Print this page
Saturday, 28 May 2022 13:43

የ‘ሰለጠኑት’ እና ‘ወደ ኋላ የቀረነው!’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)


            "ስሙኝማ...በቀደም ፌስቡክ ላይ ያነበብነው ነገር...አለ አይደል... ‘ኢንተረስቲንግ’ ነው፡፡ አንድ ቦታ እየተመገበ ያለ ደንበኛ ጭማሪ ቃሪያ ይፈልግና ያመጡለታል፡፡ ምስኪኑ ጉዱን ያወቀው ቢል ሲመጣ ነዋ፡፡ ለዛች ለጭማሪዋ አንዲት ቃሪያ ስንት ቢጨምሩበት ጥሩ ነው...ሀያ ብር!--"
              
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው...የሆሊዉድ ሬድካርፔት እኛ ዘንድ ደረሰ እንዴ? መቼስ እኛ ዘንድ አንዳንድ ለውጦች ፍጥነታቸው ‘ልዩ’ ከመሆኑ የተነሳ (በትንሹም በትልቁም ‘ልዩ’ ማለት ስለሚቀናን ነው!) እኛን እኮ መአት ጄኔረሽን ወደ ኋላ ያስፈነጠሩን ነው የሚመስለው፡፡ አሀ ልከ ነዋ...ዩቲዩብ ላይ በአንድ የሀገራችን የፊልም ሽልማት ዝግጅት ወቅት ያየነው ትርኢት ራሱን የቻለ ፊልም ያስፈልገዋል።  የፊልም ዓለሙ ሰዎቻችንን አለባበስ ልብ ብላችሁ አያችሁልኝ! እኔ የምለው የድሮ ኮሚዎች ‘ዳያሌክቲካል ማቴሪያሊዝም’ የሚሉት አይነት የማይቀርልን አይነት ለውጥ ይሄ ነው እንዴ! ግራ ገባና!
በነገራችን ላይ ሀገሪኛ ከሆኑ ዲዛይኖች አንዳንዶቹ የምር ደስ የሚል ፈጠራ ናቸው። ይሄን መካድ አሪፍ አይደለም፡፡ ለእኛ አይደለም አዳዲሱ የእንትን ተራ የ‘ሰንዴይ’ ኮትና ሱሪ ተወዶብን አማራጭ መሸለያ ላጣነው እንደ ምቁነት እንዳይመስልብን፡፡ (ስሙኝማ... ስለልብስ ቅድ እናውቃለን ብለን ሳይሆን ቀልባችን ደስ ስላለው ነው አፋችንን ሞልተን የተናገርነው እንጂ የፕሮፌሽን ሽሚያ እንዳያስመስልብን፡፡ ጣት መቀሳሰር ‘ናሽናል ፓሺን’ የሚሉት አይነት በሆነባት ሀገር አንዳንዴ እንዲህ ቀያይ መብራት እያስቀመጡ ማለፉ ሸጋ ነው፡፡)
እኔ የምለው...አንተ እንትና ደግሞ እሱኛው ዓለም ውስጥ በየት በኩል አድርገህ ነው የገባኸው? የአንዳንድ ሰው እንደየሁኔታው መተጣጠፍ እኮ ግርም የሚል ነው፡፡ ግን ለምን ይዋሻል... በሙሉ ልብስህ ተኮፍሰህ ሳይህ...አንተ ወዳጄ እንዲህ ‘ኤሌጋንት’ ነበርክ እንዴ! ስማኝ መቼስ ወዳጅ ለወዳጁ አንዳንድ ነገር ሹክ ይል የለ...ስንት ስልክ ቁጥር ተቀበልክ? ቂ...ቂ...ቂ...
