Monday, 16 May 2022 06:04

ባለ ‘ሀምሳዎች’ እና ባለ ‘ሀያዎች’

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “ብቻ መኪና የለኝም እንዳትለኝ…” ከሚሉ የሞራል አፍራሽ ብርጌዶች ተገላገልና! “አሁን አንተ የሦስት መቶ ሺህ ብር ቶዮታ ኤክስኪዩቲቭ ቢከብድህ አቶዝ አቅቶህ ነው!” ትሉ የነበራችሁ ወዳጆቻችን የት ናችሁ! ጥያቄ አለን...መኪና ‘ተፈትኖ የተመሰከረለት’ የእንትናዬዎች ማጥመጃ ዘዴ መሆኑ አሁንም አለ እንዴ!--;
            ኤፍሬም እንዳለ



             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ልክ እኮ የእኛ ሀገር የኑሮ መወደድ...አለ አይደል... “በህዝብ ጥያቄ የተደገመ...” የሚሉት የ‘ስንተዋወቅ አንተናነቅ’ ኮሜዲ አይነት ነገር አይሆንባችሁም፡፡ በቃ ይህኛው ትርኢት አልቆ መጋረጃ ሊወርድ ነው ስንል ደግሞ ተመልሶ ይመጣባችኋል። “ተመልካቾቻችን፣ የኑሮ መወደድ ይደገም ባላችሁት መሰረት ይኸው የተዋናዮቹን ቁጥር ጨምረን ደግመነዋል፣” የሚል ‘ኤም.ሲ.’ የሚሏቸው አይነት አስተዋዋቂ ነው የቀረው፡፡
ክፋቱ ደግሞ ምን መሰላችሁ...ከመደጋገሙና ‘እየተላመድነው’ ከመሄዳችን የተነሳ ‘ኖርማል’ ከሚባሉት ነገሮች አንዱ እንዳይሆን ነው፡፡
“አጅሬው በቃ ምኗንም፣ ምኗንም ቀባ እያደረግህ ሁልጊዜ ፈካ እንዳልክ ነው፡፡ ምናለ ሁላችንም እንዳንተ ኬሬዳሽ ብንሆን!”
“ጓደኛዬ፣ የጥንት የጠዋቱ ጓደኛዬ...እንደሱ ስትል ሰው ከሰማ ምቁነት እንዳይመስልብህ። ዘንድሮ እንደሁ ምቀኛ የሚመጣው ከጎረቤት ሳይሆን ከቤት ሆኗል።”
“እውነት እኮ ነው፡፡ ሩቅ ሳትሄድ እኔ አጠገብህ አለሁ አይደል... እስቲ ጠጋ ብለህ ፊቴን  ተመልከተው፡፡ ልክ ከረጢቱ ተቀዶ ሲሚንቶ የተደፋበት ይመስል ቡን ሲል አይታይህም?”
“ትያትሩን ተወውና ደህና አይደለህም እንዴ...ትንሽ ክብደትህ ቀነስብኝ ልበል!”
“አሹፍ፣ አንተ ምን አለብህ፡፡ ምን ደህንነት አለና ነው ደህና አይደለህም ወይ የምትለኝ! ጌታው እንደልቡ ንገረኛ፣ ምን ደህንነት አለ! የኑሮ መወደድ የሚሉት አልለቀን ያለ ጋኔን እያለ ምን ደህንነት አለ?”
“እኔ ደግሞ ቁም ነገር ይዘህ መጣህ ብዬ...”
“በአሁኑ ጊዜ ከኑሮ መወደድ የባሰ ቁም ነገር አለ እንዴ?”
“ጓደኛዬ...ጓደኛዬ...ምን ነካህ? የኑሮ መወደድ እኮ ‘ኖርማል’ ሆኗል፡፡ ብቻ እስከ ዛሬ አልለመድኩትም እንዳትለኝ!”
የምር ግን አንዳንድ ወገኖቻችን የማይቀር እንግዳ ነገር ያደረጉት ነው የሚመስሉት። የጓዳቸው እንዳለ ሆኖ በአደባባይ ግን አይሞቃቸው፣ አይበርዳቸው! ወይ ‘ኖርማል!’
እናማ...ይሄ የኑሮ መወደድ ነገር ፉክክር የያዙት ነጋዴዎቹ ናቸው ምርቶቹ? ቲማቲም ሆዬ “ሽንኩርት ሀምሳ ብር ገብታማ ዝም ብዬ ካየሁ ሞቻለሁ ማለት ነው፡፡ በቃ ሀያ አምስት ብር ገብቻለሁ!” አይነት ነገር ትል ይሆን እንዴ!
