Saturday, 14 May 2022 00:00

"ሥራዬ ሙዚቃና ሙዚቃ ብቻ ነው"

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

“የኔ ዜማ” ኮንሰርት ዛሬ በመቻሬ ሜዳ ይካሄዳል


           የድምጻዊ ዳዊት ጽጌ “የኔ ዜማ” ተወዳጅ አልበም መውጣቱን ተከትሎ፣ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የሙዚቃ ኮንሰርት በኮቪድ-19 መከሰትና በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ሲተላለፍ ቆይቶ፣ እነሆ ከሁለት ዓመት በኋላ በዛሬው ዕለት በመቻሬ ሜዳ ይካሄዳል፡፡ ከድምጻዊው ጋር አጭር የስልክ ቃለምልልስ ያደረገችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ፣ በጉጉት ለሚጠበቀው ኮንሰርቱ ስላደረገው አጠቃላይ ዝግጅት፣ ያለፉትን ሁለት ዓመታት እንዴት እንዳሳለፈው፣ በሰሜን ሸዋ ነዋሪ የሆኑት ቤተሰቦቹ በጦርነቱ ምን እንዳጋጠማቸው፣ ከባላገሩ አይዶል መሥራች አብርሃም ወልዴ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ጠይቃው ምላሽ ሰጥቷል፡፡ እነሆ፡-



                “የኔ ዜማ” አልበምህ በእጅጉ ተወዳጅ ነበርና አልበሙ በወጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኮንሰርት ለመስራት ማቀዳችሁ ተነግሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን ምቹ ሁኔታ ስላልነበረ እስከ ዛሬ ቆይቷል፡፡ ያኔ ኮንሰርቱን ልትሰራ ስትል ኮቪድ 19 መከሰቱ፣ ከዚያም ጦርነቱ ሲነሳ “እድለኛ አይደለሁም” ብለህ አላማረርክም?
በፍጹም አላማረርኩም! ለኛ ዋናው ነገር አልበሙ መደመጡ ነበር፡፡ አንድ አልበም ሲሰራ አራት አምስት ዓመት ይፈጃል። ከዚያ ሁሉ ልፋትና ድካም በኋላ ደግሞ ትልቁ ግብ የአልበሙ በደንብ መደመጥና መወደድ ነው። አልበሙ ከወጣ ሁለት ዓመት አልፎታል። በዚህ በሁለት ዓመት ከምናምን ጊዜ ውስጥ የተገነዘብኩት፣ ዘፈኖቹ ምን ያህል ሰው ውስጥ እንደገቡና ምን ያህል ለረጅም ጊዜ የመደመጥ አቅም እንዳላቸው ነው፤ ስለዚህ ምንም የተጨነቅኩበት ነገር የለም፡፡ ያማረርኩትም ጉዳይ የለም። ሁሉም የሚሆነው በጊዜው ነው ብዬ የማምን ሰው ነኝ፡፡ ለምን ካልሽኝ፣ ችግሮች እኔ ላይ ብቻ የመጡ አይደሉም፡፡ የሀገራችን ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ “እዬዬም ሲዳላ  ነው” የሚባል ነገር አለ፡፡ ሀገራችን ከባድ ችግር ውስጥ ነበረች፡፡ በዚያ የችግር ወቅት ኮንሰርት አለመስራት ሊያሳስበኝም ሊያማርረኝም ሊያስጨንቀኝም አይችልም፡፡ ያስጨንቀኝ የነበረው ሀገራችንና እኛ ህዝቦቿ ከዚያ ችግር ውስጥ በምን ሁኔታ እንወጣለን የሚለው ነበር። ይሄ ሁሉ ነገር ሲፈጠር እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ወዲያውኑ ወደ ሌላ ስራ ገባሁ እንጂ ያባከንኩት ጊዜ የለም፡፡
የኮንሰርት ማስታወቂያ ፖስተርህ ላይ ባስተላለፍከው መልዕክት፣ ይህን ኮንሰርት ለመስራት ብዙ መጠበቅህንና ከአድናቂዎችህ ጋር ለመገናኘት ያለህን ጉጉትና ናፍቆት ገልጸሃልና፣ እስኪ የዝግጅትህ ሁኔታ ምን እንደሚመስል አጫውተኝ?
እውነት ነው፤ ናፍቆትና ጉጉቴ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ምክንያቱም አንድ አልበም ከተወደደ በኋላ ከሰው ጋር ትዝታ ሲኖርሽ  በጣም ደስ ይላል፡፡ ሰው የወደደውን ዘፈን ከኔ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሲዘፍን፣ ሲጫወት፣ እሱ ነው ትልቁ መደምደሚያ የሚሆነው። ለዚህ ናፍቆትና ጉጉት የሚመጥን ከፍተኛ ዝግጅት አድርጌያለሁም፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ  ነው፤ አሁን በጉጉት የምንጠ ብቀው የኮንሰርቱን ዕለት  ነው።
ያለፉት ሁለት ዓመታት በተለይ ለአርቲስቱ አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡ በኮቪድ 19 ወረርሽኝና በጦርነቱ ሳቢያ እንቅስቃሴዎች ተገትተው ነበር፡፡ አንተ ሁለቱን ዓመታት እንዴት ነው ያሳለፍከው?


