Monday, 30 May 2022 00:00

ዳያስፖራዋ ሞዴል - ድምጻዊት - ኢንቨስተር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

• ሁለተኛ አልበሟን በቅርቡ ለአድማጭ ታደርሳለች
           • በሽያጭ ባለሙያነቷ ከ40 በላይ ሽልማቶች አግኝታለች


              ትውልድና እድገቷ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ወደ ግሪክ አቀናች፡፡ ለአንድ ዓመት በግሪክ ከቆየች በኋላ በአጎቷ ግብዣ እ.ኤ.አ በ1992 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ተሻገረች።
በአሜሪካ ለ18 ዓመታት የተዋጣላት የሽያጭ ባለሙያ ሆና ሰርታለች፡፡ በታዋቂ መጽሔቶች ሽፋን ላይ ለመውጣት የበቃች ሞዴልም ናት፡፡ ሁለተኛ አልበሟን እያጠናቀቀች የምትገኝ ድምጻዊትም መሆኗን ትናገራለች፡፡ በኢንቨስትመንት ዘርፍም ተሰማርታ እየሰራች ትገኛለች፡፡
ንግስት ጸጋዬ (ኒኪ) ትባላለች፡፡ ከሁለት ልጆቿ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ከመጣች አንድ ወር ገደማ ሆኗታል፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር በህይወቷ፣ በሙያዋ፣ በህልሞቿና ዕቅዶቿ ዙሪያ
አውግተዋል፡፡ እነሆ፡-                  ለምን ነበር ወደ ግሪክ የሄድሽው? ግሪክ በቆየሽባቸው ጊዜያት ምን ነበር የምትሰሪው?
ያው ግሪክ የሄድኩት እንደማንኛውም ሰው የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው፡፡ ግሪክ  ለአንድ ዓመት ስኖር መንገድ ላይ የፋሽን ኢንዱስትሪው ሰዎች አይተውኝ ሞዴል እንድሆን ተጠይቄ፣ ለሁለት ኩባንያዎች ኮንትራት ፈርሜ በሞዴልነት ስሰራ  ቆይቻለሁ፡፡
ኩባንያዎቹ እነማን ናቸው? ታስታውሻቸዋለሽ?
አዎ፤ማስቲንግ ጂንስ እና አጉስታ ለሚባሉ ኩባንያዎች ነበር የሰራሁት። የተፈራረምኩትን የ1 ዓመት ኮንትራት ጨርሼ ውል ድጋሚ ሳላድስ፣ ወደ አሜሪካ የምሄድበት አጋጣሚ ተፈጠረና ወደዚያው  ሄድኩኝ፡፡ ወደ አሜሪካ የተጓዝኩበት ዋና ዓላማ ለትምህርት ነበር። ግሪክ በሞዴሊንግ ጥሩ ተከፋይ ስለነበርኩና ዘርፉን ስለወደድኩት፣ ይህን ሙያ በትምህርት አዳብሬ ለምን ሰርቲፋይድ አልሆንም በሚል፣ በአሜሪካ “ጃንካ ዛብላንካ” የሚባል ሞዴሊንግ ት/ቤት ገብቼ ተማርኩና፣ ተመርቄ ሰርተፊኬትን አገኘሁኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ለተለያዩ ኩባንያዎች ኮንትራት እየተፈራረምኩ ለብዙ ጊዜ በሙያው ስሰራ ቆየሁ፡፡ በዚህም ሂደት በርካታ መፅሔቶች ላይ፤ ለምሳሌ፡- ፕሪንት፣ ፕሬንዌይ፣ ከቨርገርል፣ ራፕሲቲ የተሰኙ እውቅ መፅሔቶች ሽፋን ላይ የመውጣት ዕድልም አግኝቻለሁ፡፡ በርካታ ስራዎችንም በሞዴሊንግ ሰርቻለሁ፡፡
እዚያው አሜሪካ “ሚስ ኢትዮጵያ”  የሚል ማዕረግ አግኝተሽ ነበር። እስኪ ስለሱ አጫውቺኝ?