“ስማ፣ መቼም ሽንኩርት ሀምሳ ብር ገብቶ እንደነበር ሰምተሀል፡፡”
“ሰምተሀል! ከሚስቴ ጋር ቀንና ማታ ሀምሳ ጊዜ እያጨቃጨቀን ጭራሽ ሰምተሀል ወይ ትለኛለህ!”
“ምን ላድርግ ብለህ ነው፣ ግራ ቢገባኝ እኮ ነው፡፡”
“እና አንተ ግራ ገባህና እኔ  ምንድነኝ...አማካሪ ነኝ!... እንባ አባሽ ነኝ!...ሽንኩርት የመጠቀም መብት አስጠባቂ ኤን.ጂ.ኦ. ነኝ?”
“በቃ አንተ ቀጥ ብሎ የተነገረህን ነገር እንደ ቀለበት መንገድ ካላጠማዘዝክ አይሆንልህም?”
“ቆይ ቆይማ...ወይስ የሆነ ነገር አስበህ ኑዛዜህን እንድጽፍልህ ነው? አንተ አትኮሳተር፣ ስቀልድ ነው፡፡ እና..በሰላም ነው ያልለመደብህን ገና ቁርስ ሳይበላ እቤት የመጣኸው?”
“ምን መሰለህ... እንደው አንድ ሺህ ሁለት መቶ፣ ወይም ሁለት ሺህ ብር ብትፈልግልኝ ብዬ ነው፡፡”
“እንዴ አሳምሬ ነዋ! አንተ ጠይቀኸኝ እንዴት እምቢ እላለሁ”
“ቴንክ ! ቴንክ ዩ! እኔም እኮ ደረቴን ነፍቼ አንተ ዘንድ የመጣሁት እምቢ እንደማትለኝ ስለማውቅ ነው፡፡”
“ጓደኛህ አይደለሁ እንዴ! ምስጋና አያስፈለግኝም፡፡ ብቻ  የት ቦታ እንደጠፋብህ ንገረኝና ሀያ አራት ሰዓት ነው የምፈልግልህ! አንተ ሰውዬ ግን ይሄ እየሰነበተ ጭንቄህን ጦሽ የሚያደርግህ ነገር አልተወህም ማለት ነው!”
“እኔ ነኝ እኮ ሞኙ፣ አንተን ሰው ብዬ መጠየቄ!” (በአንድ ጊዜ ክርብት!)
“ምን አጠፋሁ?”
“ብር አበድረኝ  ነው ያልኩህ፡፡ ይሄን ሁሉ ያናግራል እንዴ?”
“በአሁኑ ዘመን እኔን ብድር ስትጠይቅ ትንሽ አይሰቀጠጥህም? ስማ ብር አበደርኝ አትበለኝ እንጂ ከፈለግህ ሌላውን ሙልጭ አደርገህ የምትሰድበበት ቀሽት፣ ቀሽት የሆነ ስድብ ላበድርህ እችላለሁ፡፡
“አየህ ማን ጭንቄውን ጦሽ እያደረገው እንደሆነ አሁን ታየ!”
እናላችሁ...እንዲህ ሲሆን ‘ቤስት ፍሬንድነት’ ውሀ በላት ማለት አይደል! አስቸጋሪ ነው፡፡ የምር በጣም አስቸጋሪ ነው።
እኔ የምለው... የምር ግን ለምንድነው በአስራ አምስት ሚሊዮን ብር መኪና ገዝታችሁ ገንዘብ የሚተርፋችሁ ወገኖች...አለ አይደል... ‘እስኪበቃው አጠጣው የስድብ ኤክስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ምናምን የማታቋቁሙልንሳ! አሀ...ትንሹም፣ ትልቁም ይህን ያህል እየተካነበት ከሆነ ዶላሯንና ዩሮዋን እናግኝበታ!
“ስሚ ያ እንትና የሚሉት ልጅ መንገድ ላይ የሆነች ምስኪን አንቆ ይዞ ካልገደልኩ ሲል፣ ፖሊስ ብቅ ሲልበት እግሬ አውጪኝ አይል መሰለሽ!;
“እሱ ልጅ ግን የማን ልጅ ነው?”
“የዛች ከእኔ ቤት በታች ያለችው ሴትዮ...”
