Saturday, 21 May 2022 10:58

ፋኖ ምን ይደረግ?

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

  #--ሌላው ግንዛቤ ሊቸረው የሚገባው ጉዳይ ፋኖ የሚለው ስያሜ ለአንድ ማህበረሰብ (ለአማራ) ብቻ የተሰጠ ስያሜ አለመሆኑ ነው፡፡ በውዴታ ወይም በገዛ ፈቃዱ ሀገሩንና ህዝቡን ከጥቃት ለማዳን የዘመተ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ፣ አገው፣ ቅማንት፣ ትግሬ፣ ሐረሪ፣ ሐመር፣ ሸክቾ፣ ማኤኒት፣ አኙዋክ፣ ጉሙዝ፣… ሁሉ “ፋኖ” ነው፡፡ ይህንን ወዶ ዘማችነቱን ግን ሁሉም በየራሱ ቋንቋ ሊጠራው ይችላል፡፡--;
                 (ከአብዱራህማን አህመዲን፤
                  የቀድሞ የፓርላማ አባል)
                ባለፈው ሳምንት በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “ፋኖን እንደ ጃንጃዊድ ሚሊሻ?” በሚል ርእስ ባቀረብኩት መጣጥፍ መቋጫ ላይ “ፋኖ እንዴት ይደራጅ?” የሚለውን ጥያቄ በማንሳት በጉዳዩ ላይ በዚህ ሳምንት በክፍል 2 እንደምመለስበት በገባሁት ቃል መሰረት እነሆ ተመልሼ መጥቻለሁ፡፡ ወደ ዛሬው ጽሁፌ ከማለፌ በፊት ከባለፈው ሳምንት ማስታወሻ ላይ ለመንደርደሪያ የሚሆኑ ጥቂት ነጥቦችን ደግሜ ባቀርብ ያለፈውን ሳምንት መጣጥፍ ላላነበቡ የጋዜጣው ታዳሚዎች ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡
“ፋኖ” የተሰኘውን ነባር ማህበረሰባዊ ስብስብ በተመለከተ የመዝገበ ቃላት ትርጉሙ “ሳይታዘዝ በፈቃዱ የሚዘምት፣ ወዶ ዘማች” ማለት መሆኑን፤ ከዚህ ነባር የቃሉ ትርጉም ስንነሳ የዘመናችን “ፋኖ” ከመንግስት ትጥቅና ስንቅ ሳይሰጠው፣ ደመወዝ ሳይከፈለው፣ ያለውን የጦር መሳሪያ ይዞ በራሱ ፈቃድ ዘምቶ ሀገሩንና ህዝቡን ከአሸባሪ ኃይል ጥቃት መመከቱን፤ ስሙ እንደሚያመለክተው ፋኖ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ያለው የወዶ ዘማች ስብስብ መሆኑን፤… ባለፈው ሳምንት በታተመው መጣጥፍ ላይ ለማሳየት ጥረት ተደርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አንዳንዶች ፋኖን እንደ ሱዳኑ የጃንጃዊድ ሚሊሻ አሸባሪ ከመቁጠር አልፈው “ፋኖ በአሸባሪነት ይፈረጅ” የሚል ዘመቻ መክፈታቸውን፤ ነገር ግን የጃንጃዊድ ሚሊሻ እና ፋኖ በስያሜም፣ በአፈጣጠርም፣ በዓላማም ሆነ በተግባር ሰፊ ልዩነት ያላቸው መሆኑን ለማሳየት ተሞክሯል - ባለፈው ሳምንት በቀረበው መጣጥፍ፡፡