ሙዚቃ የተፈጠርሽበት ሲሆን ከመዝናኛነት ባለፈ እንደ ስራ ታይዋለሽ። በዚህ ሙያ ላይ ያሉ አርቲስቶች ሙዚቃን የሚያዩበት መንገድ ሌላው ማህበረሰብ እንደሚያስበው አይደለም፡፡ እንደ ስራ ይታያል። ሙዚቃ ዝም ብሎ ለጭፈራና ለሆይታ ብቻ አይደለም፡፡ እኔ ለምሳሌ ዘፈኖቼን ስመርጥ በግጥማቸውም በዜማቸውም የነፍስ እንዲሆኑ እፈልጋለሁ። ሰዎች በተለያየ ስሜት ውስጥ ሆነው የሚደሰቱትም እንዲደሰቱ፣ የሚተክዙትም  እንዲተክዙ፣ የሚጨፍረውም እንዲጨፍርበት እፈልጋለሁ፡፡ እናም ሙዚቃ ከብዙ ባህሪያችን ጋር ይያያዛል ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ ሙዚቃን ለመደሰትና ሆይ ሆይ ለማለት ብቻ የሚሆን አድርጎ ማሰብ ስህተት  ይመስለኛል፡፡ እንደሚታወቀው ሀገራችን ውስጥ በነበረው ችግር ረጅም የድባቴ ጊዜ ነበር ያለፈው፤ ብዙ የሚያስጨንቁ ነገሮች አልፈዋል። በነዛ አስጨናቂ ጊዜያት ውስጥ ታዲያ ሙዚቃ ሳልሰማና ስሜቴን ሳላዳምጥ ያለፍኩበት ጊዜ የለም፡፡ ከዚህ አንጻር ሙዚቃ ከሰው ልጆች ነፍስና መንፈስ ጋር በብዙ መልኩ የተቆራኘና የሀዘን መፅናኛ፤ መውደድን፣ መደሰትን መግለጫ ትልቅ መሳሪያ ነው እላለሁ፡፡ እኔ ሙዚቃን በዚህ መንገድ ነው የምረዳው፡፡
በሰሜኑ ጦርነት ብዙ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ የሰሜን ሸዋ አካባቢ ነው። ያንተ ቤተሰቦች ደግሞ የሰሜን ሸዋ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ በጦርነቱ በቤተሰብህ ላይ የደረሰ አስከፊ ጉዳት አለ? ያንን ጊዜስ እንዴት አሳለፍከው?
እውነት ለመናገር በጣም አስጨናቂ ጊዜ ነበር ያሳለፍነው፡፡ እንዳልሽው የእኛ አካባቢ በጦርነቱ ተይዞ ነበር፡፡ ከባድ ውጊያም ነበር። በዚህ ምክንያት ቤተሰቦቼ ከ20 ቀናት በላይ ከቤታቸው ተፈናቅለው፣ በአስቸጋሪ ፈተና ውስጥ ነበሩ። ምግብም ሆነ ምንም ነገር አልነበራቸውም፡፡ እኔም ራሴን ለብዙ ነገር ያዘጋጀሁበትና ተስፋ የቆረጥኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ቤተሰብሽ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ሆኖ ከ20 ቀን በላይ ድምጻቸውን ሳትሰሚ ያለውን ስሜት አስቢው፤ በእጅጉ ከባድ ነው፡፡ አሁን ላይ ያ ሁሉ ነገር አልፎ እግዚአብሔር ይመስገን፣ ሄጄ ተገናኝተን፣ ጥሩ ጊዜ አሳልፈን ተመልሻለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል ምንም እንኳን አስቸጋሪ ጊዜያትን ቢያሳልፉም፣ ከቤተሰቤ የጎደለም ሆነ የከፋ ችግር የደረሰበት የለም፤ አሁን ሰላም ናቸው።
ቀደም ሲል ከባላገሩ አይዶል መሥራችና ባለቤት አብርሃም ወልዴ ጋር ውዝግብ ውስጥ እንደነበራችሁ ወሬዎች ሲናፈሱ ነበር። አሁን ስላላችሁበት ትክክለኛ ሁኔታ መረጃ መስጠት ከፈለግህ እድሉን ልስጥህ--
