Wednesday, 25 May 2022 00:00

የአንድ ሰው ጣት፣ ወይስ የብዙ ሰዎች ጣት?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(2 votes)

  ሕዝብ፣ ያለ ዳኝነት፣ በምልክት ብቻ ሲፈርድ፣ ሕግ የማይገዛው ባለስልጣን ሲሆን፣ አያድርስባችሁ። ከመዓቱ ይሰውራችሁ። የሁለት ቀናት ተከታታይ ውሳኔዎችን እንመለከታለን።




               የጥንቱንና የዛሬውን የአውራ ጣት ምልክት ካነፃፀርን አይቀር፣ “ከንጉሥ ጣት ይልቅ፣ የፌስቡክ ጣት ይሻላል ወይ?” ብለን መጠየቅ እንችላለን።
በአንድ ቀን ውስጥ፣ በሮም የፍልሚያ ትርዒት ላይ፣ ከሁለት መቶ የሚበልጡ ተጋጣሚዎች፣ ለሕይወትና ለሞት ይፋለማሉ። ግማሾቹ ይሸነፋሉ፣ ይዘረራሉ። ንጉሡ፣ አውራ ጣቱን ይቀስራል። ከመቶ የሚበልጡ ሰዎች እንዲሞቱ፣ እንደዘበት፣ በጣት ምልክት ብቻ፣ ያለ ዳኝነት ይፈርድባቸዋል። ይሄ፣ “የአንድ ግለሰብ አምባገነንነት” ነው። አይደለም?
ዛሬ ግን፣ “ፈራጁ”፣ ሕዝብ ነው። እዚያው በዚያው፣ ሞት አይፈርድም። ቢሆንም ግን፣ ይፈርዳል። ዛሬ፣ አንድ ግለሰብ ሳይሆን፣ ሕዝበ አዳም ነው፣ ጣቱን የሚቀስረው። “ሕዝብ ነገሠ” ቢባል አይበዛበትም።
በፖለቲካም በሌላም፣ በቦታውም ያለ ቦታውም፣ ሁልጊዜ “ዲሞክራሲ” እያሉ የሚዘፍኑ ሰዎች፣ በዚህ መደሰት አለባቸው። እነ ፌስቡክ፣ “የዲሞክራሲ አምባ” ናቸው ማለት ይቻላል።
ግን፣ አያድርገውና፣ በአንድ ግለሰብ ምትክ፣ ሕዝበ አዳም፣ እንዳሻው፣ በሰው ሕይወት ላይ ፈራጅ ቢሆን አስቡት። “ገደብ የለሽ ዲሞክራሲ”፣ “ገደብ የለሽ የሕዝብ ስልጣን” ማለት እንደዚያ ነው። እና ምን ትላላችሁ? ከአንድ ንጉሥ፣ ሕዝብ ቢነግሥ ይሻላል? ይሻል ይሆናል። ግን፣ ሊብስም ይችላል።
እንዲሁ ስታስቡት፣ በማንኛውም ሰበብ፣ ያለ ዳኝነት፣ በዘፈቀደ፣ እንዳሰኘው የሚፈርድ ሰው ሲበዛ፣ ጉዳቱ ይጨምራል እንጂ፣ እንዴት ይቀንሳል? ከአንድ አምባገነን ይልቅ፣ ሺህ አምባገነን አይሻልም። ከአንድ ፈራጅ እጅ ይልቅስ፣ ሺህ ፈራጅ እጅ ይበልጣል?
