Saturday, 14 May 2022 00:00

ከሞት በኋላ ህይወት ቢኖርስ?

Written by  ልጅ አቤኑ ( አቤንኤዘር ጀምበሩ)
Rate this item
(2 votes)

ማናችንም ብንሆን እርግጠኛ ሆነን ከሞት በኋላ ስላለው ህይወት መግለፅ ወይም ከሞት በኋላ በእርግጠኝነት ምን ሊፈጠር እንደሚችል አናውቅም። ከመላምቶችና በእምነታችን ከተቀበልነው አስተምህሮ ባሻገር ሄደን ያየነው፣ ነክተን ያረጋገጥነው፤ አሽትተን የተገነዘብነው፤ ቀምሰን ያጣጣምነው ነገር የለም፡፡ ምድራዊ ቆይታችን በእድሜ ያልታጠረ ጊዜያዊ ባይሆንስ? ከሞት በኋላ ህይወት ቢኖርስ? ነፍሳችን ከስጋችን ተሰናብታ ሞታችን ከተረጋገጠ በኋላስ አንጎላችን ምን ያህል ደቂቃዎች ንቁ ሆኖ ሊቆይ ይችላል፡፡ ወዳጃችን፤ ከሙት አፀደ ሥጋ ጋር ይነጋገሩ ይሆን? በሰውነትዎ የዞምቢ የዘረ መል ቅንጣት ይኖር ይሆን? ዓለም አቀፋዊ ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ የሰው ልጆች ህይወታቸው ካለፈ በኋላ፣ በአካላቸው ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሴሎች ለተወሰነ ሰዓት ንቁ (active) ሆነው ይቆያሉ። ከዛ ባለፈ አንዳንዴ ሴሎች እስከተወሰነ ሰዓት ቁጥራቸው ሊጨምር ይችላል። እነዚህን ነው የዞምቢ የዘረ መል ቅንጣት የምንላቸው።   
መቼም እርስዎ ወዳጃችን እራስዎ ህይወትዎ አልፎ ባያውቅም የሚወዱት ወዳጅ ዘመድዎ በህይወት ተለይቶት አልቅሰው ቀብረዋል፡፡ ድንገተኛ የሞት አደጋን ሰምተው መኖር ትርጉም አልባ ሆኖብዎትም ሊሆንም ይችላል፡፡ በመቃብር ቦታ እየተዘዋወሩ የሟቾችን የትውልድና የሞት ቀን እያዩ #ይሄ እድሜ ጠግቦ ነው የሞተው፤ ይሄ መንገዱን ሳይጀምር ነው ያለፈው; ብለውም ይሆናል፡፡ አንዳንዶች በሞት ላይ ባላቸው ፍራቻ ወደ መቃብር ቦታ ለቀብር፣ ወደ ለቅሶ ቤት ለሀዘንም መሄድ የሚፈሩ ሰዎች አሉ፡፡ ሞትን አልፈራም ባይ ጀግናም የመሞቻው ቀን ስትቀርብ ሲረበሽ ተመልክተውም ይሆናል። አንዳንዶች በእድሜ አመሻሽ ላይ ከሞት ጋር ድብብቆሽ የገቡ ሲመስላቸውና ሽሽት ሲገቡም አስተውለዋል፡፡ ሞት፣ የሁሉም ፍጥረታት ፍፃሜ፤ የሰው ልጆች የህይወት ማሳረጊያ ደውል፡፡
እ.ኤ.አ በ2013 የተደረገው ጥናት እንደገለፀው፤ 72% አሜሪካውያን ከሞት በኋላ ህይወት እንዳለ ያምናሉ። እንደ ፕሮፌሰር ሮበርት ላንዛ ያሉ ምሁራን ደግሞ ሞት አሉታዊ የሆነ ምናባዊ ስዕል እንጂ ያለ ነገር አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ሞት እንዲህ ነው ተብሎ ትርጉም ሊሰጠው የማይቻል፣ ድንበር የለሽ ክስተት ነው፡፡ ሲያጠቃልሉት፤ የሌለ ምናባዊ ገፅታ አድርገው ያስቀምጡታል፡፡
በምድር ላይ በሚኖሩባት የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ እንዳሉ ያስቡ፡፡ ወዳጃችን የመጨረሻዎቹ የቅዠት ወቅቶች ላይ ነዎት፤ ከዚያ በኋላስ ወደ ህይወት ይመለሱ ይሆን፡፡ ወዳጅ ዘመድ ከበዎት “ደክመዋል” ብሎ የእጅና የእግርዎን ሙቀት እየለካ ነው። የመገነዣ ፋሻና ጋቢ እያዘጋጁልዎት ነው፤ ለንፍሮ የሚሆን ስንዴና ሽንብራም ተገዝቷል፤ የሬሳ ሳጥን የሚያመጡትም ወዳጆቾት በቅርብ አሉ፡፡ የእድሩ ሊቀ መንበርም  ከአካባቢው እንዳይጠፉ ጥቆማ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የትኛዋ ነጥብ ላይ ነው መኖር አቁመው የሞትን መንገድ የሚጀምሩት?
