Tuesday, 24 May 2022 00:00

5 ወራትን የፈጀው የ10 ዩኒቨርስቲዎች ጥምረት የጥናት ውጤት ይፋ ሆነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   • የህወኃት ሃይሎች የአማራ ክልልን ወረው በቆዩባቸው ጊዜያት 6985 ዜጎችን መግደላቸውን ጥናቱ አመልክቷል
        • 1797 ሰዎች በጅምላ የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 579 የሚሆኑት በድብደባ ብዛት የሞቱ ናቸው ተብሏል
        • 1782 ሰዎች ላይ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ሲፈጸምባቸው፤ ሃያሁለቱ ወንዶች ናቸው ተብሏል
              

            በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ አስር የፌደራል ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጣ ከአራት ሺ በላይ ባለሙያዎችና ከብሔራዊ ስታቲስቲክ ኤጀንሲ የተውጣጡ 300 የሚደርሱ ሙያተኞች የተሳተፉባቸውና አምስት ወራትን የፈጀው ጥናት ሰሞኑን ይፋ ተደርጓል፡፡ ጥናቱ የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው በቆዩበት ወቅት ያደረሱትን ጥፋት የሚመለከት ነው፡፡
ሰሜን ወሎ፣ደቡብ ወሎ፣ሰሜን ጎንደር፣ደቡብ ጎንደር፣ዋግ ኽምራ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ የህወኃት ወታደሮች ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ ተቆጣጥረዋቸው የነበሩ ሰባት የአማራ ክልል ዞኖች ናቸው፡፡
ከህወኃት ተዋጊዎች ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ላለፉት 5 ወራት መከናወኑ በተገለጸው ለዚሁ የአስር ዩኒቨርስቲዎች ጥምር ጥናት ውጤት ላይ እንደተገለጸው፤ በጦርነቱ ውስጥ ምንም  አይነት ተሳትፎ ያልነበራቸው 6985 ንፁሃን ዜጎች በህወኃት ሃይሎች ተገድለዋል፡፡ 7460 ወገኖች ደግሞ በሃይል ታፍነው በመወሰዳቸው አድራሻቸው እስከ አሁንም አለመታወቁ ጥናቱ ተመልክቷል፡፡
የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች የአካባቢውን ነዋሪዎች በጅምላ መጨፍጨፋቸውን የጠቆመው የዩኒቨርስቲዎቹ ጥናት፣ በተለይ በጭና ቀወት፣መንዝ ጌራ፣ አንፆኪያ ገምዛ፣ አጋምሳ ኮምቦልቻና መርሳ ከተሞች ከ1797 በላይ ወገኖች በጅምላ ተጨፍጭፈዋል ብሏል፡፡ በጅምላ ከተጨፈጨፉት ወገኖች መካከል 579 የሚሆኑት በተፈፀመባቸው ድብደባ ሳቢያ የሞቱ መሆኑንም ይኸው ጥናት አመልክቷል፡፡
በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙት 10 የፌደራል ዩኒቨርስቲዎች ሰሞኑን ይፋ ያደረጉት የጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው ከ10 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ህዝቦች ሰብአዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡የህወኃት ሃይሎች አካባቢውን ተቆጣረው በቆዩባቸው ጊዜያት ከፈፀሟቸው አስከፊ ሰብአዊ ጉዳቶች መካከል አስገድዶ መድፈር ዋነኛው መሆኑን ያመለከተው ጥናቱ፤ የህወኃት ሃይሎች ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ሰባቱ የክልሉ ዞኖች ውስጥ በሚኖሩና በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 1782 ዜጎች ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መፈፀማቸውን ጠቁሟል፡፡ ጥቃቱ የተፈፀመው በቡድንና በግል ሲሆን በትዳር አጋርና በቤተሰብ ፊት፣ በመነኩሴዎችና በሃይማኖት አባቶች ሚስቶች ላይ የተፈፀመ መሆኑንም  ጥናቱ አመልክቷል፡፡ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ከተፈፀመባቸው ወገኖች መካከል ሃያ ሁለቱ ወንዶች መሆናቸው በጥናቱ ተገልጿል፡፡ ይህ ቁጥር መገለልና መድሎን በመፍራት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑትን የጥቃቱን ሰለባዎች አያካትትም ተብሏል፡፡
 ጥናቱ ከፌደራልም ሆነ ከክልል መንግስታት ተሳትፎና ፖለቲካዊ ጫና ነፃ ሆኖ መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን የህወኃት ሃይሎች በሃይል ተቆጣጥረዋቸው በነበሩት አካባቢዎች ላይ ያደረሱትን የንብረት ውድመትም ያካተተ ነው ተብሏል።
በዚህም መሰረት 1145 የትምህርት ተቋማትና 2 ሺ የሚጠጉ የጤና ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተረጋገጠ ሲሆን በአጠቃላይ በክልሉ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ሲተመን ከ288 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ በጥናቱ እንደተጠቆመው ከዚህ ውስጥ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመተው የግለሰቦች ሃብት እንደሆነም ጥናቱ አመልክቷል።

Read 2775 times