Saturday, 21 May 2022 12:52

የሀበሻ የጦርነት ጥበብ እና ሳን ዙ

Written by  ታምሩ ከፈለኝ
Rate this item
(1 Vote)

 ስለ ሳን ዙ (SUN TZU) ብዙ እየተወራ ነው። THE ART OF WAR የተሰኘው እድሜ ጠገብ መፅሐፉ ከክርስቶስ ልደት በፊት ተፅፎ፣ ከክርስቶስ ልደት በኋላም ላሉ ጦርነቶች መራሄ ሆኗል። በርግጥ መፅሐፉ ከጦርነት አልፎ ለበርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም  መነሳትና መመንደግ አገልግሏል።
‘ሳን ዙ በመፅሐፉ ያነሳቸው በርካታ ምክሮች የድል መንገድ ናቸው’ እያሉ መመሪያውን የተጠቀሙ የጦር አበጋዞችም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ለብዙዎቹ የጦር አዛዦች መፅሐፉ ከሼልፋቸው ይልቅ ለጠረጴዛቸው ቅርብ ነው።
እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በእኛ በሀበሾች ሽለላ፣ ቀረርቶና ፉከራ (war song) ውስጥ ያሉ መልእክቶች፣ ሳን ዙ ከፃፋቸው ሀሳቦች ጋር አቻ ይሆናሉ።
ስነቃሎቻችንን ስላልተረዳናቸው፤ ተረድተንም ስላልተነተናቸው፤ ተንትነንም የሼልፍ ሸክም ከማድረግ ስላላሳለፍናቸው እንጂ ሀገር በቀል የጦርነት ጥበብ በነበረን፤ ለዚህኛው ትውልድም የእነ አድዋ ድል ምክንያት ጭላንጭል በተገለጠልን ነበር።
ለአብነት ያህል ጥቂት የሳን ዙን የጦርነት መርሆዎች፣ ከኛ ቃል ግጥሞች ጋር እያነፃፀርን እንይ፦
“ደረሰባቸው ሳይታጠቁ
እንደዝንጀሮ ፀሀይ ሲሞቁ፤”
 ጠላት በተዘናጋበትና ባላሰበበት ቅፅበት ደርሶ የጠላትን ሰራዊት ሙትና ቁስለኛ ማድረግ፣ የወገንን ጦር ኪሳራ ይቀንሳል። ድልንም አፍጥኖ ያስሞግሳል። በዚች የቃል ግጥም ውስጥ ጠላትህ እንደማትደርስበት አስቦ  አንዴ ደረቱን፣ አንዴ መቀመጫውን እያገላበጠ ለፀሀይ በሰጠበት ጊዜ፣ ደርሰህ አበራየው የሚል ምክርም አለ።
ሳን ዙም በምክሩ እንዲህ ይላል፡- “... ጠላትህ ባልተዘጋጀበት ጊዜ ውጋው...”
(በርግጥ አንድን ጠላት ታጥቄያለሁ ታጠቅ ሳይሉ መውጋት በሀበሻ ልማድ ነውር ነው። ግን ታጥቄያለሁ ታጠቅ ከተባለ በኋላና ጦር ከተሳለ ጋሻ ከተራገፈ በኋላ እንዲያ ብሎ ነገር የለም)
ሳን ዙ በሌላ ምክሩ፡- “...እሩቅ ሆነህ ሳለ ቅርብ፤ ቅርብ ሆነህ ሳለ እሩቅ ምሰል...” ይላል። የኛዎቹ ጦረኞችም ደጋ ሲባሉ ቆላ፣ ቆላ ሲባሉ ደጋ ይገኙና ነው ድል የሚቀዳጁት። ለዚህ አይነቱ ሰው ደግም የመወድስ ፉከራ አለው።
“ቆላ ነው ሲሉት ደጋ እሚገለጥ፤
ጥላው ለጠላት የማይጨበጥ።”
የጦር ጠበብቱ ሳን ዙ፡- “.... ስታጠቃ እንደ መብረቅ ፍጠን...” ይላል። ግሩም ምክር ናት። እሱም እንደሚለው፤ በተለይ የጠላት ሀይል ብዙ፣ ያንተ ደግም ትንሽ ከሆነ፣ በብዙ አቅጣጫ በፍጥነት ማጥቃት ይመከራል። ይቺን ሀሳብ ሀበሻው በሁለት መስመር ግጥም እንዲህ ይገልፃታል።
