Saturday, 21 May 2022 11:32

ባይደን እንዲታሰሩ ጠይቆ ራሱ ታሰሮ አረፈው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 የአሜሪካውያን የድንገተኛና የአደጋ ጊዜ ማሳወቂያ የስልክ መስመር በሆነው 911 በመደወል “ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዘብጥያ መውረድ አለበት; ያለው የፍሎሪዳ ነዋሪ፣ ራሱ ወህኒ ተወርውሮ አረፈው።
የ29 ዓመቱ ጃኮብ ፊልቤክ ባለፈው እሁድ ለእስር የተዳረገው በተደጋጋሚ 911 በመደወል “ኢል-ቻፓ ከእስር መፈታትና ፕሬዚዳንት ባይደን ወህኒ ቤት መግባት አለባቸው” ሲል መስመሩን ያለአግባቡ በመጠቀሙ ነው ተብሏል።የ911 መልዕክት ተቀባዮች የፊልቤክ አስተያየት ከድንገተኛ ጊዜ አደጋ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በመጠቆም፣ ለዚህ ጉዳይ ዳግም እንዳይደውል አስጠንቅቀውት ነበር። እሱ ግን አልሰማቸውም፡፡
ጥቂት ቆይቶ 911 ዳግም በመደወል ያንኑ ተመሳሳይ ጉዳይ ይወተውታቸው ገባ፤ “ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወህኒ ቤት መወርወር አለባቸው” በማለት። ወዲያውኑ ፖሊስ ወደ ሰውየው ቤት በማምራት፣ ለምን 911 ላይ ድንገተኛ ላልሆነ ጉዳይ ደጋግሞ እንደደወለ ይጠይቀዋል፡፡ ፊልቤክም እንደለመደው፤ “ኢል-ቻፓ በነፃ ከእስር መለቀቅና ፕሬዚዳንት ባይደን መታሰር አለባቸው” ሲል ያለአንዳች ማመንታት መለሰ፡፡
በዚህም 911 ሽቦ አልባ የስልክ መስመርን ድንገተኛና ወንጀል ነክ ላልሆነ ጉዳይ ያለ አግባብ በመጠቀሙ በቁጥጥር ሥር ውሎ ዘብጥያ ወርዷል፡፡ ፊልቤክ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ በ911 የስልክ መስመር በግምት ለሦስት ጊዜ ያህል መደወሉን የእስር ሰነዱ ያስረዳል። ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተመኘውንም እስር ራሱ አግኝቶታል፡፡

Read 1465 times