ለትውስታ ያህል ይህን ካልኩ ወደ ዛሬው ጽሁፌ ላምራ… ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገራችን የፖለቲካ መድረክ ላይ ጎልተው ከሚጠቀሱ “ማህበረሰባዊ ቡድኖች” ውስጥ አንዱ ፋኖ ነው፡፡ ፋኖን በጥሩም በመጥፎም የሚያነሱት ወገኖች አሉ፡፡ በጥሩ የሚያነሱት “ፋኖ የጀግንነት ጥግ፣ የሀገርና የህዝብ አለኝታ፣…” ነው በማለት ያወድሱታል፣ ያሞግሱታል፣ ይኩራሩበታል፣ ይመኩበታል፡፡ ፋኖን በመጥፎነት የሚያነሱት ወገኖች ደግሞ ስሙ ሲጠራ ይርዳሉ፣ ይርበደበዳሉ፣ ይሸበራሉ፣ የሚገቡበት ይጠፋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ፍርሃታቸውን ለመደበቅ “ፋኖ ዘራፊ ነው፣ ፋኖ አሸባሪ ነው፣ ፋኖ ምህረት የለሽ ነው፣…” የሚል ጥላሸት በመቀባት ስሙን ያጠፋሉ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ “ፋኖ አሸባሪ ተብሎ ይፈረጅ” የሚል ዘመቻ መጀመራቸውን ሰምተናል፡፡
የሚገርመው ነገር የዛሬ ዓመት በመከላከያ ሰራዊት ጄኔራሎች ጭምር “ከጥቃት ያተረፈን፣ ከከበባ ሰብሮ ያወጣን…” ተብሎ በጀግንነቱ ሲወደስ የነበረው ፋኖ ዛሬ ውለታው ተረሳና፤ የሀገር አለኝታነቱ፣ ለወገን ደራሽነቱ ተዘነጋና “ኢ-መደበኛ ነው” የሚል ታርጋ ተለጥፎበት፣ የ“ይፍረስ” ጥያቄ ሲነሳበት እያየን እየሰማን ነው፡፡ አልፎ ተርፎ እንቅስቃሴውን ለመገደብ ኬላ አቁመው ትጥቅ እንዲፈታ ከማድረግ አልፈው አባላቱን ተኩሰው እስከ መግደል እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑንም ሰምተናል፡፡
በጭንቅ ወቅት “ጥምር ጦር” እየተባለ ሲሞካሽ እንዳልነበረ ዛሬ መንግስት ጭምር “ፋኖ ኢ-መደበኛ ነው፣ ይፍረስ…” የሚል መንፈስ ያለው አቋም ሲያራምድ ማየት ያስተዛዝባል፤ ያሳዝናል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች በበኩላቸው፤ “ፋኖ አሸባሪ ነው፣… ይፍረስ ይበተን፣ ለፍርድ ይቅረብ፣ ትጥቅ ይፍታ…” ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ሌሎች ወገኖች ደግሞ “ፋኖ የህዝብ አለኝታ ነው፣ ማንም ዝንቡን እሽ አይበለው፣…” በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ እንሰማለን፡፡
በመዝገበ ቃላት ትርጉሙ ላይ እንደተገለጸው ፋኖ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ያለው “ወዶ ዘማች” መሆኑ ከታወቀ፤ የፋኖ ጉዳይ አጨቃጫቂ፣ አነታራኪ፣ አወዛጋቢ፣… መሆን የለበትም ባይ ነኝ፡፡ ይልቁንስ አሁን መነሳት የሚገባው “ፋኖ በቀጣይም የሀገር አለኝታነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ዘመኑን የዋጀ አደረጃጀት እንዴት እንፍጠርለት?” የሚል ጥያቄ ነው እንጂ የይፍረስ - አይፍረስ አታካሮና እሰጥ-አገባ መነሳት አለበት የሚል እምነት የለኝም፡፡