የመጀመሪያው ማስታወስ ያለብዎት ወዳጃችን ሞት ሂደት እንጂ ፍፁማዊ አይደለም፡፡ ታዲያ እንዲህ ስንልዎት ግር እንዳይሰኙ፡፡ 95% ለሚሆኑት ሰዎች ሂደቱ የሚጀምረው የልብ ምት ጥው ጥው ማለት ሲያቆም ነው፡፡ ከዚያ በኋላ መተንፈስ ያቆማሉ፤ ጡንቻዎች መኮማተር ይጀምራሉ፣ አጥንትዎ መተጣጠፍ ያቆማል፡፡ ይሄ አንጎልዎት ሙሉ ለሙሉ ከመዘጋቱ ጥቂት ጊዜያት ወይም ሰዓታት በፊት የሚሆን ክስተት ነው፡፡ አሁንም በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ በሌላኛው ጠርዝ ላይ አይደሉም ወዳጄ፡፡ አዌር የተባለ ተመራማሪ፣ በልብ ምት መቆምና የሞት ጠርዝ ላይ ስላሉ ሁኔታዎች በሚጠቁመው ጥናቱ፣ በአንድ ሺ ሰዎች ላይ ጥናቱን አድርጓል፡፡ በዚህ ጥናት የተካተቱት ሰዎች አብዛኞቹ ሞተው ተነስተዋል የተባሉና የልብ ምታቸው ከቆመበት የተመለሱ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ተጠያቂዎች እንደገለፁት፤ የመሞታቸውን ቅፅበት ያስታውሱታል፡፡ ነብሳቸው አለፈች በተባለችበት ቅፅበት ድምፅ እየሰሙ በጆሯቸውም ያዳምጡ ነበር፡፡ ነገር ግን ልባቸው ደሞ አይረጭም፣ አይተነፍሱም። ሰዎች በአንገታቸው ግራ ያለን የደም ቱቦ እንቅስቃሴ መቆም እየገለፁ ሞታቸውን ሲያውጁም ሁኔታውን ይከታተሉ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ከሞት ወደ ህይወት እስኪመለሱ የነበረውን ቅፅበት በትክክል ገልፀዋል፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ? አንጎልዎ ነፍስዎ ከወጣ ወይም የልብ ምትዎና ትንፋሽዎ ከቆመ በኋላ ለመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች በጣም ንቁ ሆኖ ይቆያል። ያ ማለት ዶክተርዎ ወይም በቤት ከሆኑ አስታማሚ ዘመድዎ የመሞትዎን አዋጅ በበድን ሰዉነትዎ ፊት ሲያውጁ በጆሮዎ ይሰሙታል ማለት ነው። 9% የሚሆኑ ሞት ጠርዝ ደርሰው የተመለሱ የጥናቱ መላሾች እንደገለፁት፤ ሞታቸው ሲታወጅ አልጋ ላይ ከተጋደመው በድናቸው በላይ ነፍሳቸው ወደ ላይ ከፍ ብላ ስትዋኝ ተመልክተዋል፡፡ ከፍ ብላ የምትዋኘው ነፍሳቸው በማትታይ ገመድ ከበድናቸው ጋር በእጅ እንደተያዘ ፊኛ ስትውለበለብ ተመልክተዋል፡፡
