Wednesday, 25 May 2022 00:00

አድማስ ትውስታ

Written by  ጌታቸው ተድላ አበበ
Rate this item
(2 votes)

 እኔን ገርሞኝ ነው - እናንተስ ምን ትላላችሁ?

              “…እኔ የማንም ሐይማኖት ተከታይ አይደለሁም፣ የኔ ሐይማኖት የሁሉንም እኩልነት መጠበቅና ዘረኝነትን ማጥፋት ነው….”
                 
             ባለፈው ወር ለአንድ የግል ጉዳይ ወደ የሰሜኑ ዋልታ አገር ስዊድን ብቅ ብዬ ነበር፡፡ ማታ ላይ በቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ አንዲት ጥቁር ሴት፣ ከአንድ ከታወቀ የሊበራል ፓርቲ ፖለቲከኛና መሪ ጋር ስትከራከር፣ ለጋዜጠኞች ጥያቄ መልስ ስትሰጥ፣ ሰውዬው በነገር ጠቅ ሲያደርጋትና ስትስቅ እመለከታለሁ፡፡ “እዚህ ደረጃ የደረሰች ጥቁር አፍሪካዊት ሴት ማነች?” በማለት ስጠይቅ “ከሦስት ሳምንት በኋላ በሚደረገው የሊበራል ፓርቲ ምርጫ ላይ ቦታውን ለመያዝ በሚደረግ ፉክክር ላይ የምትወዳደር ሴት ነች” ተባልኩ፡፡ “ምን? ጥቁር አፍሪካዊት የአንድ ፓርቲ መሪ ለመሆን? ያውም ስዊድን አገር?” እያልኩ ከራሴ ጋር ተከራከርኩ፡፡       
 ይህች ሴት ትውልድ ሀገሯ ቡሩንዲ ነው፡፡ ቡሩንዲ በታንዛንያ፣ በኮንጎና በሩዋንዳ ተከብባ የምትገኝ ትንሽ አገር ነች፡፡ ነፃነቷን በ1962 ከመጎናጸፏ በፊት ርዋንዳ - ኡሩንዲ ትባል ነበር፡፡ የአገሪቷ ስፋት 27 ሺ 834 ስኩዌር ኪሎሜትር ነው፡፡ (በጣም ትንሽ መሆኗን የምታውቁት የኛ ሀገር ስፋት 1.104 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር መሆኑን ስትረዱ ነው) በሀገሪቷ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ህዝቦች ይኖሩባታል፡ የቡሩንዲ መዲና ቡጁምቡራ ቢሆንም በቅርቡ ወደ ጂቴጋ ተዛውሯል፡፡ አገሪቷ በወረቀት፣ በቆዳና በእርሻ ምርት ትታወቃለች፡፡  
ይህች የቡሩንዲ ተወላጅ ኛምኮ አና ሳቡኒ ትባላለች፡፡ የተወለደችው በቡጁምብራ ከተማ ማርች 31 ቀን 1969 ነው፡፡ (ስለዚህም በአሁኑ ወቅት 50 ዓመቷ ነው) አባቷ አቶ ማኡርሲ ሳቡኒ የክርስትና ሐይማኖት ተከታይ ሲሆኑ፣ የዛየር (በኋላ ኮንጎ) ተወላጅ ናቸው፡፡ ግራ ዘመም ከመሆናቸውም ባሻገር ንቁ የፓትሪስ ሉሙምባ የፖለቲካ ደጋፊ ስለሆኑ ብዙ ጊዜ የአገራቸው ወህኒ ቤት እስረኛ የተደረጉ ሰው ናቸው፡፡ እናቷ የቡሩንዲ ተወላጅ ሆነው የሙስሊም ሐይማኖት ተከታይ ስለሆኑ፣ ሳቡኒን በሙስሊም ባሕል መሠረት ነው ያሳደጓት፡፡ ስለዚህም ሳቡኒ ከክርስቲያንና ከሙስሊም አማኝ ወላጆች የተወለደች ነች፡፡ የኛምኮ ወላጆች ሰባት ልጆች አሏቸው፡፡ ሳቡኒ ስለ ሐይማኖት ግድ የላትም፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት በአደባባይ “……እኔ የማንም ሐይማኖት ተከታይ አይደለሁም፣ የኔ ሐይማኖት የሁሉንም እኩልነት መጠበቅና ዘረኝነትን ማጥፋት ነው…….” ብላለች፡፡  
