Saturday, 21 May 2022 10:56

“መካር የሌለው ንጉሥ፣ ያለአንድ ዓመት አይነግሥ!”

Written by 
Rate this item
(3 votes)


                 ከዕለታት አንድ ቀን አራት ልጆች የነበሯቸው አንድ አባት የመሞቻቸው ጊዜ መቃረቡ ሲታወቃቸው፣ ልጆቻቸውን ጠርተው፤
“ልጆቼ፤ እንግዲህ ሰው ሆኖ፣ መሞት  አይቀርምና ያለኝን ሀብትና ንብረት ልናዘዝላችሁ። ለትልቁ ልጄ እዚህ ከተማ ማህል ያለውን ትልቁን ቤት አውርሼሃለሁ!
ለመካከለኛው ልጄ፤ ገጠር ያለኝን ቤትና የእርሻ ቦታ ሰጥቼሃለሁ።
ለሶስተኛዋ ልጄ፤ የሚታለቡና የሚረቡ፣ የሚወልዱና የሚዋለዱ ላሞቼን አውርሼሻለሁ።
ለአንተ ለትንሹ ልጄ፤ ከሁሉም በላይ የሆነውን ውርስ እሰጥሃለሁ።”
ትንሹ ልጅ በጉጉት፤
“ምንድነው የምትሰጠኝ አባባ?”
አባት፤
“ምክር። ምክር ነው የምሰጥህ። ምክር ከሁሉ ነገር በላይ ነው።;
ልጅ፡- “ምን ዓይነት ምክር ነው?”
አባት፤
“ታገሠኝ። ልነግርህ ነው።
1. ጥበበኛ ሁን። ከብልጠት ይልቅ ብልህነት ይግዛህ!
2. ጊዜህን ዕወቅ! ቃታህን አትልቀቅ!
3. መካርህን እሻ።
መካር አጨብጫቢ አይደለም። ወሬ አቀባይም አይደለም። ነገረ-ሠሪ አይደለም። አጓጉል ፖለቲከኛም አይደለም። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባይዋ አህያም ዓይነት አይደለም። (apre moi le deluge እንዲል ፈረንሳይ) ጥሩ መካርህ ለአንተ አጋዥ አጋርና ወገንህ ነው!
4. መናቢ፣ ሰው አማኝ እና ተስፋ-አድራጊ ባልንጀራ ይስጥህ።
5. አዲስ አድማስ፣ አዲስ ንፍቀ-ክበብ ናፋቂ ሁን። ሀሳብህንና ትምህርትህን ይግለጽልህ፡፡
6. ከንግግርህ ቁጥብ ሁን። ለመናገር አትቸኩል። እርጋታን ተላበስ።
7. ገዢ ሁን። የአካባቢህ ተቆጣጣሪ፣ ኃላፊ የመሆን አቅሙን አይንሳህ!
8. እንደ እናት ሩህሩህ እና ለአካባቢህ አዛኝና ተንከባካቢ ያድርግህ!
9. ራዕይ ያለው ሰው ሁን! ከበጎ አድራጊና ከጥቅም-ፈላጊ የተሻለውን አስተውል! ለይና አብረህ ሁን!
10. ልብና ልቦና ይስጥህ፡፡
11. ሥርህን አውጠንጥን። ሥር የሌለው ሥርህን ከመንቀል ወደ ኋላ አይልምና መሰረትህን ጠብቅ። አጥብቅም!
12. ጀግናን ውደድ እንጂ አታምልክ!
13. አምፅ። አመጽህ ግን ለህዝብህ በጎ እንጂ ለግል ጀብድህ አይሁን!
14. ቀልድ ውደድ። ህይወት ያለቀልድ ለዛቢስና ፈዛዛ ናት! ቀልድህ ግን ቁም ነገር አዘል ይሁን!
15. ሌሎች የሰሩትን አድንቅ። አፅና!
    ለምን አልሰራሁትም ብለህ አትቅና! ይልቅ ተቆጭና ዕድሜህን አቅና!
    ገና ብዙ የምትሰራው ነገር ይጠብቅሃልና!
    በመጨረሻም፤
16. ኩሉ አመክሩ፣ ወዘሰናየ አጽንዑ!
(ሁሉንም ምከሩ፣ የተሻለውን አጽኑ) የሚለውን ቃል አጥብቀህ ያዝ!
17. የዚህ ሁሉ ማሰሪያው ፍቅር ማወቅ ነውና፤ አፍቅር! ፍቅር ስትሰጥ ፍቅር ታገኛለህ!
