Saturday, 14 May 2022 00:00

ጥቁር እና ነጭ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(2 votes)

 ዛሬ፣ ድሮ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አብሮኝ የተማረውን የወንዜን ልጅ ዳንኤል አስፋውን መንገድ ላይ አገኘሁት፣ ዌስትሚንስተር ከሚገኘው መሥሪያ ቤቴ ወጥቼ ወደ መኖሪያ መንደሬ ብሪክሰን በእግሬ እያቀናሁ (የከተማው አውቶቡስ ከመሥሪያ ቤቴ እቤቴ በአስራ አምስት ደቂቃ ውስጥ ቢያደርሰኝም፣ ብዙ ጊዜ በእግሬ ተጉዤ ነው የምገባው) ሳለ፣ መሐል ለንደን ላይ፡፡ መንገድ የማያገናኘው ሰው የለ፡፡ ለካ ሰው ካልሞተ በቀር ዳግም ይገናኛል የሚለው አባባል እውነት ነው። ዳንኤል ከእኔ ተቃራኒ አቅጣጫ ካሰበበት ሊደርስ በጥድፊያ ሲገሰግስ፡
“ዳንኤል!” ብዬ ጠራሁት፣ ዐይኔን ጋርጄበት የነበረውን ጥቁር የዐይን መከላከያ መነፅር ከዐይኖቼ ላይ አሽሽቼ፡፡ ጥሪዬን የሰማው ዳንኤል ርምጃውን ገታና ገፁ ላይ ታላቅ ግርምት ነግሶ፣ በፈገግታ ተጠጋኝ። ማንም ሰው ከአገሩ ልጅ ጋር በድንገት ፈረንጅ አገር ጎዳና ላይ ቢገናኝ መገረሙ አይቀርም፡፡
“ኦ! ማክዳ አበበ፣ ታዲያስ? ከየት በቀልሽ?” አለ ዳንኤል በዐይኖቹ ሁለመናዬን እያስተዋለ። የአገሬ ሰው ርቦኝ ነበር። እንደኔው ጤፍ እንጀራ በምሥር ወጥ፣ በድልህ፣ በስልጆ፣ በዶሮ ወጥ፣ በተልባ፣ በሽሮ ወጥ ሲበላ ያደገ፡፡ በአስራ ሦስት ወር ፀሐይ አናቱን ሲያነድ የኖረ፡፡ አደይ የበቀለበት መስክ ላይ እየተንከባለለ ልጅነቱን የሸኘ፡፡ የዶቅማ፣ የሾላ፣ የዋንዛ፣ የአጋምና የእንኮይ ፍሬ ሸምጦ የበላ፡፡ ሲያቅፉት አሪቲ አሪቲ የሚሸት፣ ጡንጅት ጡንጅት የሚያውድ የወንዜ ሰው እጅግ ናፍቆኝ ነበር፡፡ እዚህ አገር ከመጣሁ በኋላ ጥቂት ሐበሾችን ነው በአካል ማግኘት የቻልኩት፡፡ በርነል ዩኒቨርሲቲ ለንደን ውስጥ ተማሪ ሳለሁ ከተዋወቅኳት ናርዶስ ከበደ ጋር በዐይነ ሥጋ ከተገናኘን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለንደን ከተማ ውስጥ የታክሲ ሾፌር ሆኖ ሲሠራ የነበረው ተስፋዬ ኩምሳ፣ ጓዙን ጠቅልሎ አገር ቤት ከገባ ረጅም ዓመት ሆኖታል፡፡ የመኖሪያ አፓርታማዬን ተጎራብቶ ይኖር የነበረው መሳፍንት ደምሴ፣ አገር ቤት ተመልሶ አሁን አንቱ የተባለ ፖለቲከኛ ሆኗል፡፡
ዳንኤል፣ ገና እንዳየኝ ነበር መልኬን የለየው፡፡ የዳንኤል የፊት ገፅታ አእምሮዬ አትሞ ይዞት ከነበረው የቀድሞ መልኩ ብዙም አልተለወጠም፡፡ ብዙ ጊዜ፣ በኮረዳነት ዘመኔ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሳለፍኳቸውን ትዝታዎች ሳመነዥክ፣ በግንባር ቀደምትነት ትዝ ከሚሉኝ ሰዎች መካከል አንዱ ዳንኤል ነው፡፡
