Monday, 16 May 2022 05:59

መንታ ነፍሶች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ዶክትሬት ዲግሪውን ሊቀበል ጥቂት  ሳምንታት  ብቻ  የቀሩት ሉካስ፣በሚማርበት ዩኒቨርስቲ መናፈሻ ውስጥ ተቀምጦ በሰማይ አድማስ ብቅ ጥልቅ የምትለውን የምሽት ጀንበር፣ ፈሳሽ ወርቅ ያስመሰለችው ባህር ላይ አይኑን እንደተከለ በሃሳብ ነጉዷል፡፡
በኡሚኦ የህክምና ዪኒቨርስቲ (Umea university faculty of medicine) የሚሰጠውን የ6 ዓመታት የህክምና ትምህርትና የ3 ዓመት የህጻናት ህክምና ልምምድ በከፍተኛ ውጤት ካጠናቀቁ የዘንድሮ ተመራቂዎች አንዱ ነው፡፡ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ ለዚህ እስኪበቃ ከልጅነት እስከ እውቀት ለ30 ዓመታት የኖረባት የስዊድኗ የሰሜን ዋልታ ከተማዋ ኡሚኦ፣ በበጎም በመጥፎም እንደ ጡጦ የጋተችውን ወደ ኋላ እያሰላሰለ በትዝታ ይስለመለማል፡፡
የሰሜን አውሮፓ ዝናብ ከየሃገሩ ተሰዶ የመጣ ይመስል በዓመት አብላጫውን ወራት ከንጋት እስከ ምሽት እኝኝኝኝ በሚልባት በዚህች የሰሜን ስዊድን ከተማ፣ እንደ ሉቃስ አፍሪካዊ መልክ ያለው ነዋሪ ብዙም አይታይም፡፡ ኡሚኦ ዩኒቨርስቲ በዚህ ዓመት በ3ኛ ድግሪ ከሚያስመርቃቸው 26 የህክምና እጩዎች ውስጥ ጥቁር እሱ ብቻ ነው፡፡ የሚወዱት አብሮ አደግ ጓደኞች፣ የሚያደንቁት ተማሪዎችና መምህራን ያሉትን ያህል መልኩ ጠቆር ስላለ ብቻ በጎሪጥ የሚያዩትና ዝቅ አድርገው የሚያስቡትም አሉ፡፡ እሱ ግን በጥንካሬና በትጋት እልባቱ ላይ ስለደረሰ ለዶክትሬት ማዕረግ የሚያበቃውን የ9 ዓመታት መርሀ ግብር በከፍተኛ ውጤት  ለማጠናቀቅ መብቃቱን ማመን እያቃታቸው እንዴት? በሚል መንፈስ እንደሚያዩት ሲያስብ፣ ሳቁ እየመጣበት ለምትስቀዋ ጀንበር ፈግግ ይልላታል፡፡ የሚንቁትን በትምህርት አስከንድቶ አንቱ ወደሚያሰኘውና ከፍተኛ ተከፋይ ወደሚያደርገው የህክምና መስክ እየገባ ነው፡፡ ስውዲን  ውስጥ የሃኪሞች የደሞዝ ክፍያ የቀሩት  ባለሙያዎች ከሚያገኙት በላይ ነው፡፡
