መልካም ከሆነ፣ ጥሩ ነው። ህይወትን ለማሻሻል ይጠቅም ይሆናል። ምን ችግር አለው?
ምናልባት፣ ለዚህ ይሆናል፤ የአቤል ስጦታ ትኩረትንና ይሁንታን ያገኘው። በእርግጥ፤ “መልካም ነው፤ ድንቅ ነው”አልተባለለትም። የተለየ የቡራኬና የምርቃት ሽልማትም አልተሰጠውም። ነገር ግን አልተወቀሰም፤ ጥፋት ሰርተሀል አልተባለም። “ያልተለመደ ነገር ሞክረሃል፤ ወግ ልማድ ጥሰሃል። ያልተፈቀደ ነገር ፈፅመሃል፤ ከምክር አፈንግጠሀል፤ አዲስ ነገር መሞከር የለብህም” አልተባለም።
“ባይፈቀድም፤ አልተከለከለም” በሚል አይደለም ከወቀሳ ያመለጠው፤ የይሁንታ ትኩረት ያገኘው። መልካም ነገር ለመስራት በመሞከር እንጂ። “መልካም ነው” የሚል ምላሽ ግን አላገኘም፤ ሙከራው ገና ሙሉ ለሙሉ የተሳካ አይመስልም። ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ገና አዋጪ ለመሆን አልደረሰም። ምናልባት እሳት ስላልተጠቀመ ይሆናል። መልካም ነገር ለመስራት ሞከሩ ግን፣ ጥሩ ነው። ለጊዜው ሙከራው ውጤታማ ባይሆንለትም። አሳዛኙ ነገር፤ ሙከራውን ወደ ስኬት የማድረስ እድል አላገኘም። የመጀመሪያው የክፋት ተጎጂ ሆኗል።
ከ1500 ዓመታት በኋላ ኖህ የእንስሳት መስዋዕት ሲያቀርብ ግን፤ እሳት ተጠቅሟል። “እግዚሄርም፣ መልካም መዓዛውን አሸተተ” በማለት ነገሩ በጣም ስኬታማ፣ እጅግ ጥሩ እንደሆነ ትረካው ይገልፃል። ከዚያም ኖህንና ቤተሰቦቹን ይባርካል። ይህም ብቻ አይደለም፤ ከእንግዲህ፤ የስጋ ምግብ እንዲመገቡ ይመክራል። ሰዎች፣ እሳት ማንደድ ከቻሉና ምግብ ማብሰል ከለመዱ፣… የስጋ ምግብ በአግባቡ አዘጋጅተው መብላት ይችላሉ።
በአጭሩ ሰዎች ስጋ እንዲበሉ፣ ፍቃድ ወይም ምክር የተሰጣቸው፤ እሳት ከመጠቀማቸው ጋር የተያይዞ ይመስላል። ምግብ ማብሰል ወይም መጥበስ ካልቻላችሁ ግን፣ ለጊዜው የስጋ ምግብ ቢቀርባችሁ ይሻላል እንደማለት ነው ነገሩ። እሳት ካልተገኘ፣ ቢያንስ ቢያንስ አዋዜና ሚጥሚጣ፣ ሰናፍጭና ሎሚ ያስፈልጋል። የሚያስፈልጉ ነገሮች እስኪሟሉ ድረስ ግን ስጋ ብሉ የሚል ምክር ጥሩ ነው? አይደለም።
ልክ እንደዚያው ይመስላል የጥንቱ ትረካ። ለጊዜው፣ በአዳምና በሄዋን፣ በቃየንና በአቤል ዘመን፣ ስጋ፤ በምግብ ዝርዝር ውስጥ አልተካተተም ነበር። ወይም አልተለመደም፤ አልተፈቀደም ነበር። ባይከለከልም፤ አትሞክሩ ባይባልም። ያው፤ አንዳንድ ነገሮች፣ የተለመዱ ባይሆኑም፣ “ሜኑ” ውስጥ እንዲገቡ ለጊዜው ሁኔታው ባይፈቀድም፤ መጥፎ ናቸው ማለት አይደለም።
የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማሟላት ይቻላል። ጊዜና ትዕግስት ብቻ ሳይሆን አስተዋይነትና ጥረት ከተጨመረበት ቀስ በቀስ ይሳካል። የህይወንት ጣዕም የሚያሳምሩ፤ ስብዕናን የሚገነቡ አዳዲስ መልካም ነገሮች ይፈጠራሉ። ያልተለመዱ ነገሮች፣ በጥረትና በጥበብ፣ ለመልካም ውጤት ይበቃሉ፤ እየተለመዱ የአዳሜ ባህል ይሆናሉ።
