Saturday, 28 May 2022 13:56

(ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተቋሙን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ፡-)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       “በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩኅ በጣም አዛኝ በኾነው።”

                  (ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተቋሙን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ፡-)


             እስልምና ሃይማኖት በሀገራችን ከ14 ክፍለ ዘመናት በላይ ባስቆጠረው ታሪኩ በተለይም እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ አመታት ድረስ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ በሁሉም አቅጣጫ ያለምንም ልዩነት በአንድነቱ ጸንቶ የኖረ ሲሆን ከሙስሊምነት ውጭ ሌላ መጠሪያም አልነበረውም።
የኢሕአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም የተለያዩ ባዕድ አስተሳሰቦች ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገራችን የገቡ ሲሆን በተለይም የውሀብያ አስተሳሰብ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ማህበረሰባችን አንድነቱ ሲናወጥ፣ ልዩነቱ ሲሰፋ እና ሰላሙ ሲደፈርስ ቆይቷል።
በ2010 ከተደረገው የመንግስት ለውጥ ጋር በተያያዘ የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን የመደመር ፍልስፍና መሰረት ያደረገ የአንድ ሁኑ ጥሪ እና አንድነት በቁርአንም የታዘዘ እንደመሆኑና የመሻይኾቻችን ቅንነትና ሆደ ሰፊነት ተጨምሮበት ሚያዝያ 23፣ 2011 ሸራተን ላይ በተደረገው ስብሰባ የነበረው የመጅሊሱ አመራር ከህግ አግባብ ውጭ ብዙ ርቀት በመሄድ ለአንድነት ሲባል 26 አባላትን በያዘ የዑለማ ም/ቤት እና በስሩ በተደራጁ የቴክኒክ (ሙያዊ) ድጋፍ በሚሰጡ 7 የቦርድ አባላት እንዲተካ የተደረገ ቢሆንም በሚከተሉት የሰለፊ/ውሀብያው ቡድን አስቸጋሪ ባህሪያቱና በርካታ ጥፋቶች ምክንያት የታሰበው አንድነት ሊመጣ አልቻለም፦
የክልል መጅሊሶችን በአዲስ መልክ ለማደራጀት በተደረገው እንቅስቃሴ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርን፣ የኦሮሚያን፣ የደቡብን፣ የቤኒሻንጉልን እና የጋምቤላ ክልሎችን በአዲስ መልኩ የተደራጁ ቢሆንም በሁሉም ክልሎች ላይ የሰለፊ-ውሀብያው ቡድን የአመራር የበላይነትን በመያዝ በነባሩ የእስልምና መስመር መሳጂዶች፣ ዑለማዎች፣ ኢማሞች  እና ተከታዩ አማኝ ህዝብ ላይ በደሎችን በማድረሳቸው ሁኔታዎች እንዲስተካከሉ የም/ቤቱ ስራ አስፈጻሚ በተደጋጋሚ ያሳሰበ ቢሆንም ከቤኒሻንጉል ክልል በስተቀር ችግሮቹን ለመቅረፍ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፤ የጠቅላይ ም/ቤቱን ትእዛዝ የማይቀበሉ መሆናቸውን በተደጋጋሚ በጽሁፍ አረጋግጠዋል፤
የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ የሶማሊ እና የሐረሪ ክልል መጅሊስ አመራሮች አዲሱ የጠቅላይ ም/ቤቱ አመራር ከመረከቡ በፊት የቀድሞውን የመጅሊስ አመራሮች በማባረር በሰለፊ-ውሀብያው ወገን የተያዙ ሲሆን በጠቅላይ ም/ቤቱ በኩል ሁሉንም ወገኖች ባሳተፈ መልክ ለማደራጀት የተደረገው ሙከራ በሰለፊ-ውሀብያው ቡድን እምቢተኝነት አልተሳካም፤