ያለፉትን የውጣ ውረድ ዓመታት  በህሊናው ሲስል ቆይቶ ከፈዘዘበት ሲነቃ ተንጠራራና ጭቅላቱን ነቅንቆ ሃሳቡን እንደ ካፊያ አራገፈው፡፡፡ የምሽት  ጀምበር ወርቅማ ጨረሮቿን በሰማይ አድማስ ሙሉ ረጭታ ቀስ በቀስ መጥለቋን ሲያይ፣ “ተሰናበትሽን ማለት ነው? በይ ደህና እደሪ፣ ጠዋት እንገናኝ” አላት።
እዚህ ሲጨልም የትኛው የዓለም ክፍል እንደሚነጋ አሰብ አደረገና፣ በዚያው አንድ ሁሌም ከህሊናው መዝገብ የማይጠፋ ሌላ ሃሳብ  መጣበት፡፡ የትውልድ ሃገሩ ነገር ያብሰለስለው ጀመር፡፡ በጨቅላ እድሜውም በሰው እቅፍ ስለመጣ ስለ ትውልድ ሃገሩ ምንም ትዝታም ሆነ ምስል የለውም፡፡
ከኢትዮጵያ በጉዲፈቻ አምጥተው እንደ ወላጅ በፍቅር ያሳደጉት ስውዲናውያን ባልና ሚስት ስሙን ሉካስ አሉት፡፡ የዛሬ 30 ዓመት አስረካቢና ተረካቢ ሲፈራረሙ በጉዲፈቻ መዝገቡ ላይ የሰፈረው ኢትዮጵያዊ ስሙ ጸጋዬ ነበር፡፡ ይሄ ስሙ ከዚያ መዝገብ ውጪ አገልግሎ አያውቅም። እሱ ነፍስ ካወቀ ጀምሮ ስዊድኖቹ እናትና አባቱም ሆኑ፣ካደገም በኋላም አብሮ አደግ ጓደኞቹም ሲጠሩት የሚያውቀው ስሙ ሉካስ ብቻ ነው፡፡
ስለ ትውልድ ሃገሩ የተፃፉ ታሪኮችን በየመፃህፍት ቤቱ እየፈላለገ፣ ቤተሰቡ የሚያወሩትን፣ ኢትዮጵያን ጎብኝተው ከተመለሱ ሰዎችም እየጠየቀ ስለ አየሯ ተስማሚነት፣ ስለ ታሪካዊነቷ የተወሰኑ ነገሮችም አውቋል፡፡ የሃውልቶቿንና የቅርሳ ቅርሶቿን ፎቶዎች አይቷል፡፡ ካርታ ላይ የሚያውቃት የአፍሪካ ቀንድ አገር፣ በጀግንነቷ የታወቀችና የተወደሰች ብትሆንም፣ ደሃ ከሚባሉትም የባሰች ደሃ መሆኗን ተገንዝቧል፡፡ አውሮፓውያን ባሳተሙት መፃሕፍቶች ውስጥ የማገዶ እንጨት  በጀርባቸው አዝለው በባዶ እግራቸው ወደ ገበያ የሚገሰግሱ ሴቶች፣ ወንዝ ዳር አጎንብሰው ወራጅ ውሃ በሁለት እጃቸው እያፈሱ የሚጠጡ እረኞች ተመልክቷል፡፡
እሱ ካደገበት ሀገር የኑሮ ምቾት ጋር ሲያነጻጽረው በዚች ጎስቋላ ሀገር ያሉ ሰዎች ያሳዝኑታል፡፡ ያቺ ሀገር እገዛው እንደሚያስፈልጋትም ያስባል፡፡ “እንግዲህ እዚያ ሄደህ ይህችን ምስኪን ሀገር አገልግል” የሚል ሃሳብ ይመላለስበታል፡፡