ከዳንኤል ጋር እዛው ዌስትሚኒስቴር አካባቢ ወዳለ ዌስሊይስ የተሰኘ ካፌ ዘልቀን ብዙ አሮጌ ታሪኮችን እያነሳን ኮመኮምን። ዳንኤል ማውጋት ይችላል፡፡ ምን ምን አወጋኝ? እኔ ላይ ጆፌ ያልጣለ የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ጎረምሳ እንዳልነበር፣ እኔም እጅግ ትዕቢተኛ እንደነበርኩ፣ ምኒልክ ውስጥ በቀለም ቀንድነቷ ትታወቅ የነበረችው ናርዶስ ተሻገር፣ መርዝ ጠጥታ ራሷን ልትገል የሞከረችው እሱ ፈንግሏት መሆኑን፣ ጓደኛዬን አስቴር ከፍያለውን የጠበሳት ታላቅ ወንድሙ፣ ለፍቅረኛው ፅፎ ሊልክ ያዘጋጀውን የፍቅር ደብዳቤ ሰርቆ፣ ስም ቀይሮ ገልብጦ ሰዶላት መሆኑን … የመሳሰለ፡፡
ዳንኤል፣ ምኒልክ ትምህርት ቤት ውስጥ በሦስት ነገሮች ዝናው የናኘ ሰው ነበር፣ በዘፋኝነቱ፣ በቀልደኛነቱና በሴት አውልነቱ። ቅቤ እሚጠብስ ምላሱ አባብሏት ቀሚሷን ያልገለበችለት የምኒልክ ትምህርት ቤት ሸጋ የለችም ይባል ነበር ድሮ፡፡ ያው ሐሜት ነው፣ በተጨባጭ ያረጋገጥኩት ነገር የለም፡፡ ምናልባትም ተማሪ የሚነዛው ወሬ እውነት ሊሆን ይችላል፣ መቸስ ሐሜት እንደ ሰርዶ የሆነ ተጨባጭ እውነትን ሳይመረኮዝ እንዲሁ በባዶ ሜዳ አይበቅል፡፡ ዳንኤል፣ ሁሌም ሲታይ ሴት አቅፎ ነው፡፡ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲዞር እጁን ኮረዳ ወገብ ላይ ጠምጥሞ ነው፣ መማሪያ ክፍል ውስጥ ሲቀመጥ ሴት አቅፎ ነው፣ በታክሲ ሲሄድ ሴት ሸጉጦ ነው፣ ቅዳሜና እሁድ ፒያሳ መኮንን ባቅላቫ ቤት ስናገኘው ሴት ጎኑ አስቀምጦ ነው፡፡
ዳንኤልን ካገኘሁበት ዕለት አንስቶ የደበዘዙ፣ የተሰወሩ፣ የተፋቁ የሚመስሉ ግን በአሻራቸው በተበተቡኝ፣ በእርጅና ብዛት ትተውኝ ሸሽተዋል ያልኳቸው ግን ድንገት ከመሸጉበት ሥፍራ ተግበስብሰው በመውጣት ዛሬም አንለቅሽም ብለው በሚነዘንዙኝ መንቻካ ትዝታዎች መባዘን ዕጣዬ ሆኗል፡፡ ቆየ ደስታዬ ሸሽቶ ድብርት ከወረሰኝ፡፡ ያልሸሹኝ ትዝታዎቼ የሁለት ወንዶች ቁራኛዎች ናቸው፣ የሀኒባል ወርቁ እና የሮበርት ጆንሰን፡፡
*  *  *
ሀኒባል ወርቁ የመጀመሪያ ፍቅረኛዬ ነው፣ ኮረዳ ቢራቢሮ ሳለሁ በርሬ የቀሰምኩት የአዱ ገነት ሸበላ፣ ጉልቻ የመሠረተች ሴት ሳትቀር እሱን በማቀፍ አምሮት ነዳ፣ ዱካውን ተከትላ የምትባዝንለት የሸገር ጣዝማ፡፡ ሁልጊዜ አፓርታማዬ ሳሎን ውስጥ የሰቀልኩትን፣ ሥነ ጥበብ ኮሌጅ ተማሪ ሳለ (በድብቅ ቤቱ እየሄድኩ) ስሎ በስጦታ ያበረከተልኝን፣ እርቃኔን አሮጌ የቀርከሃ ሶፋ ላይ ተቀምጬ የምታይበትን የሸራ ላይ ሥዕል ሳይ አንጀቴ በትዝታው ረመጥ መንገብገብ ይጀምራል፡፡