ይህንን ማዕረግ ያገኘሁት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ነው፡፡ እንዴት መሰለሽ… ያን ጊዜ 21 ልጆች ተመርጠን ነበር፡፡ እኔ ያኔ ከሞዴሊንግ ት/ቤት የተመረቅሁበት ጊዜ ነበር፡፡ እናም ለ”ሚስ ኢትዮጵያ” ኦዲሽን ሲወስዱና ሲያዩኝ “አንቺ በጣም ታስፈልጊናለሽ፤ በሙያው የተመረቅሽና ቀደም ሲልም ግሪክ ውስጥ በሞዴልነት ልምድ ያለሽ በመሆኑ ልጆቹን ታሰለጥኚልናለሽ” አሉኝ። አዘጋጆቹም የተመረጡትም ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በዚህ ዝግጅት ውስጥ እንደነ ተስፋዬ ለማ ያሉ ትልልቅ አርቲስቶች ነበሩበት፡፡ እኔም በተሰጠኝ ሀላፊነት መሰረት አስፈላጊውን ስልጠና ለልጆቹ ሰጠኋቸው፡፡ ይህን ስራ በአግባቡ ሰርቼ በበጎ ፈቃደኝነት ስላጠናቀቅኩኝ አዘጋጆቹ ተደስተው “የኢትዮጵያ ቆንጂት” የተሰኘች አንድ ነጠላ ዜማ ከአርቲስት ተስፋዬ ለማ ተበረከተልኝ፡፡ ይህ ዘፈን በእለቱ በመድረክ ላይ ታዋቂ ለሆነ ዘፋኝ ተሰጥቶ ከዘፈነው በኋላ መልሶ ለተስፋዬ ለማ አስረከበ፡፡ ተስፋዬ ለማም “ይሄ ለንግስት ተብሎ የተሰራ ዘፈን ነው; ብሎ በስጦታነት አበረከተልኝ፡፡
ድምፃዊነቱን በዚህች ነጠላ ዜማ ነዋ የጀመርሽው?
አዎ፤ ማለት ይቻላል።
አልበም ሰርተሻል?
አዎ፤የመጀመሪያ አልበሜን ባልሳሳት ከስምንት ከዘጠኝ ዓመት በፊት እዚህ መጥቼ ሰርቼ፣ በርካታ የቲቪ፣ የሬዲዮና የህትመት ሚዲያዎች ላይ ከወጣሁ በኋላ በመቻኮሌ በደንብ ሳይሰራጭ ተመልሼ ሄድኩኝ። የአልበሙ መጠሪያ “ሰላም” ይሰኛል። እዚህ ሳይሰራጭ በመሄዴ በጣም ተበሳጭቼ ነበር። ሆኖም አሜሪካ ብዙ ተሸጧል፤ በደንብ ተደምጧል፡፡
ከሞዴልነትና ድምጻዊነት በተጨማሪም የሽያጭ ባለሙያ መሆንሽን ሰምቻለሁ ---
ሙዚቃ ፓሽኔም ሆቢዬም ነው፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ብገባበትም፣ ከሀይስኩል ጀምሮ ሙዚቃ ጎን ለጎን የምሰራው ፓሽኔ ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ በአሜሪካ ለ18 ዓመት በሙሉ ሰዓት ሥራነት የሰራሁት ለሂልተን ሆቴልና ለውንደም ሪዞርት ኤግዚኪዩቲቭ ሴልስ ሪፕረዘንታቲቭ ሆኜ ነው። በሽያጭ ስራ ላይ በቆየሁባቸው ዓመታት እግዚአብሔር ባርኮኝ፣ ከ80 ሰዎች መካከል ብዙ ጊዜ አንደኛ ወይ ሁለተኛ ነበር የምወጣው። እነሱ “ቶፕ ፕሮዲዩሰር” ይሉታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከ40 በላይ ሽልማቶችን አግኝቻለሁ፡፡ ስራችን የቫኬሽን ቤቶችን ለሀብታም ቱሪስቶች መሸጥ ስለነበር፣ በዚህ ሥራ ውጤታማ በመሆኔና ብዙ ሽያጭ በማስመዝገቤ ነው፣ ሽልማቶቹን ያገኘሁት፡፡ እነዚህን ቤቶች የምንሸጠው በሂልተን ኩባንያ ስር ስለሆነ ይኸው ወደ ሀገሬ ስመጣ ሂልተን ስፖንሰር አድርጎኝ ያረፍኩትም በሆቴሉ ነው፡፡ እዚህ እንደ ልዕልት ነው ተንከባክበው የያዙኝ። በሽያጭ ዘርፉ ለሂልተን ሆቴልና ለውንደም ሪዞርት ከ50 ሚ. ዶላር በላይ ገቢ አስገብቻለሁ፣ ብራንዱንም በጣም አከብረዋለሁ፡፡
ወደ ኢንቨስትመንቱም ገብተሽበታል ልበል?