በአጭሩ፣ በበጎ አላማ፣ አዳዲስ ያልተለመዱ ነገሮችን፣ በጥንቃቄ በትንሽ በትንሽ ለመሞከር ማሰብ ጥሩ እንጂ መጥፎ አይደለም-ጉዳት እስከሌለው ድረስ።
በወላጆች ዘንድ ወይም በቀድሞ ትውልድ የተጀመሩ፣ የተሞከሩ፣ የተለመዱ ነገሮችን ማስተዋል፣ ማወቅና ማክበር ተገቢ ነው። ነገር ግን፣ ያልተለመዱ አዳዲስ ነገሮችን እየመረጥን፤ ጠቃሚ የሆኑትን እየለየን መሞከርም ያስፈልጋል። አለበለዚያ፣ ህይወትን የማሻሻል ተስፋዎችን አጨልመን፤ የስልጣኔ እድሎችን ዘጋግተን ቆላልፈን እንደነዝዛለን። በተቃራኒው፤ ህይወትን ለማለምለም የሚጠቅሙ አዳዲስ በሮችን መክፈት አለብን።
በሌላ በኩል ግን፤ ነባር ስህተቶችን ለማስቀረት፣ የተለመዱ የጥፋት አይነቶችን ለመከላከል መትጋት አለብን። ጎን ለጎንም፣ አዳዲስ የጥፋት ቀዳዳዎች እንዳይፈጠሩ መጠንቀቅ፤ የኑሮ መንገዶች እንዳይጣመሙ ዘዴ ማበጀት ያስፈልጋል።
ካልሆነ ግን፣ ኑሮን ያበለፅጋሉ ብለን የምንሰራቸው ነገሮች መጥፊያችንን የሚያፋጥኑ መሳሪያዎች ይሆናሉ። እንደ ቃየን ታሪክ፤ መጨረሻችን፣ አሳዛኝ የውርደትና የጥፋት ጨለማ የታሪክ መዝጊያ ይሆናል።
ከስርዓት አልበኝነት ጋር መላመድ፤ ጥንት እና ዛሬ!
በቃየን ዘመን የመጡ አዳዲስ ፈጠራዎች ብዙ ናቸው። ድንቅ ናቸው። ቃየን የመጀመሪያውን ከተማ ገንብቷል። የልጅ ልጆቹም ቀላል ሰዎች አይደሉም። ድንኳን የፈጠሩና የከብት እርባታን የመረጡም አሉ-ከእርሻ በተጨማሪ ማለት ነው። ምን ይሄ ብቻ! የብረትና የነሀስ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ፈልስፈዋል- የቃየን ዘመን ጥበበኞች። ብዙ ዓይነት የብረታ ብረት መሳሪያዎችን አሳምረው የሚሰሩ ፈርቀዳጅ ጥበበኞችም ታይተዋል። ይህም ብቻ አይደለም። የበገና የዋሽንት ፈጣሪዎች፤ እንዲሁም የሙዚቃ ባለሞያዎችም፤ በያኔው ዘመን፣ የኪነጥበብ ውበትን አበርክተዋል። እነዚህ ሁሉ ጥበቦችን ለሰው ልጅ ሁሉ ያበረከቱት፤ የቃየን የልጅ ልጆች ናቸው-የላሜህ ልጆች።
ግን ምን ዋጋ አለው? ህግና ስርዓት በሌለበት ዘመን፣ የከተማ ኑሮ ብዙም አይሰነብትም። ለዚያውም፤ በብረታ ብረትና በነሐስ ቴክኖሎጂ፤ ጦር እና ጎራዴ በርክቷል።
ህግ የማይታወቅበት ስርዓት አልባ ዘመን ውስጥ፤ ጥበበኛ ሰዎች የሰሩት ነገር ሁሉ፣ መጥፊያቸው ሆነ። መጠፋፋት ተትረፈረፈ። እርስ በእርስ መገዳደል የጦዘበት ዘመን ላይ፤ ማን በሕይወት ይተርፋል? የቃየን የልጅ ልጆች ታሪክ፣ በጥድፊያ ተቀጣጥሎና ደምቆ፤ በጥድፊያ ከሰል አመድ ሆኖ ቀረ። በቃየን የተጀመረው የሰው ልጅ ታሪክ፣ ሊቀጥል አልቻለም። ወደ መጥፊያው ተጣደፈ። የጥፋት ሩጫው ፈጠነ። ታሪካቸው፤ በላሜነህ ዘመን፣ ከሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ተነቅሎ እስከ ወዲያኛው ጠፋ።