ምን መሰለሽ ውዝግብ ሳይሆን፣ አንድ እኔና አብርሽን የሚያግባባን ነገር፣ ሁለታችንም ትልቅ ስራ መስራት እንፈልጋለን፡፡ የሆነ ስራ ስንሰራና ስናዘጋጅ ድብስብስ ያለ ነገር ሁለታችንም አንወድም፡፡ ስለዚህ ሥራ  ስንሰራ  ትልቁ የሚያግባባን ነገር እሱ ነው። ከዚህ ውጭ ግን አብረሽ ስትሰሪ አንዳንድ የአካሄድ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሃል ያን ያህል አለመግባባትም ባይሆን፣ እኩል ላታስቢ ትችያለሽ እና አንዳንድ ነገሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ እንጂ፤ አብርሃም ትልልቅ ሀሳቦችን መስራት ይፈለጋል፡፡ በዚህ ምንም ጥያቄ የለኝም፡፡ በጣም አምንበታለሁ፡፡ እሱንም በማሰብ ነው ይሄንን ጊዜ ጠብቄ ስራውን እንድሰራ እግዚአብሔር የፈቀደልን።
እንጂ እንደሚናፈሰው አይነት ውዝግብ የለም?
በፍፁም የለም፡፡
ረቡዕ አመሻሽ ላይ ኮንሰርቱን አስመልክታችሁ በሰጣችሁት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ቅዳሜ በመቻሬ ሜዳ ብዙ ሰው እንደምትጠብቁ ጠቁማችኋል። አንተ ግን "የኔ ሙዚቃ አፍቃሪዎች ናቸው፤ በኮንሰርቱ ይታደማሉ" የምትላቸው በየትኛው የዕድሜ ክልል ያሉትን ነው?
እንግዲህ ኮንሰርት ላይ ከ18 ዓመት በላይ የሚባል ነገር ያለ ይመስለኛል እንጂ ከትናንሽ ልጆች ጀምሮ ዘፈኔን በቃላቸው የመያዝና የመዝፈን ነገር አደምጣለሁ አያለሁ፡፡ በጣም ትንንሾች ልጆች ነው የምልሽ፡፡ እና የሚገርምሽ ነገር፣ ይህን ስናይ ሌላ ሀሳብ እንድናስብ አድርጎናል፡፡
ምን አይነት ሀሳብ አሰባችሁ?
አንዳንዴ የኮንሰርቶቻችን ፎርማቶች ሁሌ አንድ አይነት መሆን የለባቸውም የሚል ሀሳብ እንድናስብ አድርጎናል፡፡ ለምሳሌ ሰው ቤተሰቡን ይዞ ያለ ዕድሜ ገደብ የሚዝናናበት ኮንሰርት ያስፈልጋል ብለን ያሰብናቸው ነገሮች አሉ። የእኔን ዘፈን ከህጻናት ጀምሮ ሁሉም ሰው ወዶታል፤ አልበሙን ሰምቶታል፡፡ ስለዚህ ሰው ከህጻን እስከ ታዳጊ ልጆቹ፣ ቤተሰቡን በሙሉ ይዞ የሚዝናናበት ኮንሰርት ማዘጋጀት የሁልጊዜ ህልሜ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ስራ ሰው በደንብ ካወቀኝና አልበሜን ካደመጠው በኋላ፣ የጎደለውስ ነገር ምንድን ነው የሚለው ላይ ትኩረት ሰጥቼ ነበር፡፡ የጎደለው የሚወዱኝ፣ የዘፈኔን ግጥም በቃላቸው ይዘው የሚዘፍኑ ህጻናት፣ ከወላጆቻቸው ጋር የሚታደሙበት ኮንሰርት ስለሆነ፣ እሱን በቅርቡ እናሳካዋለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ህጻናትም ብቻ ሳይሆኑ በዕድሜ አንጋፋ  የሆኑ የሀገር ባለውለታዎች መጥተው ተረጋግተው፣ ኮንሰርት መታደም የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር አስበን እየሰራን ነው፡፡ እንዳልኩሽ በቅርቡ ይሳካል፤ የጀመርናቸውም ነገሮች አሉ፡፡