የአፋር ክልልን ለማደራጀት ዑለሞች ከጠቅላይ ም/ቤቱ ቢላኩም ወትሮውንም በብቸኝነት አመራሩን ተቆጣጥሮ ይዞ የቆየው የሰለፊ-ውሀብያው ቡድን እምቢተኝነትን መርጧል፤
በአማራ ክልል እንዲያደራጁ ዑለሞች ቢመደቡም የሰለፊ-ውሀብያው ቡድን ወደ ክልሉ ለመሄድ ፈቃደኛ ባለመሆንና ይልቁንም ከሀገሪቱ የመንግስት አወቃቀር ውጭ ፖለቲካዊ አንደምታ ያለው በሚመስል መልኩ “የወሎ መጅሊስ” የሚባል ህገወጥ አደረጃጀት በመፍጠር ኢማሞችን የማባረርና መስጅዶችን የመንጠቅ ተግባሩን ቀጥሏል፤
ቦርዱ የ2011 የሐጅ አገልግሎትን የሰለፊ-ውሀብያው ቡድን አባላት ከሆኑት ከዶ/ር ጀይላን ኸድር እና ሸኽ አብዱልአዚዝ ጋር ሆኖ በመምራት የጠቅላይ ም/ቤቱ ብቸኛ ገቢ ከሐጅ አገልግሎት የሚገኝ ገንዘብ ሆኖ ሳለ ተገቢ ባልሆነ አሰራር የሐጅ ስርዓቱ ክንውን እንዳለቀ በጥቂት ወራት ውስጥ ጠቅላይ ም/ቤቱን ለሠራተኞች ደመወዝ እንኳ መክፈል በማይችልበት የፋይናንስ አቋም ላይ ከመጣሉ ባሻገር ገንዘባቸውን ከፍለው ሀጅ ባልሄዱ የ479 ተመዝጋቢዎች ገንዘብ ተቋሙን ባለዕዳ አድርጎታል፤
በፈፀመው የዲስፕሊን ግድፈት ምክንያት በዑለማ ም/ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ በታገዱ የቦርድ አባላት፣ በሕገ ወጥ መንገድ ከተቋሙ በተወሰደው በመከነ ማኅተም እና ባለአርማ ወረቀት በተደረገ ጥሪ መጋቢት 20 እና 21፣ 2013 የሰለፊ/ውሀቢው ቡድን ለብቻው ጉባኤ አካሂደናል በማለት ረቂቅ ሰነዶችን በተናጠል አጽድቀናል፤ የጠቅላይ ም/ቤቱ ዋና ፀሀፊ የሆኑትን ሸኽ ቃሲም ሙሐመድ ታጁዲንን ከስራ አባረናል በማለት ህገወጥ ጉባኤና ውጤት የሌለው ህገወጥ ውሳኔ አስተላልፏል፤
የዓሊሞች የአንድነት እና የትብብር ረቂቅ ሰነዱ ላይ በጠ/ም/ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ውይይት እንዲደረግበት አጀንዳው ቢቀርብም የሰለፊ/ውሀብያው ወገን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በተቀሩት ዑለማዎች በተደረገው ውይይት መሰረት ማሻሻያ ተደርጎበትና ተስተካክሎ ረቂቅ ሰነዱ ላይ አስተያየት እንዲሰጡበት ለክልል መጅሊሶች የተላከ ቢሆንም የእምቢተኝነት ምላሽ ሰጥተዋል፤
የጠቅላይ ም/ቤቱ ፕሬዝደንት ለስራ ጉዳይ ወደ ውጭ በሄዱበትና ከስራ አስፈጻሚው እውቅና እና ስምምነት ውጭ በሕገ ወጥ መንገድ ከተቋሙ በተወሰደው በመከነ ማኅተም እና ባለአርማ ወረቀት በጠ/ም/ቤቱ ም/ፕሬዝደንት ፊርማ ለመጋቢት 17 እና 18፣ 2014 ህገ ወጥ ስብሰባ ጠርተዋል፤
በመንግስት አካላት አደራዳሪነት በተደረገው ጉባኤ ከስምምነት ውጭ በየቀኑ አጀንዳ በማንሳት የታገደውን ቦርድ ለመመለስ ጥረት ከማድረጋቸው በተጨማሪ የጠቅላይ ም/ቤቱን ፕሬዝደንት ሰብሳቢነት በተደጋጋሚ አንቀበልም በማለት አመጸኛነታቸውን አሳይተዋል፤
ከመጋቢት 17 እስከ 24፣ 2014 በረቂቅ ደንቡ ላይ በተደረገው ውይይት በቃለ ጉባኤ የተያዙ የልዩነት ነጥቦችን መነሻ በማድረግ ዑለማንና ምሁራንን ያካተተ ከነባሩ እስልምና ተከታዮች 40 ከሰለፊ-ውሀብያው ቡድን 40 ግለሰቦች የተሳተፉበት ውይይት ግንቦት 8 እና 9፣ 2014 የተደረገ ቢሆንም የውይይቱን ውጤት ለመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫን ለማስቀመጥ በፕሬዝደንቱ ስብሰባ ቢጠራም የሰለፊ-ውሀብያው ቡድን እንቢተኝነትን በመምረጥ ሆቴል ቤት በተናጠል ለቀናት ሲዶልት ቆይቶ በመጨረሻም በትናንትናው ዕለት ማለትም ግንቦት 18፣ 2014 ህገ ወጥ መግለጫ እና ውጤት የሌላቸው ህገ ወጥ ውሳኔዎችን አሳልፏል፤