“ችግሩ በማላውቀው ቋንቋ እንዴት አድርጌ ከህዝቡ ጋር ልግባባ እችላለሁ? ቋንቋውን ልማር ብልስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድብኛል? ከባህሉና ከክህሎቱስ ጋር እንዴት እዋሃዳለሁ? ምግቡንስ እለምደው ይሆን? የአየሩ ፀባይ እንኳን ሞቃታማ ስለሆነ ከዚህ ብርዳምና የዝናብ ሃገር ይገላግለኛል” እያለ ከራሱ ጋር ሲሟገት ጀምበር እንደጠለቀች የተተካው ሃይለኛ ብርዳም ንፋስ ፊቱን ገርፎ አነቃው፡፡ ብርዱ ሲሰማው የጃኬቱን ዚፕ ዘጋና ከተቀመጠበት ተነስቶ ወደሚኖርበት የተማሪዎች ህንጻ ተራመደ፡፡ በአሳንሰር መኝታ ክፍሉ ወዳለበት አምስተኛ ፎቅ ወጣ፡፡ ከአሳንሰሩ ብቅ ሲል፣ ፊት ለፊት ባለው የተማሪዎች ካፌ ውስጥ ከሚዝናኑ የክፍል ጓደኞቹ ላርስ የሚባለው የቅርብ ጓደኛው በመስኮት አየውና፣
“ሄይ! ና ተመሳሰል፡፡ ፈተና የለ፣ በዶሮ መስፈሪያ ሰዓት ገብተህ ምን ትሰራለህ?” አለው፡፡
“ትላንት በቂ እንቅልፍ አልተኛሁም፤ ማረፍ እፈልጋለሁ” አለና እንደ አቀረቀረ ወደ ክፍሉ ሄደ። የበር ቁልፍ አውጥቶ የመዝጊያውን እጀታ ጫን ሲለው መዝጊያው ወደ ውስጥ ሄደ፡፡ ቆልፎት የሄደውን በር ማን እንደከፈተው ተገርሞ ቆም አለ፡፡ አንገቱን አስቀድሞ እንደ ድመት እያሰላ ገባ ሲል ፍቅረኛው ሶፊያ ላርሰን አልጋው ላይ በጀርባዋ ጋደም ብላ አያት፡፡ በሁለት እጆቿ የያዘችው መፅሐፍ ፊቷን ስለሸፈነው መግባቱን አላየችም፡፡ ሉካስን ያንበረከከ ለግላጋ ቁመናና ውብ ፈገግታ  ያላት ሶፊያ፤ በኡሚኦ ውስጥ ትልቅ የአሳ ማርቢያና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ካላቸው በጣም ባለጸጋ  ስድዊናውያን ቤተሰቦች የተወለደች ደልቃቃ ናት፡፡ እንደ ፍቅረኛዋ እሷም ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በህክምና መስክ ትመረቃለች፡፡ “የቆለፍኩትን በር ከፍታ ታስደንግጠኝ? እኔም እጫወትባታለሁ” አለ ለራሱ፡፡ ልክ እንዳመጣጡ እያሰላ ወደ ኋላ አፈገፈገ፡፡ መዝጊያው ላይ ከውስጥ የተሰካውን ቁልፍ በቀስታ መዞ ወጣና እንደነበረ ዘግቶት ከጓደኞቹ ተቀላቀለ፡፡
“ና ስንልህ ንቀኸን ሄደህ ተባረርክ? እኛ እንሻልህ ነበር” አለው ላርስ፡፡
“ወይ ሴራው ውስጥ ትኖርበታለህ” አለ ሉካስ፣ ቀልዱን በቀልድ እየመለሰ፡፡
በአሳንሰሩ ወደ ምድር ቤት  ወረደና ቢስኪሌቱን እየገፋ አሳንሰሩ ውስጥ አስገብቶ ወደ ፎቅ ወጣ፡፡ ከአሳንሰሩ እንደወጣ ብስኪሌቷን ወደ ክፍሉ ወሰዳት፡፡
