Tuesday, 17 May 2022 00:00

በየአመቱ 4.8 ሚ. አህዮች ለህገወጥ ንግድ ይታረዳሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በዚምባቡዌ በ5 ወራት ብቻ 60 ሰዎች በዝሆን ተገድለዋል



            በመላው አለም በሚገኙ የተለያዩ አገራት በየአመቱ 4.8 ሚሊዮን ያህል አህዮች በህገወጥ ንግድ እየተሸጡ ለባህላዊ መድሃኒት መስሪያ ተብለው እንደሚታረዱና በዚህም አህዮችን ጭነትን ጨምሮ በዕለት ከዕለት ኑሯቸው ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚጠቀሙ በርካታ አርሶ አደሮች ተጎጂ መሆናቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ዶንኪ ሳንክቿሪ የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ያወጣውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአህዮችን ቆዳ ጨምሮ የተለያዩ አካሎቻቸው ለተለያዩ ባህላዊ መድሃኒቶች መስሪያነት ለማዋል ሲባል ፌስቡክና ዩቲዩብን በመሳሰሉ ማህበራዊ ድረገጾች ሳይቀር በአሻሻጮች አማካይነት በህገወጥ መንገድ እየተሸጡ በስውር እርድ የሚከናወንባቸው ሲሆን፣ ብዙ አህዮች ከሚሸጡባቸው አገራት መካከል ቻይና ቀዳሚነቱን ትይዛለች፡፡
ቻይና የአህያ ግብይት ስምምነት የፈጸመችው ድርጊቱን በህግ ካጸደቁ 20 የአለማችን አገራት ጋር ብቻ ቢሆንም፣ ከ50 በላይ ከሚሆኑ አገራት አህዮች ወደ ቻይና እንደሚገቡም የተቋሙ ጥናት ያመለክታል፡፡
በርካታ አህዮች ከሚሸጡባቸውና ከሚታረዱባቸው አገራት መካከል አብዛኞቹ ድርጊቶቹን በህግ የከለከሉ መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ከእነዚህ አገራት መካከልም ኬንያ፣ ናይጀሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሴኔጋልና ጋና ይገኙባቸዋል፡፡
ተቋሙ በአለማቀፍ ደረጃ አህዮችን የሚሻሽጡ 382 ያህል የግብይት ድረገጾች እንደሚገኙ የገለጸ ሲሆን፣ አሻሻጮቹ እንደ አደንዛዥ ዕጽና የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ቡድኖች አለማቀፍ ስውር ትስስር እንዳላቸውም አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ በዚምባቡዌ ባለፉት 5 ወራት ብቻ 60 ያህል የአገሪቱ ዜጎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በዝሆኖች  በደረሰባቸው ጥቃት ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በአለማችን በዝሆኖች ብዛት ከቦትሱዋና ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃን በያዘችውና ከ100 ሺህ በላይ ዝሆኖች ባሉባት ዚምባቡዌ፣ ዝሆኖች በየአመቱ በ5 በመቶ ያህል ብዛታቸው እንደሚጨምርና ተገቢው ጥበቃ የማይደረግላቸው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ወደ መኖሪያ መንደሮች እየገቡ ንብረት እንደሚያወድሙና ከሰዎች ጋር ከፍተኛ ግጭት እንደሚፈጥሩ፣ በዚህ አመት ብቻም፣ በዝሆኖችና በሰዎች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች 60 ሰዎች መገደላቸውንና ሌሎች 50 ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ መንግስት ከሰሞኑ ማስታወቁ ተነግሯል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 በተመሳሳይ ሁኔታ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር 72 እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በከፍተኛ መጠን ለሚያድገው የዝሆን ብዛት መፍትሄ ካልተበጀለት ጉዳዩ አገር አቀፍ የግጭት ቀውስ ሊፈጥር ይችላል መባሉንም  አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2653 times