እስቲ፣ አቴንስ ትመስክር።
በዓለማችን የዲሞክራሲ ታሪክ ውስጥ፣ የግሪክ ጥንታዊ ሥርዓት፣ በቀዳሚነት ይጠቀሳል - የአቴንስ ዲሞክራሲ። ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉት፣ በየወሩ፣ አራቴ፣ የአቴንስ ሕዝብ ይሰበሰባል። በየሳምንቱ እንደማለት ነው።
ለማንኛውም፣ የሰላምና የጦርነት፣ የወጪና የገቢ ጉዳዮች ላይ፣ መረጃዎችን ያዳምጣል። ዲስኩሮችን ይሰማል። ውሳኔዎችን ያስተላልፋል። ማን? ሕዝብ። ሁሉም ሕዝብ አይደለም። ሕፃናት አይሳተፉም። ሴቶችም የሉበትም። በባርነት የተያዙ ሰዎችም፣ አይገቡበትም።
ለአቅመ አዳም የደረሱና ከዚያ የተሻገሩ ወንዶች ግን፣ ሁሉም “መንግሥት” ናቸው - ወይም “የፓርላማ አባል”። ቢሆኑም፣ ሁሉም ለስብሰባ ሁልጊዜ ይመጣሉ ማለት አይደለም። ስራ የሚበዛበት ይኖራል። የቦታ ርቀትም አለ - አንዳንድ ቦታዎች፣ ከከተማዋ ከ40 ኪሎሜትር በላይ ይርቃሉ። እንደ ማራቶን ማለት ነው። ከ30ሺ ዜጎች መካከል፣ ሩብ ያህሉ ቢመጡ ነው። ጉባኤ የሚካሄድበት ቦታም፣ 8 ሺ ያህል ሰዎችን ቢያስተናግድ ነው። ቢሆንም ግን፣ በዚያ ዘመን፣ ይሄ ቀላል ቁጥር አይደለም። የዛሬ 2400 ዓመት ገደማ ነው - ነገሩ።
እንደተለመደው፣ ዜጎች ይናገራሉ፤ ዜጎች እጃቸውን እየቀሰሩ፣ ውሳኔ ይሰጣሉ። በዚህ መሃል ነው፣ “ምቲሊኒ” ስለተሰኘችው ከተማ፣ ከባድ ጉዳይ የመጣው። “በምቲሊኒ፣ ትልቅ አመፅ ተፈጥሯል” ተባለ። “የምቲሊኒ ሰዎች፣ በአቴንስ ላይ አመፁ፤ በአቴንስ ላይ ሸፈቱ” የሚል ስሜት ቀስቃሽ ዲስኩር ተቀጣጠለ። አብዛኛው ሰው ተቆጣ። ማለትም፣ “ሕዝብ” ተቆጣ።
“በእርጋታ እንመርምረው፤ የግራ የቀኙን መረጃ እንመልከት። ሕግና ስርዓትን ተከትለን እንምከርበት” የሚል ሃሳብ አልጠፋም። ግን፣ የብዙ ሰዎች ስሜት በቁጣ ሲቀጣጠል፣ የሰከነ ሃሳብ፣ ብዙም አድማጭ የለውም።
እዚያው በዚያው፣ ወዲያውኑ ውሳኔ እንስጥበት ተባለ። ሕግ እና ስርዓት ተረሳ። ሕዝብ ሲሰበሰብ፣ ቁጥሩ ሲትረፈረፍ፣ የዚያኑ ያህል “ገደብ የለሽ የስልጣን ባለቤት ነን” የሚል የስካር መንፈስ ይዛመታል። የትኩሳት ስሜት ፍለቀለቃል።
“ሕግ አይገዛንም፤ ስርዓት አያግደንም” ብለው፣ ራሳቸው ከሳሽ ራሳቸው ፈራጅ ለመሆን ተሸቀዳደሙ። ዳኝነት፣ በምልክት ብቻ ሆነ። እናም፣ ተሰብሳቢዎቹ፣ በችኮላ፣ እጃቸውን ቀሰረው ፈረዱ።
የምቲሊኒ ነዋሪዎች ላይ ተፈረደባቸው። ያለ ዳኝነት ተወሰነባቸው፤ ያለ ምርመራ፣ ያለ ማስረጃ። አልሚውና አጥፊው አልተለየም። በደፈናውና በጅምላ የቅጣት መዓት ወረደባቸው።…
በእድሜ የደረሱ ወንዶች በሙሉ እንዲገደሉ ተወሰነ።
ሕፃናትና ሴቶች፣ ወደ ባርነት እንዲወርዱ ተፈረደ።ውሳኔውን እንዲያደርሱም፣ መልዕክተኞች ተመደቡ። ለጉዞም ተሸኙ።
