Saturday, 28 May 2022 13:17

ዓለማቀፍ የቅዱስ ቁርአን ውድድር ሽልማት በኢትዮጵያ ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  • ሁለት አሸናፊዎች በነፍስ ወከፍ 1 ሚ.ብር ይሸለማሉ
        • ከ56 አገራት ከመቶ በላይ ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል
               
            የኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የቅዱስ ቁርአን ውድድር ሽልማት ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡ በውድድሩ ከ56 የዓለም አገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ ታዳጊና ወጣት ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
ውድድሩን አስመልክቶ ትላንት አርብ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የሽግግር ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ አብራሂም፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት የተከበሩ ኡስታዝ ካሚል ሸምሹ፣ የአዲስ አበባ መጅሊስ ፕሬዚዳንት ሼህ ሱልጣን አማንና የውድድሩ አዘጋጅ ኑረዲን ሸህቃሲም ናቸው፡፡
ውደድሩ በአዲስ አበባ ከሰኔ 1 - 5 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን  የመዝጊያው የሽልማት ሥነሥርዓት በደመቀ ሁኔታ በወዳጅነት አደባባይ እንደሚካሄድ ተገልጧል፡፡
በዘይድ አብን ሳቢት የቁርአን ማህበር አዘጋጅነት የሚካሄደው ውድድሩ፣ ሁለት ዓይነት  ሲሆን አንደኛው ከ12 – 25 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊና ወጣቶች 30 ጁዝ ቁርአን (አንዱ ጁዝ 20 ገጽ ማለት ነው) ያለማቆራረጥና ያለስህተት ሸምድደው በቃላቸው በማቅረብ የሚወዳደሩበት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በማራኪ የድምጽ አወጣጥና ለረዥም ደቂቃ  ያለማቆራረጥ ቅዱስ ቁርአን የሚቀሩበት ሲሆን ዕውቅ የሆኑ የዓለም የቁርአን ቀሪዎች ያለ ዕድሜ ገደብ አቅማቸውንና ችሎታቸውን የሚያሳዩበት ውድድር ነው ተብሏል፡፡
ለውድድሩ ከ100 በላይ ተሳታፊዎች ከ56 የዓለም አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሲሆን በሁለቱም የውድድር ዘርፎች ከ1ኛ – 3ኛ የሚወጡ አሸናፊዎች ከ500ሺ ብር እስከ 1 ሚሊዮን ብር ይሸለማሉ፡፡ 1ኛ የሚወጣው 1 ሚሊዮን ብር፣ 2ኛ የሚወጣው 700ሺ ብር፣ 3ኛ የሚወጣው ደግሞ 500ሺ ብር የሚሸለም ሲሆን ለአሸናፊዎቹ በአጠቃላይ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡ ታውቋል።
ተወዳዳሪዎቹ አዲስ አበባ በሚቆዩባቸው ጊዜያት ለሁለት ቀን የኢትዮጵያ ቱሪስት መስህቦችን እንደሚጎበኙ የተገለጸ ሲሆን ይህም የሀገራችንን ቱሪዝምና ታሪክ ከማስተዋወቅ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አዘጋጆቹ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከ1 ሺህ 443 ዓ.ም በፊት የነብዩ መሃመድን ባልደረቦች (ሰሃቦች) ተቀብለው በፍትሀዊ መንገድ ያስተናገደች ሀገርና የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት ብትሆንም፣ ታሪኳንና እድሜዋን በሚመጥን መልኩ ሁለንተናዊ እድገት አላሳየችም ያሉት የአዲሱ መጅሊስ ሀላፊዎች፤ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርዓን ውድድር ሽልማት በየዐመቱ እንደሚካሄድና የኢትዮጵያን ታሪክና የተፈጥሮ ፀጋ የማስተዋወቂያ አንዱ መድረክ ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ይህን ፕሮጀክት ለማሳካት ከ20 ሚ. ብር በላይ እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡
በዛይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማህበር አመራሮችና በማቪ ኢቨንት ኦርጋናይዘር ትብብር የሚካሄደው የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የቀዱስ ቁርዓ ውድድር ሽልማት (Ethiopia International Holy Quran Award) በ2019 ዓ.ም የዓለማችን ተወዳጅ ውድድር ሆኖ የማየት ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ታውቋል፡፡

Read 8232 times