Saturday, 21 May 2022 11:28

በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  አሜሪካ ባለፉት 17 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በአጠቃላይ 381 ሜዳልያዎች(170 የወርቅ፤ 117 የብር እና 94 የነሐስ) በመሰብሰብ በምንግዜም ከፍተኛ 200 አገራትን የወከሉ ከ2000 በላይ አትሌቶች ይወዳደራሉ፤ ከ3000 በላይ የሚዲያ ባለሙያዎች ከመላው ዓለም ይሳተፉበታል፡፡
በአፈታሪክ የሚታወቀው ምስጥራዊ ፍጡር ቢግ ፉት ልዩ ምልክት ሆኗል፡፡
ከ9.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሽልማት ገንዘብ ተዘጋጅቷል፡፡
ውጤት ዓለምን እንደምትመራ ይታወቃል፡፡
ለመስተንግዶ የጠየቀው በጀት ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡


            የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዓለም ዋንጫና ከኦሎምፒክ ቀጥሎ የሚጠቀስ የዓለማችን ግዙፍ የስፖርት መድረክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የዓለማችንን ምርጥ አትሌቶች በአንድ መድረክ የሚያሰባስበው ሻምፒዮናው፤ ከ39 ዓመታት በፊት በፊንላንድ ሄልሲንኪ የተጀመረ ነው፡፡  ከ56 ቀናት በኋላ ደግሞ በኦሪጎን ከተማ  አሜሪካ ላይ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሲካሄድም 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚል ስያሜ ይሆናል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን መሳተፍ በዓለም ዙርያ ለሚገኙ ፕሮፌሽናል አትሌቶች  የህይወት ዘመን ትልም  ነው፡፡ አገራቸውን በመወከል በሩጫ፤ በዝላይና በውርወራ ስፖርቶች የዓለም ምርጥ መሆናቸውን ያስመሰክሩበታል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛውን የገንዘብና የሜዳልያ ሽልማት ያገኙበታል፡፡ በስፖርቱ ታሪክ አስደናቂ እና አንፀባራቂ የሚባሉ ታሪኮችን ያስመዘግቡበታል፡፡ በ10 ቀናት ውስጥ በ24 የስፖርት ምድቦች ከ163 በላይ ውድድሮችን የሚያስተናግደው ሻምፒዮናው ከ3ሺ በላይ የሚዲያ ባለሙያዎችንም ከመላው ዓለም የሚያሰባስብ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የብሮድካስት፤ የህትመት፤ የፎቶግራፍ፤ የዲጂታል ሚዲያ አውታሮችን ትኩረት በመሳብ ከ190 በላይ አገራትን የሚያካልል ልዩ ሽፋን ይሰጠዋል፡፡
የዓለም ሻምፒዮናው በምድረ አሜሪክ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ መካሄዱ በአትሌቲክስ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ አሜሪካውያንና የስፖርት አፍቃሪዎቹን ሲያነቃቃቸው ቆይተዋል፡፡ አሜሪካ ባለፉት 17 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በአጠቃላይ 381 ሜዳልያዎች(170 የወርቅ፤ 117 የብር እና 94 የነሐስ) በመሰብሰብ በምንግዜም ከፍተኛ ውጤት ዓለምን እንደምትመራ ይታወቃል፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ታላላቅ አትሌቶችም በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ለመሳተፍና እጅግ ከፍተኛ አድናቆት በሚቸረው በሄዋርድ ፊልድ ስታድዬም ለመወዳዳር  መጓጓታቸውን እየገለፁም ናቸው፡፡ ኮቪድ 19 በዓለም ስፖርት ላይ ባለፉት  ዓመታት ካሳደረው ተፅእኖ የአሜሪካ መስተንግዶ ለአትሌቲክሱ ከፍተኛ ድምቀት በመፍጠር፤ በማህበራዊ ሚዲያዎች ከፍተኛ ትኩረት ለስፖርቱ በማምጣትና  ውድድሩ በሚካሄድበት ስታድዬም በቂ ተመልካቾች በማስገኘት ስኬታማ እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡
ቢግ ፉት የሻምፒዮናው ልዩ ምልክት