ሰው ባገኘው አጋጣሚ፣ ባለው አቅም ሁሉ መስራት፣ መትጋት አለበት ብዬ አምናለሁ። እኔም ያው በሙዚቃና በፋሽን ዘርፉ ላይ ብሆንም፣ በኢንቨስትመንቱ በኩልም፣ ሪል እስቴት በመግዛት በማደስና በመሸጥ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን በዚህም ስኬታማ ነኝ፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች እዚህ ሀገሬ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እያማከርኩ ነው፡፡ እነዚህ ኢንቨስተሮች እዚህ መዋዕለ ነዋያቸውን ቢያፈሱና ወደ ስራ ቢገቡ፣ ለሀገሬ ልጆች ትልቅ የስራ እድል ስለሚፈጥሩና የሀገር ኢኮኖሚ ስለሚያሳድጉ፣ ይህ እንዲሳካ ትልቅ ጥረት እያደረግሁ ነው ያለሁት፡፡ ለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ አስፈላጊውና ሊሰራበት የሚገባው ዘርፍ የትኛው ነው የሚለውን እያጠናንና እየተመካከርን ነው፡፡ አንድ ሁለት የውጭ ኩባንያዎችን አሳምኜ መጥተው እያጠኑ ነው፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ይጨመርበት፡፡
እንደሰማሁት ከሆነ በበጎ አድራት ሥራዎች ሰፊ እንቅስቃሴዎች ታደርጊያለሽ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በተለይ ከሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በእርስ በርስ ጦርነትና በበረሃ አንበጣ ሳቢያ ለመከራና ሰቆቃ ተዳርጋለች፡፡ ዜጎች ለአሰቃቂ ሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀልና ለረሃብ ተዳርገዋል። ወገኖችሽን ለመደገፍ ያደረግሽው ነገር ካለ ብትነግሪኝ--?
ይሄ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ የሚገርምሽ ነገር አሜሪካ ላስቬጋስ ውስጥ 45 ሺህ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ይገኛሉ፡፡ እናም ለብዙ ጊዜ እዛ ኮሚዩኒቲ ውስጥ ትልልቅ አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ ብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ “ህሊና ሬዲዮ” የሚባል የኮሚዩኒቲው የሬዲዮ ጣቢያ አለ፡፡  ገና ከመጀመሪያው በገንዘብም ሆነ ለህዝቡ የሚያስፈልገውን መረጃ በመስጠት እገዛ እንዳደርግ ተጠየቅኩኝ፡፡ በዚህ መሰረት ለትርፍ ያልተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ስላለኝ በሱ ስር “ኒኪን ይጠይቁ” የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም በማዘጋጀትና ለኮሚዩኒቲው በርካታና ጠቃሚ መረጃ በመስጠት ሳገለግል ቆይቻለሁ።
የበጎ አድራጎት ድርጅትሽ በምን ሥራ ላይ ነው የተሰማራው?