“ውይ ያቺ ፍየል ምላስ ተሳዳቢዋ!”
እናማ ለኤክስፖርት የሚያበቃ አቅም አለን ለማለት ያህል ነው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...
እንደው.. አለ አይደል...ለወራት ይቅርና ለጥቂት ሳምንታት “እፎይ...” ማለት ብርቅ ሆኖ ይቅር!
እኔ የምለው... ገና በቅጡ እንኳን ምን ልትሉት እንደፈለጋችሁ ሳያውቅ ተጣድፎ “እደውልልሀለሁ” እያለ እጁን እያውለበለብ የሚሄድ ሰው ምን ማለቱ መሰላችሁ፣ በቃ...”በህግ አምላክ እንዳትጠጋኝ! አይደለም ለአንተ የምሰጠው ብደር ሊኖረኝ ማሳጅ እንኳን ከገባሁ አራት ቀን ሊሞላኝ ነው፤” ማለቱ ሊሆን ይችላል፡፡ (ስሙኝማ... ስለ ማሳጅ ቤቶችማ “በእውነት ላይ የተመሰረተ ታሪክ” ነገር የሆነ ሰው ልቅም አድርጎ ሊነግረን ይገባል!) እኔ የምለው... ብድር ፈላጊዎች ... ገና ስንታይ እናስነቃለን እንዴ! ማለት እንደው ዓይናችንም፣ ግንባራችንም፣ ምናምናችንም “ብድር የምትሰጠው ገንዘብ ያለህ እዚህ ነኝ በል!” ብሎ ተጽፎብናል እንዴ! አሀ እንደዛ ትንፋሽ እስኪያጥረን እንተቃቀፍ እንዳልነበረው፣ በቃ በሩቁ ሀይ፣ ሀይ ሆኖ ይቅር! አሀ...ተፈራራና!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ አንድ አቶዝ ነው ምናምን የሚሏት መኪና ነበረች አይደል! አሀ...‘ፍሬንዶች’ ምንም ዘመን ቢገለባበጥ እንዴት ትረሳለች...ስንቷን ከስንቱ እጅ ያስነጠቀች! እና እሷ ስድሳ ሺህ ብር ነው ምናምን ነበረች አይደል! ጉድ! ጉድ ተብሎ! እናላችሁ.... አሁን ባለ አስራ አምስት ሚሊዮን፣ ባለ ሀያ ምናምን ሚሊዮን መኪኖች መጡላችሁና፣ ቁጥር ምን ማለት እንደሆነ ግራ እየገባን ነው፡፡ መኪና...ሀያ ምናምን ሚሊዮን ብር! ያውም በእኛይቱ ‘ጦቢያ!’ ለእኛማ...ትንሽ እፎይ አለን፡፡ ልክ ነዋ!
“ብቻ መኪና የለኝም እንዳትለኝ…” ከሚሉ የሞራል አፍራሽ ብርጌዶች ተገላገልና! “አሁን አንተ የሦስት መቶ ሺህ ብር ቶዮታ ኤክስኪዩቲቭ ቢከብድህ አቶዝ አቅቶህ ነው!” ትሉ የነበራችሁ ወዳጆቻችን የት ናችሁ! ጥያቄ አለን...መኪና ‘ተፈትኖ የተመሰከረለት’ የእንትናዬዎች ማጥመጃ ዘዴ መሆኑ አሁንም አለ እንዴ! አይ...አለ አይደል... ‘ካልኩሌሽኑ’ን ስንሞክረው የአስራ አምስት ሚሊዮን ብር መኪናን “ለአንቺ ስጦታ የገዛሁልሽ ነው፣” ማለት እንደ አቶዟ “እንኪ ቁልፉን፡፡ የአንቺ ነው፣” እንደማለት ይቀላል እንዴ!
ሰዋችን በአስራ አምስትና በሀያ ሚሊዮኗ ህንጻ ሳይሆን መኪና እየሸመተ ነው የሚሉትን ነገር ሰምተን ነገረ ሥራችን ግርም ስላለን ነው። እዚህ ለሀምሳ ብር ሽንኩርት ማቃሰት፣ እዛ ለሀያ ሚሊዮን መኪና ጥርስ በጥርስ መሆን! ይህ ሁሉ በዚቹ ምድርና ይህን በመሰለ ዘመን። እናማ የባለ ‘ሀምሳዎች’ እና የባለ ‘ሀያዎች’ ሀገር ሆናለች ለማለት ያህል ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1490 times