Saturday, 28 May 2022 13:30

የአማራ ክልል የሰሞኑን ክራሞት

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

   • የጦር መሳሪያ የምዝገባ የጊዜ ገደብ ዛሬ ይጠናቀቃል
        • “የአማራ ህዝብ ገንዘቡን አውጥቶ ህይወቱን ሰውቶ ያገኘውን መሳሪያ ማንም አይነጥቀውም”
        • በክልሉ ከ4500 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
        • መንግስት በፋኖ ስም የተደራጁ ህገወጦችን አልታገስም ብሏል
        • በክልሉ በህግ ማስከበር ስም የሚደረግ አፈናና ወከባ እንዲቆም አብን ጠይቋል
           
            መንግስት ባለፍነው ሳምንት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በጀመረው ህግን የማስከበር ዘመቻ ከ4 ሺ500 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ከእነዚህ መካከል ከማረሚያ ቤት ያመለጡ ፍርደኞችም እንደሚገኙበት የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ “በፋኖ ስም ተደራጅተው በህዝብ ላይ የተለያየ ህገወጥ ድርጊት የሚፈፅሙ ወገኖችን መንግስት አይታገስም” ብለዋል፡፡
ይኸው መንግስት ህግ የማስከበር ዘመቻ በሚል በክልሉ የጀመረው እንቅስቃሴ  በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ  ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም  ሞጣና መራዊ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ህግ የማስከበር እርምጃውን በሚቃወሙ ወገኖችና በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች  መካከል ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበርም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግንቦት 14 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የፌደራል መንግስትና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ የህግ የበላይነትን ማከበር በሚል መውሰድ  የጀመሩት እርምጃ ጋዜጠኞችንና  የማህረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካቶች መታሰራቸውን አመልክቷል፡፡
ከዚሁ መንግስት በክልሉ እየወሰደ ካለው ህግ የማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ በክልሉ ከግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በግለሰቦች እጅ የሚገኙ የጦር መሳሪያዎችን ምዝገባ ማካሄድ የጀመረ ሲሆን የጦር መሳሪያ ምዝገባው ቀደም ሲል ተሰጥቶት ከነበረው የጊዜ ገደብ ለተጨማሪ 3 ቀናት ተራዝሞ ዛሬ ግንቦት 20 ቀን 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡ በዚህ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ወደሚመለከተው አካል ቀርበው የጦር መሳሪያቸውን ያስመዘገቡ የክልሉ ነዋሪዎች ቁጥር አነስተኛ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ መንግስት ምናልባትም ተጨማሪ ጊዜ እንደሚሰጥ ይጠበቃልም ተብሏል፡፡
የክልሉ ሚሊሻ ፅ/ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ባምላኩ አባይ ለአማራ ሚዲያ ኮርፓሬሽን በሰጡት ማብራሪያ፤ በህወኃት ሃይሎች ወረራ ወቅት የፌደራልና የክልል መንግስታት በተደጋጋሚ ህዝቡ ማርኮ እንዲታጠቅ ቃል የገቡ መሆኑን አስታውሰው በዚሁ መሰረትም በርካታ የቡድን መሣሪያዎች በግለሰቦች እጅ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡
“የአማራ ህዝብ ገንዘቡን አውጥቶ ህይወቱን ሰውቶ ያገኘውን መሳሪያ ማንም አይነጥቀውም ያሉት ኃላፊው፤ በህገወጥ ቡድኖች የሚነዛውን የሃሰት አሉባልታ ወደ ጎን በመተው ህዘቡ መሳሪያውን አስመዝግቦ ህጋዊ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። ከምዝገባው በኋላ በህገወጥ የመሳሪያ እንቅስቃሴ ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም የክልሉ ሚሊሻ ፅ/ቤት ከመሳሪያ አጠቃቀም አያያዝና ኃላፊነት ጋር የተያያዙ ስልጠናዎች እንደሚሰጥም ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል በህግ ማስከበር ስም እየተከናወነ ያለው አፈናና ወከባ እንዲቆምና መንግስት ከህገወጥ ተግባራት እንዲቆጠብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑ የአብን ፓርቲ አባላት ጠይቀዋል፡፡
አባላቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት፤ መንግስት በህግ ማስከበር ስም በአማራ ህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን የማጥፋትና አማራን አንገት የሚያስደፉ ተግባር እያከናወነ  ነው ብለዋል፡፡ አባላቱ በዚሁ መግለጫቸው፤ መንግስት ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ህዝባችን ማንነትን መሰረት ላደረጉ የጅምላ  ጭፍጨፋዎች፣መፈናቀልና ስደት እንዲሁም ለንብረት ውድመትና ለዘርፈ ብዙ ስነልቦናዊ ችግሮች ተዳርጓል ብለዋል፡፡
“የህዝባችን ህይወት በትህነግ እና አጋሮቹ አደጋ ላይ ወድቆ ባለበት በዚህ ወቅት መንግስት አገራቸውንና ህዝባቸውን ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ባገለገሉ ግለሰቦችና የጦር መኮንኖች ላይ ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የአፈና፣ የህገወጥ እስርና መንግስታዊ እገታ ላይ መጠመዱ አሳዝኖናል” ብለዋል የአብን አባላት፡፡ በመንግስት እየተደረገ ያለው ህግ ማስከበር ሳይሆን በአማራ ህዝብ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ማፈንና ጠያቂዎቹን የማጥፋት፣ ህዝቡንም አንገት የማስደፋት እንቅስቃሴ ነው ሲሉ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡
ጉዳዩን በቸልታ እንደማይመለከቱትና እንደሚታገሉት የገለፁት አባላቱ፤ በመፈፀም ላይ ነው ያሉት መንግስታዊ እገታና ስወራ በአስቸኳይ እንዲቆምና በመንግስት የታገቱ አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አገርና ህዝብ በጉጉት የሚጠብቀው አገራዊ ምክር እንዲደናቀፍ የሚያደርግ ውጤት ያስከትላል ብለዋል፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ፤ በክልሉ እየተወሰደ ያለው የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር፣ ክልሉን ከወንጀለኞች የጸዳ ለማድረግና የክልሉ ህዝብ አንድነት ኖሮት ሊመጣ የሚችለውን ጠላት በብቃት እንዲመክት ለማስቻል ነው ብሏል፡፡
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ዶ/ር ስማ ጥሩነህ  ለክልሉ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በክልሉ አፈና ዝርፊያ ግድያ፣ በሃይማኖት ሰበብ ግጭት ቀስቃሽነትና ሌሎችም ወንጀሎች ተበራክተዋል፡፡ ይህንን  ችግር ለመቅረፍም የተቀናጀ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ለመስራት ተገደናል ብለዋል።
በክልሉ ከተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ጋር ተያያዘ ቁጣ የተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ ሲመልሱ በህግ ማስከበር ስራው ስህተቶች ተፈጥረው ያለ ወንጀላቸው የሚያዙ ሰዎች ካሉ ይቅርታ እንደሚደረግላቸውና በፍጥነት ተጣርቶ እንዲለቀቁ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የህግ የበላይነት የማስከበሩን ዘመቻ የግል ቂም መወጫ የሚያደርጉ  አካላት ካሉ ከተጠያቂነት አያመልጡም ብለዋል፡፡ ወደ እንቅስቃሴ የገባነው  ህዝቡን ካወያየን በኋላ ነው ያሉት አስተባባሪው፤ ከህዝብ የተሰወረ ምንም አይነት ዓላማ የለንም ብለዋል፡፡

Read 11575 times