በላሜህ ዘመን፣ እስከጫፍ ድረስ የጦዘው የጥፋት ሩጫ፣ ሀ ተብሎ የተጀመረው በቃየን ነው-የመጀመሪያውን ክፉ የግድያ ጥቃት በመፈፀሙ። በወቅቱ ህግ ስላልነበረ ቃየን የዳኝነት ቅጣት አልተፈረደበትም።
ነገር ግን የክፉ ተግባር መዘዞች ብዙ ናቸው። ህግ ቢኖር ይሻል ነበር። ችግሩ፣ ህግ በሌለበት ስርዓት አልባ ዘመን፤ የህግ ቅጣት አይኖርም። ደግሞም አልተቀጣም። ነገር ግን የህግ ቅጣት የማይኖረው ለቃየን ብቻ አይደለም።
ሌሎች ሰዎች ላይም የህግ ቅጣት የለም። ይሄ ምን ማለት እንደሆነ አስቡት። ቃየን እራሱ ገብቶታል። ለግድያና ለበቀል አዙሪት፤ አገሬው ሁሉ ወለል ብሎ እንደተከፈተ ገብቶታል።
የሲዖል በሮችን የሚበረግድ የመጀመሪያው ክፉ ተግባር እንደፈጸመ ቃየን ታውቆታል። የሰውን ሕይወት በጥላቻና በግፍ ሲያጠፋ፣ የራሱንም ህልውና አዋርዷል። ሌሎች ሰዎች እንደ አውሬ ቢቆጥሩትና ለአደን እንደወጡ ታጣቂዎች ቢሆኑበት፣ ሊገድሉት ቢያሳድዱት፣ ምንም ማለት ይችላል? በራሱ መሥፈሪያ ቢሠፍሩበት፤ ምን ሊል ይችላል? የአፀፋ በቀል መመለስ?
የሰውን ህይወት አጥፍቶ፤ እንደቀድሞ በሰላም መኖር አይችልም። ከህሊና (ወይም ከፈጣሪ መንፈስ) የመሸሽ እዳ አለበት። የቱንም ያህል ህሊናው ቢዶለዱም፣ ከጭንቀት ይገላገላል ማለት አይደለም። ከጭንቀት ቢገላገል እንኳ፤ የአዕምሮ ጤንነቱን ያጣል እንጂ አይመቸውም።
ግን የህሊና እዳ ብቻ አይደለም ፍዳው። የህግ ቅጣት ባይኖርበትም፤ በዚያ ምትክ የበቀል ጥቃት ይመጣበታል። ከመኖሪያ አካባቢው መልቀቅና መኮብለል ይኖርበታል። ኮብልሎም በሰላም አይኖርም። የሰውን ህይወት ማጥፋት የሚችለው፤ ቃየን ብቻ አይደለም። ቃየን እንዲህ ይላል ለእግዚሄር።
“ከፊትህም እሸሸጋለሁ። በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች እሆናለሁ። የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል” አለ ቃየን።
እና ምን የሚል መልስ አገኘ?
“አይ ማንም አይገድልህም” የሚል ምላሽ አላገኘም። “ግድያ ክልክል ነው” የሚል ህግ በአንድ ጀንበር አልታወጀለትም። ቃየን፣ በክፉ ተግባሩ ሳቢያ፤ የሚመጣበትን የበቀል መዘዝ ማስቀረት አይችልም።
ያው፤ ቃየንን የገደለም፣ እንደዚያው የበቀል ኢላማ መሆኑ አይቀርም።
መጥፎነቱ ደግሞ፤ የበቀል ጥቃት እንደ ህግ ቅጣት አይደለም። ልክና ወሰን የለውም። ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ጥቃትና፣ አፀፋ፣ በቀልና፣ እጥፍ የአፀፋ በቀል፤ እየተመላለሰ ይባባሳል። ለዚህም ነው፤ “ማንም አይገድልህም” የሚል መልስ ያላገኘው።
እናስ?
