Saturday, 14 May 2022 00:00

22ኛዋ የዓለም ዋንጫና አስደናቂ ታሪኳ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ይህ ፅሁፍ በኢትዮጵያ ለሶስተኛ ጊዜ ታሪካዊ ጉብኝቷን የምታደርገውን 22ኛዋን የፊፋን ዓለም ዋንጫና አስደናቂ ታሪኳን ያስተዋውቃል፤ መልካም ንባብ፡፡
በትሬዘጌት አጃቢነት ኢትዮጵያ ውስጥ ለ2 ቀናት   ትቆያለች
ኳታር በምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ለአሸናፊው የምትሸለመው ዋንጫ ለጉብኝትና ከእግር ኳስ አድናቂዎች ጋር ለመገናኘት ወደ ኢትዮጵያ እንደምትመጣ ታውቋል። የኮካ-ኮላ ኩባንያ ከፊፋ ጋር በመተባበር በሚያዘጋጁት ልዩ መርሃግብር  የዓለም ዋንጫዋ አዲስ አበባ የምትገባው ግንቦት 16 ላይ ነው፡፡ 22ኛው የዓለም ዋንጫ ከመንፈቅ በኋላ በኳታር የሚካሄድ ሲሆን ከዚያ በፊት የፊፋ የዓለም ዋንጫ በዓለም ዙርያ ለጉብኝት ከምታካልላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች፡፡ የዓለም ዋንጫውን በማጀብ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው  በ1998 እኤአ ላይ ከፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ጋር ሊያሸንፋት የበቃው ታዋቂው የቀድሞ ተጨዋች ዴቪድ ሰርጂዮ ትሬዘጌት ታጅቦ ይመጣል። የጉብኝት መርሃግብሩን ያዘጋጁት እንዳስታወቁት የዓለም ዋንጫዋ ከትሬዘጌት ጋር  ግንቦት 16 እና 17 ላይ በአዲስ አበባ በሚኖራት ቆይታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎችና አድናቂዎች ከዋንጫዋና ከታዋቂው ተጨዋች ጋር  በቅርበት የሚገናኙበትን እድል ይፈጥራል።
በኮፓ ኮካ-ኮላ ውድድሮች የኢትዮጵያን የእግር ኳስ ዕድገት በሰፊው የሚደግፈው እንዳስታወቀው  የዓለም ዋንጫዋ ጉብኝት መሪ ሃሳብ “ቢሊቪንግ ኢዝ ማጂክ” ነው። የዓለም ዋንጫዋ ለተመሳሳይ  ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ   ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ዘንድሮ በአፍሪካ የምታደርገውን ጉብኝት የመጀመሪያ መዳረሻዋ በማድረግ ነው። ‹‹እንከን የለሽ የዋንጫ ጉብኝት ለማድረግ ከተለያዩ የሀገሪቱ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን እየሰራን ነው። የሁለት ቀናት የዋንጫ ጉብኝቱ የሁሉም አይን ኢትዮጵያ ላይ ስለሚሆን አወንታዊ ገፅታችንን ለአለም የምናሳይበት ግሩም አጋጣሚ ነው። ስለዚህም  ሁላችሁም የዚህ ታሪካዊ ወቅት ተካፋይ እንድትሆኑ እንጋብዛለን፡፡››  በማለት ኮካ-ኮላ ቤቨሬጅስ አፍሪካ - ኢትዮጵያ  በልዩ መግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን የዋንጫ ጉብኝት ለማሳመር  በወጣው መርሃ ግብር መሰረት ከ12 ሺ በላይ የስፖርቱ አድናቂዎች እንደሚሳተፉ ተጠብቋል፡፡ ከ200 በላይ በሆኑ አገሮች እና ግዛቶች የሚሸጡ ምርቶች ያሉት የኮካ-ኮላ ኩባንያ ከ1978 ጀምሮ የፊፋ የዓለም ዋንጫን በይፋ ስፖንሰር ሲያደርግ ቆይቷል። ከ1950 ጀምሮ በእያንዳንዱ የፊፋ የዓለም ዋንጫ በየስታዲየሞቹ  ማስታወቂያ የነበረውና በሁሉም ደረጃዎች ለእግር ኳስ ሁለገብ ድጋፍ በመስጠት ከዓለማችን ታላላቅ ኩባንያዎች የሚስተካከለው የለም፡፡ ከእያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ በፊት  በሚካሄደው የፊፋ የአለም ዋንጫ ጉብኝት ኮካ ኮላ እና ፊፋ ተባብረው ዓለምን ሲዞሩ አምስተኛ የዓለም ዋንጫቸው ነው፡፡።