መኝታ ክፍሉ ዘንድ ሲደርስ ቀጥ ያዘ። የመዝጊያውን እጀታ በቀስታ ተጭኖ አላቀቀውና ወደ ኋላ ተመለሰ፡፡ የብስክሌቷን የቀኝ እግር ፔዳል ወደ ፊት በኃይል ተጭኖ አዘለላትና በመጣበት ፍጥነት መዝጊያውን በፊት ጎማው በርግዶት ገባ፡፡ በምታነብበው መጽሐፍ የተመሰጠችው ፍቅረኛው፣ የተበረገደው መዝጊያ ተወርውሮ ከግድግዳ ጋር ሲጋጭ በፈጠረው ጩኸት ደንግጣ እየጮኸች፣ ከተንጋለለችበት ተንከባልላ አልጋ ስር ገባች፡፡
“ተርፈሻል! ተርፈሻል!” አለ ሉካስ፣ ከአልጋው ላይ መውደቋ ሊፈጥረው ከፈለገው ጨዋታ በላይ እንዳስደነገጣት ሲሰማው፡፡ ምን እንደገባ ባለማወቋ በጭንቀት አፍና የያዘችውን ትንፋሽ በረዥሙ አስወጣችና፣
“ቀፋፊ! እብድ ነገር ነህ!” እያለችው ከተደበቀችበት አልጋ ስር ተነሳች፡፡ ጫማዋን አንስታ ሹል ታኮውን እያሳየችው ከንፈሯን ነክሳ መጣችበት፡፡
“እንዴት እንደማስብልሽ ላሳይሽ ፈልጌ ነው” አላት፣ በሽሽት እያፈገፈገ፡፡
“በእውነት? እንደዚህ ቀልቤን የገፈፍከው እንዴት እንደምታስብልኝ ልታሳየኝ ነው?” ስትለው፣ ወገቧን በሁለት እጁ ቀብ አድርጎ ከቆመችበት አነሳት፡፡ እንደ ባሌት ተጨዋች አሽከርክሮ አልጋ ላይ ወረወራትና እራታቸውን ሊያበሳስል ወደ ወጥ ቤቱ ሄደ። ሳህኖች ሲከፋፍት የተዘጋጀ ምግብ አገኘና፤
“የኔ ቆንጆ! እራትም ሰርተሻል?” አለ ባድናቆት እየተመለከታት፡፡ ግማሽ ፊቷን ሸፍኖ ትከሻዋ ላይ የወደቀውን ቢጫ ፀጉሯን ወደ ኋላ ወርወር አደረገችና፣
“ምን ዋጋ አለው፣ ቀዘቀዘ፡፡ ዛሬ ላስደስትህ ምግብ ሰርቼ ስጠብቅህ ጠፋህ፡፡ ይህን ያል ውጪ ያቆየኽ ምንድን ነው?” አለች፡፡ ሰሀኖቹን ይዞ ወደ ጠረጴዛው እየመጣ፤
“ፀሃይ ስትጠልቅ ባህሩ ላይ የረጨችበትን የሚያንፀባርቅ ቀይ ወርቃማ ቀለም እያየሁ ስዝናና አመሸሁ፡፡ የዛሬ ደግሞ ልዩ ነበር። የቀለጠ ወርቅ ባህር ላይ ሲንሳፈፍ እያየሽ ችላ ማለት ትችያለሽ? መሀሉ ላይ አይኖችሽን ስለማገኛቸው ማየት ከጀመርኩ መላቀቅ አልችልም” አላት፡፡  ሶፊያ በአነጋገሩ ተማርካ አንገቷን ወደ ትከሻው ዘንበል አደረገችና፤
“ሉክ!” አለችው፤ ስሙን በፍቅር እያቆላመጠች፡፡
“ወዬ! የኔ ማር!”
