Saturday, 28 May 2022 13:32

መጅሊሱ ለሁለት ተከፈለ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(5 votes)

   “ህዝበ ሙስሊሙ ሌላ የመከፋፈል አደጋ ተጋርጦበታል” - ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ
                         

                 “አዲሱ መጅሊስ እውቅናም ተቀባይነትም የለውም” ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ ይህን የገለፁት በትላንትናው ዕለት በፅ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው። “በበርካታ ጥረትና ትግል ወደ አንድነት የመጣው ህዝበ ሙስሊሙ አሁንም ሌላ የመከፋፈል አደጋ ተጋርጦበታል” ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ፤ “ሰለፊ ውሃብያ” በሚል የጠሩት ቡድን፤ ሀሙስ እለት ያለ ምክር ቤቱ እውቅና በሸራተን አዲስ ሆቴል  ምርጫ አድርጎ አዲስ መጅሊስ ነኝ ማለቱ ህጋዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ እውቅናም ሆነ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
“ሁለት ሙስሊም የለም  ታይቶም አይታወቅም” ያሉት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት፤ የቡድኑ አካሄድና ምስረታ ህገወጥና እውቅና የሌለው መሆኑን መላው የሙስሊም ማህበረሰብ፣ መንግስትም ሆነ ኢትዮጵያውያን እንዲያውቁት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የተጋረጠውን ዳግም የመከፋፈል አደጋ ለማክሸፍ ሁሉም እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እንድሪስ አክለውም፤ ከመከፋፈልና ከሌሎች ሴራዎች ታቅበን በመተባበር ሀገራችንን ከድህነትና ከችግር ለማውጣት መረባረብ አለብን ሲሉም አሳስበዋል፡፡


አዲሱ  የሽግግር መጅሊስ ከትናንትና በስቲያ ባካሄደው ምርጫ፣ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የመረጣቸውን ሀላፊዎች ይፋ ያደረገ ሲሆን በዚህም መሰረት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም የሽግግር ኮሚቴው ፕሬዚዳንት፣ ሺህ አብዱልከሪም በድረዲንን ም/ፕሬዚዳንት  አድርጎ  የሾመ ሲሆን፣ ሺህ አልመርዲን አብዱላሂ፣ ዶ/ር ጄይላን ገለታ፣ ሺህ ሰዒድ አህመድ ሙስጠፋ፣ ሼህ አብዱል ላዚዝ፣ ሺህ ኑረዲን ደሊል፣ ሺህ መሃመድ አህመድ ያሲን፣ ሼህ መሃመድ ሲራጅ፣ ሼህ መሃመድ አወሎ፣ ሼህ አህመድ መሃመዲ አሊ፣ ዶ/ር ጀማል መሃመድ፣ ሼህ አሚን ኢብሮ፣ ሼህ መሃመድ አሚን ሰይድና ኢ/ር አንዋር  ሙስጠፋን በጊዜያዊ በስራ አስፈጻሚነት መርጧል፡፡ አዲሱ የሽግግር ምክር ቤት የቀደሙትን አመራሮች ማለትም የምክር ቤቱን ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስን፣ዶ/ር ጄላይን ከድርንና ሼህ መሃመድ ሐሚድን ከሀላፊነታቸው በማንሳት ወደ ፈትዋ ምክር ቤቱ እንዲካተቱ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡


በጉዳዩ ላይ አስተያታቸውን የጠየቅናቸው የሽግግር ጊዜ ኮሚቴዎች ፕሬዚዳንት አማካሪና ልዩ ረዳት የሆኑት አባሰላም ሀጂ አባመጫ በበኩላቸው እ”ስካሁን የተደረገ ሹም ሽር የለም፤  በድምጽ ብልጫ የተመረጡ የሽግግር ኮሚቴ አባላት እንጂ አዲስ የመጅሊስ አመራር አልተመረጠም” ብለዋል፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ መግለጫ ስለመስጠታቸው መረጃው የለኝም ያሉት አማካሪው፤ መግለጫ ሰጥተውም ከሆነ ከግንዛቤ እጥረት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ “ሀጂ ኡመር እድሪስም ሆነ ምክትላቸው አሁን ከቀድሞው ስልጣን ከፍ ወደላ ሀላፊነት ማለትም በመላው ኢትዮጵያ ለመላው የህዝበ ሙስሊም ጥያቄ ብይን ሰጪ ከሆኑት ውስጥ (ፈተዋ ምክር ቤት አባላት) አንዱ ሆኑ እንጂ ከስልጣን የወረደም የወጣም የለም” ሲሉ አክለዋል፡፡ መጅሊሱ ተከፋፍሏል የሚባለውስ ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄም “የተከፋፈለ መጅሊስ የለም፤ ባለፈው ሳምንት በስካይ ላይ ሆቴል እስከተካሄደው ስብሰባ  ድረስ ሁሉም ባለድርሻ አካል በህገ ደንቡ ላይ በሰላምና በእርጋታ ሲሳተፍና ሲመካከር ነበር ብለዋል፡፡
አሁን የተመረጡት እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም  አዲስ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ መጅሊሱን በሽግግር የሚመሩ ናቸው ያሉት አማካሪው “አሁን እየተወራ ያለው በግንዛቤ እጥረትና በእኛም በኩል ከተፈጠረ የማስረዳት አቅም እንጂ ይህን ያህል የከበደና የተጋነነ ነገር የለም”  ብለዋል ለአዲስ አድማስ፡፡


Read 12618 times