የቀድሞዋ ጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ
ብራዚል– 1958, 1962, 1970
ኡራጋይ – 1930, 1950
ጣሊያን– 1934, 1938
ጀርመን – 1954
እንግሊዝ– 1966
የዓለም ዋንጫ በፊፋ ዋና አዘጋጅነት በ1930 እ.ኤ.አ ላይ በደቡብ አሜሪካዋ ኡራጋይ እንደተጀመረ ይታወቃል፡፡ ኛው የዓለም ዋንጫ ከመካሄዱ ሁለት ዓመት በፊት የውድድሩ ደንብ ሲቀረፅ ለአሸናፊ ለየት ያለ የክብር ዋንጫ እንዲሸለምም ውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡ ዋንጫዋን በጥሩ ዲዛይን እንዲሰራ  ታሪካዊው ኃላፊነት የወሰደው ፈረንሳዊው ቀራፂ አቤል ላፍሌዌር ነበር፡፡ ፈረንሳዊው የስነጥበብ ባለሙያ  የተሰጠውን የታሪክ አደራ ባግባቡ በመወጣት አስደናቂዋን ዋንጫ ሰርቶ አቅርቧታል፡፡ በገፅታዋም የግሪኳን የድል ጣኦት ‹‹ናይኪ›› እንድትወክል ቪክትሪ በሚል ስያሜም እንድትወከል ከጅምሩ አድርጎታል፡፡ ከግዜ በኋላ በ1946 ዋንጫዋ ድል የሚለውን ስያሜ ቀይራለች፡፡ ለውድድሩ መመስረት ምክንያት በሆኑትና ለረጅም ጊዜያት የፊፋ ፕሬዚዳንት ለነበሩት ፈረንሳዊው ጁሊየስ ሪሜት መታሰቢያ ሆና ‹የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ›  ተብላ እንድትታወቅ ሆኗል፡፡
የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ከ1ኛው የዓለም ዋንጫ አንስቶ ለአሸናፊዎች መሸለም ከጀመረች በኋላ በየስታድዬሙ ካስተናገደቻቸው አስደናቂ የእግር ኳስ ገድሎች ባሻገር የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶች ተፈራርቀውባታል፡፡ 1ኛው የዓለም ዋንጫ ኡራጓይ ላይ በ1930 እ.ኤ.አ ላይ ፤ 2ኛው የዓለም ዋንጫ በ1934 እአኤ ጣሊያን ላይ እንዲሁም 3ኛው የዓለም ዋንጫ  በ1938 እ.ኤ.አ በፈረንሳይ ከተካሄዱ በኋላ 2ኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ፡፡  የፊፋ ም/ፕሬዚዳንት የነበሩት ጣሊያናዊው ዶ/ር አሪኖ ባራሲ  የዓለም ዋንጫው በጦርነቱ ምክንያት በተቋረጠባቸው 12 ዓመታት የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫን በአደራ እንዲያስቀምጡ ሃላፊነት ነበራቸው። ጣልያናዊው የዓለም ዋንጫዋን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወራሪ ኃይሎች ዘረፋ ለመጠበቅ ሲሉ በጫማ ሳጥን ውስጥ መደበቅ ነበረባቸው። በአንድ አጋጣሚ በቤታቸው ፋሽቶች ፍተሻ ሲያደርጉም አልጋቸው ስር በመደበቃቸውም ከዘረፋ አትርፈዋታል፡፡
የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ከሜዳ ውጭ የነበራት ታሪክ ግን በዚህ አላበቃም፡፡ በ1966 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ የዓለም ዋንጫን አዘጋጅታ እዚያው አገር በአሸናፊነት ባስቀረችው እንግሊዝም ብዙዎችን ያስደነገጠና ያስደነቀ ታሪክም ገጥሟታል፡፡ የእንግሊዝን የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ እንዲያሟሙቅ ተብሎ በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ ለእይታ ከቀረበችበት የኤግዚቢሽን ማዕከል በመጥፋቷ ነበር፡፡  የዋንጫዋ መጥፋትና መሰረቅ ከታወቀ በኋላ የዓለም ዋንጫውን ተዓማኒነት አደጋ ውስጥ እየጣለና ተሳታፊ አገራትን አለመረጋጋት ውስጥ እየከተተ ቆየ  ፡፡ መላው ዓለም ባልጠበቀው ሁኔታ ግን  የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫለኤግዚቢሽን ቀርባ ከነበረችበት ግዙፍ ህንፃ አካባቢ በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ስር መሬት ውስጥ በጋዜጣ ተጠቅልላ እንደተቀበረች ተገኘች። በደቡብ ለንደን ለሕዝብ እይታ ቀርባ ከነበረችበት ስፍራ የጠፋችው ባልታወቁ ሌቦች ተሰርቃ ነበር፡፡ አንዲት ፒክልስ የምትባል ውሻ ግን ከጌታዋ ጋር ስትንሸራሸር ዛፍ ስር የሚገኘውን መሬት ምሳ የተቀበረችውን ዋንጫ አግኝታለች፡፡ ለእንግሊዝና ለእግር ኳሱ አለም ታላቅ ውለታን ያደረገችው ውሻዋ ፒክልስ በዓለም ዙርያ በአድናቆት ከፍተኛ የዘገባ ሽፋን አግኝታ ነበር፡፡
በ1970 እ.ኤ.አ ላይ በሜክሲኮ  8ኛው የዓለም ዋንጫ ሲካሄድ ብራዚል የዓለም ሻምፒዮናነቱን ለሶስተኛ ጊዜ በማሸነፏ የውድድሩ መስራቾች ባፀደቁት  ሶስት ጊዜ ያሸነፈ ዋንጫውን የግሉ ያደርጋል በሚለው ህግ መሰረት የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ የዘላለም ንብረት አድርጋት ነበር፡፡ ዘጠኝ የዓለም ዋንጫዎች ያሳለፈቸው የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በታላቁ የስፖርት መድረክ ህልውናዋ ያበቃው አሳዛኝ ክስተት ያጋጠመው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ በ1983 እ.ኤ.አ ላይ በብራዚል ዋና ከተማ ሪዩዲጂኔሮ በሚገኘው የፌደሬሽን ፅህፈት ቤት ጥይት በማይበሳው ማሳያ ውስጥ ተቀምጣ ከቆየች በኋላ ዘራፊዎች ማሳያው የተቀመጠበተን እንጨት ሳጥን በመሰርሰር ሰረቋት።  ወሮበሎቹ ሌብነታቸው እንዳይነቃ በማለት የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫን በፍም እሳት አቅለጠው መሸጣቸውም ተዘገበ፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ የዓለም ዋንጫዋን ከተመሳሳይ አደጋ ለመታደግ ወሳኝ ደንብ ያስቀመጠው በዚህ መነሻነት ነው፡፡ ዋናዋን ዋንጫ በማህበሩ ጥብቅ ምስጥር ውስጥ ማስቀመጥ ለአሸናፊው አገር ደግሞ በተመሳሳይ ጥራት የተሰራ ዋንጫን መሸለምን የሚመለከት ነው፡፡ ብራዚል ለሶስት ጊዜ በማሸነፍ  ለዘላለም ማስቀረት የምትችላትን ኦርጅናል የጁሊዬስ ሪሜት ዋንጫ ማጣቷ ያደናገጠው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ መፍትሄውን ያገኘው ከብራዚል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቀረበውን ጥያቄ በመቀበል ነበር፡፡  የጁሊየስ ሩሜት ዋንጫ ምትኳ እንዲሰራ ተደርጎ ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን ዘላለማዊ ንብረት እንዲሆን ተበርክቷል፡፡
የፊፋ የመጀመርያዋ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ በመጠኗ አነስተኛ ነች፡፡ 35 ሴ.ሜ ቁመት ያላት ስትሆን እስከ 3.8 ኪ.ግ. የክብደት መጠን ነበራት። የዋንጫዋ አብዛኛው ክፍል የተቀረፀው በጠራ የብር ማዕድን ነው፡፡ ዙሪያዋ ደግሞ በተወሰነ የወርቅ ለምድ ተለብጧል፡፡ የዋንጫዋ መሰረት በመጀመርያ ከእምነበረድ ተሰርቶ የነበረ ሲሆን ከዚያም ባለ ሰማያዊ ቀለም  በከፊል የከበረ ድንጋይ Lapis Lazuic ከተባለ ማዕድን የተሰራ ነው፡፡ በዋንጫዋ ታችኛው ክፍል ያሉት አራት ጎኖች ዙሪያቸውን በወርቅ የተለበጡ ሲሆን ስፍራው የአሸናፊዎች ዝርዝር እንዲሰፍርበት የተዘጋጀ ነበር፡፡ ዓለም ዋንጫ በጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ሽልማትነት ከ1930-70 እ.