ድርጅቴ “Too helping hands” ይሰኛል። ለትርፍ ያልተቋቋመና ማህበራዊ ሃላፊነቴን ለመወጣት የምሰራበት፤  ሰዎችን የማገለግልበት ድርጅት ነው። “ኒኪን ይጠይቁ” የተሰኘው ፕሮግራምም በዚህ ስር ነበር የሚዘጋጀው። በሌላ በኩል፤ ሬዲዮው በፋይንስ እጥረት እንዳይቋረጥ የገንዘብ ድጋፍ ሳደርግ ነበር-ለረጅም ዓመት። ይህን ኮሚዩኒታችን የሚገናኝበትን ሬዲዮ በመደገፌም መረጃና ግንዛቤ በመስጠት በማገልገሌም ኩራት ይሰማኛል። ሬዲዮው እስካሁን አለ። ከዚህ በተጨማሪ ለተፈናቀሉት ወገኖችም ይሁን ለህዳሴው ግድብ የገቢ ማሰባሰብ ስራ እንዲያስተባብሩ ከተመረጡት ውስጥ አንዷ ነበርኩኝ።
በሌላ በኩል፤ እዛው ላስቬጋስ ውስጥ መንገድ በሀገራችን ስም ለማሰየም በሚደረገው እንቅስቃሴ ከተመረጡት የኮሚቴ አባላት አንዷ ነኝ። መንገዱን “Little Ethiopia” ብለን ለማሰየም እየሰራን እንገኛለን። ይህ ጉዳይ ከዚህ ስመለስ ይሳካል ብዬ አስባለሁ። በአጠቃላይ በሀገሬ ጉዳይ በሚደረግ ማንኛውም መልካም ነገር ላይ እሳተፋለሁ፤ አስተባብራለሁ፤ የሚጠበቅብኝን አደርጋለሁ።
ሁለተኛውን አልበምሽን ሰርተሽ ለማስተዋወቅ እንደመጣሽ ሰምቻለሁ። እስኪ ከአልበሙ ውጪ ሌሎች እቅዶችም ካሉሽ አጫውቺኝ---የአሁኑ አመጣጥሽ ለየት ያለ ነገር ካለውም እግረመንገድሽን ብትነግሪኝ …
የመጣሁት  በጣም ደስ የሚል እቅድ ነድፌ ነው። ለኔ ይሄኛው ጉዞዬ ታሪካዊ የሚባል ነው። አንደኛው፤ ሁለቱ የምኮራባቸው ከኮሌጅ የተመረቁ ውድ ልጆቼ፤ ሜሎዲ አሮንና ናትናኤል አሮን ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራቸውን ለማየት አብረውኝ መጥተዋል። በዚህ በጣም ኩራት ተሰምቶኛል። ለረጅም አመታት ብቻዬን ሆኜ ያሳደግኳቸው ልጆቼ ለቁም ነገር በቅተው ሀገራቸውን ለማየት ሲመጡ የሚፈጥረውን ስሜት አስቢው። ገና እግራችን ኢትዮጵያን እንደረገጠ ለሶስት ቀን ጸበል ቦታ ሄደን ተጠምቀንና ጸሎት ቆይተን ነው የወጣነው።
እንዴት እንደዛ አደረጋችሁ? ማለቴ እግራችሁ እንደገባ ወደ ጸበል መሄዳችሁ ገርሞኝ ነው…
እኔ በህይወቴ እግዚአብሔርን ካስቀደምኩኝ የማስበው ሁሉ ይሳካል የሚል እምነትን በውስጤ ይዤ ነው እዚህ የደረስኩት። አሁንም በዛው መንፈስ በኢትዮጵያ ላሳካ ያቀድኳቸውን ነገሮች ከመጀመሬ በፊት ጸበልና ጸሎት ያስፈልግ ስለነበር፣ ሁሉንም ከጸሎትና ከጸበል ነው የጀመርኩት። እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ሁሉም እየተሳካ ነው ያለው። ሁሌም እምነቴን አጠናክሬ መሄዴ ነው፣ ህልሜን እንድኖር ያደረገኝ። ከዚያ ልጆቼን ጸበል አስጠምቄ፣ ለ15 ቀናት የሚጎበኙትን አስጎብኝቼ ደስ ብሏቸዋል። እዚህ ከመጣሁ  አንድ ወር ተኩል ሆኖኛል። የአልበሙ መጠሪያ “ንጉሱ” ዘፈን ቪዲዮው አላለቀም ነበር፤ እሱ በጥሩ ሁኔታ አለቀ። በቤተሰብም በኩል አንዳንድ ጉዳዮች ነበሩ። ለምሳሌ የአባቴ የንግድ ቦታዎች ነበሩ። እነሱም ጉዳዮች አለቁልኝ። ብቻ ሁሉም በተያዘለት ጊዜና እቅድ እየሄደልኝ ነው።
እስኪ ስለ አዲሱ አልበምሽ ንገሪኝ፤ ግጥምና ዜማውን ማን ሰራው? ስንት ዘፈኖች ይዟል? አንቺስ ግጥምና ዜማ ትሰሪያለሽ?