ታዲያማ... አልፎ አልፎ በኮሌስትሮል የተጨናነቀ ሰውነት ይዞ ፋሽኑ በደንብ ይታሰብበታ! (እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ይሄ ኮሌስትሮል የሚሉት ነገር እኛ ...አለ አይደል...”ነጋ ጮማ ነው፣ መሸ ጮማ ነው! አይደለም ሻኛ ማውጣት ለምን ሊፈነዳ አይደርስ?” የምንለው አይነት ነው! አሀ...ግራ ገባና! የአንገት ቁጥሩ አስራ ሦስት የሆነ ሸሚዝ እንደሚሰፋን እንደ እኛ ያሉ “ኮሌስተሮሌን መታየት አለብኝ፣” ሲሉን ግራ እየገባን ነው። ነው፣ ወይስ ኮሌስትሮል የ‘ክላስ’ ማሳያ ሆኗል! ቂ...ቂ...ቂ... ማለትም በፊት፣ በፊት ጊዜ እኮ...
“ስኳር የሀብታም በሽታ ነው፣”
“ካንሰር የባለጸጎች ችግር  ነው፣” ሲባል ተኑሮ አሁን ወላ ሀብታም የለ፣ ወላ ምን የለ...እንዲህ ሊያምሱን!)
እናላችሁ...አይደለም በአለባበስ በኩል እንዳየነው አይነት ትርኢት የአደባባይ ሲሳይ ሊሆን፣ ይህች ሀገር እኮ ለየት ያሉ አመለካከቶች ነበሯት፤ አሁንም አሉ፡፡ ግን ሙሉ ለሙሉ ከስዕሉ ተገፍተው ዳር የቀሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስላሉ ማን ሀሳባቸውን ሰምቶ!
“አንቺ የዛች የእከሊትን ልጅ አየሻት?”
“እንደውም፣ ምን ሆነች?”
“በአደባባይ ሹራቧን ገለጥ አድርጋ አትሄድ መሰለሽ?”
“ቆይ ቆይ...እንዲሁ የትከሻዋ ቆዳ ይታይ ነበር ነው የምትዪኝ?”
“ታዲያሳ!”
“አበስኩ ገበርኩ! አበስኩ ገበርኩ! ምን አይነቱን ዘመን አመጣብን!” ይባል ነበር፡፡
ደግሞላችሁ...
“ኸረ እናንተ ሰዎች ያቺ እንትና የሚሏትን አንድ ነገር በሏት! በኋላ እኮ ጦሱ የሁላችንን በር ነው የሚያንኳኳው!”
“ምን ብታደርግ ነው ይህን ያህል ያሳሰበሽ?”
“ጉልበቷ ላይ የተንጠለጠለ መሀረብ አይሉት ቀሚስ አንጠልጥላ ከተማውን ሁሉ እየዞረች ነው አሉ!”
“ይሄ ሁሉ ሲሆን ያቺ እናቷ የማንን ብቅል ትፈጫለች?”
“እሷንማ ጭራሹን ትፎክርባታለች አሉ።”
እናላችሁ... ብዙ ነገሮች እየተለዋወጡ ነው፡፡ በጣም በ‘ሰለጠኑት’ና በጣም ‘ወደ ኋላ  በቀረነው’ መሀል ልዩነቱ ሰፋማ!
ስሙኝማ...እንደው አንዳንዴ ዝም ብላችሁ ስታስቡት ነገራችን ሁሉ ቀይ መስመር የሌለበት፣ ቀይ መብራት የሌለበት ብሎም ሀይ ባይ የሌለበት እየሆነ አይመስላችሁም! “ሰዉ ምን ይላል?” የለ! “ከታች የሚመጣ ትውልድ ላይ ምን ይፈጥራል?” የለ! “እንዲህ፣ እንዲህ ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው ወይ?” ብሎ መጨነቅ የለ! የምር ግን ይህች ሀገር በምኑም በሉት በምኑም ይሄ ሁሉ ድንግርግር፣ ጥልፍልፍ....አይገባትም ነበር! “አፈር በበላሁ!” የሚለው አነጋገር...አለ አይደል.... “አፈር ብላ!” ተብሎ የሚተረጎምባት ሀገር!