ኤ.አ ሲካሄድ በዋንጫዋ ታችኛው ክፍል በሚገኘው በዚሁ የወርቅ ለምድ ላይ  ሻምፒዮን ለመሆን የበቁ ዘጠኝ ሀገራት ተነቅሰውበታል፡፡ ብራዚል በ1958, 1962, 1970፣ ኡራጋይ በ1930, 1950፣ ጣሊያን በ1934, 1938፣ ምዕራብ ጀርመን በ1954 እና እንግሊዝ በ1966 እ.ኤ.አ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫን አሸንፈዋል፡፡
የአሁኗ የፊፋ ዓለም ዋንጫ
ጀርመን – 1974, 1990, 2014
አርጀንቲና – 1978, 1986
ጣሊያን– 1982, 2006
ብራዚል – 1994, 2002
ፈረንሳይ – 1998, 2018
ስፔን – 2010 እኤአ
 በ1970 እ.ኤ.አ ላይ ሜክሲኮ ባዘጋጀችው 9ኛው የዓለም ዋንጫ ብራዚል የዓለም ሻምፒዮናነቱን ለሶስተኛ ጊዜ አሸንፋ  የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ የዘላለም ንብረቷ ብታደርጋትም መሰረቋ ዓለምአቀፉን የእግር ኳስ ማህበር ወደሌላ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አድርጎታል፡፡ 9 ዓለም ዋንጫዎችን ያስተናገደችው የጁሊዬስ ሪሜት ዋንጫን በአሁኗ  የፊፋ የዓለም ዋንጫ ለመቀየር ውሳኔ ተላለፈ፡፡  የዓለም ዋንጫዋን ሽልማት  በመቅረፅ ከ7 ሀገራት የተውጣጡ ታዋቂ ቀራፂዎች  53 የተለያዩ ዲዛይኖች ለውድድር አቀረቡ፡፡ በመጨረሻም የፊፋ ኮንግረስ ባሳለፈው ውሳኔ የጣሊያኑን ቀራፂ ሲልቪዮ ጋዚንጋን የዋንጫ ቅርፅና የስራ ሃሳብ ተቀባይነት አገኘ፡፡ በዚህ መሠረት በ1974 እ.ኤ.አ በተከናወነው 10ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ፊፋ አዲሷንና የአሁኗን የዓለም ዋንጫ ለታላቋ የስፖርት መድረክ ለማቅረብ በቃ። የአሁኗ የፊፋ የዓለም ዋንጫ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ንብረት ሆኖ ለዘላለም እንድትቆይ የተደነገገውም ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ፊፋ በመተዳደሪያ ደንቡ እንደሚያመለክተው ዋንጫዋን ያሸነፈ ብሔራዊ ቡድን ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተሰራችውን ሽልማት ለተወሰኑ የፌሽታ ሰሞናት ጠብቆ እንዲያቆይ ይፈቀድለታል፡፡ ቀነ ገደቡ ሲያበቃ ኦርጅናሌዋን ዋንጫ አስረክቦ በፊፋ የተዘጋጀውን ተመሳሳይ ዋንጫ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡የአሁኗ የዓለም ዋንጫ ሽልማት እንደጁሊዬስ ሪሜት ዋንጫ ብዙ ውጣውረድ ሳይገጥማት ከእነክብሯ ገዝፋ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ዋና መስርያ ቤት ዙሪክ ውስጥ አንጡራ ሃብት ሆና  ትገኛለች።
የአሁኗ የፊፋ ዓለም ዋንጫዋ 36.5 ሴ.ሜ ርዝማኔ ሲኖራት የተሰራችው 6 .175 ኪሎ ግራም ክብደት ከሚመዝን 18 ካራት ንፁህ ወርቅ ነው። የዋንጫዋ የታችኛው ክፍል በከፊል የከበረ ድንጋይ ከሆነው ማልቺይት ከተባለ ማዕድን ተለብጦ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚሁ የዋንጫው ክፍል ላይ እስከ 2018 እኤአ የተከናወኑት  ዓለም ዋንጫዎች  በሻምፒዮናነት ታሪክ የሰሩ አገራት ስም ተፈልፍሎ ሰፍሮበታል። የዓለም ሻምፒዮናዎቹ ዝርዝር የሚፃፍበት ይኸው የዓለም ዋንጫዋ ቦታ እስከ 2030 እ.ኤ.አ ለሚያሸንፉ ብሔራዊ ቡድኖች ቦታ እንዳለው ይገለፃል፡፡