እንደ ሃይማኖት ተቋም ቅድሚያ ትኩረትን የሚሻው የዓሊሞች የአንድነት እና የትብብር ረቂቅ ሰነድ ሆኖ እያለ ቡድኑ ትኩረት ያደረገው በረቂቅ መተዳደሪያ ደንቡ ላይ መሆኑ ተቋሙን ለመቆጣጠር አቋራጩ መንገድ ነው ብሎ በማመኑ ሲሆን በረቂቅ መተዳደሪያ ደንቡ ላይ በውይይቱ ወቅትም የታዩት የልዩነት ነጥቦች እንደሚያመለክቱት የሰለፊ-ውሀቢው ቡድን መጅሊሱ በኃይማኖቱ ሊቃውንት (ዑለማ) የሚመራ የኃይማኖት ተቋም መሆኑን እና የነባሩን የእስልምና መስመርና ትውፊት እንዲቀጥል እና አወቃቀሩም እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ያገናዘበ እንዲሆን ካለመፈለግ እና ልዩነትን በውይይትና በመነጋገር ከማጥበብ ይልቅ በሀገራችን ለ1400 ዓመት የነበረውን የእስልምና መስመር በመቀልበስ ከ30 አመት ወዲህ በቅርቡ ወደ ሀገራችን በገባው መጤ የውሀብያ አስተሳሰብ የመተካት አካሄድን በመምረጡ እንደሆነ ከላይ የተዘረዘሩት የቡድኑ አስቸጋሪ ባህሪያትና በርካታ ጥፋቶች ያስረግጣሉ።
በመሆኑም ጠቅላይ ም/ቤቱ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫ ነጥቦች አውጥቷል፦
ሚያዝያ 23፣ 2011 ለአፋዊ ሳይሆን ለልባዊ አንድነት ሲባል ህግ በመጣስ የተደረገው የሸራተን ስምምነት እላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች እንደሚያሳዩት የሰለፊ-ውሀብያው ቡድን በአስቸጋሪ ባህሪያቱ፣ በርካታ ጥፋቶች እና የተናጠል ጉዞ ምክንያት ያፈረሰው መሆኑን ለማህበረሰባችን እያሳወቅን የጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች መነጠል የሙስሊሙን ማህበረሰብ አንድነት እንደማያውከው እያስገነዘብን እያንዳንዱ ሙስሊም ሃይማኖቱን፣ ተቋሙንና መስጅዶቹን ለመጠበቅ ከመሻይኾቹ ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ከሚያዝያ 23/2011 የሸራተን አዲስ ስምምነት እራሱን ነጥሎ ያደራጀው ቡድን ግንቦት 18 ቀን 2014  ያስተላለፈውን ውሳኔ ጠቅላይ ም/ቤቱ ውድቅ አድርጎታል። በመሆኑም ውሳኔው በየትኛውም ተቋም ተፈፃሚነት ሊኖረው እንደማይገባ ጠቅላይ ም/ቤታችን በጥብቅ ያስገነዝባል።
በአዋጅ ህጋዊ ዕውቅና የተሰጠው ጠቅላይ ም/ቤቱ ከ14 ክ/ዘመናት በላይ ያስቆጠረው የነባሩ እስልምና ተከታይ በሆኑ የሃይማኖት አባቶቻችን የተቋቋመ ነባር ተቋም እንደመሆኑ የመሻይኾቻችን መንገድ  የሆነውን የአህሉ ሱና ወልጀማዐ መስመር ያስቀጥላል።
ጠቅላይ ም/ቤቱ በተጓደሉ የስራ አስፈጻሚ አባላት ምትክ ከዑለሞቻችን መካከል በመምረጥ የሚተካ ሲሆን ከሀጁ ስራ ጎን ለጎን በሀገር አቀፍ ደረጃ የዲኑ ባለቤት የሆኑትን ዑለሞቻችንን በመጥራትና ረቂቅ ሰነዶችን በማስጸደቅ ጠቅላይ ም/ቤቱን የሚያዋቅር መሆኑን እናሳውቃለን።
የሸራተኑ ስምምነት የተደረገው ከምንጩ እየደረቀ የነበረውን የሰለፊ-ውሀቢ አስተሳሰብ ወደ ተቋሙ በማስገባት ከነባራዊ ሁኔታው በመረዳት ወደ ነባሩ እስልምና የሚቀየርበትን መደላድል ለመፍጠር እንጅ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከአብሮነት ይልቅ መራራቅን መሰረት ያደረገ፣ የሰላምና እርጋታ ቦታ የሆኑ መስጅዶችን ወደ ሁከት መድረክ የቀየረ፣ ከውይይት ይልቅ ግጭትን የሚመርጥ፣ የማህበረሰብን ሰላም የሚያውክና መልካም እሴቶችን የሚንድ ስርዓት አልበኛን ተቋማዊ ለማድረግ አልነበረም። በመሆኑም መንግስት ህግና ስርዓት የማስከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ እየጠየቅን ለዚህ ስርዓት አልበኛ ቡድን ድጋፍ የሚያደርጉ አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናትና ውስን ባለሃብቶች ከዚህ አድራጎታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።
አሏሁ አክበር!
አላህ የሀገራችንን አንድነት እና የህዝባችንን ሠላም ይጠብቅልን!!!  
ግንቦት 19 ቀን፣ 2014
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Read 1772 times