የበቀል አዙሪት፣ አይቀሬ መዘዝ ነው ህግ በሌለበት ዘመን።
“ማንም ቃየንን ቢገድል ሰባት እጥፍ የበቀል ጥቃት ይቀበላል” የሚል ነበር ቃየን ያገኘው መልስ።
በቃየን የተጀመረው የግድያ ክፋት ተለመደ። ከዚያስ ደግሞ፣
ሰባት እጥፍ በቀል ተለመደ ማለት ነው። ህግ ከሌለ፣ ሌላ ምን ዘዴ አለ? አንዱ ሰባት እጥፍ በቀል ይፈፅማል። ሌላውም በአፀፋው ሰባት እጥፍ ይመልሳል። መተላለቅ ነው። ምን ይሄ ብቻ።
ከትውልድ ትውልድ፤ ግድያና በቀል እየከፋ፣ አዙሪቱ ይጦዛል።
ቃየን የአዳምና የሄዋን ልጅ አይደል? ሁለተኛ ትውልድ ማለት ነው። ላሜህ ከቃየን የልጅ ልጆች በኋላ ነው የሚመጣው። ያኔ፣ በሰባተኛው ትውልድ ላይ፤ በላሜህ ዘመን ላይ ነገር አለሙ ሁሉ ከጣያ በላይ ይተኮሳል። ተስፋ የሌለው የቅዠት ጫፍ ላይ ይደርሳል።
ላሜህ ለሁለት ሚስቶቹ እንዲህ ብሎ ይፎክራል።
“ዓዳ እና ፂላ ሆይ፣ ስሙኝ”
“የላሜህ ሚስቶች ሆይ፣ አድምጡኝ”
“አንድ ሰው ቢያቆስለኝ፣ የሆነ ልጅ ቢጎዳኝ፣ ገደልኩት
ሰባት እጥፍ ነው የቃየን በቀል
የላሜህ ደግሞ ሰባ ሰባት እጥፍ!
እውነትም፣ በቀል መልክና ልክ የለውም። ላሜህ ነገሩን ሲያጦዘው፤ ሌላውም ሰው ከማዶ ሆኖ የዚያኑ ያህል መፎከር ይጀምራል። በዚህ ሁኔታ በህይወት የሚተርፍ ሰው ይኖራል? ተጠፋፍተው ያልቃሉ እንጂ።
ታሪክ ለማውራት በህይወት የሚተርፍ ባይገኝ ነው፤ የቃየን የትውልድ ታሪክ፤ በላሜህ ፉከራ የተቀጨው። ከዚያ በኋላ ምንም የተፃፈ የቃየን ወይም የላሜህ ታሪክ የለም። ወሬ ነጋሪ አልተረፈም።
ሰባት እጥፍ አፀፋ፤ ሰባ ሰባት እጥፍ በቀል እያሉ እየተባባሉ፤ እንዴት ይተርፋሉ? ሌላ ምን ይጠበቃል? ያኔ ህግ አልነበረም።
ሕግና ስርዓት አይታወቅም ነበር።
ዛሬ፤ ግን የመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ የምንገባው፤ ካለማወቅ አይደለም። ሕግና ስርዓት አይታወቅም ነበር ብለን ማሳበብ አንችልም። ህግና ስርዓት ከቁም ነገር ባለመቁጠር ቸል በማለት፣ ነው የምንተራመሰው። ሕግና ሥርዓት፣ እንደመጫወቻ እንዲሆንልን በመፈለግ፤ ከዚያም ባሻገር ሕግ የተናቀበትና የቀለጠ ስርዓት አልበኝነትን በማስፋፋት ጭምር ነው የምንጠፋፋው።
ከጥንቱ ዘመን ይብሳል የጥፋታችን ክብደት። የጥንቱ ጥፋት፣ ከእውቀት እጦት ነው። የዘመናችን ጥፋት ግን ከእውቀት ጋር በመጣላት ነው።


Read 8455 times