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ.... ድሮ ይሄ ኤስፔራንቶ ነው ምናምን የሚሉት የዓለም ቋንቋ የሚባለው ነገር ወሬ ትዝ ይላችኋል? ሲነገር ሰምተነው ባናውቅም፣ አለ ብለውናል በቃ አለ ብለን ተቀብለናል! (ኮሚክ እኮ ነው...ጥርት ባሉትና ለስንት ሺህ ዓመታት አብረው ባኖሩን ቋንቋዎች መግባባት አቅቶን ጭራሽ ሌላ!) እናላችሁ... ኤስፔራንቶ የብዙ ቋንቋዎች ቅልቅል ነው ምናምን ሲባልም እንሰማ ነበር። እና ይጥፋ፣ ይኑር ሹክ የሚለን አላገኘንም፡፡ ግን የሆነ ፈንድ ምናምን የሚፈስበት ጥናት ሳያስፈልግ አፋችንን ሞልተን አንድ ነገር ማለት እንችላለን፤ ኤስፔራንቶ ካለ የዋነኛው የ‘ሴንትራል ኮማንዱ’ መቀመጫ የት መሰላችሁ... እኛው ዘንድ! እንትና...“ክብደት ቀንሰሀል፣ ከቅዳሜ የዶሮ ማነቂያ ቁርጥ ጋር ተለያይታችኋል ወይ!” ያልኩህ በንጹህ ልቦና እንጂ “ዘመናዊ አቦጫጨቁን አላወቀበትም እያሉ ከሚያሙህ ጋር መዳበሌ አይደለም፡፡
“አንቺ በቃ ዘለዓለም ዓለምሽን ምንድነው እንዲህ የሚያንከረፍፍሽ?”
“ዛሬ ደግሞ ምን ሆንሽ ልትዪኝ ነው?”
“ምንድነው ይሄ መሬት ለመሬት የሚጎተት ዝተት!”
“በቃ ረጅም ቀሚስ ነዋ! ረጅም ቀሚስ አይተሽ አታውቂም?”
“ለምንድነው አንደኛሽን ፒስኮር የማትሆኚው?” 
“እና እንዴት ልበሺ ነው የምትዪኝ?”
“ይኸውልሽ ይህንን ዝተትሽን ከፈለግሽ የመስኮት መጋረጃ አድርጊው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቀሚስ ከጉልበት ትንሽ ከፍ ካላለ ምኑን ዘመናዊ ተባለ!”
እናላችሁ አስቸጋሪ ነው፡፡ እያንዳንዳችን ያለን የዘመናዊነት አስተሳሰብ፣ አራምባና ቆቦ ሆነና ተዘባራርቆ አዘበራረቀን፡፡
እናም በመጨረሻ....
“አንተ የት ጠፍተህ ነበር? ተወው፣ ተወው አውቄዋለሁ፡፡ እኔን እንቁላል ቁጭ፣ ቁጭ ላለመጋበዝ ነው፡፡”
“አሁንም እንቁላል ቁጭ ቁጭ ትመገባለህ?”
“የሚጋብዝ ከተገኘ እንክት አድርጌ!”
“አንተ የእውነት እድለኛ ነህ፡፡”
“እንዴት እንደዛ አልክ?”
“በአሁኑ ጊዜ እንቁላል ቁጭ፣ ቁጭ መጋበዝ የሚችል ወዳጅ ያለው ሰው እድለኛ ካልሆነ ማን ሊሆን ነው?” ቂ...ቂ...ቂ...! ስሙኝማ...በቀደም ፌስቡክ ላይ ያነበብነው ነገር...አለ አይደል... ‘ኢንተረስቲንግ’ ነው። አንድ ቦታ እየተመገበ ያለ ደንበኛ ጭማሪ ቃሪያ ይፈልግና ያመጡለታል፡፡ ምስኪኑ ጉዱን ያወቀው ቢል ሲመጣ ነዋ፡፡ ለዛች ለጭማሪዋ አንዲት ቃሪያ ስንት ቢጨምሩበት ጥሩ ነው...ሀያ ብር! (ቃሪያ አንቺም! አንቺም! እንዲሁ ማቃጠልሽ አንሶ አንድሽ ሀያ ብር እያስጠየቅሽ በአንጀት ቁስለት ላይ የቆሽት ቁስለት ትጨምሪብን! ቃሪያ ወዳጆች ሆይ፤ ጭማሪ ቃሪያ ስትጠይቁ “ዋጋውንም አብራችሁ ንገሩን፣” በሏቸውማ!)
ደህና ሰንብቱልኛማ!


Read 1759 times