የአሁኗን የፊፋ ዓለም ዋንጫ  ለመጀመሪያ ጊዜ በድል ሊስማት የቻለው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አምበል ፍራንዝ ቤከን ባወር ነበር። በ1974 እ.ኤ.አ በተካሄደው በዚህ ዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ የተደረገው በሆላንድና በአዘጋጇ ምዕራብ ጀርመን መካከል ነበር፡፡ ጀርመንም ይህችኑ ዓለም ለመጀመርያ ጊዜ ያሸነፈች የአውሮፓ አገር ሆናለች፡፡ በ1978 እ.ኤአ ላይ ደግሞ በሞናሞናታል ስታድዬም ቦነስ አይረስ ከተማ ላይ ይህችኑ ዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ተቀዳጅታ የመጀመሪያዋ ደቡብ አሜሪካ ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ጣሊያናዊው ቀራፂ ሲሊቪዮ ጋዚንጋ የሰሯት የአሁኗን የፊፋ ዓለም ዋንጫ  12 ዓለም ዋንጫዎችን በሚያካልለው ታሪኳ በርካታ የዓለማችንን ታላላቅ ከተሞችን በሻምፒዮኖቹ እና በአዘጋጆቹ አገራት አማካኝነት መቀመጫዋ አድርጋለች፡፡ ቦነስ አየረስ፤ ሳንቲያጎ፤ ማድሪድ፤ ሮም፣ ሎስ አንጀለስ፣ ፓሪስ፣ ዮክሃማ፤ በርሊን፤ ጆሃንስበርግና ሪዮዲጄኔሮ ይገኙበታል፡፡ የዓለም ዋንጫ ሽልማት የእግር ኳስ ስፖርትን ዓለም አቀፋዊነትና ታላቅ ውበት ተምሳሌት ለማድረግ እንደሰሯት  ቀርፂዋ ሲልቪዮ ጋዚንጋ ይናገራሉ፡፡ ስለ አንዱ የዓለም ዋንጫ ትዝታቸው ሲናገሩም “ጣሊያናዊ እንደመሆኔ” ስኳድራ አዙራ የተባለውን ብሔራዊ ቡድናችንን እደግፋለሁ። ስለዚህም በ1982 እ.ኤ. በሳንቲያጎ በርናባኦ ስታድዬም ማድሪድ ከተማ ውስጥ የጣሊያን ቡድን ዋንጫውን በማንሳት የፈፀመው ገድል ምንጊዜም አልዘነጋውም፡፡ ግብ ጠባቂው ዲኖ ዞፍ በጣሊያናዊ የተሠራቸውን ይህችን ዋንጫ ሲያነሳ በጣም ኮርቻለሁ። ዓለም ዋንጫዋ በገጽታዋ ጣሊያንን ብታንፀባርቅ አይደንቅም” ብለው ነበር፡፡
 ከ1974 እ.ኤ.አ ወዲህ የአሁኗን የፊፋ የዓለም ዋንጫን ሶስት ጊዜ በመውሰድ ግንባር ቀደም የሆነችው ጀርመን (በ1974 ፤ በ1990ና በ2016 እ.ኤ.አ) ላይ በማሸነፍ ነው፡፡ ሁለት እኩል ያሸነፉት ደግሞ ብራዚል (በ1994 እና በ2002 እ.ኤ.አ) ፤ (ጣሊያን በ1982 እና በ2006 እ.ኤ.አ) እና አርጀንቲና (በ1978 እና በ1986 እ.ኤ.አ) ላይ እንዲሁም ፈረንሳይ በ1998ና በ2018 እኤአ ሲሆን ስፔን በ2010 እ.ኤ.አ የዓለም ዋንጫዋን  አንዴ በሻምፒዮናነት አንስተዋታል፡፡
የዓለም ዋንጫዋ ዋጋና የመስተንግዶዋ ገቢ
ሲልቪዮ ጋዚንጋ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩት ከ6ዓመት በፊት ነው። የዓለም ዋንጫዋን ከሰሯት በኋላ  እንደ ልጄ የምቆጥራት የስነ ጥበብ ውጤት ናት ብለው ነበር፡፡ ከዓለም ዋንጫዋ ዲዛይን በኋላ የአውሮፓ ማህበረሰብ ዋንጫን በ1972፤ የአውሮፓ ሱፕር ካፕ ዋንጫን በ1973 እንድሁም የቤዝቦል የዓለም ዋንጫን በ2001 እኤአ ላይ በመስራት ከበሬታን አትርፈዋል፡፡ ሲልቪዮ ጋዚንጋ የአሁኗን የፊፋ ዓለም ዋንጫ በ1971 እ.ኤ.አ ላይ ዲዛይን አድርገው እንደጨረሷት የዋንጫዋ ዋጋ እስከ 50 ሺህ ዶላር ይገመት ነበር፡፡ ከ4 ዓመት በፊት ግን ታዋቂው የአሜሪካ ጋዜጣ ዩኤስኤቱዴይ ከ4 ዓመት በፊት በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ በሰራው ጥናታዊ ዘገባ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ ተምኗል።