ለ18ኛው  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ልዩ ምልክት እንዲሆን የተመረጠው Bigfoot ቢግፉት ወይንም በተለምዶ ሳስኳች ተብሎ የሚጠራው በሰሜን አሜሪካ ደኖች ውስጥ እንደሚኖር የሚነገር የዝንጀሮ መሰል ፍጡር ነው። በዚህ አስደናቂ ፍጡር ህልውና ዙርያ በርካታ አፈታሪኮች፤ ጥናታዊ መጣጥፎችና እማኝነቶች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን ከዚህ አፈታሪክ ጋር መያያዙ ሰሞኑን በይፋ ከተነገረ በኋላ መነጋጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ቢግ ፉትን አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት ፍጡሩን መመልከታቸውን የሚገልፁ የአይን እማኞች፤ የቪዲዮ እና የድምጽ ቅጂዎችን፣ ፎቶግራፎችን እና በመሬት ላይ ያረፉ ትላልቅ ዱካዎችና  አሻራዎች ቢኖሩም የፍጡሩን መኖር አለመኖር እስከዛሬ በይፋ ለማረጋገጥ አለመቻሉ ይገለፃል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ  ላይ ሃላፊነት ያላቸው እንደገለፁት የሻምፒዮናውን ልዩ ምልክት ለመፍጠር ብዙ ፅንሰ-ሀሳቦች ለመመልከት ተሞክሯል፤ ከቀረቡ ልዩ ምልክቶች  መካከል አንዳንዶቹ ልብ ወለዳዊ ፤ ሌሎች ደግሞ ብርቅዬ  የዱር አራዊቶችን ፣  ረቂቅ ምስሎችን የሚያሳዩ ይገኙበት ነበር፡፡ በመጨረሻም ግን ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ቢግ ፉት ልዩ ገፀባህርይ ይፈጥራል በሚል ስምምነት ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ በፓሲፊክ ውቅያኖስ ሰሜናዊ ምዕራብ የሚገኘው የዓለም ሻምፒዮናው አዘጋጅ ከተማ  በተፈጥሮ ውበት፣ አስደናቂ ባህልና ለአትሌቲክስ ስፖርት ባለው ፍቅር በመላው ዓለም የሚታወቅ ነው፡፡  ቢግፉት ደግሞ በዚሁ የሰሜን አሜሪካ ክፍል አፈታሪክ ሆኖ የሚንከራተት ሚስጥራዊ ፍጡር ነው ሲባል በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በ270 ሚሊዮን ዶላር ተገንብቶ ዓለምን ያጓጓው ሄይዋርድ ስታድዬም
በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው ሻምፒዮናው በዘመናዊውና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ግዙፍ ስታድዬም መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከሚካሄዱ ውድድሮች የብዙዎቹ የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች ተሸጠው ማለቃቸው ሲገለፅ የቆየው ከአጓጊው የሄይዋርድ ፊልድ ስታድዬም ተያይዞ ነው፡፡ በዩጂን ኦሬጎን ከተማ ውስጥ አጋቴ ስትሪት 15ኛ አቬኑ ላይ የሚገኘው ሄይዋርድ ፊልድ ስታድዬም በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኦሬጎን ክልል ውስጥ ተገንብቷል፡፡  ስታድዬም ከጅምሩ የነበረው መደበኛ የማስተናገድ አቅም እስከ 10ሺህ 500 ተመልካች ነበር፡፡  ለመጀመርያ ጊዜ ተገንብቶ በ1919 እኤአ ላይ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለእግር ኳስ የነበረ ሲሆን ከ1921 እኤአ ጀምሮ ደግሞ የትራክና ሜዳ ላይ ስፖርቶችን የሚያስተናግድ መድረክ ሆኖ እስከዛሬ ቀጥሏል፡፡ የስታድዬሙ መጠርያ  በኦሬጎን በአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኝነት ላገለገሉት ቢል ሄይዋርድ  መታሰቢያ ተደርጓል፡፡ ስታድዬሙ ከ2018 እስከ 2020 እድሳት ተደርጎለት የማስተናገድ አቅሙን ወደ 12650 ተመልካች እንዳስፈላጊነቱም እስከ 25ሺ ተመልካች እንዲይዝ ሆኗል፡፡ ለስታድዬሙ እድሳት የወጣው በጀት ከ270 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን  ከታዋቂው የአሜሪካ ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ መስራቾች አንዱ የሆነው ፊል ናይት የሰጠው ድጋፍ የአንበሳውን ድርሻ  ቢይዝም  ሌሎች ከ50 በላይ ድጋፍ ሰጭዎችም በአጋርነት ተሳትፈውበታል፡፡ ስታድዬሙ በዓለምና የአሜሪካ አትሌቲክስ ታሪክ አስደናቂ ታሪኮች ያሉት ነው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ስር ከሚካሄዱ የዳይመንድ ሊግና ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ባሻገር የአሜሪካ አገር አቀፍ ሻምፒዮና የኦሎምፒክ ዝግጅትና ማጣርያዎችን በየዓመቱ ያስተናግዳል፡፡ ከዓለማችን ታዋቂ የረጅም ርቀት ሯጮች አንዱ የሆነው ስቲቭ ፕሮፎንታይኔ፤  በ1970ዎቹና 80ዎቹ ከፍተኛ ዝና የነበራት ሯጭ ማሪ ዴከር፤ በ2012 ለንደን እንዲሁም በ2016 በሪዮ ዲጄኔሮ ኦሎምፒኮች  በዴካትሎን ለአሜሪካ የወርቅ ሜዳልያ የወሰደው አሽተን ኢተን እንዲሁም በ2020 ቶኪዮ ኦሎምፒክ በመካከለኛ ርቀት የነሐስ ሜዳልያ ያገኘው ራይቨን ሮጀርስ በሄይዋርድ ፊልድ ስታድዬም ከተገኙ የዓለማችን ምርጥ አትሌቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የስታድዬሙ ሁለገብና ዘመናዊ አሰራር ለትራክና የሜዳ ላይ አትሌቲክስ ውድድሮች ልዩ ልምድ  እንደሚፈጥርም ታምኖበታል፡፡ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ  ከ200 በላይ አገራትን የሚወክሉ ከ2ሺ በላይ አትሌቶችን ሲያወዳድርም በተሟላ አቅም ላይ እንደሚገኝ ተረጋግጧል፡፡   በብዙ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ምርጥ ፉክከሮች፤ ምርጥ ሰዓቶች ክብረወሰኖችና የዓለም ሪከርዶች የሚመዘገቡበት እንደሚሆንም የተለያዩ ባለሙያዎች እየመሰከሩ ናቸው፡፡ የስታድዬሙ የመሮጫ ትራክ፤ ለሜዳ ላይ ስፖርቶች ምቹ ሆኖ የተዘጋጀው ሜዳ ለምርጥ ብቃቶች ምክንያት እንደሚሆን ተነግሯል፡፡ በስታድዬሙ ለሚታደሙ የአትሌቲክስ አፍቃሪዎች የስፖርት መድረኩን እንደቲያትር ለመልከት የሚችል እድልም ይፈጥራል ነው የሚባለው፡፡ ለዚህም ምቹ መቀመጫዎችና መመልከቻ ስፍራዎች ፤ ዘመናዊ የስታድዬም አገልግሎቶች፤ ከአትሌቶችና ከውድድሮች ጋር ልዩ ቅርበት የሚፈጥሩ እይታዎችና ዲጂታል ስርጭቶችን ለማከናወንም የተዘጋጀ መሆኑም ይገለፃል፡፡ስፖርት አፍቃሪውን ከዝናብ እና ከጎጂ ጨረሮች የሚከላከል ልዩ ሽፋን በተደረገበት ዘመናዊ አሰራርም ተምሳሌት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡
የዓለም ሻምፒዮናነት ክብርና ከ9.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለሽልማት
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በ2019 እኤአ ላይ ኳታር ካስተናገደችው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጀምሮ ለሽልማት በሚያቀርበው ገንዘብ ላይ ለውጥ አድርጓል፡፡ ከ2 ዓመት በፊት ሻምፒዮናው ሲካሄድ በየውድድሩ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ለሚያገኙት የገንዘብ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን  በአጠቃላይ የተበረከተው የሽልማት ገንዘብ 7 ሚሊዮን 530ሺህ ዶላር ነበር፡፡
በኦሬጎን በሚካሄደው 18ኛውና በቡዳፔስት በሚቀጥለው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ይህን የሽልማት ገንዘብ በ2 ሚሊዮን ዶላር  ለማሳደግ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ተወስኗል፡፡ በሻምፒዮናው በሚደረጉት 44 የውድድር መደቦች ላይ በእያንዳንዳቸው 23ሺ ዶላር ተጨማሪ የሽልማት ገንዘብ የተቀመጠ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የሽልማት ገንዘቡን 9 ሚሊዮን 530ሺህ ዶላር ያደርሰዋል፡፡ በገንዘብ ሽልማቱ ዝርዝር አከፋፈል መሰረት  ለወርቅ ሜዳልያ 60ሺ፤ ለብር ሜዳልያ 30ሺ ዶላርና ለነሐስ ሜዳልያ 30ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡ ለ4ኛ ደረጃ 15ሺ፤ ለ5ኛ ደረጃ 10ሺ፤ ለ6ኛ ደረጃ 6ሺ፤ ለ7ኛ ደረጃ 5ሺ እንዲሁም ለ8ኛ ደረጃ 4ሺ ዶላር እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡
የ80 ሚሊዮን ዶላር መስተንግዶና ትርፋማነቱ「