የሚገርምሽ ነገር አልበሜ በጣም በታወቁ የግጥምና ዜማ ጸሀፊዎችና በራሴም ነው የተሰራው። አንድ አራቱን እራሴ ነኝ የጻፍኳቸው። ሌሎቹን ግን ከአንጋፋዎቹ እንደነ አብርሃም ወልዴ፣ አለምጸሐይ ወዳጆ፣ ተስፋዬ ለማ ሲሳተፉበት፣ ከአዳዲሶቹ ኢዮኤል መሃሪ የተባለ በጣም ድንቅ የሆነ ልጅ ተሳትፎበታል። ግጥም ጸሀፊም አቀናባሪም ሆኖ እየሰራ ነው። ማስተሪንግና ሚክሲንግ ደግሞ ይትባረክ የተባለ ሰው ከጎኔ ሆኖ እየረዳኝ ይገኛል። ታምራት አበበ የተባለ ብሩህ ገጣሚ አለ። እሱም ዘፈኖች ጽፎልኛል። በጣም የተዋጣለት ስራ እንደሚሆን አምናለሁ። እኔ ስራው አስደስቶኛል ብዬ ለአልበም አብቅቼዋለሁና፣ ሌላውን ለአድማጮች ፍርድ ነው የምተወው።
አሁን አልበሙ ተጠናቅቆ እስኪለቀቅና እስኪመረቅ እዚሁ በመቆየት በደንብ እሰራለሁ። የመጀመሪያ አልበሜ ሳይለቀቅ በመሄዴ የቆጨኝን ቁጭት በዚህ አካክሳለሁ። እንግዲህ ለሁሉም እግዚአብሔር ይጨመርበት።
ታዲያ አልበምሽን መቼ እንጠብቅ?
ከአንድ ከሁለት ወር በኋላ ይለቀቃል። አድማጮች በጣም ይወዱታል ብዬ አስባለሁ።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ስትመጪ ያዘንሽበትና ያስከፋሽ ነገር አለ?
ያው እዛም ሆኜ አገሬን አስባለሁ። ምን አስተዋጽኦ ማድረግስ እችላለሁ ብዬ ሳስብ ከሁለት ዓመት በፊት በህይወቴ አሳዛኝ ነገር ተፈጠረ። ወንድሜ ከ8 ዓመት በፊት እዚህ አገር መጥቶ ያለ አባት የሚያድጉ ወይም አባትና እናት የሌላቸውና አያት ወይም አክስት ጋር ተጠግተው  የሚኖሩ ግን ደግሞ በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑ ልጆች ይፈልግና አዶፕት ያደርጋቸዋል፤ አሳዳጊያቸው ይሆናል። ከዚያም ከጓደኞቹም ከራሱም ገንዘብ እያዋጣ እነዚህን ልጆች ለስምንት ዓመት ሲያግዝና ሲረዳ ነበር። ከሁለት ዓመት በፊት እዚያው አሜሪካ በኮቪድና በአስም በሽታ ሞተብኝ፡፡ እጅግ የምወደውና የማከብረው ታላቅ ወንድሜ ነበር። በሙያው መሃንዲስ ነው። እሱ ሲሞት አጠገቡ ስለነበርኩ የመጨረሻ ቃሉ፤ “እነዚህን ልጆች አደራ” የሚል ነበር። በዚህ ቃል መሠረት፤ ከ2 ዓመት በፊት ልጆቹን ተረክቤ እዛው ሆኜ እሱ የሚያደርግላቸውን እያደረግሁ፣ ገንዘብ እየላኩኝ ማስተማሬን ቀጠልኩ። ይሄ ጉዞዬ ታሪካዊ ነው ብዬሽ ነበር ቅድም። አንዱ ታሪካዊ የሚያደርገው እነዚህን ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ያገኘሁበትም በመሆኑ ነው። እነሱን ሳገኛቸው ደስታም ሀዘንም ነው የተሰማኝ። ሃዘኑ፤ ወንድሜ ቢኖርና አብረን ብናገኛቸው ከሚል ነው። ደስታው፤ ቃሌን ጠብቄ ሃላፊነቴን በመወጣቴና በአካል መገናኘቴ ነው።
ዕድሜያቸው ስንት ነው? በምን ሁኔታ ላይ ናቸው?
