Sunday, 22 May 2022 00:00

ስፔን የ3 ቀናት የወር አበባ እረፍት ልትሰጥ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)


             የስነተዋልዶ ጤና ፖሊሲዋን ለማሻሻል ልዩ ትኩረት እንደሰጠች የሚነገርላት ስፔን፣ ሴቶች የወር አበባ በሚመጣበት ወቅት ከሚከሰትባቸው ህመም እንዲያገግሙ ለማገዝ በየወሩ የሶስት ቀናት የስራ እረፍት ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል ህግ ማርቀቋን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ረቂቅ ህጉ በመጪው ሳምንት ለአገሪቱ ፓርላማ ለውሳኔ እንደሚቀርብ የጠቆመው ዘገባው፤ ህጉ ጸድቆ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ስፔን የወር አበባ እረፍት በመስጠት በምዕራቡ አለም የመጀመሪያዋ አገር እንደምትሆን ቢነገርም አንዳንዶች ግን ሴቶችን ከስራ ገበታ የሚያገልል ነው ሲሉ ህጉን እንደተቃወሙት ገልጧል፡፡
ህጉ የሚጸድቅ ከሆነ የወር አበባ ሲመጣባቸው ከፍተኛ ህመም የሚሰማቸው ሴቶች በየወሩ የ3 ቀናት የስራ እረፍት እንደሚሰጣቸው የጠቆመው ዘገባው፤ በመጪው ማክሰኞ ለአገሪቱ ፓርላማ የሚቀርበው ረቂቅ ህጉ ከወር አበባ እረፍት በተጨማሪ ለተማሪዎችና ለችግረኛ ሴቶች የንጽህና መጠበቂያዎችን በነጻ መስጠትና የሞዴስ ቀረጥ ማንሳትን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ህጎችን ማካተቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ለሴቶች ተመሳሳይ የወር አበባ እረፍት በመስጠት ላይ የሚገኙ የአለማችን አገራት ጃፓን፣ ደቡብ ኮርያ፣ ኢንዶኔዢያና ዛምቢያ ብቻ መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡

Read 1888 times