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዓለም አትሌቲክስ ማህበር ስር ከሚካሄዱ ውድድሮች በትርፋማነቱ ተስተካካይ ያልተገኘለት ነው፡፡ በ2017 እኤአ ላይ በተካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አዘጋጇ የለንደን ከተማ በኢኮኖሚያዋ ላይ በቀጥታ ያስገባችው መዋዕለንዋይ ከ104.1 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑም ይህን ያመለክታል፡፡ በወቅቱ ከሻምፒዮናው በተያያዘ በእንግሊዝ ኢኮኖሚ ላይ በአጠቃላይ የተንቀሳቀሰው ደግሞ ከ159 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ መገመቱን መጥቀስም ይቻላል፡፡
ይህንኑ ከግምት በማስገባት ይመስላል የኬንያ መንግስት በ2025 እኤአ ላይ 20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማስተናገድ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የዓለም ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ሰሞኑን ገልፀዋል፡፡ በናይሮቢ ከተማ የሚገኘውና በቻይና ኩባንያ ተገንብቶ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኪሳራኒ ስታድዬም ለመስተንግዶ ብቁ መሆኑንም ቢዝነስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡
በእያንዳንዱ ሻምፒዮና ላይ አዘጋጅ ከተማ ከተለያዩ የአትሌቲክስ አጋሮችና ባለድርሻዎች፤ ከአትሌቶች፤ ከባለሙያዎችና ልዑካናትና ከውድድሩ አስተናጋጆችና ነዋሪዎች ከፍተኛ ገቢን ይሰበስባል፡፡ የአዘጋጅ አገርን ስፖርት ከማነቃቃት ባሻገር፤ በቱሪዝም፤ በትራንስፖርት እና በስፖርት መሰረተልማቶች የኢኮኖሚ አቅም ላይ የጎላ አስተዋፅኦ ይፈጥራል፡፡ በ2017 ላይ የንግስት ኤልዛቤት ስታድዬም የዓለም ሻምፒዮናው 205 አገራትን የወከሉ 2038 አትሌቶችን ሲያስተናግድ ከ705ሺ በላይ የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች መሸጣቸው በውድድሩ ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው ለለንደን ኢኮኖሚ ገቢ ከሆነው የስፖርት አፍቃሪዎች ከ75 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ በማድረግ ከፍተኛውን ድርሻ ወስደዋል፡፡
18ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማስተናገድ የኦሬጎን ከተማ አስተዳደር ከአሜሪካ ትራክ ኤንድ ፊልድ አሶሴሽን ጋር የሰሩ ሲሆን ለዝግጅት ፈሰስ የሆነው በጀት ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው አዘጋጆች የበጀቱን ግማሽ ከሸፈኑ በኋላ ቀሪውን 40 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ላዓመታት ዘመቻ አድርገዋል፡፡ ትራቭል ኦሬጎን የተባለ የቱሪዝም ተቋም 20 ሚሊዮን ዶላር ኦሬጎን ሎተሪ 10 ሚሊዮን ዶላር ያዋጡ ሲሆን የጆ ባይደን አስተዳደር ደግሞ ከ9 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመስጠት ቀሪውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ተወስቷል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በሰራው ጥናት አንድ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ የሚያስፈልገው በጀት ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል፡፡ ከዚህ በጀት ሲሶውን የሚወስደው የስፖርት መሰረተልማቶች ናቸው፡፡ ለዓለም ሻምፒዮና እስከ30ሺ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለውና የኦሎምፒክ ደረጃ የሚሰጠው ዘመናዊ ስታድዬም፤ በቂ የማማሟቂያ ሜዳ ፤ በቂ የቴክኒክ ስራዎች ማከናወኛ ስፍራ እና ክፍሎች በስታድዬም ውስጥ እና ግቢ ያስፈልጋል፡፡ ስታድዬሙ ከዓለም ሻምፒዮናው መስተንግዶ 1 አመት ወይምን 4 ወራት ቀደም ብሎ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር የሚገመገም አለም ቀፍ ውድድርንም በተሳካ ሁኔታ ማካሄድንም ይጠየቃል፡፡

Read 10468 times