Saturday, 28 May 2022 13:29

ሲፒጄ የታሰሩት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  ድርጊቱ የአገሪቱን የፕሬስ ነፃነት አደጋ ላይ የጣለ ነው ብሏል
                               
              በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ 11  ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች ከሰሞኑ በመንግስት መታሰራቸው እንዳሳሰበው ያስታወቀው አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጂ) ጋዜጠኞችን  የማዋከብ ድርጊት እንዲቆም ጠይቋል፡፡
ሲፒጄ ፤በኢትዮጵያ የጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች እስርና እንግልት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ባመለከተበት መግለጫው፤ ድርጊቱ የሃሪቱን የፕሬስ ነፃነት አደጋ ላይ እየጣለ ነው ብሏል፡፡
ሲፒጂ መግለጫውን ባለፈው ማክሰኞ እስካወጣበት  ጊዜ ድረስ  ዘጠኝ የዩቲዩብ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የ”ኢትዮ ንቃት ሚዲያ መሥራችና ዋና አዘጋጅ መስከረም አበራና፣ የ“ገበያኑ” ሚዲያ መስራችና ባለቤት አቶ ሠለሞን ሹምዬ መታሰራቸውን አመልክቷል፡፡
 ከትላንት በስቲያ ሃሙስ ደግሞ የፍትህ ጋዜጣ መሥራችና ማኔጂንግ ኤዲተር ተመስገን ደሳለኝና “የኢትዮ ፎረም” ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ መታሠራቸው ታውቋል፡፡
በመንግስት ቁጥጥር ስር ከዋሉት ጋዜጠኞች መካከል “አሻራ” ሚዲያ ዩተሰኘው የዩቲዩብ ሚዲያ ሶስት ጋዜጠኞችና ሁለት የካሜራ ባለሙያዎች እንደሚገኙበት የጠቆመው ሲፒጄ፤ከባህርዳር ከተማ 185 ኪ.ሜ ርቀው በንፋስ መውጫ ከተማ በሚገኝ  እስር ቤት መታሰራቸውንና ከቤተሰባቸውም  ሆነ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ “ንስር” የተሠኘው የዩቲዩብ ሚዲያ አራት ጋዜጠኞች መታሠራቸውንና ሁለቱም የዩቲዩብ ሚዲያዎች በተለይ በፋኖ ጉዳይ ዘገባዎችን በመስራት የሚታወቁ እንደሆኑ ሲፒጄ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች እስር በዚህ መልኩ መበራከቱ “የኢትዮጵያን የፕሬስ ነጻነት አንድ  እርምጃ ወደፊት፣ ሶስት እርምጃ ወደ ኋላ የሚመልስ እንዲሁምነው ያው ሲፒጄ፤ ይህም  መንግስት ለዜጎች ከተለያዩ ምንጮች መረጃ የማግኘት መብት ግድ እንደሌለው የሚያሳይ ነው” ብሏል፡፡
ሲፒጂ የታሰሩ ጋዜጠኞች በሙሉ በአፋጣኝ እንዲፈቱ፣ የጋዜጠኞች እስርና  እንግልት በአስቸኳይ  እንዲቆምና የጋዜጠኞች መረጃ የመሰብሰብና ያለገድብ የማሰራጨት መብት እንዲረጋገጥ ጠይቋል።
በተያያዘ ዜና፣የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር፣ የጋዜጠኞችንና የሚዲያ ባለሙያዎችን ሰሞነኛ እስር አስመልክቶ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በፃፈው ደብዳቤ፤ የጋዜጠኞች አፈና እና እስር እንዳሳሰበው ጠቁሞ፤ ጋዜጠኞች በህግ አግባብ ብቻ እንዲጠየቁና ጋዜጠኞችን ያለአግባብ ያፈኑ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ፤ በተለያዩ አካባቢዎች በመፈጸም ላይ  ያሉ የጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና የሌሎች ሰዎች እስራትን በተመለከተ ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ፤ የፌደራልም ሆኑ የክልል ፀጥታ ሃይሎች፣ ተጠርጣሪዎችን ከፍ/ቤት ትዕዛዝ ውጪ ከማሰር እንዲታቀቡ አሳስቧል፡፡
ከሰሞኑ የሚዲያ ባሙያዎችና ጋዜጠኞች እስር ጋር በተያያዘ ከአገር ውስጥና ከዓለማቀፍ የሠብአዊ መብት ተቋማት የሚቀርቡ ክሶችና ወቀሳዎችን የፌደራል ፖሊስ አይቀበለውም፡፡ ጋዜጠኞችንና የሚዲያ ባለሙያዎች እየታሰሩ ያሉት ከሙያቸው ጋር በተያዘ ሳይሆን በሽብር የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ነው፤ ፖሊስ።
የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠ/መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙሳ አብዲሳ ለኢቲቪ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከሰሞኑን በተጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጋዜጠኞችም ሆኑ የማህበረሰብ አንቂዎች፤ ብሔርን ከብሔር ወይም ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩ የሽብር ድርጊት ውስጥ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ናቸው ብለዋል፡፡
“ወንጀል ከፈፀሙ በኋላ ጋዜጠኝነትን ወይም ሚዲያን ለመከላከያነት ማቅረብ አይቻልም፤ በወንጀል ላይ የተሳተፈና መረጃ የተገኘበት ማንኛውም ሰው በህግ ይጠየቃል” ሲሉ አስረድተዋል፤ የኦፕሬሽን መምሪያ ሃላፊው፡፡

Read 10918 times