1993 ዓ.ም ማብቂያ ላይ ከሀኒባል ጋር ፍቅር በጀመርን በሳምንቱ (ቅዳሜ ነበር ዕለቱ) ሲኒማ ጋብዞኝ፣ ተያይዘን ፒያሳ ሲኒማ አምፒር ገብተን፣ ዘ ላስት ታንጎ ኢን ፓሪስ የተሰኘ የባህር ማዶ ፊልም አየን፡፡ (ቅዳሜ ተቀጣጥረን አርብ ሌሊትን እንዲሁ ሀኒባልን ሳስብ እንቅልፍ በዐይኔ ሳይዞር አነጋሁ፡፡ ከወንድ ጋር ስቀጣጠር ያ ቀን የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ የወንድ ወዳጅ የያዙ ታላላቆቻችን ሲያወጉ የሰማሁት ብዙ ታሪክ፣ ብዙ ገጠመኝ አለ፤ እኔ ያላለፍኩበት፡፡) በእዛች ለመጀመሪያ ጊዜ ወንድ ተከትዬ አሮጌዋን ፒያሳን በረገጥኩባት እለት፣ ለስንቱ የነፈግኩትን ለጋ ሴትነቴን በሀኒባል አስገሥሼ ተመለስኩ፣ ፍቅር አክንፎኝ፡፡ ለሚወዱት ሰው ምንስ የሚከለክሉት ነገር ይኖራል?
*  *  *
ሮበርት፣ ከሦስት ዓመታት በፊት፣ ምድረ በዳ እንደተጣለ ሰው፣ የባይተዋርነት ጅራፍ ሲልጠኝ በወዳጅነት ይዤው የነበረ እንግሊዛዊ ነው፡፡ ዘጠኝ ዓመት እንግሊዝ ስኖር የፍቅር አጋር አልነበረኝም፡፡ ሮበርት የቴአትር ሮያል ስትራትስፎርድ ኢስት ተዋናይ ነው፡፡ ስድስት እጅግ አስደሳች የፍቅር ወራትን ካሳለፍን በኋላ ነው የተለያየነው፤ የሸሸገውን አመንዝራነቱን ደርሼበት፣ የሚያንሰፈስፍ ፍቅሩ ሳይወጣልኝ፡፡
*  *  *   
እነሆ ዘ ሀይደን የተሰኘ ሆቴል ከተጎለትኩ ሰዓታት አልፈዋል፡፡ ይህ ሆቴል ከቀድሞ ፍቅረኛዬ ማክዳ አበበ ጋር ሳንለያይ በፊት እናዘወትረው የነበረ ሆቴል ነው፡፡ ዛሬ፣ ከእሷ ጋር ከተለያየሁ ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው ዳግም ሆቴሉን የረገጥኩት፣ ከእሷ ጋር እዚሁ ሥፍራ ያሳለፍኩት ታሪክ ጎትቶኝ፡፡ እዚህ ከመምጣቴ በፊት በንግስት ቪክቶሪያ ጎዳና ብቻዬን ስመላለስ ነው የዋልኩት፣ ማክዳ የተመላለሰችበትን የእግር ማህተም የማስስ ይመስል፡፡ ሰው የአንድ ሥፍራ ቁራኛ የሚሆነው በተለየ ምክንያት ነው። ይህ ባይሆን የቀትር ሐሩር፣ የሌሊት አመዳይ ሳይበግረኝ ከእሷ ጋር እጅ ለእጅ ተቆላልፈን በተንሸራሸርንባቸው የለንደን ጎዳናዎች ላይ ብቻዬን እንከራተት ነበር? ይህ ባይሆን ጠረኗን ኀሰሳ አብረን የዋልንባቸውን ሥፍራዎች ዞሬ ሳካልል እውል ነበር? ግን ከእዚህ ሁሉ ድካም ምን አተረፍኩ? ምንም። ቁጭት ብቻ፣ እህህ ብቻ፡፡
ማክዳን የመሰለ አፍቃሪ ሴት ያጣሁት በአባይነቴ ምክንያት ነው፣ ተጣብቶኝ የነበረውን የሽፍትነት ነቀርሳ ነቅዬ ስላልጣልኩ፡፡ እንዲህ ዛሬ፣ ሽፍትነቴ ውሎ አድሮ ደም እሚያስነባ ፀፀት እንደሚያተርፍልኝ ባውቅ ኖሮ ዕንቁዬን በወጉ እይዝ ነበር፡፡ ማክዳ ዕንቁዬ ነበረች፡፡ ከቶ እሷን ማን ይመስላታል?