መጨረሻ ላይ አዶፕት ያደረጋቸው እህትማማቾች ናቸው። እድሜያቸው 4 እና 6 አመት ነው። ትልቅ የሚባለው 19 ዓመት ነው። እናም ኮምፒዩተሮች፣ ስልኮች፣ ልብሶችና ሌሎች በርካታ ነገሮች ይዤላቸው ነው የመጣሁት፡፡ እዚህም ከመጣሁ በኋላ ለበዓል፣ ለትምህርታቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር አሟላሁ፤ ልጆቹን ደስ ብሏቸው ሳይ "በቃ ወንድሜ አልሞተም; ነው ያልኩት፤ በጣም ተደሰትኩ። በሌላ በኩል፤በርካታ ሊታገዙ ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገቡ እናቶችና ልጆችን አይቻለሁ። አቅሜ ቢፈቅድና ብችል ሁሉንም እንደነዚህ ልጆች ብረዳቸውና ባግዛቸው ደስ ይለኝ ነበር። ነገሩ ግን በአንድ ግለሰብ የሚሆን አይደለም። እኔ እግዚአብሔር ፈቅዶ የምችለውን እያደረግሁ ነው።
ይሄ ችግር ተቀርፎ ባይ ደስ ይለኛል። ሃገሬ ከድህነት ተላቃ፤ ሰላም አንድነት፣ ፍቅርና መረጋጋት የሰፈነባት ሆና ማየት ምኞቴ ነው። ለዚህ በግሌ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። ሌላውም የድርሻውን ከተወጣ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያን ማየት እንችላለን። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ብዙ አቅም ያላትና ለሁላችንም የምትበቃ ሀገር ናት። ፍቅርና ሰላም ካለ፣ ሁሉም ይኖራል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከመሰነባበታችን በፊት የምትይው ነገር ካለ ዕድሉን ልስጥሽ---
እኔ ብናነሳው ደስ የሚለኝ የቱሪዝም ጉዳይ ነው። እንደነገርኩሽ እኔ ለ18 ዓመታት በሂልተን ሆቴልና በወንዶም ሪዞርት ከብዙ ቱሪስቶች ጋር የመገናኘት ዕድል ነበረኝ። በዚህም ስኬታማ ነኝ። የእነዚህ ቱሪስቶች ዳታ ቤዝም ስላለ እነዚህ ቱሪስቶች ወደዚህ ሀገር ተጋብዘው መጥተው የሀገራችንን የአየር ንብረት፣ መልክአ ምድር፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች፤ ክብራችንን ጭምር አይተው እንዲመለሱ የማደርግበትን ሁኔታ እያሰብኩ ነው።
በዚህ ረገድ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አብረውኝ እንዲሰሩ እጠይቃለሁ። ይህ እድል ሊያመልጠን አይገባም። ከዚህ በፊት ይህን ሀሳብ አቅርቤ የሰማኝ ያደመጠኝ አካል አልነበረም። እኔ ግን ተስፋ አልቆርጥም፤ ተደማምጠንና ተረዳድተን ለሀገራችን የሚበጀውን ማድረግ አለብን። በመጨረሻም ለዚህ ሁሉ ያበቃኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ማናጀሬን ለተብርሃንን፣ ደረጀ በለጠን፣ ግርማ በላሜን፣ ልጆቼንና ከጎኔ ሆነው የሚያግዙኝን ሁሉ አመሰግናለሁ።


Read 8928 times