ህጻናት ምን ያህል ዘፈኖችህን እንደሚወዷቸውና እንደሚዘፍኗቸው ልብ ያልኩት በኮሜዲያን እሸቱ መለሰ “ዶንኪ ቲዩብ” በሚዘጋጀው “ድንቅ ልጆች” ላይ የቀረቡ መንትያ አይነስውራን ህጻናትን ስመለከት ነው፡፡  አንተን ጋብዞ ሰርፕራይዝ ሲያደርጋቸው የተሰማቸው ደስታ ሁሉ ትዝ ይለኛል…. ስለዚህ የቤተሰብ ኮንሰርት ያልከው ለእንደነዚህ አይነት ህጻናትም መልስ ይሆናል ብዬ አምናለሁ ----
ትክክል ነሽ! የሚገርምሽ ይሄ አጋጣሚ በሚዲያ ወጣ እንጂ ብዙ እናቶችና አባቶች ይደውልሉኛል፡፡ ለልጆቻቸው ብለው ማለቴ ነው፡፡ እና ህጻናቱ ዘፈኖቹን በቃላቸው ይዘው ይዘፍኑልኛል፤ በጣም ነው የምገረመው፤ ስለዚህ ከነዚህ የኢትዮጵያ ህጻናትና ታዳጊዎች ጋር ከነወላጆቻቸው የምንገናኝበትን የቤተሰብ ኮንሰርት የግድ እናፈጥነዋለን፡፡እትቱ: አዲስ የሙዚቃ ቪዲዮ በዳዊት ፅጌ - YouTube
አዲስ አልበም ጀምሬያለሁ ብለኸኝ ነበር፤ እስኪ በደንብ አብራራልኝ?
ያው ጊዜው ሲደርስ በደንብ የምንገልጸው ቢሆንም፣ በነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ ሁለት አልበም ነው ስሰራ የቆየሁት፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ ሙዚቃ የተፈጠርኩበት በመሆኑ ሥራዬ ሙዚቃና ሙዚቃ ብቻ ነው፤ ሌላ ሥራ የለኝም፡፡ ሁልጊዜ የማስበው ስለ ሙዚቃ ብቻ ነው፤ ሌላ ስራ የለኝም፡፡ ስለዚህ ከነአበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ ጋር በመነጋገር በሙሉ ባንድ አሬንጅ የተደረገ ሲሆን፤ አንዱ ደግሞ ሌላ ራሱን የቻለ አልበም ነው። አንዱ ግን  በጣም በቅርቡ እንደሚወጣ ሙሉ ተስፋ አለን፡፡ ምናልባትም ክረምት ላይ ቢበዛ መስከረም ላይ ከሁለት አንዱን ለሙዚቃ አፍቃሪዎች ለማድረስ እቅድ ይዘናል፡፡ ያው ጊዜው ሲደርስ ሁሉንም ይፋ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡
ኮንሰርቱን በጉጉት እየጠበቁ ለሚገኙ አድናቂዎችህ ምን መልዕክት አለህ?
እንግዲህ እኛም ሙሉ ዝግጅት አድርገን እንግዶቻችንን በጉጉት እንጠብቃለን፤ ሁሉም ሰው እንዲመጣ እንፈልጋለን። ስለ ሀገራችን አብረን በመዘመር፣ ስለ ፍቅር በማሰብ የተሻለ ጊዜ እናሳልፋለን፡፡ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን። ዕድሜ ጤናውን ይስጠን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡











Read 1162 times Last modified on Monday, 16 May 2022 06:02