Saturday, 28 May 2022 13:53

የዝንጆሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ 18 አገራት ገብቷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  - በመላው አለም 237 ሰዎች ቢጠቁም የሞተ ሰው የለም
       - የአለም የጤና ድርጅት ቫይረሱ ያን ያህል አያሰጋም ብሏል

                  በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተለመደውና ከሁለት ሳምንታት በፊት በእንግሊዝ የተከሰተው የዝንጆሮ ፈንጣጣ አውሮፓ፣ አሜሪካና አውስትራሊያን ጨምሮ በአለማችን 18 አገራት በወረርሽኝ መልክ መስፋፋቱ የተገለጸ ሲሆን፣ እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በመላው አለም 237 ሰዎች በበሽታው ቢያዙም፣ አንድም ሰው አለመሞቱን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
አገራት ቫይረሱን ለመከላከል የፈንጣጣ ክትባትን መጠቀም መጀመራቸውና ቫይረሱ የተገኘባቸውን አግልሎ ማስቀመጥን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን፣ ቫይረሱ ወደሌሎች የአለማችን አገራትም እንደሚዛመት ቢጠበቅም፣ የአለም የጤና ድርጅት ግን ቫይረሱ ብዙ ሰዎችን የማጥቃት ዕድሉ ዝቅተኛ መሆኑንና በወረርሽኝ መልክ ባልተከሰተባቸው አገራት በፍጥነት በቁጥጥር ስር ማዋል እንደሚቻል አስታውቋል፡፡
ቫይረሱ ከተስፋፋባቸው የአለማችን አገራት መካከል ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ አሜሪካ፣ እስራኤል፣ ስዊዘርላንድና ዴንማርክ እንደሚገኙበት የተነገረ ሲሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ቫይረሱ የተገኘባት የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች፡፡
የራሱ ክትባት እንደሌለውና በንክኪ እንደሚተላለፍ የተነገረለት የዝንጆሮ ፈንጣጣ በሽታ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ መሆኑንና ምልክቶቹም ከፍተኛ ትኩሳት፣ ማሳከክ፣ የቆዳ ውሃ መቋጠር ሽፍታና እብጠት መሆናቸውን ያስታወቀው የአለም የጤና ድርጅት፤ የመግደል ዕድሉ 10 በመቶ በሆነው በዚህ ቫይረስ የሚጠቁ ሰዎች ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት ከበሽታው እንደሚያገግሙም አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1970 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው የዝንጆሮ ፈንጣጣ በስፋት የሚገኘው በአፍሪካ መሆኑንና ከዚህ በፊት ከታየባቸው 11 የአፍሪካ አገራት መካከል ቤኒን፣ ካሜሩን፣ ጋቦን፣ ላይቤሪያና ናይጀሪያ እንደሚገኙበትም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2281 times