ከማክዳ ጋር እስከመጨረሻው ለመለያየት ያበቃኝ ማዲሰን ከተባለች የሥራ ባልደረባዬ ጋር የነበረኝ ድብቅ ግንኙነት ነው፡፡ የገና በአል በተከበረ በሳምንቱ (ዕለቱ ዓርብ ነበር) ከማዲሰን ጋር ከሥራ ወጥተን በእኔ ግብዣ ስትራትስፎርድ ወደሚገኝ ዝነኛ የጣሊያን ሬስቶራንት ተያይዘን ሄድን፡፡ እዛ ሬስቶራንት፣ ከማዲሰን ጋር እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ወይን እየተጎነጨን ስናወጋ ከአመሸን በኋላ ተያይዘን ዋንስወርዝ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቴ ሄድን፡፡ ማክዳ በማግስቱ ቅዳሜ ጠዋት፣ ፈፅሞ ትመጣለች ብዬ ባልጠበቅኩበት ሰዓት በድንገት ቤቴ ከች አለች፡፡ ሌላ ጊዜ ቅዳሜን እጅግ ባተሌ ሆና ነበር በሥራ የምታሳልፈው፡፡ መኝታ ቤቴ ከማዲሰን ጋር ተቃቅፈን ተኝተን ነበር፡፡ ከማዲሰን ጋር ከሥራ የዘለለ ግንኙነት አልነበረንም፤ እራት አብረን በበላንበት ምሽት ግን የወሰድነው መጠጥ ገፋፍቶን ወንድማዊነትና እህታዊነት የሚሉትን የግንኙነት ኬላ ጣስን፡፡ ማዲሰን ዕፀ በለስ ነበረች፣ የገላዋ ውበት ፈተነኝ፣ ብስል ወይን ከንፈሮቿ ረቱኝ፡፡ ዛሬ እንዲህ የቁጭት አርጩሜ ሊያነክተኝ፡፡ ማክዳ ቤቴ ታዛ ላይ ቆማ በር አንኳኳች፡፡ በምሬት እያጉተመተምኩ ከሞቀው የማዲሰን እቅፍ ወጥቼ፣ በስካር የዛለ ጅስሜን እየጎተትኩ ሄጄ በር ከፈትኩ፣ የእኔው ማክዳ የንጋትን ፀሐይ በሚቀናቀነው ፈገግታዋ ተሞልታ ተገትራለች፡፡ ‘ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም’ ትል ነበር ይችው የእኔ ጠንበለል፣ የአገሯን ተረትና ምሳሌ ተውሳ። በድንጋጤ አፌ መላወስ አቃተው፣ የጨው ሐውልት ሆኜ እንደተገተርኩ ነው፡፡ የገጠመኝ ዱብዳ በካበተ የቴአትር ጨዋታ ክህሎት የሚሸፋፈን አይነት አልነበረም፡፡ ሁሉም የማምለጫ መንገዶች ዝግ ነበሩ፡፡ ሁኔታዬን ከቁብ ያልቆጠረችው ማክዳ፡
“ታዲያስ አንተ ሽፍታ? ሰው አይናፍቅህም?” ብላ ከንፈሬን ስማ ወደ ውስጥ ዘለቀች፡፡ የውርደት ቀን ቀርቧል፡፡ በሕይወቴ እንደ እዛ ቀን ነፍሴ የተሰቀቀበት ጊዜ የለም፡፡ ማክዳ ካፖርቷን ሳሎን ግድግዳ ላይ ሰቅላ፣ አፏን በድንጋጤ ከፍታ፣ ወለሉ ላይ እዚህና እዛ የወደቁትን የማዲሰን አልባሳትና ባለ ታኮ ጫማ መመልከት ጀመረች፡፡   