“እነሱ ብዙ ማለት ምንድነው
ፈጥነን እንሂድ ድሉ የኛ ነው፤”
ሀበሻ ሲፈልገው ይቺንው ግጥም ቤት መድፊያ ስንኟን ብቻ “...እንግጠማቸው ድሉ የግዜር ነው...” ብሎ ይቀይርና በፈጣሪ መተማመኑንም ይነግርሀል። (ተለዋዋጭነት የስነቃል አንዱ ባህሪ መሆኑን ልብ ይሏል)
በዚህ ብቻ አይበቃውም ሀበሻው፤
“የሌሊት አውሬ የቀን ጃውሳ
ጠዋት የሚያደርስ ያሞራ ምሳ”
ይልና ምሳን በቁርስ ሰአት የሚያደርስ ፈጣን ሁን ይልሀል። በዚችው ግጥሙ ቀንና ማታ የተለያየ አይነት ባህሪ ይኑርህ ብሎ፡- “..በጦርነት ውስጥ አንድ አይነት አፈፃፀም የለም፤ እንደ ሁኔታው ይለዋወጣል።” የሚለውን የሳን ዙን የጦር መርህም ደርቦ ይገልጣል።
“...ዛሬ ነገ እያልክ እድልህን አታባክን ...” ይላል ጠቢቡ ሰውዬ። እርግጥ ነው ዛሬ ነገ ማለት ውስጥ ላጥቃ አላጥቃ የሚል መወላወል አለና፣ በዛ መሀል የልብ መፍረክረክ ይመጣል። ያ ብቻም ሳይሆን ጠላትም ጊዜ እንዲሸምትና እንዲደራጅ ወይም እንዲሸሽ ይረዳዋል። ለዛ ነው ሳን፤ ዛሬ ነገ አትበል የሚለው። ዛሬ ነገ ሲል ጠላቱ ያመለጠው ሀበሻስ ቁጭቱን እየገለጠ፣ በተራውም ሌላውን ሲመክር እንዲህ አይደል የሸለለው፡-
“ያረባ ወንድ ልጅ እየወላወለ
ሰደደው ጠላቱን ዛሬ ነገ እያለ”
ጠቢቡ፤  “ጠንካራ ሆነህ ሳለ ደካማ፤ ደካማ ሆነህ ሳለ ጠንካራ ምሰል” እያለ ይመክራል።
ደካማ በሆንክበት ጊዜ ጠንካራ መስለህ ካልታየኸው በቀላሉ ትጠቃለህ።
ጠንካራ በሆንክ ጊዜ ደግሞ ደካማ መስለኸው የመጣ ጠላትን በውስጡ ያሳደረው ንቀት አግዞህ፣ ብዙ መስዋዕት ሳትከፍል ካፈር ትቀላቅለዋለህ። ይቺኑ ሀሳብ ሀበሻ በቀረርቶው እንዲህ ብሎ ይገልጣታል።
“አጭር ናቸው ብለው በኛ ላይ መጡብን
ቀጭን ናቸው ብለው በኛ ላይ መጡብን
መች አወቁንና አመል እንዳለብን”
“ጠላትህ ንዴት ካለበት ተንኩሰው፤ ከተረጋጋም እረፍት አትስጠው” ይላል ሳን።
“ነካካየው ነካካቸው አትስጣቸው ጤና
ምንጊዜም ደህና ሰው አልተባልክምና” ይላል ደግሞ ያገራችን ሸላይ።
ከማፈትለካችን በፊት .... እኔ እንዲህ አይነቶቹን የቃል ግጥሞች የምወዳቸው በውስጣቸው ብዙ እምቅ ነገር ስላለ ነው። አሁን ተነካኩ እንጂ በወግ አልተገለፁም። ምናልባት እኔ የነካካሁትን ሌላ ባለሙያ ደርጀት ቢያደርጋቸው፣ ሳን ዙ ካለውም ሌላ ተጨማሪ ሀሳቦች  (ከጦርነት ውጪም የሆኑ ፍልስፍናዊ ሀሳቦች) በቃል ግጥሞቻችንና ተረቶቻችን ውስጥ በተገኙ። ምናልባት ሀገር በቀል እውቀት ላይ የሚሰሩና የፎክሎር ተመራማሪዎች፣ ይቺ ጉዳይ ትለፈኝ የማይሏት ፅዋቸው ናትና ቢመክሩባት ባይ ነኝ።(በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የተካተቱት የሳን ዙ ሀሳቦች ትርጉም የተወሰዱት እሸቴ አስፋው በሸገር ኤፍኤም ስለ መፅሐፉና ፀሀፊው ካጠናቀረው ዝግጅት ላይ ነው)

Read 1459 times