***
ምክሮች ምክር የሚሆኑት የሚሰማ ሲገኝ ነው! ማንም አይስማ፤ መናገር ያለበት ይናገራል። ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው፤
#በታፈንክ ቁጥር ነው ድምጽህ ይበልጥ የሚጠራ!”
የዱሮ ታጋዮች እንዳሉትም ደግሞ ዛሬም “ምላሴን ተውልኝ!” እንላለን። ለዲሞክራሲ እንቆረቆራለንና! ማንም ምንም ቢል ውልፊት አንልም። ቁጭትም ቅጭትም አይኖርብንም። “ካፍ  ከወጣ አፋፍ;ም፣ “ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባበትም”ም፣ “ባፍ ይጠፉ፣ በለፈለፉ;ም አንልም። ተናጋሪውን ይጭነቀው! #ከሺ ጦረኛ አንድ ወረኛ; ብለንም፣ ለወሬኞች እጅ አንሰጥም! “የተማረ ይግደለኝ!” ብለንም አንሞኝም- “ዩኒቨርስቲ ደጃፍ ተኛ!” የሚል አፈ-ጊንጥ አለና! የሆነው ሁሉ ሆኗልና ጸጸታችንን አናመነዥግም!
“አንዴ የሆነውን ነገር፣ እኮ ለምን ሆነ ማለት፤
 ለማለት ብቻ ማለት!”
(እያጎ-ኦቴሎ ሼክስፒር፣ ሎሬት ጸጋዬ እንደተረጎመው)
ኢትዮጵያ ከዘመነ-መሳፍንት ጀምሮ በርካታ መሳፍንትና ነገስታት ተፈራርቀውባታል፡፡ ከሩሲያ ነገስታትም ከአስትሮ ሐንጋሪያን ግዛት -አስፋፊያንም ወይም  ከፈረንሳዮቹ (ፕሌቢያን እና  ፓርቲሺያን ገዢዎችም) ሁሉ  የማይተናነሱ  ገዢዎች አጥታ የማታውቅ ቢሆንም፣ ድህነቷን አክብራ፣ “ታፍራና ተከብራ” የኖረች አገር ናት! ዛሬም ስለመከበሩ እንኮራባታለን! ማንነቱ የተደፈረበት የአፍሪካ አገርም ሁሉ ይኮራባታል! በቅርቡ ያከበርነው “የአድዋ በዓል” ያልደበዘዘ ልዕልናችን ነው!
አፍሪካን አንድ የሚያደርግ ታሪክ ያላት አገር፣ ልጆቿን አንድ ማድረግ ለምን አቃታት? የሚል፣ልባም ሰው መቼም አይጠፋም!
እዚህ ላይ ከቅርቡ የጣሊያን ወረራ ጊዜ እንጀምር (1928-1933 ዓ.ም) ብንል፣ ያኔ ባንዳ እና አርበኛ የሚል ስም ተከሰተ! አገር ወዳድና ከዳተኛ እንደማለት ነው! መንግስቱ ነዋይና ግርማሜ ነዋይ፣ ዋና የለውጥ ማነሳሻ  መዘውር  ሆኑ፤ የዐመፅ ጥንስሱ ሆኑ (እንደ ሪቻርድ ግሪን ፊልድ ነገረ- ታሪክ) ከዚያ ወታደሩ ተነሳሳ፡፡ ተማሪውም መንግስትን እረፍት ነሳ፡፡ ባላገሩ እዚህም እዚያም እምቢኝ- አልገዛም አለና ገሰለ! አሻፈረኝ ዘይቤው አደረገ! በዚህ መሀል “የሆድ ነገር ሆድ  ይቆርጣል; ነውና የቤንዚን ውድነት፣ የአውቶብስና  የታክሲ ዋጋ መናር የምስኪኑ ህዝብ ኑሮን ለመቋቋም አለመቻል ዋና ጉዳይ ሆነና፣ ወደ ምሬት ወደ አመፅ  ወደ ስራ ማቆም፣…. ወደ መንግስትን መገርሰሱ ተጓዘ! መንግስትስ? “ስዩመ-እግዚአብሔር ነኝ!; የሚለውን ዕምነቱን  አጠበቀ፡፡ እንዳሰበው ሳይሆን ቀረና ወደቀ! ተንኮታኮተ!