በህልፈትዎ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የሚሆነውን ነገር እየሰሙ እርስዎ ግን ሞተዋል፣ ኦክስጅን አይቀበሉም፣ ካርቦንዳይኦክሳይድ አያስወጡም። ልብዎት ሰውነትዎ ውስጥ ላሉ ብልቶች ደምን አይረጭም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሰውነትዎ አካላት በምን ፍጥነት ስራቸውን ያቆማሉ? የሰውነት አካልዎ ስራቸውን እያቆሙና ከጥቅም ውጭ እየሆኑ ሲሄዱ፣ እያንዳንዱ ሴሎች እንደ አዲስ ስራ ሊጀምሩ ይችላሉ። በቀጣዮቹ 12 ሰዓታት ሰውነትዎ ሙሉ በሙሉ ሥራውን ያቆማል። በዚህ 12 ሰዓት ጊዜ ውስጥ አንዳንድ በሰውነትዎ የሚገኙ የዘረ መል ቅንጣቶች በፍጥነት የሚባዙ ሴሎችን ያመርታሉ፡፡ እነዚህም አንጎል ውስጥ የተፈጠረን ነገር ለማስተካከል ጥረት የሚያደርጉ ሴሎች ናቸው፡፡ ሰውነትዎ እየቀዘቀዘ በሚሄድበት የሰውነት ክፍሎች ስራ ሙሉ ለሙሉ በሚያቆሙበት የመጀመሪያ ጊዜያት ሁሉ ጥረታቸው አይቆምም። እነዚህ የዞምቢ ዘረመል ተብለው ይጠራሉ፡፡ የአንጎልዎ ሥራ እየቆመ ባለበት የመጀመሪያ ሰዓታት በአንጎል ላይ ተቀጥላ ሆነው በመጀመሪያዎቹ ሰዓታት ጥረታቸው እንደማይቆም ጥናቱ ያመለክታል፡፡  
እርስዎ ወዳጃችን በቤትዎ ወይም በአካባቢዎ የከብት እርድ ሲደረግ አይተው እንደሚያውቁ አልጠራጠርም፡፡ በሬው ታርዶ ተበልቶ ካበቃ በኋላ ስጋው ለብቻው ሲንቀጠቀጥ እንደተመለከቱትም እገምታለሁ፡፡ ይሄ በከብቱ ሥጋ ውስጥ ያሉ ሴሎች ሙሉ ለሙሉ ሥራ እስኪያቆሙ ድረስ የሚያጋጥም ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ግን ያ አይኖርም፡፡
ነገር ግን አሁንም የተረጋገጠ፣ ይሄን ይመስላል የምንለው ከሞት በኋላ ህይወት የለም። ብዙ ሰዎች በሞት ከተለያቸው ወዳጅ፣ ልጅ፣ ጓደኛ ወይም ዘመድ ጋር በመነጋገር የውስጥ እረፍትን ማግኘትን ይመኛሉ፣ ይሞክራሉ፡፡ እስኪ የህይወት ፍፃሜ መንፈሳዊነትን ያልተሞላ እንደሆነ ለአፍታ ያስቡና ብርሃናማ ሰማይን ከመመልከት ይልቅ የዲጂታል ኮምፒዩተር መተግበሪያ ቁጥሮች አንድና ዜሮን ብንመለከትስ፡፡ ሬይ ኩርዝዊል የተባሉት የጎግል ካምፓኒ የኢንጂነሪንግ ክፍል ሃላፊ እንደገለፁት፤ በቀጣዩ ጊዜያት የአንጎላችን ዲጂታል ቅጂ (ኮፒ) በድረ-ገጾች ላይ የሚለቀቁበት፣ በፍላሽና በሌሎች መረጃ ቋቶች የሚቀመጡበት ሁኔታ ሊመጣ ይችላል፡፡ ያ ከሆነ የአዕምሮዎ አስተሳሰቦችና አድራጎቶች ቴክኖሎጂው እስከቀጠለ ድረስ እርስዎ ቢያልፉም ሊቀጥል ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ያንን ፈፅመው አድራጎትዎን ለማስቀጠል (ሌጋሲዎን ለማስቀረት) ዋጋ በገንዘብ ሊከፍሉ የሚችሉበት ዘመንም ይመጣ ይሆናል፡፡ አሁንም ከሞት በኋላ ህይወት እንዳለ ካመንን አሁን ያሉበትን ወቅት በመንፈስ ተሃድሶና በአድናቆት ይቀጥሉታል፡፡ ነገር ግን ለዛም ጊዜ ባይኖርዎት የቀረዎት የህይወት ጊዜ 24 ሰዓት ብቻ ቢሆንስ? እድሜና ጤናን ይስጥዎት ወዳጃችን።


Read 2279 times