የእለቱ ስብሰባ በዚሁ ተጠናቀቀ። ከባድ ፍርዶችን ለማጽደቅ ወደ ሰማይ የተቀሰሩ የሕዝብ እጆች፣ ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል። ደም የተጠሙ የንዴት ዲስኩሮች፣ ደም ደም የሚሸትቱ የቁጣ ስሜቶች፣ ረግበዋል።
በማግስቱ ስብሰባው ይቀጥላል። ወደ ስብሰባው የመጡት አብዛኞቹ ሰዎች ግን፣ የትናንትኖቹ አይመስሉም። ሰዎቹ አልተቀየሩም። ግን ሁለመናቸው ተቀይሯል። የምቲሊኒ ነዋሪዎች ላይ፣ የጅምላ የሞት ቅጣት የወሰኑ የትናንት ተሰብሳቢዎች፤ በማግስቱ ነገሩን ሲያስቡት፣ ዘገነናቸው። ራሳቸውን ታዘቡት።
የትናንት ውሳኔያቸውን ለመሻር፣ እንደገና እጃቸውን ወደ ላይ ቀሰሩ።
“የእልፎች የሞት ፍርድ፣ የእልፎች የባርነት ኩነኔ ተሸሯል” ተብሎ ተወሰነ።
ውሳኔውን በቶሎ የሚያደርሱ መልእክተኞች ተመርጠው፤ ለጉዞ ተጣደፉ። ደግነቱ ፈጥነው በመድረሳቸው የምቲሊኒ ነዋሪዎች ከሞትና ከባርነት ተረፉ።
ያው፤ የጅምላ ጭፍን ፍርጃ፣ በምልክት ነው - ሽቅብ በተቀሰሩ እጆች።
የማስተካከያ መልካም ውሳኔ የሚጸድቀውም በምልክት ነው፣ ወደ ላይ በተዘረጉ እጆች። የአንድ ሰው ወይም የብዙ ሕዝብ መሆኑ ላይ አይደለም ጥያቄው። ምልክቱ አይደለም ችግሩ።
ለዚያ ለዚያማ፣ ምልክት የሌለው ሰው፣ የትም ቦታ፣ የትም አገር የለም። እንደ ጥንቱ፣ ዛሬም፣ ወደፊትም፣ ያለ ምልክት መኖር አይቻልም። ከማዕተብ እስከ ማህተም፣ ከፊርማ እስከ አርማ፣ ከመታወቂያ እስከ ባንዴራ፣ ከደንብ ልብስ እስከ ወታደራዊ ማዕረግ፣ ከእልልታ እስከ ኡኡታ፣ ከቀለበት እስከ ንቅሳት፣ … በምልክት ያልተከበበ ኑሮና ውሎ የለም።
“ማዕተቡ ሌላ ንግግሩ ሌላ”፣ “ማዕረጉ ሌላ ስራው ሌላ” መሆኑ ነው ችግሩ።
“እሷ ሌላ መታወቂያዋ ሌላ”፣ “ቃልኪዳኗ ከእገሌ፣ የተነቀሰችው ለሌላ እገሌ”፣ “ሕግ ሌላ ውሳኔ ሌላ”፣ “የዳኝነት ስርዓት ሌላ፣ የፍርድ እጆች ሌላ” መሆናቸው፤… ቁም ነገርና ምልክቶች ተነጣጥለው መራራቃቸው ነው - ኃጥያቱ።
የአንድ ሰው ጣት፣ ወይም የእልፍ ሰው ጣት መሆኑ አይደለም - ልማቱና ጥፋቱ።
ይልቅስ፣ እውነትንና ሃሰትን መርምሮ ማረጋገጥ፣… እያንዳንዱን ሰው እንደየስራው የመመዘን፣ ለሰው ሕይወት ክብር መስጠት፤ ሕግና ሥርዓትን በተከተለ ትክክለኛ አሰራር ዳኝቶ መፍረድና ፍትህን መፈጸም፣…
እነዚህ ስራዎች፣ ብቃትንና ጥረትን ይጠይቃሉ፤ የስነ-ምግባር መርህንና ፅናትን የሚጠይቁ ስራዎች ስለሆኑም፣ ቀላል ሃላፊነቶች አይደሉም።
ነገር ግን፣ ማምለጫ ዘዴዎች አሉ። በጣም ቀላሉ ዘዴ፣ ቁምነገሮችን ሁሉ መተው፣ ምልክቶችን ማውለብለብ ብቻ! እጅ ማውጣት፣ አውራ ጣት መቀሰር ብቻ!



Read 5997 times