አባቷ በግራ ዘመም የፖለቲካ አቋማቸው በኮንጎ አገራቸው መኖር ስላልቻሉ ወደ ሩዋንዳ ከዚያም ወደ ታንዛንያ ተጓዙ፡፡ እዚያም እያሉ ብዙ ጊዜ የግድያ ሙከራ ስለደረሰባቸው የስዊድን መንግሥት ጥገኝነት ሰጥቷቸው ወደ ስዊድን ገቡ፡፡ ጥቂት ጊዜ ቆይቶም ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን በሙሉ በ24 ማርች 1981 ጓዟቸውን ጠቅልለው የስዊድን አገር መዲና ስቶክሆልም ገብተው ከባለቤታቸውና ከአባታቸው ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ሳቡኒ ምድረ ስዊድንን ስትረግጥና ወደ አዲሱ አገሯ ስትመጣ ገና የ12 ዓመት ልጅ ነበረች፡፡
ሳቡኒ የስዊድንን ቋንቋ ከተማረች በኋላ ሜላርዳለንስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምራ፣ ወደ ኡፕሳላ ክፍለ ሀገር ሔዳ በታዋቂው የኡፕሳላ ዩኒቨርስቲ በሕግ ትምህርት ተመረቀች፡፡ ከዚያም ስለ ስደትና ሚዲያ ኮሙኒኬሽን ጥናት አደረገች፡፡ ወጣቷ ሳቡኒ ኪስዋሂሊ፣ እንግሊዝኛና ስዊድንኛ አቀላጥፋ ትናገራለች፡፡ በሂደት አፍሮ - ስዊዲሽ ማኅበር አቋቁማ የፕሮጀክቱ ማናጀር ሆና በመሥራት በስዊድን   ክፍለተ ሀገራት በመዞር የስደተኞችን ችግር ለመፍታት ትሞክር ነበር፡፡ ቀጥሎም በልዩ ልዩ መሥሪያ ቤቶች እየሠራች እያለ በ2004 አቶ አላን በርግክቪስትን አግብታ፣ ሁለት መንታ ወንድ ልጆች ወለደች፡፡
በስዊድን የወጣቶች ሊበራል ፓርቲ ውስጥ ገብታ፣ በጥቂት ጊዜ በቦርዱ አባልነት ከ1996 እስከ 1998 ድረስ አገለገለች፡፡ ከ2001 እስከ 2013 በፎልኬት ፓርቲ (የሕዝብ ፖለቲካ ቡድን) ገብታ ስትሠራ ፓርቲዋን ወክላ በሕዝብ ምርጫ ፓርላሜንት ተመርጣ ወንበር ያዘች፡፡ ነገሩን ላሳጥረውና የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በ2002 የኢንተግሬሽንና ጄንደር ኢኳሊቲ (Minister for Integration and Gender Equality) ሚኒስትር አድርጎ ሾማት፡፡ በዚህም በስዊድን ታሪክ የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሚኒስትር መሆኗ ነው፡፡ ሳቡኒ እስከ 2013 ድረስ ማለትም ለ11 ዓመታት በሚኒስትርነት አገልግላ ከመንግሥት ሥራ በፈቃድዋ ለቀቀች፡፡ ይህም ከውጭ ሆኜ ፓርቲዬን የበለጠ ላሳድገው በሚል ሰበብ ነው፡፡ በየሥፍራው ንግግር በምታደርግበት ሁሉ ሕዝቡ እያጨበጨበ ድጋፉን ይሰጣታል፡፡ ብዙ ተቃዋሚዎችዋም፣ ጥቁር ብትሆንም ዘረኛ ነች እያሉ ይተቹዋታል፡፡ እኔ በበኩሌ አንድ ቦታ ከተናገረችው ውስጥ ስሜቴን የነካው፣ “ብዙ ስደተኞች መብታቸውን በስህተት ይረዱታል፣ የሐይማኖት ነፃነት ማለት፣ ምንም ነገር በሐይማኖት ሳቢያ የሚፈፀም ይመስላቸዋል…….. እዚህ ስዊድን ሀገር ቤት ሠርታችሁ፣ ተደላድላችሁ እስከኖራችሁ ድረስ፣ ልጆች ወልዳችሁ፣ የልጅ ልጆች አይታችሁ ስትኖሩ፣ ከሕብረተሰቡና ከባህሉ ጋር ተዋህዳችሁና ተስማምታችሁ መኖር ያለባችሁ ግዴታ ነው” ያለችው ነው፡፡
