በምትነድ ሀገር ላይ አይኖርም እልልታ
ባዘነች እናት ቤት አይሰማም ፌሽታ
በስብሰባ ብዛት አያልቅም ስሞታ
ትናንትናን እንጂ ...........
ነገን አያውቀውም የዘፈን ትዝታ!
በረገፈ ጥለት - ላይደረብ ኩታ
ጥርስን ቢነቀሱት ...........
ውስጡን እያመመው አይስቅም ለአፍታ!
የሰው ልኩ ከብሮ ካልሞላ ሚዛኑ
ዓመት በዓል ተብሎ .....
ቢበላ ቢጠጣ መች ይደምቃል ቀኑ ?
-
ከልብ ካልፈለቀ .........
ከነፍስ ካልሸተተ የፍቅር እጣኑ
በርግጎ ካልወጣ የቤት ውስጥ ሰይጣኑ
-- እንደተካሰሱ
--- እንደተዋቀሱ
---- እንደተላቀሱ
----- እንደተቧቀሱ እንደተኳነኑ
ወንዝ ዳር ሲደርሱ
እንደ ተማማሉ
አንድ ቤት አይተኙም አዋቂና ህጻኑ ?
***
ደስ ይላል
እንደ ቀልድ አጫውቶ ጉም ደመና ሆኖ
<አለ!> ሲሉት ተንኖ የሚጠፋ በንኖ
ከእጅ እየጠፋ ከመዳፍ ውስጥ መክኖ
ጊዜ ጉድ አረገን በማያልቅ ተቃርኖ !
-
ከእግር የሚያዳልጥ የማይረጋ ጸንቶ
ሲረግጡት የሚያሰምጥ እንደ ውሃ ረግቶ
እድሜ ይሉት ተአምር ጊዜ ይሉት ጸጋ
ጤዛ ነው ርጋፊ የሰው መሆን ሥጋ !
-
<< የወዛ ፍካቱ የበዛ ድምቀቱ
እንደምን ረገፈ የዚያን ክንደ ብርቱ ?
የፀና ጉልበቱ ተፈትቶ ጅማቱ
ምን ነክቶት ታጠፈ ስንት ቻይ አንጀቱ ?
አስተዋይ ጥበቡ ድንቅ ብርቅ እውቀቱ
እንዴት ከአፉ ጠፋ ከርቱእ ከአንደበቱ?>>
ብሎ እየጠየቀ በቆላ በደጋ
መልሱን አነበበው
ቆዳው ተጨራምቶ
ዓይኑ አቅም አትቶ በለበሰው ሥጋ !
-
ወፌ ቆመች ብሎ የእናት እግር ይዞ
በእንግድግድ የቆመ ጉልበት ተመርኩዞ
አድጎ ከዘመን ጋር ሲላፋ ከኑሮ
ጊዜ ድል አረገው
እንደ ሰፈር ሩጫ እድሜውን አባርሮ !
-
እድሜ ሲያጃጅለው ሰው ዘመኑን ረስቶ
እሞታለሁ አይልም ..........
አፈር መሸከሙን ለሰከንድ ዘንግቶ!
-
ትከሻው ላይ አዝሎ ደረቱ ላይ ሰፍቶ
ክንዱ ላይ ተነቅሶ ነፍሱ ላይ አጣፍቶ
እየተተካካ ኡደቱን ጠብቆ
የመጣው ይሄዳል ቀን ወሩን ጠብቆ!
-
ካልቀረ መሄዱ ከዓለም ተገንጥሎ
ፍቅርን እንደ ችግኝ በሰው መንፈስ ተክሎ
ትዝታውን ቢተው ቅዱስ ስሙን ጥሎ
ማለፍ ደስ ያሰኛል
በልጆች ልብ ላይ አዲስ ቀለም ስሎ!
ነፃነት አምሳሉ አፈወርቅ