“ምንድን ነው የማየው ጉድ? ማን መጥቶ ነበር?” ዐይኖቿን ጠቅላላ ሳሎኑን በመፈተሽ ጠመደቻቸው፡፡ የእኔ ዐይኖች ጠረጴዛው ደርዝ ላይ የተቀመጠው የማዲሰን ቦርሳ ላይ ተተክለዋል፡፡
“መልስልኝ እንጂ!” አለች በቁጣ፣ ፊቷ ሳምባ መስሏል፡፡ አንደበቴ መላወስ አልቻለም፡፡ መኝታ ቤት ውስጥ የነበረችው ማዲሰን፣ የማክዳን ድምፅ ሰምታ ኖሮ፣ በር ከፍታ በውስጥ ልብስ ብቅ አለች፡፡     
“ምንድን ነው እየተሠራ ያለው ድራማ? ማን ናት ይቺ ሴት!” እሳት የሚተፉ የመሰሉ ዐይኖቿ፣ ዐይኖቼ ላይ አፍጥጠዋል፡፡ እንደተለጎምኩ ዐይኖቼን ከአስፈሪ ዐይኖቿ አሽሽቼ አቀረቀርኩ፡፡ ዐይንን ከጠሉት ነገር ላይ ማሸሽ እጅግ እጅግ ቀላል ነው፣ አዳጋቹ ጉዳይ ሳይታሰብ ከሚገጥም ቀውስ መሸሽ አለመቻል ነው፡፡ አቅም ቢኖረኝ እንደ ንስር አሞራ ይኸን ደባሪ ኩነት፣ ይኸን ቤት፣ ይኸን አካባቢ፣ ይኸን ከተማ፣ ይኸን አገር፣ መላው አውሮፓን ለቅቄ እሰደድ ነበር፡፡
ማክዳ ቃል ሳትተነፍስ፣ ካፖርቷን አፈፍ አድርጋ በመጣችበት እግሯ መሰሰ ብላ ከቤት ወጣች፡፡   እየተጣደፍኩ አጠገቤ ያገኘሁትን ልብስ ለብሼ ተከትያት ወጣሁ፡፡ ቅጥር ግቢውን ጨርሳ መኪናዋ ጋ ልትደርስ ጥቂት ርምጃ ሲቀራት ደረስኩባት፡፡ ዞራ መንታ ዕንባ ባቀረሩ ዐይኖቿ በጥላቻ ድባብ ገላመጠችኝና፣ መኪናዋ ውስጥ ገብታ አስነስታ፣ በተገተርኩበት ጥላኝ ሄደች፡፡ የእኔ ንግስት፣ ኩሸት የማታውቅ እርግብ፣ የመልካምነት አብነቷ፣ የፈፀምኩባት ክህደት ልቧን ሰብሮት፣ ዳግም ደጄን ላትረግጥ ርቃ ተሰደደች፡፡
ማክዳ አለት ነበር ልቧ፣ ከእዛ ቀን በኋላ ዳግም ዐይኗን አላየሁም፡፡ እኔም ምልጃዋን መማፀን የሚያስችል ሞራል ስላልነበረኝ በቁጭት ረመጥ እየተንገበገብኩ፣ ጭንጋፍ ህልሜን ታቅፌ፣ ከሕይወቷ ገለል አልኩ። ሁሉ ነገር ተበለሻሽቶ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ናፍቆቷ ያንሰፈስፈኛል፣ እንደ ወትሮው ሰንደል ገላዋን አቅፌ፣ የከንፈሯን ማር ወለላ እየጠባሁ ማደር እመኛለሁ፡፡ ግን ምኞቴ ከንቱ ነበር፣ ጉምን እንደመታቀፍ፡፡

Read 275 times