በነገራችን ላይ የዓለም ዋንጫን የሚያህል ታላቅ የስፖርት መድረክ በማዘጋጀት እድል ያገኙ አገራት በአማካይ እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸው የዋንጫዋን ውድ ስጦታነት ያመላክታል፡፡ በ2002 እ.ኤ.አ ላይ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ 17ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ 9 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2006 እ.ኤ.አ ላይ ጀርመን 18ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ 12 ቢሊዮን ዶላር፤ በ2010 እ.ኤ.አ ላይ ደቡብ አፍሪካ 19ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ 5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2014 እ.ኤ.አ ብራዚል 20ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ እስከ 14 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል፡፡ የዓለም ዋንጫን ለ32 አገራት አዘጋጅቶ ለአሸናፊው የሚሸልም አገር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ 30 ቢሊየን ዶላር እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል፡፡ ዓለም ዋንጫውን በሚያዘጋጅበት 4 ዓመታት ውስጥ ደግሞ እስከ 4 ሚሊየን ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል።
የዓለም ዋንጫዋ ዋጋ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር መተመኑን የሚስተካከል ሌላ የስፖርት ሽልማት የለም። ከእግር ኳሱ ዓለም ውድ ዋጋ ያለው ሽልማት ተብሎ ቢጠቀስ የዓለማችን አንጋፋው የክለቦች ውድድር የሆነው የእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ ነው፡፡ ለ5 የተለያዩ ጊዜያት የተቀረፀው ይሄ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ እስከ 420 ሺ ፓውንድ ያወጣል፡፡ የዓለማችን ቁጥር 1 የክለቦች ውድድር የሆነው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ከ1992 እ.ኤ.አ አንስቶ ለሻምፒዮኖቹ የሚበረከት ነው፡፡ ምንም እንኳን በቴሌቪዥን ስርጭት መብት፣ በስታድየም ገቢ፣ በስፖንሰርሺፕ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ቢያገኝም ዋንጫው ግን ያን ያህል አያወጣም፡፡ በብር ተለብጦ የተሰራው የእንግሊዝ ፕሮሚር ሊግ ዋንጫ ማልቻለት የተባለ የከበረ ማዕድን መሰረት የሆነለት ነው። 104 ሴ.ሜትሮች የሚረዝምና 25 ኪ.ግ የሚመዝን ነው፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የተለበጠበት ብር በዋጋ ቢተመን ከ10 ሺ ዶላር አይበልጥም፡፡ በ1967 እ.ኤ.አ ላይ የተሰራው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ 71 ሴ.ሜትር የሚረዝምና 7.5 ኪ.ግ ክብደት ያለው ሲሆን፤ በምንም አይነት ዋጋ አልተተመነም፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ደንብ መሰረት ማንም ቀርፆ የመሸጥ መብት የለውም፡፡


Read 9207 times