ሌላው ግንዛቤ ሊቸረው የሚገባው ጉዳይ ፋኖ የሚለው ስያሜ ለአንድ ማህበረሰብ (ለአማራ) ብቻ የተሰጠ ስያሜ አለመሆኑ ነው፡፡ በውዴታ ወይም በገዛ ፈቃዱ ሀገሩንና ህዝቡን ከጥቃት ለማዳን የዘመተ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ፣ አገው፣ ቅማንት፣ ትግሬ፣ ሐረሪ፣ ሐመር፣ ሸክቾ፣ ማኤኒት፣ አኙዋክ፣ ጉሙዝ፣… ሁሉ “ፋኖ” ነው፡፡ ይህንን ወዶ ዘማችነቱን ግን ሁሉም በየራሱ ቋንቋ ሊጠራው ይችላል፡፡ ስለሆነም፤ “ፋኖነትን” በዘመናዊ አደረጃጀት፣ ተጠያቂነት ባለው መልኩ፣ በሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች እንዲተገበር ህግና ስርዓት ማበጀት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በኔ እይታ ፋኖ ዘር የለውም፡፡ ፋኖነት ኢትዮጵያዊ አርበኝነት ነው፡፡ እናም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፋኖ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ራሴ መሳሪያ አልባ ፋኖ ነኝ፡፡ ከሰሜን ወሎ ሽርጥ ለባሽ ዘመዶቼ ከእነ ሼህ ሀሰን ከረሙ ጋር፣ ከእነ ደምሌ አራጋው ጋር፣… ከአላማጣ እስከ ደብረሲና በብዕርም፣ ድጋፍ በማሰባሰብም፣ በመረጃ ስርጭትም… ተዋግቻለሁ፡፡ ዛሬ እነ ሼህ ሀሰን ከረሙ እና እነ ደምሌ አራጋው ወደ ግብርናቸው ተመልሰዋል፡፡ እኔም ወደ ግል ስራዬ ተመልሻለሁ፡፡ ፋኖነት እንዲህ ነው! እውነተኛዎቹ ፋኖዎች ጠላት ሀገርና ህዝብን ባስቸገረበት ወቅት፣ መሳሪያቸውን ወልውለው፣ በገዛ ገንዘባቸው ጥይታቸውን ገዝተው ስራቸውን ሰርተው ወደየቤታቸው ተመልሰው፣ መሳሪያቸውን አስቀምጠው ዛሬ ላይ መደበኛ ስራቸውን እየሰሩ ነው፡፡ ፋኖ ነኝ እያለ መሳሪያ አንግቦ በየከተማው እንገፍ እንገፍ የሚለው እውነተኛው ፋኖ ነው ብዬ አላምንም፡፡ እንዲህ ያለው ፋኖ ነኝ ባይ ነው በመዝገበ ቃላቱ “አውደለደለ፣ ቦዘነ” (አውደልዳይ ቦዘኔ) የሚል ትርጉም ነው  የተሰጠው፡፡ እናም፤ በፋኖ ስም የሚነግዱ ሌቦችን - ሌባ፣ ዘራፊዎችን - ዘራፊ፣ አሸባሪዎችን - አሸባሪ ልንላቸው ይገባል፡፡በመጨረሻም፤ አንድ ነገር ብዬ ጽሁፌን ልቋጭ… ይህ ሁሉ እርጥቡም ደረቁም፣ ድንጋዩም ጠጠሩም… በፋኖ ላይ የሚወረወረው፣ ፋኖ ጣፋጭ ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ ስለሆነ ነው እንጂ ፋኖ መራራ ፍሬ የሚያፈራ እምቧይ ቢሆን ኖሮ ዞር ብሎ የሚያየው አልነበረም፡፡ እናም ይህንን ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ፍሬ የትም መበተን ጥፋት ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ፋኖን በተመለከተ መፍትሄው ትጥቅ ማስፈታት ሳይሆን ህግ አውጥቶ ፋኖን ተጠያቂነት ባለው አደረጃጀት እንዲደራጅ ማድረግ ነው፡፡ መፍትሄው ፋኖ እንዲበተን ማድረግ ሳይሆን ፋኖ በአግባቡ ሰልጥኖ ወደ ቤቱ ተመልሶ፣ መሳሪያውን አስቀምጦ በመደበኛ ስራው ላይ እንዲሰማራ ማድረግ ነው፡፡
**
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 5540 times Last modified on Saturday, 21 May 2022 13:38