ስዊድን እያለሁ ላገኛትና የበለጠ እሷን ለማወቅ ፈልጌ ወደ ቢሮዋ ደወልኩኝ፡፡ ነገር ግን  አሁን በፓርቲው ምርጫ ስለተወጠረች ከምርጫው በኋላ እንደሚያገናኙኝ ነገሩኝ፡፡ ግን የመመለሻዬን ቲኬት ለማራዘም ስላልፈለግሁ፣ ሳላገኛት ተመለስኩ፡፡ ወደ አገሬ ለመመለስ አንድ ቀን ሲቀረኝ ወይዘሮ ሳቡኒ የሊብራል ፓርቲ መሪውን አሸንፋ፣ እሷ አዲሷ መሪ ሆና መመረጧና አሸናፊ ሆና ወንበሩን መረከቧን በሁሉም ጋዜጦችና በቲቪ ለማየት በቃሁ፡፡
“ታዲያ ይህ ምን ያስገርማል? ደስ ይላል እንጂ” ትሉ ይሆናል፡፡ እኔን ያስገረመኝ ከአገሬ ጋር የተከሰተውን በማሰብ እያወዳደርኩት ነው፡፡ “እንዴት?” ካላችሁ፣ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡
እስቲ እናንተም አስቡት! ይህች ሴትዮ በብዙ ሚዛኑ እኛ አገር ብትሆን አሁን ያለችበት ደረጃ ትደርስ ነበር? ወይንስ “የኛ አገር ሰው አይደለሽም፣ ብሔርሽ ሌላ ነው፣ እዛው ቡሩንዲሽ ተመለሺ!” ተብላ ትፈናቀል ነበር? ለነገሩ በጥሩ ህሊና ካሰብነው፣ ከነጮቹ አገር የኛ የጥቁሮቹ አገር ይቀርባት ነበር፡፡ እንደገና አስቡ! ሳቡኒ ቆዳዋ ጥቁር ነው፡፡ ዐይኗ፣ ፀጉሯ፣ ከንፈሯ፣ ባጭሩ ሁለመናዋ በፍፁም የነጮቹን መልክም ሆነ ባህሪም የላትም፡፡
እዚያም አልተወለደችም፡፡ በስደትና በጥገኝነት በ12 ዓመቷ የመጣች ሰው ነች፡፡ ነገር ግን እዚያ አድጋ፣ እዚያ ተምራ፣ የሕብረተሰቡን ኑሮና ባህል ተለማምዳ፣ ሳትሳቀቅ ኮርታ፣ አገሬ ስዊድን ነች ብላ የምትኖር እመቤት ነች፡፡ በዚህ አጋጣሚ ስዊድን ሁሉም ሰዎች በዴሞክራሲና በእኩልነት አንድ ላይ እንዲኖሩ ስላደረገች የምትመሰገን አገር ነች፡፡
“ታዲያ ይህ ምን ያስገርማል?” አላችሁ? ለምን አልገረም! እኔ በአንድ ክፍለ ሀገር፣  ቅድመ አያቶቼ፣ አያቶቼና ወላጆቼ በኖሩበት ሥፍራ፣ እኔም እዚያው ተወልጄ፣ ጓደኞች አፍርቼ ስቦርቅ ስጫወት አድጌ፣  ከጎረቤቶቼ ጋር በሀዘንም በደስታም በመሶብ ምግብ አብሬ ተቋድሼ፣ ወግ ማዕረጉ ደርሶኝ አግብቼ፣ ልጅ አፍርቼ፣ የጎረቤት ሰው ልጄን ክርስትና አንስቶ፣ ለብዙ መቶ ዓመታት ወላጆቼ የኖሩበት፣ የኔ ቀዬ ብዬ የምጠራውና የምኖርበት መንደሬ ተረስቶ፣ አብረውኝ የበሉት፣ የጠጡት፣ ክፉውንም ደጉንም አብረን ለብዙ ዓመታት ያሳለፍነው መጥተው፣ “አንተ’ኮ ብሔርህ አማራ ነው፣ አንተ’ኮ ብሔርህ ኦሮሞ ነው፣ አንተ’ኮ ብሔርህ ደቡብ ነው፣……. አንተ’ኮ መጤ ነህ፣ ወደ ክልልህ ሒድ” ተብዬ፣ ተፈናቅዬ እወረወራለሁ፣ እደበደባለሁ፣ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እንጅ - እገደላለሁ፡፡  ታዲያ ይህ አያስገርምም? የሚያፈናቅሉኝስ ያደረጉት ድርጊት ስህተት መሆኑን አውቀው አይፀፀቱም? ይህን በኛ አገር በመከሰት ላይ ያለውን ሳቡኒ ብትሰማ ምን ትል ይሆን? እንኳን እርሷ እኔም የአገሩ ተወላጅ ግርም፣ ግርምርም እያለኝ ነው ይህችን ጽሑፍ ያቀረብኩላችሁ፡፡  
በጠቅላላው ሠላም በአገራችን ይስፈን፣ የጥንቱ፣ የጧቱ አብረን መኖራችን፣ ፍቅራችንና ትብብራችን ይመለስ፡፡ ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ ለዘላለም ትኑር፡፡ ጤና ይስጥልኝ!

Read 6380 times