“ልቤን ሸርሽረህ ባትጨርሳት ምናለበት?” ከአልጋው ወርዳ መጣችና አብረው እራታቸውን በሉ፡፡ ሉካስ ሆዱን እያሻሻ፤
“ኡፍ! ቁንጣን ያዘኝ፡፡ አንቺ የሰራሽውን ምግብ ሳገኝ ለምንድን ነው ብዙ የምወስደው?” አለ፡፡ ከምግብ ጠረጴዛው ተነስቶ ሄደና ሶፋው ላይ በደረቱ ተጋደመ። ከደቂቃዎች በኋላ መጣችና ጀርባው ላይ በደረቷ ተጋደመችበት። እንደ አንበጣ ተነባብረው ቴሌቪዥን መመልከት ጀመሩ። ጆሮ ግንዱ ላይ ጣል ያደረገችው ቀኝ እጇን አምስት ጣቶች እንደሚዶ አሹላው ወደ ጸጉሩ ስትሄድ ሰሞኑን ስር ድረስ ስለተከረከመው አልያዝ አላት። ከርደድ ያለ አፍሪካዊ ጸጉሩ ጥንካሬ ከራሷ ልስላሴ ለየት ስለሚልባት ጣቶቿን እያስገባች መሞዠቅ ትወዳለች፡፡ ጸጉሩ አልያዝ ሲላት ተናዳ፤
“ጸጉርህን እንደዚህ ሙልጭ አድርገህ አትከርከም አላልኩህም?” አለች፡፡
“ብለሽኛል”
“እና?”
“ከጤና አንጻር ስለማየው ነው፡፡ ሀኪም መሆኔ አይደል፡፡ ያንቺም አይቀርለትም፡፡ ሰሞኑን እወስድሻለሁ”
“የት ?”
“ፀጉር አስተካካይ ቤት”
“ምላሴ ይታይሃል?”
“እያየሁት ነው፡፡ አታስገቢው ፎቶ ላንሳሽ። በነገራችን ላይ፣ ሀኪም ስል እጠይቅሻለሁ ብዬ የረሳሁት ነገር ታወሰኝ፡፡ ስትመረቂ የት ለመስራት አሰብሽ?”
“ይሄን ጥያቄ ስንቴ ነው የምትጠይቀኝ? መንግስት የሚመድበኝ ቦታ ነው አላልኩህም?”
“አዎ! አዎ! ግን…”
“ግን ምን?ጨርሰዋ!”
“እ….፣እኔ እንኳን ……” ብሎ አሁንም ዝም አለ፡፡
“ሉክ!" አለችው፤ “የምትደብቀኝ ነገር ካለ መብትህ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ጀምረህ እእእ…. እያልክ ልቤን  እእእ….አታድርጋት” ብላ አንድ ኩርኩም ሰጠችው፡፡
“ካንቺ የተደበቀ ነገር እንደሌለኝ ታውቂያለሽ፡፡ ከተመረቅሁ በኋላ እዚሁ መንግስት የመደበኝ ቦታ ልስራ ወይስ አፍሪካ ሄጄ ያቺን ምስኪን ሀገር ትንሽ ላገልግላት እያልኩ ከራሴ ጋር ሙግት ገጥሜያለሁ፡፡ አንዱ ላይ ማረፍ ስላቃተኝ ነው የማቃስተው” አላት።
ከሶፊያ ጋር በተዋወቁበት ሰሞን እዚህ ሀገር የመጣው በጉዲፈቻ መሆኑን፣ የትውልድ ሃገሩ ኢትዮጵያ የምትባለው የምስራቅ አፍሪካ ሀገር መሆኗን፣ የአየሯን ተስማሚነት፣ ጀግንነቷንና ታሪካዊነቷን በጨዋታ መሃል ነግሯታል፡፡ ከ5 ዓመት በላይ በጓደኝነት ሲኖሩ አንድም ቀን ወደ ትውልድ ሀገሩ ስለመመለስ አንስቶላት አያውቅም፡፡ ከሀሳቡ አዲስነትም በላይ መሄድ ማለት መለያየታቸው የመሆኑ ነገር በውስጧ በቀሰቀሰው ሁከት ተወስዳ ጸጥ አለች። ትወደዋለች፡፡ እንዳይሄድ መያዝ የፈለገች ይመስል፣ ጣቶቿን በእጁ ጣቶች አስገብታ እየጨመቀች  ውስጧን ማዳመጥ ጀመረች፡፡
(ከደራሲ ጌታቸው ተድላ አበበ "መንታ ነፍሶች" ታሪካዊ ልብወለድ የተቀነጨበ)


Read 1636 times