ያን ጊዜ በመንግስት ሚዲያ፣ በኢትዮጵያ አንድ ለእናቱ ቴሌቪዥን የታየው፣ በተዋናይ ዳሬክተር ተፈራ ብዙአየሁ የተዘጋጀና የተሰራው፣ “የእሳት አደጋ” የተሰኘው ድራማ፤ ሁኔታውን እጅግ ያፀኸየና ፍንትው ያደረገ ትዕይንት ነበር፡፡ ግን ማን ሰምቶ!?
“አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
 መስማት ከማይፈልግ የባሳ ደንቆሮ?!”
(ከበደ ሚካኤል)
አለመስማት ለአያሌ ነገሮች ዳርጎናል፡፡
“ፋሺስት” እና “ባንዳ” አባብሎናል!
“ኢህአፓ; እና #መኢሶን; አባብሎናል!
“ደርጊስት; እና #ፀረ- ደርግ” አሰኝቶናል!
“ፊዲስትና (የኃይሌ ፊዳ (የመኢሶን መሪ) ተከታይ አስብሎናል! ጸረ-ፊዲስት የሚል ምዳቤ አሰጥቶናል፡፡
ከሀሳብ ጦርነት ወደ ደም መፋሰስ ከትቶናል!
መደበኛ ትምህርት እንድናቆም አስገድዶናል! ሥራ ማቆም ግድ ሆኖብናል!...
ምኑ ቅጡ!
ዛሬም፤ ወደድንም ጠላንም ያ ክፉ ቀን እንዳይደገም መሆን አለበት! የቀመሰ ያውቀዋልና #አደራ!; ቢል መጪውን ትውልድ የማዳን ያህል ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፤ “ጥረታችን ስለ ትናንት የሚባለውን የሚያዳምጥ ሁነኛ መንግስት ለመፍጠርና ለማሳደግ ነው!” ልብ ያለው መንግስት፣ ይሄን ልብ ይላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን!
“ተስፋ ባጣ ምድረ-በዳ
ያንድ ዕውነት ይሆናል ዕዳ!”  ሳንባባል እንግባባለን የሚል ዕምነት አለን፡፡
የበዓል ሰሞናችን ብዙ ነው፡-
-እንቁጣጣሽን ለምን ወደድነው? በዘመን መለወጥ  ስለምናምን!
-ደመራን ለምን ወደድነው? ከየቦታው የሠበሰብነውን ችቦ አንድ ላይ ስለምናበራ!
ትንሳኤን ለምን  ወደድነው? ዳግም ስለምንነሳ!
ፋሲካን ለምን ወደድነው? ፆመን ፆመን ስለማንቀር
ባህላችንን ለምን ወደድነው? ከአሁጉራት፤ ከአገራትና ከዓለም ህዝቦች ሁሉ፤ መለያችን ስለሆነ!
እነሆ ይሄን ሁሉ ካልን ዘንዳ፣ ማናቸውም የፓርቲ ኃላፊ፣ የድርጅት አለቃ፣ የማህበር ተመራጭ ወይም የቀበሌና የከፍተኛ ሊቀ-መንበር፤አንዳች ግንዛቤ እንዲጨብጥ እንሻለን፡-
“ብርቱ ብርቱ ሰዎችን፤ ከራሳቸው ጥቅም በላቀ ደረጃ ለአገር አሳቢ የሆኑ አገር ወዳዶችን፤ ከመንቀፍ በተሻለ ማገዝና መለወጥን የሚፈልጉ ልሂቃንን፣ የምታሳድግና የምታበረታታ ምድርን ለማለምለም፣ የሚታትሩ ዜጎችን፤ የምትወልድ ልጆች ይስጠን!; የምንል ጀግኖች ያድርገን! እጣ ፈንታችን እጃችን ላይ ነው፡፡ አገራችንን ለማሳደግ የሚችሉ አዕምሮዎችን እናማክር-አለበለዚያ፡-
“መካር የሌለው ንጉስ
አለ አንድ ዓመት አይነግስ!” የሚለው ብሂል ዕውን ይሆናል፡፡
የሚያዳምጥ ንጉስ አያሳጣን!
“እሠይ! እሠይ!” የሚሉ “የጎሽ-ጎሽ!” ኮሚቴ አባላትን ሳይሆን “ዋ!”  ብለው የሚያስጠነቅቁ አማካሪዎችን በብራ ቀን፣ በፋኖስ፣ እንደ ዲዮጋን መፈለግ ነው የሚያዋጣን!    
ትምህርታችንን ይግለጥልን!!


Read 11895 times